የማህበረሰቡ ግማሽ አካል እንደሆኑ የሚነገርላቸው ሴቶች በማህበራዊና ኢኮኖሚ ዘርፎች ጉልህ አበርክቶ እያበረከቱ መሆናቸው ይታወቃል። ‹‹ሴት ልጅን ማስተማር ማህበረሰብን ማስተማር ነው›› የሚባለውም ሴቶች በተለይም በማህበራዊ ተሳትፏቸው የላቀ አበርክቶ ያላቸው በመሆኑ ነው። እነዚህ ሴቶች አቅምና ችሎታቸውን አውጥተው መጠቀም እንዲችሉ ትምህርት ዋናው ቁልፍ ጉዳይ ቢሆንም፣ ሴቶችን ከትምህርት ገበታ የሚያጎድሏቸው በርካታ ጉዳዮችን መጥቀስ ይቻላል። ከእነዚህ መካከልም የሴቶች የንጽህና መጠበቂያ ምርትን በቀላሉ አለማግኘት አንዱ የራስ ምታት ነው።
የአብዛኞቹ ሴት ተማሪዎች ወርሃዊ ጭንቀት የሆነውን ከባድ ሸክም ለማቅለል ጥረት የሚያደርጉ ጥቂቶች ቢኖሩም፣ እነዚህ ጥቂቶች በርክተው ችግሩን በዘላቂነት መቅረፍ አልተቻለም። ዓመት ጠብቆ የሚከበረውን የሴቶች ቀን ወይም ማርች ስምንትን ጨምሮ የተለያዩ ቀኖችን በማስመልከት ሴት ተማሪዎች በንጽህና መጠበቂያ እጦት ምክንያት ከትምህርት ገበታ አይጉደሉ በማለት ጥረት የሚያደርጉ ግለሰቦችና ድርጅቶች ጥቂት የሚባሉ አይደሉም።
ከእነዚህም መካከል አደይ ዘላቂ የሴቶች የንጽህና መጠበቂያ ድርጅት አንዱ ነው። የድርጅቱ መስራች ወይዘሮ ሚካል ማሞ፤ የብዙ ሴቶች በተለይም የበርካታ ተማሪዎች ወርሃዊ ፈተናን ለማቃለል የሚታጠብ የሴቶች የንጽህና መጠበቂያ እያመረተች ከከተማ እስከ ገጠር ተደራሽ ለመሆን እየተጋች ትገኛለች።
አዲስ አበባ ከተማ ተወልዳ ካቴድራል ትምህርት ቤት የተማረችው ሚካል፤ የመጀመሪያ ዲግሪዋን በንግድ አስተዳደር አግኝታለች። በአብዛኛውን ጊዜዋንም በሥራው ዓለም በግል ሥራ አሳልፋለች። ከተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ የውጭ ድርጅቶች ጋር የመሥራት ዕድልም አግኝታለች። በተለይም ዓለም አቀፍ ከሆኑ እርዳታ ለጋሽ ድርጅቶች ጋር በነበራት ቀረቤታና የሥራ ግንኙነት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የወር አበባ መቀበያ ድህነት መረዳት ችላለች።
ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሴት ተማሪዎች በንጽህና መጠበቂያ ምርት እጦት በብዙ እየተፈተኑ እንደሆነና ችግሩ ስር የሰደደ መሆኑን የተረዳችው ሚካል፤ በወቅቱ የልጆች ልብስ በማምረት ሥራ ላይ ተሰማርታ እንደነበር ታስታውሳለች። የችግሩ አሳሳቢነት የቱን ያህል እንደሆነ ለመረዳት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ባሉ የተለያዩ ትምህርት ቤቶች ተዘዋውራለች። በወቅቱ ተማሪዎች በንጽህና መጠበቂያ እጥረት ምክንያት ከትምህርት መጉደላቸው ሳያንስ የሚፈጠርባቸውን የስነልቦና ጫና አሳዛኝና አስገራሚ በሆኑ ገጠመኞች ታጅቦ ከተማሪዎች አንደበት መረዳት ችላለች።
በመሆኑም ከወር አበባ ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር በሚገባ ለመረዳት ጊዜ አልፈጀባትም። ያደመጠቻቸው ለማመን የሚከብዱ ታሪኮችም እንቅልፍ አልሰጧትም፤ እናም ሳትውል ሳታድር የህጻናት አልባሳት ማምረቷን አቁማ የሴቶች ንጽህና መጠበቂያ ምርቶችን ለማምረት ስትወስን ሁለት ጊዜ አላሰበችም። የአፍሪካ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ ከተማ ሳይቀር የወር አበባ መቀበያ ድህነቱ ሥር የሰደደ መሆኑን የተረዳችው ሚካል፤ ተማሪዎች በአማካኝ በአንድ ወር ውስጥ ከሶስት እስከ አምስት ቀናት በወር አበባ ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው እንደሚጎድሉ፤ እንዲሁም ጭርሱኑ ትምህርት እንደሚያቋርጡ አጫውታናለች።
‹‹በወር አበባ ቁሳቁስ እጥረት ተማሪዎች እንዲሁም ሠራተኞች ሳይቀሩ ይቸገራሉ›› የምትለው ሚካል፤ ወደ ሥራው ስትገባ 10 ሚሊዮን ብር መነሻ ካፒታል በመያዝ የተለያዩ መነሻዎችን ወስዳ ማሽኖችን ከውጭ በማስመጣት ወደ ምርት ገብታለች። በወቅቱ ያመረተቻቸውን የንጽህና መጠበቂያ ምርቶች በምትኖርበት ለገጣፎ አካባቢ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም ለተፈናቃዮች በመለገስ የጀመረች ሲሆን፤ በዋናነት ግን ትኩረቷ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ እንዳይጎድሉ ለማድረግ ነውና ትልቁን ትኩረት ለተማሪዎች አድርጋለች።
‹‹አደይ የሴቶች የንጽህና መጠበቂያ ድርጅት እንደማንኛውም ቢዝነስ በንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ ያለ ቢሆንም በዋናነት በማህበረሰቡ ላይ በጎ ተጽዕኖ የሚያሳርፍ ድርጅት ነው›› የምትለው ሚልካ፤ የንጽህና መጠበቂያ ምርቶቹን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማህበረሰቡ የሚያደርስ አንደሆነና ማህበረሰቡ ላይ በሚያሳድረው በጎ ተጽዕኖ ደግሞ በሺዎች ለሚቆጠሩ ተማሪዎች ምርቶቹን የሚለግስ እንደሆነ ታስረዳለች። በቀጥታ ከሚለገሱት ተማሪዎች በተጨማሪ ከየትምህርት ቤቶቹ የሚመጡ የሴቶች ክለብ፣ ስካውትና ሌሎችም በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተሰማሩ ሴቶችን ለማነቃቃት በሚል ምርቶቹን በመለገስ ታግዛለች።
አደይ ዘላቂ የሴቶች የንጽህና መጠበቂያ እየታጠበ ለሁለት ዓመት የሚያገለግል ሲሆን፤ አንዱ እሽግ አራት የንጽህና መጠበቂያዎችን በውስጡ ይይዛል። አንዲት ሴት አራቱን የንጽህና መጠበቂያዎች በንጽህና በመያዝ እየቀያየረች ለሁለት ዓመታት መጠቀም የሚያስችላት ይሆናል። ምርቶቹን ለማምረት ንጹህና ጥራት ያላቸውን ኮተን የሆኑ ጨርቆችን በግብዓትነት የምትጠቀም መሆኑን የጠቀሰችው ሚካል፤ ፈሳሽ የመምጠጥ አቅማቸውም የተሻለና ምቹ እንደሆነ ነው ያስረዳችው። ምርቱም በተለይም ገና የወር አበባ ማየት ለጀመሩ ኮረዳዎች ሴቶች ደስ እንዲላቸውና እንዲወዱት በማሰብ ባለአበባና ሳቢ በሆኑ ኮተን ጨርቆች ይዘጋጃል።
የጨርቅ ግብዓቶቹን ከዚህ ቀደም ከውጭ አገራት ታስመጣ እንደነበር የምታስታውሰው ሚካል፤ በአሁኑ ወቅት ግን በአገሪቷ ውስጥ ካሉ ትላልቅ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ጋር ትስስር በመፍጠር በብዛትና በጥራት እያመርቱ እንደሆነም ገልጻለች። ከዚሁ ጋር በተያያዘም ዘላቂ የንጽህና መጠበቂያ ዘላቂነቱ መረጋገጥ የሚችለው ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ ምርት መመረት ሲችልና ከውጭ የሚገባውን ሞዴስ ማስቀረት ሲቻል እንደሆነ የምትናገረው ሚካል፤ አገር በቀል ምርቶችን በማበረታታት ከማህበራዊ አገልግሎቱ ባለፈ ኢኮኖሚውን መደገፍ እንደሚገባ አስረድታለች።
‹‹ለዚህም ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር እንዲሁም ከሴቶችና ህጻናት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ጋር በጋራ በመሆን ሴቶችን መደገፍ እንዲቻል እየተሠራ ነው›› የምትለው ሚልካ፤ ‹‹የአገሩን ሰርዶ በአገሩ በሬ›› እንዲሉ የሴቶች የራሳቸው ጉዳይ የሆነውን ዘላቂ የንጽህና መጠበቂያ ለማምረት ሴቶች ተሳታፊ እንዲሆኑና ምርቱም ሙሉ ለሙሉ በአገር ውስጥ እንዲመረት በማድረግ ከውጭ የሚገባውን ምርት ለማስቀረት በግሏ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቶቹ ጋር በመነጋገር ጥረት እያደረገች እንደሆነ አጫውታናለች።
የሴቶች የንጽህና መጠበቂያ እጥረት እንደ አገር የሴት ተማሪዎች ፈተና ሆኖ መቀጠሉን ያመለከተችው ሚልካ፤ ሴት ተማሪዎች በዚህ ምክንያት ከትምህርት ገበታ ከመቅረታቸው ባለፈ ዛሬም የውስጥ ሱሪ ምን እንደሆነ የማያውቁ፣ የተፈጥሮ ህግ የሆነው የወር አበባ በመጣ ጊዜ ከቤተሰብ የሚገለሉና የሚሸማቀቁ ሴቶች ቁጥራቸው ቀላል አይደለም ትላለች። ስለዚህ ከምርቱ ጎን ለጎንም የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶችን እንዲሁም የተለያዩ ቅስቀሳዎችና ጉትጎታዎች የግድ እንደሆኑ ነው ያስረዳቸው።
ምርቶቹን ከመለገስ በተጨማሪ ቅስቀሳ በማድረግና ግንዛቤ በመፍጠር ጭምር ማህበራዊ ኃላፊነቷን የምትወጣው ሚካል፤ አደይ ዘላቂ የንጽህና መጠበቂያን አምስት ሺ ለሚደርሱ ተማሪዎች በቋሚነት የምትለግስ ሲሆን፣ በተጓዳኝ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶችንና ቅስቀሳዎችንም ለተማሪዎችና ለሌሎችም ታደርጋለች። በተለይም ስለጉዳዩ ምንም አይነት ግንዛቤ ለሌላቸው እንዳይፈሩና የንጽህና መጠበቂያውን እንዲጠቀሙ ትምህርት ትሰጣለች። ይህን ተግባር የሚደግፉ አይ ኬር እና ጀግኒት ኢትዮጵያ የተባሉ ሁለት የበጎ ፈቃድ ድርጅቶች ስለመኖራቸው ያነሳችው ሚካል፤ ብርቄ በሚል መጠሪያ ‹‹አበባ አየሽ ወይ ትምህርት ቤት ትሄጃለሽ ወይ›› የሚል ንቅናቄው በ2014 ዓ.ም እንደጀመሩና በአሁን ወቅትም 50 ሺ ተማሪዎች ጋር መድረስ እንደቻሉ ነው ያስረዳችው።
በንቅናቄው አደይ ዘላቂ የንጽህና መጠበቂያ ምርቶቹን በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ እንዲሁም ሳሙናና ፎጣ በመጨመር ሁሉን አቀፍ በሆነችው የብርቄ ባልዲ ‹‹አበባ አየሽ ወይ ትምህርት ቤት ትሄጃለሽ ወይ›› በሚል የሚቀርብ ነው። የንቅናቄው ዋና ዓላማም በንጽህና መጠበቂያ እጦት ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው የሚጎድሉ የሴት ተማሪዎችን ቁጥር ለመቀነስ እንደሆነ ሚካል አስረድታለች።
የ‹‹አበባ አየሽ ወይ ትምህርት ቤት ትሄጃለሽ ወይ›› ንቅናቄ ተማሪዎችን ብቻ ዓላማ አድርጎ የተነሳ ቢሆንም በአገሪቱ ውስጥ በነበረው ጦርነት ምክንያት ተማሪዎችን ጨምሮ በርካታ ሴቶች ተፈናቃይ በመሆናቸው ከተማሪዎች ውጭም በተለያዩ አካባቢዎች ተደራሽ መሆን ችላለች። አዲስ አበባ መርካቶ አካባቢ የሚገኙ እንደ ሃሌሎያ፣ ሜዴይና ፈለገ ዮርዳኖስ ትምህርት ቤቶች ላሉ ሴት ተማሪዎች የሚታጠብ የንህጽህና መጠበቂያ ምርቶቹን በቋሚነት ያገኛሉ፡፡ በተጨማሪ ለአብነትም አፋር፣ ሀመር፣ ዋግህምራ፣ ሰቆጣ፣ ባሌ፣ ደብረብርሃንና ከሚሴ በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብና ተደራሽ መሆን ተችሏል።
ውሃ መቅጃ፣ ማጠቢያና ማስቀመጫ መሆን በምትችለው ባልዲ ሴቶች ዘላቂ የንጽህና መጠበቂያውን ጨምረው ምንም ሳይሳቀቁ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ እንደሚችሉ ያነሳችው ሚልካ፤ በተዘዋወረችባቸው አካባቢዎች የንጽህና መጠበቂያ ብቻ ሳይሆን የውስጥ ሱሪም የሌላቸው በርካቶች እንደሆኑ መታዘብ ችላለች። ሳሙናውና ውሃውም ቢሆን የብዙዎች አንገብጋቢ ችግር እንደሆነም ነው ያጫወተችን።
በአገሪቱ በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች በተለይም ርቀት ባላቸው አካባቢዎች ጭምር አደይ ዘላቂ የንጽህና መጠበቂያ ተደራሽ መሆን እንዲችል መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ የውጭ ድርጅቶች ጋር በጋራ እየሠራች እንደሆነ የተናገረችው ሚልካ፤ እነዚህ ድርጅቶች ምርቶቹን ከድርጅቱ ገዝተው በተለያዩ አካባቢዎች ተደራሽ የሚያደርጉ እንደሆነና የገበያ መዳረሻዋም በዚህ መልኩ እንደሆነ ነው ያስረዳችው። አንዳንድ ድርጅቶች ከንጽህና መጠበቂያው በተጨማሪም የውስጥ ሱሪዎችንም ጨምረው በመግዛት ተደራሽ እንደሚደርጉ ገልጻለች።
ዛሬም ድረስ ከባድ ራስምታት የሆነው የንጽህና መጠበቂያ በተለያዩ አካባቢዎች በተለየ መንገድ ይታያል ያለችው ሚካል፤ የውስጥ ሱሪ እንኳን የማያውቁ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ በርካታ ሴቶች የወር አበባው ፈሶ እስኪያልቅ አመድ ላይ በመቀመጥና ከቤታቸው ራቅ ብለው ላስቲክ አንጥፈው በመቀመጥ ጊዜውን የሚያሳልፉ ስለመኖራቸውም ትናገራለች። ሩቅ ሳንሄድ በየዩኒቨርሲቲው የሚገኙ ፍራሾች ስፖንጃቸው ተቦጫጭቆ የሚታየው የንጽህና መጠበቂያዎች መግዛት በሚቸገሩ ሴት ተማሪዎች ምክንያት ነው የምትለው ሚልካ፤ የችግሩ አሳሳቢነት ጥልቅና ሰፊ ነው ትላለች።
ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ አስቀድሞ በተካሄደ ጥናት 72 በመቶ የሚሆኑ የወር አበባ ማየት የጀመሩ ሴቶች የንጽህና መጠበቂያ ማግኘት የማይችሉ እንደሆኑ የጠቀሰችው ሚልካ፤ ይህን ችግር ለማቃለል አገር በቀል የሆኑ ዘላቂ የንጽህና መጠበቂያ ምርቶች በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ መሆን እንዲችሉ መሥራት ያሰፈልጋል ትላለች። አገር በቀልና ዘላቂ በሆኑ ምርቶች የእሴት ሰንሰለቱ ከምርቱ ጀምሮ እስከ ስርጭቱ ሁሉን ያማከለ መሆን አለበት። በተለይም ከምርት እስከ ስርጭት ሴቶች የሚመሩት ቢሆን ይበልጥ ውጤታማ መሆን ይቻላልም ብላለች።
ከአደይ ዘላቂ የንጽህና መጠበቂያ አምራች ድርጅት በተጨማሪ ሌሎች ተመሳሳይ ደርጅቶች ስለመኖራቸው ያመለከተችው ሚልካ፤ እነዚህን አምራቾች መንግሥት እንደ ሌሎች አምራች ድርጅቶች ሁሉ በአንድ አሰባስቦ ድጋፍና ክትትል ቢያደርግ በብዙ መልኩ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል አስታውቃለች። በተለይም ከስልጠና ጋር በተያያዘ ሴቶችን በማሰልጠን የሰለጠኑት ሴቶች ደግሞ በየአካባቢያቸው አምርተው ተደራሽ ማድረግ እንዲችሉ በማድረግ ትርጉም ያለው ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ነው ያስረዳችው።
‹‹አመቺ የሆነ የወር አበባ ቁስ ሳይቀርብ ሴቶችን ማብቃት አይቻልም›› የምትለው ሚካል፤ ሴት አምራቾችን ማበረታታት ተደራሽነትን ማስፋት እንደሚገባ ታስገነዝባለች። በወር አበባ ቁስ ምክንያት አንዲት ሴት በአማካኝ በዓመት 50 የትምህርት ቀናት ከትምህርት ቤት የምትቀር ሲሆን በዚህ ሁኔታ ሴቶችን ማብቃት የማይቻል እንደሆነና ብቁ ሴቶችን ማፍራት የሚቻለው የንጽህና መጠበቂያን ከማሟላት ጀምሮ እንደሆነ ነው ያስታወቀችው።
በአደይ ዘላቂ የንጽህና መጠበቂያ አምራች ድርጅት ውስጥ ለሚሠሩ 80 ሴቶች የሥራ ዕድል የፈጠረችው ሚካል፤ በቀጣይም ከንጽህና መጠበቂያ ምርቶች በተጨማሪ ሌሎች አልባሳትን ለማምረት ባገኘችው የማስፋፊያ ቦታ ላይ ተጨማሪ ማሽኖችንና ከ150 እስከ 200 ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር በዝግጅት ላይ ናት። በአሁኑ ወቅትም መደበኛ ከሆነው የንጽህና መጠበቂያ በተጨማሪ ለእርጉዞች የሚሆን የውስጥ ሱሪና አካል ጉዳተኛ ሆነው ዊልቸር ላይ ለዋሉ ሴቶች አመቺ የሆነ የንጽህና መጠበቂያ እያመረተች ለገበያ ታቀርባለች።
ተደራራቢ የአካል ጉዳት ላለባቸውና የአዕምሮ እድገት ውስንነት ለተጋለጡ ሴቶች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት መስጠት የግድ እንደሆነ የጠቆችው ሚካል፤ በተለይም የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ሴቶች ስለምንነቱ መረዳት ባለመቻላቸው መጠቀም አይፈልጉም። ስለዚህ ለእነሱና መሰል ችግር ላለባቸው ሴቶች ማስተማር ግንዛቤ መፍጠር የግድና ዋና ሥራ እንደሆነም አጫውታናለች።
በመጨረሻም ዘላቂ የንጽህና መጠበቂያ ምርቶቹን ለሁሉም ኢትጵያዊ ሴቶች በተለይም ለተማረዎች ተደራሽ ማድረግ ዋናውና የሁልጊዜ ምኞትና ዕቅዷ እንደሆነ የገለጸችው ሚልካ፤ ይህን እቅድ ለማሳካትም ከላይ ታች በማለት ግስጋሴዋን ቀጥላለች። እኛም ይህ ዕቅዷ ተሳክቶ ዘላቂ የንጽህና መጠበቂያ ምርት ኢትዮጵያ ውስጥ ችግር መሆኑ እንዲቀር ልባዊ ምኞታችን ነው። ሰላም!
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 21/2015