
ግብጾች የዓረቡን ዓለም ሚዲያ በሙሉ በግል ተቆጣጥረው ቆይተዋል። በዚህም ኢትዮጵያን የተመለከቱ ሀሰተኛ መረጃዎችን በማሰራጨት የዓረቡ ዓለም ሕዝብ ስለሀገራችን የተሳሳተ አረዳድ እንዲኖረው ለማድረግ ሰርተዋል። ባለፉት አራት ዓመታት ጥቂት በጎ ፈቃደኛ ኢትዮጵያውያን በአረብኛ ቋንቋ በሚሰራጩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በመቅረብ እና በተለያዩ ማሕበራዊ ድረ ገጾች ላይ በመውጣት የኢትዮጵያን ትክክለኛ ገጽታ የሚያሳዩ መረጃዎችን ማጋራት ጀምረዋል፡፡
እነዚህ በጣት የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በተናጠል ያደረጉት እንቅስቃሴ አስገራሚ በሆነ ደረጃ የዓረቡ ዓለም ሕዝብ ኢትዮጵያን የሚመለከትበትን መነጽር እንዲቀይር ማስገደዱን ብዙዎች ይስማሙበታል። ለመሆኑ ኢትዮጵያውያን በዓረቡ ዓለም ሚዲያዎች በመውጣት በዓባይ ግድብ እና በሌሎችም ጉዳዮች የሀገራቸውን አቋም የሚያንጸባርቁ ሙግቶችን ማድረግ የጀመሩበት ሂደት ምን ይመስላል፤ ምን ያህልስ ውጤታማ ሆነዋል ?
በዓረቡ ዓለም ሚዲያዎች በመቅረብ የኢትዮጵያን አቋም በማንጸባረቅ ከሚታወቁት ተሟጋቾች አንዱ የሆኑት አቶ ሙሳ ሼኮ እንደሚናገሩት፤ እንደ አልጀዚራ፣ ስካይ ኒውስ አረቢያ፣ አልአረቢያ እና አል አረቢያ ላሃደስ ያሉ ትላልቅ የዓረቡ ዓለም ሚዲያዎችን በባለቤትነት የሚያስተዳድሯቸው ሌሎች ቢሆኑም በሙያተኝነት ተቀጥረው የሚዘውሯቸው በሙሉ ግብጾች ናቸው። እስካሁንም ትልቁ ተግዳሮት ሆኖ የቀጠለው ይህ ነው። አልጀዚራ ውስጥ ፈላጭ ቆራጭ ሆነው ነገሮችን ሁሉ የሚያንቀሳቅሱት ግብጻውያን ናቸው። 22 የዓረብ ሀገራት ውስጥ የሚገኘው ሕዝብ አንድ ቋንቋና ተመሳሳይ ባሕል የሚከተል ሕዝብ ነው። የእነዚህ ሀገራት ሕዝብ ሁሉ በዋነኝነት መረጃ የሚያገኘው ከአልጀዚራ ነው። ግብጻውያን ይህን የሚያክል መድረክ ላይ ፕሮግራም አቅራቢም አዘጋጅም እንግዳም ሆነው መጥተው ስለኢትዮጵያውያን የፈለጉትን አውርተው ደምድመው ይሄዱ ነበር። የሚቃወማቸው አካል ስላልነበር የ22 ሀገራት ሕዝብ በዚህ መንገድ የሚያገኘውን የውሸት መረጃ ተቀብሎ ሲኖር ነበር።
አቶ ሙሳ የኢትዮጵያ እውነት በዓረቡ ዓለም ሚዲያዎች መንጸባረቅ የጀመረበትን ሂደት ሲተርኩ፤ በአውሮፓውያን አቆጣጠር 2019 አካባቢ በዲጂታል ፕላትፎርም በማሕበራዊ ድረ ገጾች የተወሰንን ሰዎች መጻፍ ስንጀምር ደነገጡ። ጽሁፋችን እየበዛ ሲሄድ ግብጻዊ ያልሆኑ እንዲያውም የሚቃረኗቸው የዓረብ ሀገራት ጋዜጠኞች ጽሁፎቻችንን በማየት ከእኛ ጋር የመቀራረብ ፍላጎት አደረባቸው። ከዚያ በግል እነማን ማን ናችሁ? ኢትዮጵያዊያውያን ናችሁ ወይ ? የሚሉ ጥያቄዎችን በማንሳት ከእኛ ጋር መነጋገርና መግባባት ጀመሩ። እንዲህ ባለ መንገድ በተፈጠረ ግንኙነት መሀመድ አል አሩሲ ለመጀመሪያ ጊዜ አልጀዚራ ላይ ወጣ። ግብጾች ይሄ ሰውዬ ዓረብ እንጂ ኢትዮጵያዊ አይደለም በሚል የስም ማጥፋት ዘመቻ ጀመሩ። እርሱን ተከትለን አንድ ሶስት የምንሆን ሰዎች ብቅ አልን። ግብጾች ተቆጣጥረዋቸው ሲፈነጩባቸው በቆዩት በአረብኛ ቋንቋ በሚሰራጩ ሚዲያዎች ላይ ትልቅ ፍልሚያ ጀመርን ይላሉ።
መሀመድ አልአሩሰሲ በአልጀዚራ ላይ መቅረቡን ተከትሎ እርሳቸው ቲአርቲ በሚባል በአረብኛ የሚሰራጭ የቱርክ ጣቢያ ላይ መቅረባቸውን የሚገልጹት የፖለቲካ ተንታኙ፤ በጣቢያው ላይ ከታየው በኋላ በማግስቱ ወደ 19 ያህል የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ደወሉልኝ። በሁለተኛ ቀን ተሳትፎዬ ከቀድሞ የሱዳን ውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ጋር ተከራካሪ ሆኜ ቀረብኩ። በወቅቱ ትልቅ አንድምታ ነበረው። እዚህ እኛ ሀገር ውስጥ አረብኛ ቋንቋ ብዙ ሽፋን ስለሌለው አልታየም። በአረቡ ዓለም ግን ትልቅ ረብሻ አስነስቷል። ምክንያቱም ቀደም ብለን ተነጋግረን ምን ማድረግ እንዳለብን ተዘጋጅተንበት ነበር። በግላችን በዓባይ ግድብ በሚደረገው ድርድር ላይ የሚሳተፉ ተደራዳሪዎችን እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን አነጋግረን የኢትዮጵያን አቋም የሚገልጹ የተወሰኑ መረጃዎችን ሰብስበን ነበር። ቀጥሎ ደግሞ ኡስታዝ ጀማል በሽር መጣ። ዛሂል ዚዳል፣ አብዱል ሽኩር እና ሌሎችም መጡ። በማለት የትግላቸውን አጀማመር ያወሳሉ።
በመገናኛ ብዙሀን ላይ ጊዜው ስለማይበቃ በጽሁፍ እና በቲተር ስፔስ ላይ ትልቅ ክርክሮችን ማካሄድ ችለናል። አንዳንድ ሰዎች እኛ የምናደርገው ትግል በሁለት ቀን እና ሦስት ቀን ብቅ እያልን የሚደረግ ይመስላቸዋል። እንደዛ አይደለም ረጅም ሰዓት ወስደን ማታ እስከ ዘጠኝ ሰዓት በመቆየት ሌሊቱን ሙሉ በቲተር ሜዳ ላይ ስለኢትዮጵያ ማወቅ ለሚፈልጉ አረቦች መረጃ የመስጠት ሥራ ነው የምንሠራው። እነ ኳታር በዚያን ጊዜ ከግብጽ ጋር ትንሽ የፖለቲካ ልዩነት ስለነበራቸው በተቃራኒ ቆመው ስለነበር ከእኛ ጎን ተሰልፈዋል። በዚህ ላይ አልጀዚራ ትልቅ ሚና ተጫውቷል። ዓለም አቀፍ ሚዲያ ወደ አንድ ሀገር ሲመጣ የራሱ አጀንዳ አለው። እኛ የሰራነው አጀንዳውን መቶ በመቶ እንዳይጭንብን ሃምሳ በሃምሳ እንዲሆን ማድረግ ላይ ነው እየሰራን ያለነው። የእኛንም ሀሳብ እንዲቀበሉና የራሳቸውን አጀንዳ በተቻለ መጠን እኛን በማይጎዳ መልኩ እንዲያስኬዱ በማድረግ በደምብ ሰርተናል ሲሉም ያክላሉ።
ባለፉት አራት ዓመታት መሀመድ አል አሩሲን ተከትለን የወጣን በጣት የምንቆጠር ኢትዮጵያውያን ተናበን በሠራነው ሥራ ኢትዮጵያ ማን እንደሆነች የአረቡ ዓለም በአግባቡ በመረዳቱ ግብጾች ተሰብረዋል የሚሉት የፖለቲካ ተንታኙ፤ በአረቡ ዓለም ሚዲያዎች ላይ በተደጋጋሚ በመቅረብ የሀገራችንን አቋም በሰፊው ማንጸባረቅ በመቻላችን የብዙዎችን ዐይን መግለጥ ችለናል። በአሁን ሰዓት በቋሚነት በአረቡ ዓለም ሚዲያዎች ላይ በመቅረብ ስለኢትዮጵያ መሟገትን መደበኛ ሥራ አድርገን የያዝን ስድስት እንሆናለን። ሌሎች ደግሞ በዋትስ አፕ እና በቲውተር ግሩፕ ላይ የሚሠሩ ብዙ አሉ። በተጨማሪም በሰሜን አሜሪካ እና በአውሮፓ ካሉ ወንድሞቻችን ጋር ብዙ ውይይቶችን አድርገናል። ይህ እንቅስቃሴ የመንግሥትን ትኩረት መሳብ ችሎ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰብስቦ እንዳነጋገራቸውም ጠቅሰዋል።
አቶ ሙሳ እንደሚናገሩት፤ ግብጾች በትንሹ ሁለት መቶ የሚደርሱ የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን የያዘ የሚዲያ ኢንዱስትሪያል ዞን አላቸው። ከዚህ ውጭ ያሉትን ዌብሳይቶችና ዲጅታል ፕላትፎርሞች ከተጨመሩ አንድ ሺህ ገደማ ይደርሳሉ። ይሄ ሁሉ መድረክ በአንድ ጊዜ በኢትዮጵያውያኖች ላይ የሚዘምት ነው። በተጨማሪም አረብ ሊግ መቀመጫውን ግብጽ ያደረገና በግብጾች የሚዘወር በመሆኑ ኢትዮጵያ ላይ ብዙ ተጽዕኖ ለማድረግ ይሞክራል፡፡
ጥቂት በጎ ፈቃደኛ ኢትዮጵያውያን ይሄን ያህል የተደራጀውን ሚዲያ ነው የሰበርነው ማለት ይቻላል የሚሉት ሙሳ፤ እኛ ጥቂት ሆነን እነዚህን ሰዎች ማሸነፍ የቻልነው ሀቅ ስለያዝን ነው። ይሄ ሀቅ አለም ዓቀፉ ማሕበረሰብ ከእኛ ጋር እንዲቆም አድርጓል። የአረቡ ዓለም ሕዝብ ስለ ዓባይ ግድብ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ምን እና ምን እንደሆነች ታሪኳን እንዲያውቁ አድርገናል። በዚህ ረገድ የተሰራው ትልቅ ሥራ ጥቂት ሰዎች እንኳን በቆራጥነት ከተንቀሳቀሱ ምን አይነት ለውጥ ሊመጣ እንደሚችል የሚያስተምር ነው ባይ ናቸው።
ጥቂቶች በአረቡ ዓለም ሚዲያዎች ላይ በመቅረብ የኢትዮጵያን እውነት ለመግለጽ ባደረጉት ጥረት የተገኘውን ውጤት በጉልህ ያሳያል የሚሉትን መረጃ ሲጠቅሱም፤ የዓባይ ግድብ ግንባታ ሲጀመር አዲስ አበባ ቢሮ የነበረው በአረብኛ የሚተላለፍ ሚዲያ አልጀዚራ ብቻ ነበር። በአሁን ሰዓት መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ የአረብኛ ቋንቋ ሚዲያዎች ቁጥር 12 ደርሷል። ከእነዚህ ሚዲያዎች ጋዜጠኞች ጋር ሁልጊዜ እንወያያለን፤ ስብሰባም እንቀመጣለን። በአጠቃላይ በሠራነው ሥራ ምክንያት አንድ ሰው በእነዚህ ሚዲያዎች መድረክ ላይ ወጥቶ ደፍሮ ስለኢትዮጵያ መጥፎ ነገር መናገር እንዳይችል ሆኗል ብለዋል።
አቶ ሙሳ ከመንግሥት ይደረግላቸው የነበረ ድጋፍ ስለመኖሩ ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ መንግሥት እንደ ቡድን እናመሰግናለን ፤ እስካሁንም ያደረገልን ሞራል ድጋፍ ነው። በፌዴራል መንግሥትና በክልል ደረጃ እውቅናዎች ሰጥተውናል። ብዙ ጊዜም መንግሥት ሥራውን በበጎ ዐይን እንደሚያየው በተለያየ አጋጣሚ ይገለጻል። ነገር ግን ይህን ቡድን አደራጅቶ ከዚህ በበለጠ ደረጃ መሄድ ይቻል ነበር። አሁን እየተሰራ ያለው በተበታተነ መልኩ ነው። መጀመሪያም ቡድኑን የፈጠርነው በሀገራችን ላይ በአረብኛ ቋንቋ የሚካሄደው ዘመቻ እልህ ውስጥ አስገብቶን ለሀገራችን በመቆርቆር ነው። በሙያችንም ጋዜጠኞች ሳንሆን አንባቢዎችና ምሁራን ነን። በሂደት ግን ሁላችንም ጋዜጠኞች ሆነን ነው የተገኘነው። በግል የምናገኘው ምንም አይነት ጥቅም የለም። የሀገር ጉዳይ ሆኖብን ነው፤ ትልቅ አደጋ የሚደቅን ሥራ ውስጥ ኃላፊነት ወስደን የገባነው ነው የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
እንደ ፖለቲካ ተንታኙ ማብራሪያ፤ ከአውሮፓውኑ 2019 በፊት 90 በመቶ የግብጽ ሕዝብ ዓባይ ወንዝ ከአስዋን የሚመነጭ መሆኑን ነው የሚያውቀው። ምክንያቱም ግብጾች በስርዓተ ትምህርታቸው ውስጥ እንደዛ ብለው ነው የሚያስተምሩት። ይህ ትርክት የተቀየረው በአረቡ ዓለም ሚዲያዎች ወጥተን ዓባይ የኛ መሆኑን በመናገራችን ነው። ግብጾች በዚህ ልክ ነው በዓባይ ጉዳይ ትውልድ ላይ የሚሰሩት። ኢትዮጵያ ግን ስለዓባይ ገና የራሷን ትርክት አላበጀችም። ክፍተቱን ለመሙላት ኢትዮጵያውያን ከሕዳሴ ግድብ በኋላ አንድ ትልቅ ፕሮጀክት አድርገን መውሰድ ያለብን እንደ ግብጾች እኛን ዓለም ላይ የሚያስተዋውቅ የምንከላከልበት ትልቅ የሚዲያ ኢንዱስትሪያል መገንባትን ነው። በቀጣይም ብዙ ፈተናዎች ይኖራሉ ምክንያቱም ግብጾች ምንጊዜም ለኢትዮጵያ አይተኙም።
ሀቁ ከእኛ ጋር ስለሆነ ሁልጊዜ እንደዚህ ይቀጥላል ማለት አይቻልም በማለት የሚያሳስቡት አቶ ሙሳ፤ ጦርነት የተከፈተብን በሰው ሀገር ሚዲያ ነው። እኛ ደግሞ ዓለምን የምናናግርበት ቢያንስ በአንድና ሁለት ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች 24 ሰዓት የሚሰራ ሚዲያ ሊኖረን ይገባል ብለን እናምናለን። በየሚዲያ ተቋማቱ በአረብኛ ቋንቋ ለአንድ ሰዓት የሚሰራጨው ዜና እና የተለያየ ዝግጀት በቂ አይደለም። የሚዋጋን ወታደር አንድ ሺህ ሆኖ በእኛ በኩል መድረኩ ባዶ ከሆነ ልክ አይሆንም። አልጀዚራ ረድቶናል ደግፎናል ነገር ግን ነገ እየደገፈን ይቀጥላል የሚል እምነት የለኝም። ስለዚህ የራሳችን የሆነ መድረክ ልንፈጥር ይገባ ነበር ይሄ እስካሁን አልተሳካም። እንድ ጊዜ ሄደን የዓለም አቀፍ መድረኩን ተጋፍጠናል። ወደ ኋላ መመለስ ስለሌለ ራሱን የቻለ ሚዲያ በመፍጠር ረገድ ያለብንን ድክመት መቅረፍ አለብን ሲሉ ይመክራሉ።
በውጭ ሀገር ሚዲያዎች ላይ በመቅረብ ስለኢትዮጵያ አቋም በመናገር የሚታወቁት የታሪክ ተመራማሪው ረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚል በበኩላቸው፤ በአረቡ ዓለም፣ በአውሮፓም ሆነ በአሜሪካ የሚገኙ ሚዲያዎችን የአረብኛ ዘርፍ የሚመሩት ግብጻውያን ናቸው። በየትኛውም የዓለም ክፍል በሚገኝ በአረብኛ የሚተላላፍ ስርጭት ላይ ግብጻውያን አሉ። አንቀሳቃሾቹ እነርሱ ናቸው። ግብጻውያን ይሄን አቅማቸውን ተጠቅመው ነው ኢትዮጵያ ላይ የሀሰት ፕሮፓጋንዳቸውን የሚነዙት ይላሉ።
እንዲህ አይነቱን መዋቅራዊ ስም የማጥፋት ዘመቻ በተበጣጠሰ መንገድ ግለሰቦች በሚያደርጉት ጥረት መግታት አዳጋች መሆኑን የሚጠቁሙት የታሪክ ተመራማሪው፤ የግድ 24 ሰዓት ለውጭው ዓለም በአረብኛ፣ እንግሊዝኛ እና ፈረንሳይኛ የሚተላለፍ የተደራጀ ሚዲያ እንደሚያስፈልግ ታምኖበት ከአሁኑ እንቅስቃሴ መጀመር እንዳለበት ገልጸዋል።
አልጀዚራ ከ 70 ሚሊየን ሕዝብ በላይ የሚከታተለው በዓለም ላይ አሉ ከሚባሉት ከፍተኛ ቦታ ያለው የቴሌቪዥን ጣቢያ ነው። ከሁለት ዓመታት በፊት በአልጀዚራ የተላለፈ አንድ ቃለመጠይቅ ነበረኝ። በቦታው ተገኝቼ የሚጠቀሙትን ቴክኖሎጂ እና አሰራራቸውን ተመልክቻለሁ። በእነርሱ ደረጃ ባይሆንም አረብኛን ጨምሮ የግድ በዓለም አቀፍ ቋንቋዎች ኢትዮጵያን የተመለከቱ መረጃዎችን የሚያሰራጭ የቴሌቪዥን ጣቢያ ሊኖረን ይገባል በማለት የአቶ ሙሳን ምክረ ሀሳብ አጠናክረዋል።
ተስፋ ፈሩ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 7 ቀን 2017 ዓ.ም