በቅርቡ እንደ አዲስ ተቋቁሞ ሥራውን የጀመረው የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በአገሪቱ የሚገኙና ተጠሪነታቸው ለፌዴራል መንግሥት የሆኑ 45 ዩኒቨርሲቲዎችን በማስተዳደር ላይ ይገኛል። ይህ አዲስ መስሪያ ቤት ካሉበት በርካታ ሥራዎች መካከል ቅድሚያ ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰበት ያለው ተግባር ዩኒቨርሲቲዎቹን ፈር ማስያዝ ሲሆን ፈር ማሲያዣውን ዘዴም አጥንቶና አስጠንቶ ለውይይት አቅርቧል። ይህ ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት በጊዮን ሆቴል በጉዳዩ ላይ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል።
ሚያዝያ 16 እና 17 2011 ዓ.ም በተካሄደው የሁለት ቀን ውይይት በርካታ ቁም ነገሮች የተገኙበት መሆኑን፤ የተገኙት ግብአቶችም ለወደፊት ሥራ ጠቃሚ መሆናቸውን በመግለጽ ኃላፊዎቹ ተሳታፊዎችን አድንቀዋል። የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ፕሮፌስር ሂሩት ወልደማርያም ውይይቱን ሲከፍቱም ሆነ በውውይቱ ወቅት እንደተናገሩት ባለድርሻ አካላት እንዲወያዩበትና ግብአት እንዲሰበሰብበት የተፈለገው አቢይ ጉዳይ በአገሪቱ የሚገኙትን 45 ዩኒቨርሲቲዎች በሦስት ዘርፍ ለመክፈልና አገሪቱ ለምትፈልጋቸው ዓላማ እንዲውሉ ለማድረግ ሲሆን፤ ዘርፎቹም የምርምር፣ የትምህርት እና የፖሊ ቴክኒክ መሆናቸውን ነግረውናል።
እንደ ፕሮፌሰር ሂሩት ማብራሪያ ዩኒቨርሲቲዎቹን በተጠቀሱት ሦስት ዋና ዋና ዘርፎች ከፍሎ እንዲሠሩ ለማድረግ የሚያስችል የመነሻ ጥናትም ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል። ከውይይቱም ከፍተኛ የሆነ ግብአት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል። በውይይት መድረኩ ላይ ለውይይት መነሻ የሆኑ ጥናቶች የቀረቡ ሲሆን የሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ንጉሴ ደቻሳ “Differentiating The Ethiopian Higher Education System” በሚል ርዕስ ያቀረቡትና ማዕከላዊ ጭብጡን “ልየታ/Differentiation” ላይ ያደረገው የመጀመሪያው ነበር።
ፕሮፌሰር ንጉሴ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት ኢትዮጵያ ውስጥ የዩኒቨርሲቲዎቻችን ቁጥር ይብዛ እንጂ አንዱ ካንዱ የሚለይበት ምንም መስፈርትም ሆነ መንገድ የለም። ባብዛኛው አንዱ ያንዱ ግልባጮች ናቸው። ይህ በፍፁም ሊሆን የሚገባውም፤ መደረግ የነበረበትም አልነበረም። ስለዚህ ይህ ስህተት አሁኑኑ ሊታረም፣ ሊስተካከልና አገርና ህዝብም ከዩኒቨርሲቲዎቹ ማግኘት ያለባቸውን ማግኘት አለባቸው።
የፕሮፌሰር ንጉሴ ጥናት በ“ልየታ/ Differentiation” ፅንሰ-ሃሳብ ላይ በሚገባ ያተኮረ፣ የበርካታ አገራትን ልምድ የዳሰሰና በቂ ማብራሪያን የሰጠ በመሆኑ የተሳታፊዎችን ቀልብ ስቦ የቆየ መሆኑን፤ ከሌሎች ተሳታፊዎች በተሰጡ አስተያየቶች እየዳበረ ሞቅ ያለ ውይይት ሲደረግበት እንደነበርም መመልከት ተችሏል። በዚሁ ጥናት ላይ በርካታ ምሁራንና ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች አስተያየታቸውን የሰጡ ሲሆን አምባሣደር መሃመድ ድሪር አንዱ ነበሩ።
እንደ አምባሰደሩ አስተያየት የቀረበው ጥናት በጣም ጥሩና የዓለምን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ ሲሆን አፈፃፀሙ ላይ ግን እንደገና ወደ ኋላ እንዳይመልሰን ተደርጎ በጥንቃቄ መሠራት ይኖርበታል። የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የቦርድ ሰብሳቢዎች በውይይቱ የተሳተፉ ሲሆን የሚዛን-ቴፒ፣ አዲስ አበባ እና የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲዎች ቦርድ ሰብሳቢዎች ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እያከናወነ ያለውን ተግባር አድንቀው ሊመሰገን እንደሚገባ፤ የሚወቀስ ቢሆን እንኳ በመዘግየቱ እንጂ በሌላ ሊሆን እንደማይችል ጠቅሰው ያለ ምንም ማንገራገር፤ የተገነባ ሕንፃም ሆነ ሌላ ኢንቨስትመንት ሳያሳሳን ቀጥታ ወደ ሥራ መግባት አለብን ሲሉ አሳስበዋል።
ሚኒስትሯ ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደ ማርያም በበኩላቸው እንዳሉት የትምህርት ሂደታችን ተፈትኗል፤ ታይቷል፤ ተግዳሮቶች አሉበት። ምሩቃኖቻችን የተፈለገውን አቅም ይዘዋል ወይ፣ ለገበያው ብቁ ናቸው ወይ፣ ባሠሪዎች ተፈላጊ ናቸው ወይ፣ ሥራ እየፈጠሩ ነው ወይ፣ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ አስተዋፅኦ እያደረጉ ነው ወይ? የሚለው ሲታይ፤ ተገቢውን የቋንቋ፣ ሎጂክ፣ ምክንያታዊነትን እና የመሳሰሉትን ዕውቀትና ክሂሎት ተላብሰው ወጥተዋል ወይ? የሚለው ሲፈተሽ ችግር አለ። ለዚህ ደግሞ በርካታ ምክንያቶች አሉ።
በጥራትም ሆነ በቁጥር የመምህራን እጥረት መኖሩ፣ ተማሪዎች ለመማር ያላቸው ዝግጁነት፣ ከመሰናዶ ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲመጡ በቂ ዕውቀትና ለመቀበል የሚያስችል አቅም ይዞ ያለመምጣት፣ ስለራሳቸው፣ ስለአገራቸውም ሆነ ስለዓለም ያላቸው ዕውቀት ውሱን መሆኑ ሁሉ ችግር ሆኖ ነው የቆየው። ይህ ሁሉ እንዳለ ሆኖ ሌላው ችግር ደግሞ የዩኒቨርሲቲዎቻችን ስምሪት ነው።
የዩኒቨርሲቲዎቻችን ስምሪት ለከፍተኛ ብክነት የተጋለጠ ሆኖ ነው የተገኘው። ሁሉም አንድ ዓይነት ዓላማ እና ተልእኮ ያላቸው፣ ሁሉም አንድ ዓይነት ትምህርት የሚሰጡ፣ በአንድ ዓይነት ትምህርት የሚያስመርቁ፣ በተመሳሳይ ደረጃ የሚገኙ፣ አንድ ዓይነት ፕሮግራም ያላቸው፣ አንዱ ያንዱ ግልባጭ የሆኑ ናቸው፤ የኋለኛው የፊተኛውን ኮፒ እያደረገ ነው የሚጀምረው። በሌለ የሰው ኃይል፣ በሌለ ባለሙያ፣ በሌለ ግብአት፣ በሌለ አቅማቸው አንድ ዓይነት ነገር በመስጠት ነው ተጨናንቀው ያሉት የሚሉት ሚኒስትሯ ችግሩ ይህ ብቻ እንዳልሆነም ይናገራሉ።
የእነዚህ ዩኒቨርሲቲዎች ሌላው ችግር በሌላቸው አቅም እስከ መጨረሻው ደረጃ (ፒኤች.ዲ) ድረስ መሄዳቸው ሲሆን ይህ ደግሞ ጎድቶናል። ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች በማስተማሩም፣ በምርምሩም፣ በቴክኖሎጂውም፣ በግብርናውም፣ በሁሉም ዘርፎች ነው የሚያስተምሩት። ይህ ደግሞ ውጤታማ ሊሆኑ በሚችሉበት መስክ እንኳን እንዳይሠሩና ሀብትም እንዲበታተን አድርጓል ያሉት ሚኒስትሯ ችግሩ ሊፈታ እንደሚገባውም አሳስበዋል። “ቅርስ ሲበላሽ ከውጭ ለምነን አምጥተን ነው የምናሠራው፤ እዚያ ላይ አጥንቶ በርካታ ሥራዎችን ሊሠራ የሚችል መፍጠር ሲገባን ባለማድረጋችን ነው ይህ ሊሆን የቻለው።”
የሚሉት ፕሮፌሰር ሂሩት እያንዳንዱ ዩኒቨርሲቲ እንደየአካባቢው ባህርይ፣ ሪሶርስና ተጨባጭ ሁኔታ ቢቋቋምና ቢሠራ ይህ ዓይነቱ ችግር ሊከሰት እንደማይችልም አስረድተዋል። “በመሆኑም በእነዚህ ሦስት ዘርፎች ለይቶ እንደገና ማደራጀት አስፈልጓል።” ከሚኒስትር ሂሩት ማብራሪያ፣ ከቀረቡት ጥናቶች እና ከተሰጡት አስተያየቶች በጥቅሉ መረዳት የተቻለው ዩኒቨርሲቲዎቹን በተልዕኮና በትኩረት አቅጣጫ የማደራጀት ጉዳይ በቅርቡ የሚጀመር ሲሆን አተገባበሩም በከፍተኛ ጥንቃቄና በጥናት ላይ የሚመሰረት መሆኑን ነው።
በእንደገና አወቃቀሩ (Reorganize የማድረግ) ሂደትም ለምርምር የተሻለ የመሠረት ልማትና የሰው ኃይል ያላቸው ዩኒቨርሲቲዎች የጥናትና ምርምር ዩኒቨርሲቲ መደብ ውስጥ እንደሚገቡና በዶክትሬት ዲግሪ ደረጃ ፕሮግራሞችንም እንደሚሰጡ፤ የንድፈ ሐሳብና ተግባራዊ ትምህርትን አጣምረው የሚሰጡ የፖሊ ቴክኒክ ዩኒቨርሲቲዎች መደብ ሥር እንደሚገቡና የተቀሩት ደግሞ የትምህርት (Teaching ላይ ያተኮሩ) ዩኒቨርሲቲዎች ሆነው የሚዋቀሩ ይሆናሉ።
በተለያዩ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ምሁራን የሚሳተፉበትና 134 አባላት ያሉት የአማካሪ ምክር ቤት ተቋቁሞ አብሯቸው እየሰራና እስከ ማስተማር ድረስ የዘለቀ ድጋፍ እያደረገላቸው መሆኑን የገለፁት ሚኒስትሯ በከፍተኛ ትምህርት ስርአተ-ትምህርት ውስጥ ያሉትን ከተማሪዎች ህይወት ክሂሎት ጋር ያለመዛመድ፣ ለስራ የሚያዘጋጁ አለመሆን፣ ከኢኮኖሚ ኮሪደሮች ጋር ያለመተሳሰሩ ጉዳይ፣ የጥናት መስኮች ባብዛኛው በጥናት ላይ ሳይሆን በግለሰቦችና መምህራን ፍላጎት ላይ የተመሰረቱ መሆናቸው፣ የአገሪቱን ችግር በሚፈትሹ ጉዳዮች ላይ ያለማተኮራቸውና ያተኮሩትም ቢሆኑ ከሼልፍ ማለፍና ስራ ላይ መዋል አለመቻለቸውን የመሳሰሉ ችግሮችን ለመፍታት በሚያስችል መልኩ እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል። ሌላው በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተከናወነውና ወደፊትም ተጠናክሮ የሚቀጥለው ከግሉ ዘርፍ ጋር አብሮ የመስራቱና እነሱን የማጠናከሩ ጉዳይ ነው። ሚኒስትር ሂሩት እንዳስረዱት የግሉ የከፍተኛ ትምህርት ዘርፈ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው፤ ይሁን እንጂ የዛኑ ያህልም የህግ ጥሰት ይታያል።
ይህንኑ የህግ ጥሰት እያስተካከሉ የመሄድ ጉዳይ የተጀመረ ሲሆን ለዚህም እርምጃ የተወሰደባቸው 46 የግል ከፍትኛ የትምህርት ተቋማት ማስረጃዎች ናቸው። ስርአተ-ትምህርቱን ከማሻሻል አኳያ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ከሁለቱ ቀን የውይይት መድረክ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን የማሻሻሉ ስራ እስካሁን የሌሉ አዳዲስ ኮርሶችን እስከ መጨመር ድረስ እንደሚሄድም ታውቋል። ለዚህ ማሳያ የሚሆነው የተመራቂ ተማሪዎችን የክሂል (በእንግሊዝኛ ቋንቋ ማንበብና መፃፍ ካለመቻል ጀምሮ ያለውን) እና እውቀት እጥረትን መነሻ ያደረገና ከችግር ያላቅቃቸዋል ተብሎ የሚዘረጋው የአንድ አመት ኮርስ ነው። በጥናቶቹ ላይ እንደተጠቀሰው ይህ ኮርስ ተማሪዎች ወደ ዲፓርትመንታቸው ለይተው እዛ ከመግባታቸው በፊት የሚሰጥ ሲሆን የቋንቋ ክሂላቸውን፣ አስተሳሰባቸውን፣ ተጠየቃዊና ምክንያታዊ ሰብ እናቸውን ለመገንባት የሚያስችላቸው ሆኖ የተቀረፀ ነው።
በጠቃላይ ዩኒቨርሲቲዎቻችን አሁን ካሉበት የማይጠቅም አካሄድ ባስቸኳይ መውጣት ያለባቸው መሆኑ፤ ያሉበትን አካባቢና መልካም ዕድሎችን ባገናዘበ መልኩ ድልድል ማድረግ እንደሚገባ (ቅርሶች ባሉባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች አርኪዮሎጂ ላይ በማተኮር የልህቀት ማዕከላት እንዲሆኑ፤ በግብርና ላይ ተሞክሮና ታሪክ ያላቸው ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ በግብርና ውጤታማ የሆነ ባለሙያዎች ማፍራት እንዲችሉ የማድረግ ሥራ እንደሚሠራ) በመድረኩ ላይ ተነስተው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን መግባባት ላይም ተደርሶባቸዋል። እነዚህንም በጊዜ ወደ ተግባር ማስገባት እንደሚገባ መግባባት ላይ ተደርሷል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 21/2011
ግርማ መንግሥቴ