መለስ ቀለስ የሚለው የጤናቸው ችግር በእጅጉ እየፈተናቸው ነው። እንዲህ መሆኑ ሮጠው ለሚያድሩት ወይዘሮ የበዛ ዕንቅፋት ሆኗል። ሁሌም ቢሆን ሀሳብ አያጣቸውም። ያለአባት የሚያድጉት ልጆች፣ የእሳቸውን እጅ ይጠብቃሉ። ያለገቢ የሚያድረው ጎጆም የግላቸው ዕዳ ነው።
ወይዘሮ ደጊቱ መኮንን እጃቸው ከሥራ፣ እግራቸው ከመንገድ ታቅቦ አያውቅም። ቤተሰብ ለማሳደር፣ ልጆች ለማሳደግ ለፍቶ አዳሪ ናቸው። ኑሮን ለማቅናት ለዓመታት በጉልት ንግድ ቆይተዋል። ማለዳ ነቅተው አትክልት ማምጣት፣ ያመጡትን ለይተው በችርቻሮ መሸጥ የእስከዛሬ መተዳደሪያቸው ነበር።
ደጊቱ አትክልቱን ተሸክመው ሰፈር ለማድረሰ ሰፊ ትከሻ፣ ጠንካራ ጉልበት ያሻቸዋል። እስካሁን ይህን ለማድረግ ደክመው አያውቁም። አቅማቸው የቻለውን አምጥተው ለጉልት ሥራቸው ይደርሳሉ። አሁን ግን ይህ ዓይነቱ እውነት ታሪክ ብቻ ሆኗል። ትናንት ከእርሳቸው የነበረ ብርቱ ጉልበት ደክሟል። ብርቱ እጆቻቸው ከትጋት፣ ፈጣን እግሮቻቸው ከመሮጥ ታቅበዋል።
ወይዘሮዋ እንዲህ የሆኑበትን የክፉ አጋጣሚ ፈጽሞ አይረሱትም። የሕመማቸውን መነሻ ዛሬም ያስታውሱታል። አንድ ማለዳ ደጊቱ ማልደው ከቤት ወጡ። በጠዋት የመነሳታቸው ምክንያት እንደልማዳቸው ከአትክልት ተራ ለመሄድ ነበር። ዛሬም ክፉኛ እየሳሉ ነው። በጀርባቸው የሚወርደው የሞቀ ላብ ወበቅ ሆኖ ያጋያቸው ይዟል። የሰቀዛቸው ውጋት ቢያስጨንቃቸውም እጅ መስጠትን አልፈለጉም። ጥርሳቸውን ነክሰው ጉዞ ጀመሩ።
ሲመለሱ የጉልት ንግዱ ይቆያቸዋል። በዕለት የሚያገኙት ጥቂት ገቢ ቤት የሚደግፍ፣ ችግር የሚታደግ ነው። ይህን እያሰቡ ከአትክልት ገበያው ገቡ። እንደወትሮው ከሽንኩርቱ፣ ከድንቹ፣ ሸማመቱ። ሁሉም ማዳበሪያ ሆዱ ሲሞላ ታያቸው። አልበቃቸውም። ሊጨምሩ ፈለጉና ከቲማቲሙ በርከት አድርገው አከሉ። እያመማቸው ነው። ሳላቸው በርትቷል። ትኩሳቱ አይሏል።
የአትክልት ሸመታው እንዳለቀ ደጊቱ የሚሸከም ልጅ ጠርተው ከታክሲው አናት ማዳበሪያውን አስጫኑ። ውስጥ ገብተው ወንበር ሲይዙ ሕመማቸው እየበረታ፣ እየዞረባቸው ነበር። ልባቸውን ደግፈው ከሰፈር ደረሱ። ታክሲው የተጫኑ ማዳበሪያዎችን ሊያወርድ ከሰፈራቸው ቆመ።
የተፈተነ ብርታት…
ደጊቱ ከነበሩበት ተነስተው ሊራመዱ ሞከሩ። እጅ እግራቸው ዛለ። ሰማይ ምድሩ ዞረባቸው፣ አቅም እየከዳቸው የጫኑትን ለማውረድ ሞከሩ። አልቻሉም። ማዳበሪያው እንደቀድሞ ልምዱ ከጉልቱ አልደረሰም። በሌሎች ትከሻ ተጭኖ ከቤታቸው ገባ።
ቀናት ተቆጠሩ። ደጊቱ ክፉኛ ታመዋል። ደረታቸውን ደግፈው ያለአፍታ እየሳሉ ነው። አትክልት የታጨቁ ማዳበሪያዎች እንደተቋጠሩ ሳይፈቱ ተቀምጠዋል። ቤት ከገቡ ጀምሮ ለገበያ አልበቁም። ተማሪዋ ልጃቸው ከቤት አትውልም። የእሳቸው መታመምና የሚተካቸው ሰው አለመኖር ዋጋ ያስከፍል ይዟል።
አሁን ለትርፍ የገዟቸው አትክልቶች እየተበላሹ ነው። ደጊቱ አንዳች ማድረግ አልቻሉም። ዓይናቸው እያየ ለኪሳራ ተዳረጉ። ቆጫቸው፣ አንገበገባቸው። ወይዘሮዋ ያለአንዳች መፍትሄ እንደተኙ ከረሙ። ለትርፍ የተገዙት አትክልቶች እንደዋዛ በስብሰው ከተጣሉ በኋላ የኑሮ ጉዳይ አስጨነቃቸው። አሁን እንደ ትናንቱ ለገበያ የሚተርፍ፣ ሮጦ የሚገባ ጉልበት የላቸውም። ልሞክር ቢሉም ሥራው ከሕመሙ አይስማማም። ተጨነቁ። ጊዜ ወስደው ስለነገው አሰቡ።
ዳግም ለመቆም…
ደጊቱ አንድ ቀን ያሰቡትን ሥራ ጀመሩት። ከሰል በጋሪ አስምጥተው በችርቻሮ መሸጥ ያዙ። የተቋጠረው የላስቲክ ከሰል ዕለቱን መሄዱ ለገበያው መልካም ሆነ። የጤና ጉዳይ ግን መላ ታጣለት። ደጊቱ አሁንም ልባቸውን ይዘው ይስላሉ። ላብ ያጠምቃቸዋል፣ እጅ እግራቸው እየዛለ ይደ ክማቸዋል።
ሁሌም ለከሰል ችርቻሮው ማዳበሪያውን ፈተው ማዘጋጀት አለባቸው። ደቃቁን ከአንኳሩ፣ እንጨቱን ከድንጋዩ፣ ሊለዩት ግድ ነው። ይህ ሥራ እጅን ብቻ አቆሽሾ አያልፍም። ለእሳቸው የበዛ ድካም አለው። ሁሌም የከሰሉ ብናኝ በአፍ በአፍንጫቸው ይገባል፣ እያሳላቸው ይሠራሉ፤ እየደከማቸው ይቋጥራሉ።
ሕመሙ ባስ ሲል ለጤናቸው ትኩረት ሰጡ። ከጤና ተቋም ተመላለሱ። ቆይቶ የሀኪም ውጤት ታወቀ። ጤናቸውን ክፉኛ ያወከው ችግር የሳንባ ሕመም ነበር። ደጊቱ ይህን እንዳወቁ ሕክምናውን ቀጠሉ። ለሦስት ወራት ከሥራ ታቅበው ከቤት ዋሉ። ሻል ሲላቸው አልዘገዩም። የታዘዘላቸውን የስድስት ወር መድኃኒት ጀም ረው ወደ ሥራ ተመለሱ።
የከሰል ችርቻሮው ከሕመማቸው አይስማማም። ለመኖር ግን ከእሱ መታገል ግድ ይላል፤ ለመኖር በዚህ መስመር ማለፍ ያሻል። በታመሙ ጊዜ የተዝረከረከው የከሰል ትራፊ ዛሬም በደጃቸው ነው። ገንዘብ አውጥተውበታል፤ ጉልበት አፍሰውበታል። ላለመክሰር እሱን መሰብሰብ፣ ማስተካከል አለባቸው። የወቅቱ ዝናብ ደግሞ የሚያላውሳቸው አልሆነም። ከሰሉ የእንጀራቸው ምንጭ ነውና ከአፋቸው ‹‹ማስክ›› ሳይለዩ ሲተጉ፣ ሲደክሙ ይውላሉ። ሁሌም ፊታቸውን ከልለው ከሰሉን ይሸጣሉ።
ኑሮን በትግል …
በእሳቸው ዘንድ ደቃቅ ይሉት ከሰል አይባክንም። ያለው ተጠራቅሞ ከአመድ ከአፈሩ ተለውሶ ‹‹ጥፍጥፍ›› ይሠራበታል። ጥፍጥፉ ልክ እንደከሰሉ ለማገዶ ይፈለጋል። እሱም ቢሆን የገቢውን ያህል የራሱ ወጪ አለው። የተመረጠ አፈርና ደቃቅ ከሰል በኩንታል መግዛት አለባቸው።
የዝግጅቱ ድካም የበዛ ነው። ሲጠፈጠፍ ከተሰበረ ያከስራል፣ ርጥበት ካለ ለመድረቁ ጊዜን ይሻል። ሁሌም የእሱ ሥራ በፀሐይዋ ሙቀት የሚወሰን ነው። ያሉበት ሰፈር ውሃ የለውም። ጥፍጥፉን በአመድና አፈር ለውሶ ለመጋገር በቂ ውሃን ይጠይቃል። ይህን ለማድረግ ደጊቱ ውሃ መግዛት፣ ለጉልበት ዋጋ መክፈል አለባቸው። ምርጫ የላቸውም። የተጠየቁትን ሰጥተው ጥፍጥፉን እንደከሰሉ ለማገዶነት ይሸጡታል።
አንዳንዴ ውሃውን የሚያመጣ፣ የሚታዘዝ ይጠፋል። ደጊቱ ምርጫ ሲያጡ፣ ስለሥራው ሲጨነቁ ለሸክም ትከሻቸውን ይሰጣሉ። ዕለቱን እንዳሰቡት ቢሞክሩም ማግስቱን መመለስ አይችሉም። ደጋግሞ ሕመም የጎበኘው አካላቸው ይዝላል። በድካም ይንቀጠቀጣል።
ደጊቱ በተለያዩ ጊዜያት ቀዶ ሕክምና አድርገዋል። በእጅና እግራቸው ላይ የቀረው የጠባሳ ምልክት ዛሬም ድረስ ይታያል። ልጃቸውን ሲወልዱም ከዚህ አጋጣሚ አላለፉም። እንዳይሸከሙ፣ ሥራ እንዳያበዙ የተሰጣቸው የሀኪም ትዕዛዝ ተከብሮ አያውቅም። እስከዛሬ ደንበኞቻቸው ከሰል ሲገዙ ይታዘዛሉ። ካሰቡት የሚያደርሱትም በእሳቸው ጉልበት ነው።
ብርቱ ማንነት…
ከሰልና ጥፍጥፍ መሸጥ ከጀመሩ ወዲህ የጎደለውን ለመሙላት ዕንቅልፍ ይሉት የላቸውም። የቀድሞው ብርታታቸው ቢፈተንም ለሥራ ያላቸው ፍላጎት አልጠፋም። ከብናኙ እየታገሉ፣ ከሽታው እየተጣሉ ኑሮን መግፋት ይዘዋል።
ወይዘሮዋ ቀጣዩን አዲስ ቀን መድኃኒት በመውሰድ ይጀምራሉ። መድኃኒቱ በቂ ምግብ፣ ወተትና ሌላም ድጋፍ ይፈልጋል። ቤት ያፈራውን ቀምሰው፣ ፈጣሪያቸውን አመስግነው ይውላሉ።
ደጊቱ ከሰል የመሸጥ ሕይወት ከባድ መሆኑን ያውቁታል። ሥራውን ለመለወጥ ግን ሌላ ምርጫ አላገኙም። ትንሽዋ ልጃቸው ዛሬም ድረስ ተማሪ ናት። አባቷ እሷን ነፍሰጡር ሳሉ ነበር በሞት የተለዩት። ለብቻቸው አሳድገው፣ አስተምረው ካሰበችው ለማድረሰ ብዙ ዋጋ ከፍለዋል። በቀን ከአራት ቤት ልብስ አጥበው፣ እንጀራ ጋግረው ቀን ወጥተዋል። ዛሬ ልጃቸው በእርሳቸው ጥረትና ልፋት በግል ዩኒቨርሲቲ እየተማረች ነው። በአስራሦስት ዓመታቸው የወለዱት ትልቁ ልጅ ግን በኑሮ መክበድና በቤት ጥበት ከእሳቸው ከራቀ ቆይቷል።
ዛሬን በነገ ውስጥ…
ወይዘሮዋ ከጥቂት ጊዜያት በፊት የቀበሌ ቤት አግኝተዋል። ይህ በመሆኑ ምስጋናቸው የላቀ ነው። እንዲያም ሆኖ የቤቱ ወጪ የዋዛ አይደለም። ለውሃ፣ ለመብራት፣ ያስፈልጋል። ለዕለት ወጪ፣ ለጓዳው ድጎማ፣ ለዕድርና ማህበራዊ ሕይወት ሁሉ መቀነታቸውን ሊፈቱ፣ ቦርሳቸውን ሊፈትሹ ግድ ይላል።
ደጊቱ ኑሮን አሸንፎ፣ ልጆች ለማሳደግ ያልሞከሩት የለም። በክፍያ የድግስ ወጥ ሠርተዋል። እጃቸው እስኪዝል በየቤቱ ልብስ አጥበዋል። እንጀራ መጋገር፣ የቀን ሥራ መከወን፣ የዕለት ተግባራቸው ነበር። በኮሮና ሰበብ ሥራው እስኪቀዛቀዝ ኑሯቸው በዚህ ጸንቶ ቆይቷል።
ቀድሞ የቆዩበት የወጥ ሥራ ይበልጥ ቤታቸውን ሲደጉም ነበር። አሁንም ቢሆን ዕድሉን ቢያገኙ ልባቸው ያሰበውን መሥራትን ያስባል። በእርግጥ ለዚህ ሥራ አቅምና ጉልበት ግድ ነው። እሳቸው እጀ መልካም ባለሙያ ሴት መሆናቸውን ያውቃሉ። አልቻሉም እንጂ ዛሬም ቢሆን ሁሉን ተቋቁመው ሥራውን ቢሞክሩት ይወዳሉ ።
ዘመነ ኮሮና ከእሳቸው ሕመም ተዳምሮ ደንበኞቻቸውን አርቋል። ይህን የሚያውቁት ወይዘሮ ፈተናውን ሰብረው መውጣት ይሻሉ። እንዲህ ማሰባቸው የተለየ ጉልበት አግኝተው አይደለም። ዛሬም በወጉ ያልሞላ ጓዳቸውን ያስባሉ። የከበደው የኑሮ ጫና አሁን ባላቸው ገቢ ብቻ አለመገፋቱ ያሳስባቸዋል።
የደጊቱ ከእጅ ወደአፍ ኑሮ ፈተናው ብዙ ነው። ጠንክረው ለመሥራት የጤና ችግር ይዟቸዋል። ይሁን ብለው እንዳይተዉት የሚተማመኑበት፣ ነገን የሚሻገሩበት በቂ ጥሪት የለም። የሕይወት መርሀቸው ግን ሁሌም በብርታት የተሞላ ነው። እሳቸው ያለፉበትን ፈታኝና ሻካራማ መንገድ ልጆቻቸው እንዲደግሙት አይሹም። የአቅማቸውን ሠርተው ድህነትን ማለፍ፣ መሻገር ይፈልጋሉ።
ብሩህ ተስፋ ስለ ልጆች …
ዘወትር እንደሚሉት እሳቸው በሕይወት እሳካሉ የልጆቻቸውን ትካዜ ማየት አይፈልጉም። በራሳቸው ትከሻ፣ በእጆቻቸው ብርታት ጥንካሬን ማሳየትና ማስተማር ዕቅዳቸው ነው። አሁን የሚኖሩበት የከሰል ንግድና አድካሚ ሥራው በየቀኑ ከሕይወታቸው አንድ ክር እንደሚመዝ ያውቃሉ። ጥቂት ቢያገኙበትም ብዙውን የሕይወት መልክ በግልጽ እየነጠቃቸው ነው።
ሁሉም የሆነው ስለልጆቻው መሆኑን ሲያስቡት ግን ውስጣቸው ደምቆ ይፈካል። በሥራ የሚዝል አካላቸው በብርታት ይቆማል። ደጊቱ አቅሙ ቢኖራቸው ከአቧራ የራቀ፣ ከብናኝ የጸዳ ንጹህ ቤት ቢገነቡ ይወዳሉ። ፍላጎት እንጂ በቂ አቅም ከእሳቸው እንደሌለ ሲያውቁ ግን ኀዘን ሲጎበኛቸው ይውላል። አንዳንዴ ደግሞ ሸክማቸውን የሚያቀል፣ ቀኝ እጃቸው የሚሆን አጋር ከጎናቸው ያለመኖሩ ትካዜን ይጠራባቸዋል።
ደጊቱ ዛሬም ቢሆን እንደቀድሞው መሥራትን ይሻሉ። ይህ እንዳይሆን በመውደቅ የተሰበረው ቀኝ እጃቸው ጥንካሬን ተነፍጓል። እንደትናንቱ እንጀራ መጋገር፣ ልብስ ማጠብ፣ ወጥ መሥራት አልቻሉም።
ደጊቱ ከዚህ ቀድሞ ሕመማቸውን ውጠው ለመሥራት ሞክረዋል። የውስጣቸውን ድካም ችለውም ከሥራ ውለዋል። ሁሉም ግን እንዳሰቡት አልሆነም። ሰባራው እጃቸው ከእሳቸው አላበረምና የልባቸውን አልሰማም፣ ከሀሳባቸው አልተስማማም።
ደጊቱ ብዙ የለፉላቸውን ልጆቻቸውን ዓለም ማየት ምኞታቸው ነው። ስለእነሱ ብዙ ሆነዋል፣ ጠቁረው ከስተዋል፣ አግኝተው አጥተዋል። እናም ያለፈው ድካማቸው ዛሬን አልፎ ነገን እንዲከፍላቸው ይሻሉ።
ደጊቱ ሁሌም እንዳለፈው ትናንት ብቻ መኖር ፍላጎታቸው አይደለም። ነገን በጤና ከቆሙ ኑሯቸውን መለወጥ፣ ሕይወታቸውን ማሻሻል ያቅዳሉ። ለዚህ ምኞታቸው መንግሥት ቀኝ እጃቸው እንዲሆን ማሰባቸው አልቀረም። ደሳሳዋ የንግድ ቤት በኮንቴነር ተለውጣ፣ በአካባቢው ውሃ መብራት ገብቶ፣ የእጃቸው ጥሪት ጨምሮ ማየት የዘወትር ህልማቸው ነው።
ይህ ህልም ዕውን እንዲሆን የአካባቢው አቅመ ደካማ እናቶች፣ ኑሯቸው ከእጅ ወደአፍ የሆነ ነዋሪዎች ሕይወት መለወጥ አለበት ብለው ያምናሉ። በአካባቢው አንዱ ከአንዱ የተሻለ ኑሮ የለውም። ሁሉም በዕድሜው የገፋና ተደጋግፎ መኖር የማይችል ነው።
ደጊቱ ስፍራውን ለአነስተኛ ንግድ ለማቋቋም የአስር ብር ዕቁብ ጥለው ቦታውን ካቆሙ ወገኖች አንዷ ናቸው። ዛሬ አብዛኞቹ በጤና ማጣትና በዕድሜ መግፋት ከቤት ውለዋል። እንዲህም እንዲያም ብለው የሚኖሩት እነ ደጊቱ የአንድ ወገን ድካማቸው በአንድ እጅ የማጨብጨብ ያህል ጎድሎባቸዋል። እሳቸውን መሰል ጠንካራ ሴቶች ዛሬን ኖረው ነገን ለመሻገር ተስፋ የሚሰጣቸው፣ ‹‹አለን፣ አለናችሁ›› የሚላቸውን አንደበት ይናፍቃሉ።
መልካምሥራአፈወርቅ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 21/2015