ወንድማማችነት በሰው ልጆች የሰውነት መለኪያ፣ የአብሮነት ማጠንጠኛ አምድ ነው። ወንድማማችነት በፍቅር ሲታጀብ ደግሞ በአለት ላይ የተመሰረተ የማይናወጥ አብሮነትን ይፈጥራል። ይሄ በፍቅር የተዋጀ አብሮነትም “ሰላም” በሚባል ስጋንም ነፍስንም የማረጋጊያ መሳሪያ አማካኝነት ወንድማማችነት ከፍ ብሎ እንዲገለጥ ያደርጋል። በጋራ አብሮ የመኖርን፤ በጋራ አብሮ የመልማትን፤ በጋራ አብሮ የመስራትና የመበልጸግን፤ በደስታም ሆነ በችግር ጊዜ በጋራ አብሮ የመቆምን ልዕልናም ያጎናጽፋል።
በፍቅር የተሳሰሩ ወንድማማቾች በሰላም አብሮ ለመኖር አይቸግራቸውም። ምናልባት እለታዊ አለመግባባት ቢያጋጫቸው እንኳን ወንድማማችነታቸው በልባዊ ፍቅር የተሳሰረ ነውና ግጭታቸውን በውይይት ለመፍታት፤ ከውይይታቸው ማግስትም ከልብ በሆነ ይቅርታ ግጭታቸውን ትተው በፍቅርና በሰላም አብሮ ለመኖር አይቸገሩም። እናም የሚዋደዱ ወንድማማቾች ስለ አብሮነታቸው፣ ስለ ሰላምና ልዕልናቸው ሲሉ ፀባቸውን በይቅርታ ይሽራሉ። ወንድማማችነታቸው ሻክሮ፣ ፍቅራቸው ተሸርሽሮ፣ አብሮነታቸው በጥርጣሬ ታጥሮ፣ ሰላማቸው ደፍርሶ፣ የነገ አብሮነታቸው ከተስፋ ተነጥሎ እንዲቆይ አይፈቅዱም።
ኢትዮጵያውያንም ትናንትን ተሻግረው ዛሬን የደረሱት፤ ዛሬን አሸንፈው በመሻገር ስለነገ ብሩህ አብሮነታቸው የሚታትሩት በዚሁ በፍቅር የተመላ የወንድማማችነት አውድና ለሰላምና ልዕልናቸው ካላቸው ተቆርቋሪነት የመነጨ ነው። ትናንትን በአብሮነት የዘለቁት ሳይጋጩ አልነበረም፤ ይልቁንም ወንድማማችነታቸውን አስበልጠው ከችግሮቻቸው ባሻገር በመመልከት በይቅርታ እያለፉት እንጂ። ዛሬም አብረው ያሉት ያላንዳች ኮሽታ አይደለም፤ ይልቁንም ለህልውናቸው ሲሉ ነፍጥ አንስተው ጭምር አብሮነታቸውን ለማጽናት በታገሉ ማግስት አብሮነታቸውን አተልቆ ለሚያጸናው ይቅርታና ሰላም ተሸንፈው እንጂ።
ለዚህ ማሳያው ደግሞ ባለፉት ሦስት ዓመታት እንደ ሃገር በተለይም በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ከነበረው ጦርነት ማግስት ስለ ሰላም፣ ስለ ይቅርታ፣ ስለ ፍቅርና አብሮነት፣ ስለ ነገ ልዕልናቸው ሲሉ ፀቡን በይቅርታ፤ ጥላቻውን በፍቅር፤ ጦርነቱን በሰላም ለመተካት በከፈሉት ከፍ ያለ ዋጋ እንጂ። ይሄ ይቅርታና ሰላም ደግሞ እንዲሁ አይገኝም። ምክንያቱም ይቅር ለማለት የፍቅር ልብ ይጠይቃል፤ ሰላምን ለማጽናትም ቂምና ቁርሾን መሻርን በእጅጉ ይሻል። ኢትዮጵያውያን ይሄንን ለማድረግ የሚሳናቸው አይደሉምና አደረጉት።
በጦርነት ውስጥ ሆነው ስለ ሰላም ተነጋገሩ፤ መነጋገራቸውም በፍቅርና በወንድማማችነት ነበርና በንግግር ሰላምን ወለዱ። ይሄ ሰላም ደግሞ ከቃል ያለፈ ተግባርን ስለሚጠይቅ ሰላምን የማጽናት ርምጃዎችን ወሰዱ። በይቅርታ ሰላምን ማጽናት ከፍ ያለ ጀግንነት የሚጠይቅ ቢሆንም፤ ለትግል የጀገነ ሕዝብና መንግስት ለሰላም ሃሞት አያጣምና ድፍረት በተሞላባቸው ውሳኔዎች ሰላሙን መሬት ማውረድ ተቻለ። ለሰላም ዋጋ የከፈሉ ወገኖችንም አገር አመሰገነች።
ከምስጋናው ማግስት የሰላሙን መንገድ የበለጠ ለማቅናት፤ የሰላሙን አውድ የበለጠ ለማስፋትና ለማጽናት የሚያስችል ሌላ ታላቅ ርምጃ ተወሰደ። ክቡር የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አሰቀድመው ባስታወቁት መሰረት በብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንትና የፓርቲው ጽሕፈት ቤት ዋና ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ የተመራ እና የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮችን እንዲሁም ሚኒስትሮችና ሌሎች ባለስልጣናትን የያዘ ልዑክ ትናንት መቐለ ገባ። ይህም በከፍተኛ የመንግስት አመራሮች የተደረገ የወንድማማችንት ማጽኛ የሰላም ጉዞ ነው። የወንድማማቾች የፍቅር ጉዞ ነው፤ የወንድማማቾች ነገን በጋራ ለመራመድ የሚያስችልን መደላድል የማጽናት ጉዞ ነው።
ይሄ ጉዞ ባሳለፍነው ሳምንት “ጦርነት ይብቃ፤ ሰላምን እናጽና” በሚል መሪ ሀሳብ በተካሄው ሰላም የማፅናት የዕውቅና መርሃ ግብር ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ የሁሉም ክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች በብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት እየተመሩ ወደ መቀሌ እንደሚሄዱ በገቡት ቃል መሰረት የተከናወነ ነው። የጉዞው ዓላማም እንዲሁ ደርሶ የመመለስ ሳይሆን፤ በጦርነቱ ምክንያት በጦርነት ቀጠናው ውስጥ የነበሩ ወገኖችን እንባ በማበስ፤ እንዲሁም የወደሙና የተበላሹ አካባቢና መሰረተ ልማቶችን ለመጠገን በሚደረገው ጥረት ክልሎች እንደወንድም ሕዝቦች ካላቸው ለማጋራት እና ይህን የሰላም ጅማሮ አጽንቶ ለማስቀጠል ያለመ ነው።
ሰላምና አብሮነትን ሽቶ፣ በፍቅር እና በይቅርታ ተሞልቶ ወደ ወንድሙ ደጅ የሄደው ወንድም ታዲያ፤ ከወንድሙ ደጅ ሲደርስ የተደረገለትም አቀባበል ይሄንኑ የሰላም፣ የፍቅር፣ የይቅርታና ወንድማማችነት ናፍቆት ያስተጋባ ነበር። ወንድማማቾች ሊጋጩ ቢችሉም የይቅርታ አቅም እንደማያጡ፤ አብሮነትና ሰላማቸውን አብዝተው እንደሚናፍቁም የገለጠ ነበር።
ወንድማማቾች በይቅርታ ተግባብተው ዳግም በፍቅር ተቃቅፈዋል፤ በሰላማቸውና በነገው የአብሮነት ጉዟቸው ዙሪያ ቁጭ ብለው መክረዋል፤ ያለፈው ጥፋት በማይደገምበት ብቻ ሳይሆን ቁስሉ በሚሽርበት ጉዳይ ላይ ተነጋግረዋል፤ የሕዝቦችን ሰላምና አብሮነት ለማጽናት ተግባብተዋል። በመሆኑም የተደረገው የወንድማማቾች ጉዞ ከዛሬ ባሻገር ላለምነው የነገ የከፍታ ግስጋሴው መሰረት የሚሆነውን ሰላም እና ፍቅር የማጽናት፤ ቁስልን የማሻር እና ወንድማማችነትን የማጽናት ከፍ ያለ ሚና አለው!
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 20/2015