በዓለማችን የሚገኙ የአክራሪና ፅንፈኛ አስተሳሰብና ዓላማ ባለቤቶች ሰዎችን በመግደል ዓላማቸውንና ሃሳባቸውን ለመጫን ጥረት ያደርጋሉ።እነዚህ ኃይሎች ይህን የሚያደርጉት ሃሳባቸው በፖለቲካና የሃሳብ ትግል ማሸነፍ እንደማይችል እንዲሁም በፖለቲካ ገበያው ተቀባይነትና ዋጋ እንደሌለው ስለሚረዱ ነው።
የሃሳብ ብዝሃነት ፀጋ ነው።ብዙ ሃሳብ ሲኖር የተሻለ ለመምረጥ ዕድል ይሰጣል።የተሻለው ሃሳብ ደግሞ አገርንና ሕዝብ ያበለፅጋል፤ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን ያስችላል።የሃሳብ ብዝሃነትን ለማስተናገድ አለመፈለግ ግና የጥፋት እና የግጭት መንገድ ስለሆነ ለአለመረጋጋት መንስኤ በመሆን ሕዝብን እና አገርን ለችግር ይዳርጋል።ፅንፈኝነትና አክራሪነት እንዲገነግንም ዕድል ይሰጣል።
በየትኛውም ሁኔታ ሃሳብን በሃሳብ እንጂ በኃይልና በግድያ ለማስፈፀም መሞከር ትክክል አይደለም።ሃሳብን በሃሳብ ለማሸነፍ ደግሞ እውቀትም ብልሃትም ጥበብም ይጠይቃል።እውቀት፣ ብልሃትና ጥበብ ሳይኖር ሲቀር ሃሳብን በኃይል ለመጫን ጥረት ስለሚደረግ የሚወሰደው እርምጃም ግድያ ስለሚሆን ዳፋው ለብዙዎች ይደርሳል።ስለዚህ ይህ የጥፋትና የፅንፈኝነት መንገድ መወገዝ አለበት።ምክንያቱም የሃሳብ ልዩነትን በጉልበትና በኃይል ለመፍታት መሞከር ወይም መተግበር ጥፋት እንጂ ትርጉም የለውምና።ሰውን በጥይት መግደል ቢቻልም ሃሳብና ዓላማን ግን አይገድልም።ሃሳብንና ዓላማን በሃሳብና በዓላማ ማሸነፍ ካልተቻለ ደግሞ ተሸናፊው ገዳዩ ነው።
ከትናንት በስቲያ ሃሳብን በሃሳብ ማሸነፍ ያቃታቸው የታጠቁ ፅንፈኞች የብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ የሺጥላን በሰሜን ሸዋ ዞን ልዩ ቦታው መንዝ ጓሳ በተባለ አካባቢ ለሥራ እየተንቀሳቀሱ ባሉበት ወቅት ጥቃት ፈጽመው ነፍሳቸውን ነጥቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ባስተላለፉት የኀዘን መግለጫ ‹‹ልዩነትን በሠለጠነ መንገድ መፍታት ባህል በሆነበት ክፍለ ዘመን፣ በሃሳብ የተለየንን ሁሉ በጠመንጃ ለማሳመን መነሳት የፅንፈኝነት የመጨረሻው ጥግ ነው። ተወልዶ ባደገበት አካባቢ፣ ከእኛ የተለየ ሐሳብ ማሰብ አልነበረበትም ብለው የሚያምኑ ነውጠኛ ፅንፈኞች የፈፀሙት አስነዋሪና አሰቃቂ ተግባር፣ ፅንፈኝነትን በጊዜ ታግለን ካላስወገድነው ወደ መጨራረስ እንደሚወስደን ጉልሕ ማሳያ ነው›› ብለዋል።
የአንድን ሰው ሕይወት በመንጠቅ የሰውየውን ሃሳብና ዓላማ ማስወገድና ማሸነፍ እንደማይቻል፤ በአሁኑ ዘመን ልዩነትን በውይይትና በንግግር የሚፈታበት ሁኔታና ሥርዓት እያለ በኃይል ሃሳብንና ዓላማን ለመጫን የሚደረግ ጥረት የአክራሪነትና የፅንፈኝት እኩይ ተግባር መሆኑን ማረጋገጫ ነው።በየትኛውም ወቅት ሃሳብና ዓላማቸውን በኃይል ለመጫን ጥረት የሚያደርጉ ኃይሎች መቼም ቢሆን ሕዝባዊ ቅቡልነት የላቸውም።
አክራሪና ፅንፈኛ ኃይሎች ለሃሳብ ልዕልና በሃሳብ መታግልን ከመምረጥ ይልቅ በመሣሪያ ቃታ ሰውን መግደል እንደ ስልት ወስደዋል።ነገር ግን ይህ ተግባር የእነዚህን ኃይሎች መሸነፍ የሚያረጋግጥ እንጂ፤ የሕግ የበላይነት የተረጋገጠባትና የሃሳብ ብዝሃነት የሚከበርባት አገር ለመገንባት የተጀመረውን ጥረትና ጉዞ ማስቆም አይችሉም።ምክንያቱም የሚገድሉት ሰውን እንጂ አገርን የሚያሻግር ሃሳብንና ዓላማን አይደለምና።በተጨባጭ የዚህ ዓይነቱ አስተሳሰብ በዚህ ዘመን አይሠራም። ወደፊትም አይሠራም።
አሁን ባለንበት የ21ኛው ክፍለ ዘመን ልዩነት በምክክር እና በውይይት መፍታት ሲቻል የመሣሪያ አፈ ሙዝን በመፍትሄነት መጠቀም ተስፋ ቢስነትን ያመላክታል።ከዚህ ቀደምም አክራሪና ፅንፈኛ ኃይሎች በአቋራጭ ስልጣን ለመያዝ ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም።ነገር ግን አልተሳካላቸውም።ሰውን መግደልን አማራጭ ማድረጋቸው ግና ሃሳባቸው ወይም ዓላማቸው በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንደሌለው ከማረጋገጥ ውጪ የሚፈይደው ሌላ ነገር አይኖርም።
እነዚህ አክራሪና ፅንፈኛ ኃይሎች በሰለጠነ መንገድ ፖለቲካዊ አካሔዳቸውን ማስፈፀም የማይችሉና ሁልጊዜ ፀብና ግጭት በመፍጠር አጀንዳቸውን ለማስፈፀም ነፍጥ የሚያነሱ ከዘመኑ ፖለቲካ ስልጣኔ አንፃር ችግሮቻቸውን በውይይት ለመፍታት አቅም የሌላቸው፤ የህብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያን ከፍታና አንድነት ለመናድ የሚታትሩ የአገር ጠላቶች ናቸው። በሃሳብ የተለየን ሰው በሃሳብ ሞግቶ፤ በአመለካከት የተለየን በአመለካከት ረትቶ መነጋገርና የሚበልጠውን የሚበጀውን ለአገርና ለወገን ፍሬ የሚያፈራውን ሃሳብ ማስፋትና ማጎልበት ሲቻል ክቡር የሆነውን የሰውን ልጅ እስከ መግደል መሄዳቸው መሸነፋቸውን ነው የሚያረጋግጠው።
በአቶ ግርማ ላይ የተፈጸመው ግድያ በአገራችን እየታየ ያለው የአክራሪነትና ፅንፈኝነት አስተሳሰብ እና ከአስተሳሰቡ የሚነጩ እኩይ ድርጊቶች ከፍተኛ አደጋ ውስጥ ሊከቱን እንደሚችሉም ተጨባጭ ማሳያ ነው። በአጠቃላይ ሰውን መግደል እንጂ ሃሳብንና ዓላማን መግደል አይቻልም!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 21/2015