
በዛሬው ወቅታዊ ዝግጅታችን የላዛሪስት ማሕበር ካህን እና በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የጽዮን ማርያም ቤተክርስቲያን ቆሞስ ከሆኑት አባ አማኑኤል ተክሉ ጋር ሰሞነ ሕማማትን እና ትንሳኤ በዓልን የተመለከተ ቆይታ አድርገናል።
አዲስ ዘመን፡- አብይ ጾም በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ምን አይነት ቦታ አለው ?
አባ አማኑኤል፡- ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጾመው 40 ቀን እና 40 ሌሊት ስለሆነ በቤተክርስቲያናችን ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል። ምዕመናን በዚህ የጾም ጊዜ ቤተክርስቲያን በመምጣት የመስቀል መንገድ በሚባል ጸሎት 14ቱ ማረፊያ የሚባሉትን ጸሎቶች ያደርሳሉ። አንደኛ ማረፊያ ክርስቶስ ሞት የተፈረደበት፣ ሁለተኛ ማረፊያ መስቀሉን ለመሸከም የተቀበለበት፣ ሦስተኛ ማረፊያ ለመጀመሪያ ጊዜ የወደቀበት፣ አራተኛ ማረፊያ ከእናቱ ጋ የተገናኘበት እያለ እስከ 14ኛው እና መጨረሻው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተቀበረ የሚለው ማረፊያ ድረስ በጾም፣ በጸሎት፣ በመዝሙር እና በመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ በቤተክርስትያን ውስጥ ተሰባስበን እናስበዋለን። ክርስቶስ ስለእኛ ብሎ ደሙን እያፈሰሱ፤ የሾህ አክሊል እየደፉ ምራቅ እየተፉበት እያንገላቱት የተጓዘውን ጉዞ፣ስቃይ እና መከራ እኛም እንካፈላለን በማለት የምናደርገው ትልቅ የጸሎት እና አስተንትኖ ጊዜያችን ነው።
የዓብይ ጾም ወቅት በድጋሚ ንስሐ የምንገባበት ወደ እግዚአብሔር የምንመለስበት፣ ቀድሞ ከነበረን ከእግዚአብሔር መንገድ ርቀን የምንኖር ከሆነ ወደ መንገዱ ተመልሰን የምንኖርበት ወቅት ነው።
“ዮሐንስም ተላልፎ ከተሰጠ በኋላ ኢየሱስ የእግዚአብሔርን መንግሥት ወንጌል እየሰበከና፡ ‘የእግዚአብሔርም መንግሥት ቀርባለች ንስሐ ግቡ በወንጌልም እመኑ’ እያለ ወደ ገሊላ መጣ” (ማር 1፡14-15)። ከዚህ የማርቆስ ወንጌል የምንረዳው ነገር ቢኖር በዐብይ ጾም ወቅት የእግዚኣብሔር መንግሥት መምጣት በጉጉት በመጠባበቅ ይህንን የሚመጣውን የእግዚኣብሔር መንግሥት ተገቢ በሆነ ሁኔታ መንፈሳዊ ዝግጅቶችን በማድረግ መቀበል እንችል ዘንድ መንፈሳዊ ዝግጅት የምናደርግበት ነው።
የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን የዐብይ ጾምን የምንጀምረው ግንባራችንን በአመድ የመቀባት መንፈሳዊ ሥርዓት በመፈጸም በሰራነው ኃጢአት በመጸጸት ወደ ንሰሐ በመመለስ፣ መንፈሳዊ ለውጥ በማምጣት ሕይወታችንን ለእግዚኣብሔር የተገባ እንዲሆን በማድረግ ነው።
ስርዓቱ የሚከናወነው አምና አክብረነው በነበረው የሆሳዕና በዓል ወቅት “ሆሳዕና ለእግዚኣብሔር ልጅ ምስጋና” በማለት የወይራ ዛፍ ዝንጣፊ ይዘን የዘመርንበትን የወይራ ዛፍ ዝንጣፊ ደርቆ እንዲቃጠል ይደረግና ይህ ዐመድ ለአንድ ዓመት ያህል እንዲቀመጥ ተደርጎ ዐመዱ ዐብይ ጾም ከመጀመሩ በፊት ባለው ረቡዕ ቀን ላይ በሚደረገው የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ላይ ቅዱስ ወንጌል ተነቦ ስብከት ከተደረገ በኋላ በቀሳውስት አማካይነት በሚደረግ መንፈሳዊ ሥነ-ሥርዓት በምዕመኑ ግንባር ላይ ይቀባል።
ይህ አመድ የመቀባት ሥነ-ሥርዓት የሚፈጸመው ምዕመኑ በሰራናቸው ኃጢአት መጸጸቱን እና በትህትና ዝቅ ማለቱን ለመግለጽ እና በቀጣዮቹ 40 ቀናት የዐብይ ጾም ወቅት ውስጥ በጸሎት፣ በጾም እና ምጽዋዕት በመስጠት መንፈሳዊ የሆነ እውነተኛ ለውጥ በማምጣት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የትንሳሴ በዓል ወቅት በኃጢአታችን ምክንያት ተቀብረንበት ከነበረው መጥፎ ሕይወት ተላቀን፣ ከኃጢአታችን ነጽተን፣ ከእርሱ ጋር ከሞት ወደ ሕይወት መሻገር የሚያስችለንን ጸጋ ይሰጠን ዘንድ ይህንን ጸጋ እንድንጎናጸፍ በሚረዳን መልኩ የዐብይ ጾም ወቅትን በተገቢው መልኩ መጠቀም እንድንችል እንዲያስችለን ነው።
ይህ ዐብይ ጾም ከመጀመሩ በፊት በዐመድ ግንባርን የመቀባት መንፈሳዊ ሥርዓት ዐመዱ በጸበል ከተባረከ እና ይህንን መንፈሳዊ ሥነ-ስርዓት በተመለከተ የተዘጋጀው ጸሎት ከተደረገ በኋላ ምዕመኑ በሰልፍ ወደ ካህኑ በመምጣት ካህኑ “አንተ አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ!” የሚለውን ቃል በመድገም በምዕመኑ ግንባር ላይ የተባረከውን እና በጸበል የተለወሰውን አመድ የመስቀል ምልክት በማድረግ ይቀባዋል። በዚህ መልኩ የዐብይ ጾም በይፋ መጀመሩ ይገለጻል።
በመስቀልና በትንሣኤው የተሰበረው ይጠገናል፤ የደከመው ይበረታል፤ የወደቀው ይነሣል፤ የተሸነፈው ያሸንፋል ይህንንም ለማክበር በትንሣኤው እንሰበሰባለን። የአምልኮ ሥርዓታችን በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ላይ የተመሠረተ ነውና። መስዋዕተ ቅዳሴ በመስቀልና በትንሣኤው አዲስ ፍጥረት መሆናችንን የምናከብርበት በዓል ነው። በመስቀሉና በትንሣኤው እግዚአብሔር እራሱን ከዓለም ጋር አስታርቋል። ቅዱስ ጳውሎስም የማስታረቅን ምስጢር በሰፊው አስተምሯል። ክርስቲያን የዚህ የዕርቅ መሣሪያ መሆኑን ገልጾልናል። በምድር ላይ ያሉ ውብ ነገሮች እውነተኛውን ውበት የሚላበሱት በትንሣኤው ብርሃን ነው። የተስፋ ጭላንጭል ደምቆ የወደፊቱን የሚገልጠው የፍቅር እሳት ከጫፍ እስከ ጫፍ ተስፋፍቶ የሚቀጣጠለው የእምነት ብርሃን ጠቢባንን የሚወልደው በትንሣኤው ብርሃን ነው።
አዲስ ዘመን፡- ዛሬ የሚከበረው ጸሎተ ሐሙስ በካቶሊካውያን ዘንድ የሚሰጠው ትርጓሜ ምንድን ነው፤ እንዴትስ ባለ መንገድ ይከበራል ?
አባ አማኑኤል፡- ጸሎተ ሀሙስ እኛ ካቶሊካውያን በሰሞነ ሕማማት ትላልቅ ነገሮች እንደተፈጸሙ እናምናለን። ድርጊቶቹን እኛ በመፈጸም በክርስቶስ ላይ የደረሱ መከራዎችን እንካፈላለን። ጸሎተ ሐሙስ ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታም አገልጋይም እንደሆነ ያሳየበት ትልቅ ቀን ነው። ይህን ጌታ ሆኖ እንደ አገልጋይ ዝቅ ብሎ የደቀመዛሙርቱን እግር በማጠብ ገልጾታል። ይህ ለእኛ ትልቅ አንድምታ አለው። እግራቸውን ካጠበ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ የተናገረው ነገር አለ። እናንተ ጌታ እያላችሁ የምትጠሩኝ እኔ እግሮቻችሁን ካጠብኩኝ እናንተም እርስ በእርሳችሁ እንዲሁ አድርጉ ብሏቸዋል። ዝቅ ብለን ራሳችንን በማዋረድ ሌሎችን ማገልገልና ሌሎችን መንከባከብ እንደሚገባን ክርስቶስ ራሱ በተግባር ያሳየበት ቀን ነው። በተጨማሪም ጸሎተ ሐሙስ ክርስቶስ ቅዱስ ቁርባንን የመሰረተበት ቀን ነው። የመጨረሻ እራት ስርዓትን የሠራበት ቀን ነው ብላ ቤተክርስቲያናችን ታምናለች።
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጸሎተ ሀሙስን በተለያዩ መርሃግብሮች ታከብረዋለች። ከጠዋት ጀምረን በቤተክርስትያን እንሰባሰባለን። ጳጳሶች፣ ካህናቶች እና ምእመናን ባሉበት በቅድሚያ የመጀመሪያውን ቅዳሴ በካቴድራል እናደርጋለን። ተሰብስበን ቅዳሴውን እንዳደረግን ሚስጥራቶች ፣ ቅባተ ክርስቲያን ፣ ቅብዓ ቅዱስ ሜሮን፣ ቅብኣተ ጥምቀት እንዲሁም ቀንዲል ወይም ቅብዓተ ሕሙማን የሚባረኩበት ቀን ነው። ስለዚህ በዚህ ቀን ሁሉም ምእመን ከየአቅጣጫው ወደ ካቴድራል ይመጣል። የየሀገረ ስብከቱ ጳጳስ የካህናቶችን እግር ያጥባል። ክርስቶስ እንዳደረገው ዝቅ ብሎ ካባውን በማውለቅ ተከታዮቹን ያጥባል።
ቅዳሴው እንዳለቀ ሁላችንም ሦስቱን ቅብዓ ቅዱሶች በመያዝ በቁምስና ወደ ምናገለግልበት ደብራችን እንመለሳለን። ከዚያ በካቴድራል መገኘት ላልቻሉት ምእመናን ከሰዓት በኋላ ወደ 10 ሰዓት አካባቢ ተሰባስበን በየደብራችን ቅዳሴ እናደርጋለን። ክርስቶስ ያደረገውን ጳጳሱ እንዳደረገው ሁሉ ካሕኑም ደግሞ በቁምስናው 12 ሰዎችን ከሕጻናቶች፣ ከወጣቶች፣ ከእናቶች እና ከአባቶች ሁሉ በመምረጥ እግራቸውን ያጥባሉ።
አዲስ ዘመን፡- ከጸሎተ ሐሙስ በኋላ የሚመጡት በዓለ ስቅለት እና የእለተ ትንሳኤ ዋዜማ ለካቶሊካውያን ምን ማለት ናቸው፤ እንዴት ባሉ ሃይማኖታዊ ተግባራት ይታሰባሉ ?
አባ አማኑኤል፡- ስቅለት ትልቅ ትርጉም ያለው ቀን ነው። ምክንያቱም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሁሉ ቤዛ በመሆን የተሰቀለበት ቀን ነው። ስቅለት የክብር ባለቤት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ዓለም ድኅነት በሥጋ በመስቀል የተቸነከረበት ዕለት ነው። ፈጣሪዋ በዕንጨት መስቀል ላይ ተዘርግቶ ተሰቅሎ በአየችው ጊዜ ፀሐይ ጨለመች፤ እርሱም ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም የነሣትን ለባዊት ነባቢት የሆነች ነፍሱን ከሥጋው ለያት ሐዋርያ ጴጥሮስ በሥጋ የሞተ ሲሆን በመለኮት ሕያው ነው እንዳለ ነፍሱ ከመለኮት ሳትለይ ከሥጋ ተለየች በዚያ ጊዜ ሥጋ ከመለኮት ሳትለይ በዕንጨት መስቀል ላይ ተሰቅሎ ነበር።
እንዲሁም ነፍስ ከመለኮት ጋራ አንድ ሁና እሥረኞች ነፍሳትን ትፈታቸው ዘንድ ወደ ሲኦል ወረደች። እርሱ ከሰማያት በላይ ከፍ ከፍ ያለ ልዑለ ባሕርይ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ በጌትነቱ ዙፋን ተቀምጦ ያለ ለእርሱም ምስጋና የክብር ክብር ገንዘቡ የሆነ ራሱን ሠውቶ ያዳነን የመንግሥቱን ደጆች በፈሳሽ ደሙ ከፈተልን።
ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ እስከ አንድ ሰዓት ባለው ጊዜ ሁሉም ምዕመን በቤተ ክርስትያን ይሰበሰባል። ከዚያም ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ጀምረን እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት ባለው የስግደት ስነስርዓት የሚካሄድበት መርሃግብር ይኖረናል። ግብረ ሕማማት የሚባል የዓርብ ስቅለትን የያዘ ስርዓት አለን በዚያ ተመርኩዘን ሕጻናት፣ ወጣቶች፣ አዛውንቶች፣ ካሕናቶች፣ ሲስተሮች፣ እናቶችና አባቶች በተገኙበት በጸሎትና በመዝሙር ስቅለተ ዓርብን እናሳልፋለን። ክርስቶስ ስለእኛ ብሎ በአሰተና ምስክሮች ተከሶ ደሙን ያፈሰሰበት የእንጨት መስቀል የተሰቀለበት እና እኛን ለማዳን ብሎ ራሱን የሰዋበት ቀን እንደመሆኑ በስግደት፣ በጸሎት እና በመዝሙር እናሳልፈዋለን ማለት ነው።
ከሰሞነ ሕማማት መጨረሻ ቀን በኋላ እንዲሁም ከትንሳኤው በፊት ያለችው ቅዳሜ ቀን ቀዳም ስኡር፣ ለምለም ቅዳሜ እና ቅዱስ ቅዳሜ እየተባለች ትጠራለች። ቀዳም ስኡር በመባል የምትጠራበት ምክንያት ካህናቶች በምእመናን ቤት በመዞር ሰላም ለእናንተ ይሁን በየአይሁድ በደልና ወንጀል ተፈጽሞበተ የነበረው ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነገ ደግሞ በትንሳዔ እንደዚህ ሳር የለመለመ ሕይወት ይሰጠናል በማለት ለምለም ሳር ቄጤማ የሚያድሉበት ቀን ስለሆነ ነው።
ካህናት ለሕዝበ ክርስቲያኑ ቄጤማውን የሚሰጡት “ገብረ ሰላም በመስቀሉ” ይላሉ። ትርጓሜውም በመስቀሉ ሰላምን መሰረተ፤ በመስቀሉ ሰላምን ፈጠረ
የምስራች አለን የሚል ነው። ስለዚህ ክርስቶስ በመስቀሉ ሰላምን እና እንድነትን ሰጥቶና በማለት ምዕመናንት ቀኑን እንዲያስታውሱት እናደርጋለን። አስቀድመን ግን ጠዋት ላይ ቅዳሴ ይኖረናል። ከቅዳሴው በኋላ ነው የምስራች ምልክት የሆነውን ለምለም ቄጤማ በመያዝ ወደ ምዕመናን ቤት የምንሄደው።
ከቅዳሜ ዕኩለ ሌሊት በፊት ባለው ጊዜ ወጣቶች በቤተክርስትያን በመገኘት መዝሙሮች፣ ድራማዎች እና መነባንቦች ያቀርባሉ። ሥድስት ሠዓት ላይ ለሚጀምረው ቅዳሴ ቀደም ብሎ የሚመጣው ህዝብ ዝግጅቶችን ይከታተላል። ከቅዳሴው በፊት ዑደት ይኖረናል። ከዑደቱ በኋላ ልክ ስድስት ሰዓት ሲሆን የፋሲካ በዓል ቅዳሴያችንን እንጀምራለን። እስከ ሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ቅዳሴ ላይ እንቆያለን። ቅዳሴው ሲጠናቀቅ “ክርስቶስ ተንስአ እሙታን በዓቢ ኃይል ወሥልጣን አሰሮ ለሰይጣን አግዓዞ ለአዳም ሰላም እም ይእዜሰ ኮነ ፍስሐ ወሰላም” በማለት ሕዝቡ ሰላምታ በመለዋወጥ ወደ ቤቱ ይሄዳል። ትርጓሜውም ክርስቶስ ሰላምን ሰጥቶናል፤ ሰይጣንን አስሮታል አዳምን አግዟል የሚል ነው። ምእመኑ መስቀል እየተሳለመ ነው ወደ ቤቱ የሚያመራው።
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን አስተምዕሮ ዕለተ ትንሳኤ እንዴት ይገለጻል ?
አባ አማኑኤል፡- ትንሳኤ በዋናነት የመሻገር በዓል ነው። በክርስቶስ ማመን ከሞት ወደ ሕይወት፤ ከጨለማ ወደ ብርሃን እንዲሁም ከሠይጣን መንግሥት ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የተሸጋገርንበት ነው። ከሰይጣን ባርነት ነጻ የወጣንበት ዕለት ስለሆነ ክርስቶስን በተለያዩ መንገዶች እናከብርበታለን።
የትንሣኤ በዓል የክርስቲያን ሕይወት መሠረትና ምሶሶ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳለው ትንሣኤ ባይኖር እምነታችን ከንቱ በሆነ ነበር። ከሁሉም በላይ የሚታዘንልን ሰዎች በሆንን ነበር። ቅዱስ ጳውሎስ መልዕክቱን የጻፈው በቆሮንጦስ ክርስቲያኖች መካከል ትንሣኤን የሚጠራጠሩ ሰዎች ስለነበሩ ነው፤ በሌላ አነጋገር ትንሣኤን እየካዱ ወይንም እየተጠራጠሩ ክርስቲያን ነን ማለት ትርጉም እንደሌለው እያስተማረ ነበር ማለት ነው።
ሰውን በመልኩና በአምሳሉ የፈጠረ ጌታ አሁንም ሰውን በትንሣኤው አዲስ ፍጥረት አደረገው። ሰውን በመልኩና በአምሳሉ መፍጠሩ ብዙ ያስተምረናል። የተለየ ቦታና ኃላፊነት ለሰው እንደተሰጠ ያሳየናል። ትንሣኤው ደግሞ ሰውን በሙሉ በድጋሚ ወደ አንድ ማምጣቱን ያሳየናል። ትንሣኤ በሰው ውድቀት የተጨማደደውን መልክ ያስተካክላል። ትንሣኤ ሁሉንም ነገድ፤ ሁሉንም ቋንቋ፤ ሁሉንም ባሕል ወደ አንድ ያመጣዋል። ትንሣኤ የጎደለውን ይሞላል። የተረሳውን ያስታውሳል። የሕይወትን ወሳኝ ጥሪ ወደ ትክክለኛው ቦታ ይመራዋል። የትንሣኤው የምሥራች ከምንም በላይ የምርምር ውጤት ሳይሆን የእምነት ፍሬ ነገር መሆኑንም ማስተዋል ያሻል። ትንሣኤን መስበክ የተቀበሉትን እምነት ማስተላለፍ ነውና።
ቅዱሳት መጽሐፍ ስናነብና ስናሰላስል በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ብርሃን የምናይበት ወቅት ያስፈልገናል ማለት ነው። ስለዚህ የሰውን ልጅ ታሪክም ሆነ የራሳችንን ታሪክ እንዲሁም በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ብርሃን ልንቃኘው ያሻል። በዚያን ወቅት አዲስ መረዳትን እናገኛለን። ዘመናችንን በልዩ ብርሃን እንረዳለን። የታሪክ ትርጉማችንንም ይቀይራል፤ ለሕይወትም የምንሰጠው ትርጉም ሙላትና በረከት ይኖረዋል። ምናልባት መልስ ያጣንባቸው እንቆቅልሾች መልስ ያገኛሉ። ሐዋርያት ክርስቶስን እስከ ቀራንዮ ድረስ መከተል ከብዷቸው ሸሽተው ነበር። በድፍረት ወጥተው መመስከር የቻሉት በትንሣኤውና በጰራቅሊጦስ ምስጢር የተነሣ ነው። ቀራንዮና የመስቀል ሞት ያለትንሣኤ አሁን ያለውን ትርጉም ባላገኙ ነበር። የወንጌል የምሥራች የተገለጠው በክርቶስ ትንሣኤ ነው።
የመጀመሪያ የምናደርገው ካህን በየቤቱ እየዞረ ሰላም ለእናንተ ይሁን ክርስቶስ ከሞት ተነስቷል እያለ ክርስቶስ ከሞት መነሳቱን የሚያበስሩ የተዘጋጁ ጸሎቶችን ያደርሳል። ከዲያቆናቶች ጋር በመሆን የምእመናን ቤትን በመጎብኘት ምእመኖችን ማበረታታት ትልቁ የእኛ የካህናት ሥራ ነው። በየቤታቸው በመሄድ ከቤተክርስቲያን የጠፉ እና ከንስሃ የራቁ ሰዎችን እንደጠፉት በጎች ክርስቶስ አንዱን በግ ለመፈለግ ዘጠና ዘጠኙን በርሃ ላይ ጥሎ እንደመጣ ሁሉ ሕይወታቸው እንዴት እንደሆነ እና እንዴት አድርገው እንደሚኖሩ በመመልከት ወደ ቤተክርስቲያን እንዲመጡ ጥሪ ታስተላልፋለች። ቢዘህ ጊዜ ቤተክርስትያናችን ባላት አቅም ከራሷ እና ሕዝቡን በማስተባበር አቅመ ደካሞችን ትረዳለች። ጾሙን ለመፍታት የማይችሉ ማሕበረሰቦችን በመጎብኘት ጾሙን የሚፈቱባቸውን ነገሮች ታድላለች። በአጠቃላይ ትንስዔ ከሞት በኋላ በሕይወት መኖር እንደሆነ ቤተክርስትያናችን ታስተምራለች።
ከትንሳኤ በኋላ ያሉትን እሁዶች ቤተክርስትያናችን ዳግማዊ ትንሳኤ በቅጽል ስሙ ዘቶማስ፣ ትንሳኤ ሦስተኛ እሁድ፣ ትንሳኤ በአራተኛ እሁድ እያለች እስከ እርገት ወይም በአለ አርባ ድረስ ያሉትን ጊዜያት የክርስቶስን መነሳት ትዘክራለች። በቤተክርስትያናችን በዓለ አርባ ሁልጊዜም ሐሙስ ቀን ነው የሚውለው። ነገር ግን ቡዙ ጊዜ ሐሙስ ቀን ምዕመናን በሥራ ላይ ስለሚያሳልፉ ዕለቱን ሁሉም ምእመን በሚገኝበት እሁድ ቀን ታከብረዋለች። ሐሙስም ዕለት ታከብረዋለች ነገር ግን እሁድ ቀን ሕዝቡ ተሰብስቦ ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰማይ ያረገብትን ቀን ታከብራለች። ከዚያም ደግሞ በትንሳኤ ስምንተኛ እሁድ ጰራቅሊጦስ በማለት ክርስቶስ በኃዋሪያቶቹ ላይ መንፈስ ቅድሱን የላከበትን እና ወደ ዓለም ሄዳችሁ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችሁ የእኔ ደቀመዛሙርት አድርጓቸው በማለት ትዕዛዝ የሰጠበትን ዕለት እናከብረዋለን። ሐዋሪያት ከዚያች ዕለት አንስተው በመንፈስ ቅዱስ ተሞልተው ወደ ዓለም ሁሉ በመሄድ ክርስትናን ሰብከዋል።
አዲስ ዘመን፡- ምእመናን ከኢየሱስ ክርስቶስ ስቃይ እና ፍቅር መቅዳት የሚገባቸው የሕይወት መርህ ምንድ ነው ?
አባ አማኑኤል፡- ኢየሱስ በቀያፋና በጲላጦስ ፊት ጠላቶቹ አይሁዳውያን በሐሰት ሲከሱት አልተከላከለም። አፉን ዘግቶ ዝም አለ፤ በዚህም ጲላጦስ ሳይቀር ስለገረመው «አትመልስምን?» አለው። ኢየሱስ ዝም ማለቱ በደል ኖሮት ወይም ደግሞ መከላከል አቅቶት አልነበረም ስላልፈለገ ብቻ ነው። አይሁዳውያን ደጋግመው በሐሰት ይከሱት ነበር። እርሱ ግን ሐሰተኛ ክሳቸውንና ስድባቸውን ዝም ብሎ ተቀበለው። እኛ ግን እንኳንስ ሳንበድል በድለንም ቢሆን ሰው ሲከሰን በጣም እናዝናለን፤ ከክሱ ነጻ ለመውጣትና በጥፋተኛነት ላለመጠየቅ አቅማችን በፈቀደል መጠን ራሳችንን እንከላከላለን፤ የሚከሰንንም ሰው እንጠላዋለን። የክርስቶስ መንፈስ ይህ ነው ወይ? የኛ አስተሳሰብና መንፈስ ጌታ ከተወልን የሚያስደንቅና የሚገርመን መልካም አብነት፣ ትዕግስት፣ ዝምታ፣ ትሕትና እንዴት ይስማማል? የእርሱን አብነት ተከትለን መንፈሳችንን እንቀይር፣ ክርስቶስን እንምሰል፣ የሰላም ወዳጆች በመሆን ፍቅርን እንጠብቅ።
አይሁዳውያን ኢየሱስን ከያዙት በኋላ እንደ ትልቅ በደለኛ አስረው እያዋረዱና እየሰደቡ ወሰዱት። እርሱ ግን እንደ በግ አንድም ቃል ሳይናገር ተከተላቸው። አምላክ ሳለ ፍጥረቶቹ ሲቀልዱበትና ሲዘባበቱበት ዝም ብሎ ተመለከታቸው፣ ንጹሕ ሳለ እንደ በደለኛ ተቆጠረ። እንዴት ያለ ትህትና ነው? እኛን ሰው ሲበድለን በፍጥነት እንቆጣለን፣ እንነቅፋለን፣ ብርቱ ውርደት ሆኖ ይሰማናል፣ በልባችን ቂም እናሳድራለን፤ ክርስቶስን መምሰል አለብን።
ጲላጦስ አይሁዳውያንን ፈርቶ ኢየሱስን በደል ሳይኖረው ሞት ፈረደበት፣ ኰነነው። እኛም ብዙ ጊዜ እንደዚህ እናደርጋለን፣ ከኢየሱስ ይልቅ ሰዎችን ፈርተን ኢየሱስን እንክዳለን፤ ሰዎችን ለማስደሰት ብለን ኢየሱስን እናሳዝናለን። በኃጢአታችን ብዛት እንደገና በኢየሱስ ሞት እንፈርድበታለን። ኢየሱስ ስለእኛ ይህን ሁሉ ውርደትና መከራ ተቀብሎአል። ለደኀንነታችን ብሎ ሲፈርዱበትና ሲያዋርዱት ዝም ብሎ ተመለከታቸው። ፍቅሩንና ስቃዩን በልባችን ውስጥ እናትመው። ሁለቱንም ዘወትር እያሰብን ከሁሉ አስቀድመን ወደ ኃጢያት እየተመላለስን አናሳዝነው፣ ቀጥለን ደግሞ እርሱ እንደ ወደደን እንድንወደው ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።
መከፋፈል፤ መድሎ፤ ምቀኝነት፤ ጭካኔ የተፈጠርንበት ዓለም አይደሉም። አፍራሽ ሐሳብ፤ ጎጂ ንግግርና ተግባር ከተፈጠርንበት ዓላማ እጅግ የራቁ ነገሮች ናቸው። እውነተኛ መፍትሔዎች የሚመጡት ከእግዚአብሔር ነው። ወደ መስቀሉ ስንቀርብ ወደ ትንሣኤውም እንቀርባለን። መስቀል መሸሸጊያችን ሲሆን ትንሣኤም እንዲሁ አምባችን ይሆናል። ምክንያቱም እግዚአብሔር በመስቀልና በትንሣኤው አማካኝነት አዲስ ኪዳንን፤ አዲስ ፍጥረትን፤ እውነተኛ እርቅን አምጥቷልና ነው።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ እምነት እንዳላቸው ያውቃል፣ ጥያቄው ግን ማዕበል ሲነሳ ጭንቀት በሕይወታችሁ ውስጥ ሲነግስ ለመልሳችሁ እምነታችሁን ለምን አትጠቀሙበትም የት ነው ያለው ማለቱ ነው። እኛም ዛሬ እንደ ግለሰብም ሆነ ማሕበረሰብ ላለንበት ሁናቴ በእምነታችን አማካይነት መልስ ልናገኝለት ይገባል። ችግሩ የኑሮ ውድነቱ፣ ውጣ ውረዱ፣ ለመኖር ተስፋ የሚያስቆርጡ ሁኔታዎች ሁሉ መልስ ልናገኝላቸው የሚገባው ከእምነታችንና ነገሮችን ሊያቀና ከሚችለው አምላካችን በመተማመን ሊሆን ይገባል፤ የምናመልከው አምላክ ከገዘፉብን አስጨናቂ ነገሮች ይበልጣልና በጸሎታችንና በጾማችን እምነት ጨምርልን በማለት እንማጸነው።
አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻ በዓሉን በተመለከተ የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ ዕድሉን ሰጥቼዎታለሁ።
አባ አማኑኤል፡-ሰዎች ሁሉ ወደ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲመለከቱት ቤተክርስቲያን ዛሬም ትጋብዛለች። ኢየሱስ በልባችን እንዲኖር ከፈቀድንለት፣ ምንም ዓይነት የውድቀት ወይም የሐዘን ልምድ፣ ምንም ያህል ስቃይ መከራ ቢሆንም፣ የእኛ የሕይወታችን ዕጣ ፈንታ ሁሌም ጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲሆንልን ጥረታችን መቀጠል አለበት።
በትንሣኤው ጌታ እንድንነሳ ከፈቀድን ምንም መሰናክል፣ መከራ ወይም ሞት ወደ ሕይወት ሙላት የምናደርገውን ዕድገት ሊያቆመው አይችልም። የእኛ ፋሲካ፣ የሕይወት አምላክ የሆነውን ጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንኳን ደህና መጣህ በማለት እኛ እሱን “አዎ” በማለት፣ ምንም ድንጋይ የልባችንን መንገድ አይዘጋውም፣ የትኛውም መቃብር የልባችንን ደስታ አይገድበውም።
በትንሣኤ በዓል መላው ምዕመናን ልናደርገው የሚገባን የተቸገሩትን ወገኖች በመርዳትና በመተሳሰብ፤ ያዘኑትን በማጽናናትና በማሰብ እንድታከብሩና ደስታቸውንም ፍፁም እንድታደርጉ ፀጋችሁንም እንድታበዙ አደራ ማለት እወዳለሁ። የሰላም ባለቤት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓሉን የደስታና የምሕረት በዓል ያድርግልን። ለሕዝቦቻችንና ለአገራችንም ሰላሙን ይስጥልን።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ!
አባ አማኑኤል፡- እኔም አመሰግናለሁ!
ተስፋ ፈሩ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 9 ቀን 2017 ዓ.ም