ጅማ ዩኒቨርሲቲ እንደ መርህ ይዞ ከሚንቀሳቀሳቸው ነገሮች ዋነኛው ለማህበረሰቡ በምርምር የታገዘ ድጋፍ ማድረግ ሲሆን በዚህ ውጤታማ ሥራ አከናውኗል።በጅማ አካባቢ ለሚገኙ አርሶ አደሮች ምርታማት እገዛ በማድረግ በጅማ ዩኒቨርሲቲ የግብርናና እንስሳት ኮሌጅ ተጠቃሽ ነው።ኮሌጁ በምርምር የሚያገኛቸውን ቴክኖሎጂዎች ለአርሶ አደሩ በማድረስ ረገድ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል።በተጨማሪም ደግሞ በእንስሳት እርባታና ምርጥ ዘር በማስተዋወቅ የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትናና የገበያ ተጠቃሚ እንዲሆን ኮሌጁ አስተዋፅኦ አድርጓል። በጅማ ዩኒቨርሲቲ የግብርናና እንስሳት ኮሌጅ ዲን ዶክተር ፍቃዱ ምትኩ ኮሌጁ በአካባቢው እያደረገው ስላለው እንቅስቃሴና ሌሎች ጉዳዮች ከጋዜጣው ሪፖርተር ጋር ቆይታ አድርገዋል።ከእሳቸው ጋር የተደረገውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
አጠቃላይ የኮሌጁ እንቅስቃሴ የጅማ ግብርናና እንስሳት ኮሌጁ አምስት ዓላማዎች ይዞ ይንቀሳቀሳል።እነሱም የመማር ማስተማር፣ ምርምርና ስርፀት፣ የማህበረሰብ አገልግሎት፣ ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ እና መልካም አስተዳደር ሥራዎች ናቸው።ከዚህ ውስጥ ደግሞ የማህበረሰብ አገልግሎት ትልቁን ድርሻ ይይዛል።ኮሌጁ የማህበረሰብ አገልግሎት ሲሰጥ ሦስት ጉዳዮች ላይ አተኩሮ ነው።የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች ወደ ማህበረሰቡ እንዲሄዱ በማድረግ የማህበረሰቡን ችግር እንዲለዩ ይደረጋል።ተማሪዎቹ በመቀጠል ተዘዋውረው ላዩት ችግር መፍትሔ የሚሆኑ ነገሮችን ይሠራሉ።የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎች ደግሞ በራሳቸው የገንዘብ ፈንድ አፈላልገው የተለዩ የህብረተሰቡ ችግሮች ላይ ይሠራሉ።የተወሰነም ስልጠና ይሰጣሉ።ሌላው ምርምር ማድረግ ሲሆን የተሠራው ምርምር ውጤት ወደ ማህበረሰቡ እንዲወርድ ይደረጋል።ከእነዚህ ውጪ ዩኒቨርሲቲው በራሱ ገንዘብ በማፈላለግ የማህበረሰቡን ችግር የሚቀርፉ ቴክኖሎጂዎች ቀርፆ ይሠራል። የኮሌጁ ግብ ለአርሶ አደሩ ቴክኖሎጂ በመስጠት ክትትልና ድጋፍ በማድረግ የገበያ ትስስር እንዲፈጠር ማድረግ ነው። ለዚህ ደግሞ ውጤታማ የሆነ የምርምር ሥራ እየተሠራ ይገኛል።
በተጨማሪም ቀጣይነት ባለው የማህበረሰብ አገልግሎት ይሠራል። በቀጣይ አርሶ አደሩ ምን ቢሠራ ውጤታማ መሆን ይችላል የሚለውን ይጠናል። አርሶ አደሩ ድንች፣ ሽንኩርትና ቲማቲም ማምረት ቢጀምሩ ማስቀመጥ የሚችሉበት ቀዝቃዛ መጋዘን ተሠርቶ ተሰጥቷቸዋል። የድህረ ምርት ቴክኖሎጂ እየተሠራ የሚገኝ ሲሆን በተለይ የፍራፍሬ ምርትን ለማውረድ ወይም ለመቁረጥ ቴክኖሎጂዎች እየተሰጡ ይገኛሉ። በአገር አቀፍ ደረጃ ዩኒቨርሲቲው በዶሮ እርባታ ሽልማት አግኝተናል። ቴክኖሎጂው በኡጋንዳ፣ ታንዛኒያና ኬንያ ተሞክሮ ወስደውበታል።በቀጣይ በዶሮ ህክምና ውጤታማ ሥራ ለማከናወን ሥራዎች ተጀምረዋል። መንግሥት በጀት በመመደብ ድጋፍ ያደርጋል። ኮሌጁ በአገሪቱ ተመራጭ የሆነው ከማህበረሰቡ ጋር የሚሠራ በመሆኑ ነው። ማህበረሰቡን ለመደገፍ በፕሮጀክት ሥራ ይከናወናል።አሁን የምርምር ውጤቶችን ተግባር ላይ ለማዋል እንቅስቃሴ ተደርጓል። አቅራቢያ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በትብብር እየተሠራም ይገኛል።በአካባቢው የሚገኙ አርሶ አደሮች ገቢያቸው እየተሻሻለ ይገኛል። ዩኒቨርሲቲው ምርቶችን ለአካባቢው በጨረታ የሚሸጥ ሲሆን በስሩ ያሉ አርሶ አደሮች ግን ውጭ መላክ ጀምረዋል።
የሰብል ምርቶችና አትክልትን በተመለከተ እስከአሁን የተሠሩት ሲታይ ባለፈው ዓመት የተለያዩ ሰብሎች ላይ ትኩረት ተደርጎ ተሠርቷል። በተለይ የተለዩ ዝርያዎች ወደ አርሶ አደሩ ለማድረስ የተከናወነው ይጠቀሳል።ለምሳሌ ባለፉት ዓመታት ብቻ የሩዝ ምርት በአካባቢው አይታወቅም ነበር።ለአርሶ አደሩ የሩዝ ምርትን በማስተዋወቅ ረገድ ሰፊ ሥራ ተሠርቷል።በተጨማሪም የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተቀርፀው ወደ ተግባር ገብተዋል።ከዚህ ውስጥ የማሽላ ማሻሻያ ፕሮጀክትን ደረቃማ የሆነ አካባቢ ላይ እንዴት አደርጎ ድርቅን ተቋቁሞ ምርታማ ሊሆን እንደሚችል የሚታይበት ፕሮጀክት ይጠቀሳል።ይህ ፕሮጀክት በአሜሪካ መንግሥትና በአውስትራሊያ መንግሥት ድጋፍ የሚሸፈን ነው። ሌላው የተለያዩ ዝርያዎችን ወደ አርሶ አደሩ የሚያደርስ ፕሮጀክት ይገኝበታል።ለምሳሌ እንደ በቆሎና በከፍተኛ የፕሮቲን የዳበሩ እንደ ጤፍ፣ ስንዴና ባቄላ የመሳሰሉት ወደ አርሶ አደሩ እየደረሱ ይገኛሉ።
በአጠቃላይ ወደ 500 የሚሆኑ የቡና፣ የአቦካዶ እና የፍራፍሬ ዝርያዎች እንዲሁም የሞሪንጋ ሽፈራው ጨምሮ አርሶአደሩ እንዲጠቀም ተደርጓል።ለአርሶ አደሩም የተለያዩ ስልጠናዎች ይሰጣሉ።85 ለሚሆኑ ሞዴል አርሶ አደሮች በአትክልትና ፍራፍሬ ላይ በሥራ ላይ ስልጠና ተሰጥቷቸዋል።አካባቢው በአታክልትና ፍራፍሬ በጣም የታወቀ ነው።በዚህ ላይ አርሶ አደሩ የራሱ የሆነ ዕውቀት አለው።ያለውንም ዕውቀት እንዲጠቀምበት ድጋፍና ክትትል ይደረጋል። በአትክልት ዘርፉ ደግሞ ለአርሶ አደሩ ቅድሚያ ስልጠና እንዲወስድ ይደረጋል።በመቀጠል ደግሞ የተሻሻሉ ምርጥ ዝያዎችን ለአርሶ አደሩ ይሰጣል።አዳዲስ ነገሮች ሲመጡ በስልጠና አርሶአደሩ እንዲያውቀው በማድረግ ወደ ተግባር ይገባል።አንዳንዴ በምርምር የተገኙ ጥሩ ነው የሚባሉትን ዝርያዎች አርሶ አደሩ ላይቀበል ይችላሉ።ለምሳሌ የበቆሎ ምርት ወደ አርሶ አደሩ ተወስዶ በፍጥነት እንደሚደርስ በተግባር እንዲያዩ ይደረጋል።ነገር ግን ሲደርስ የመቆምና ከጫፉ የመድረቅ ባህሪ ስላለው ላለመጠቀም ፍላጎት ያሳያሉ።
የእንስሳት እርባታን በተመለከተ በእንስሳት እርባታ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች ተከናውነዋል። የዶሮና የዓሣ የተቀናጀ ልማት የሚባል ፕሮጀክት ተቀርፆ ሥራ ላይ ውሏል። በዚህ ፕሮጀክት ወደ 250 የሚሆኑ አባወራዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል። ግብርናንና ዓሣን በማቀናጀት አርሶ አደሩ ተግባራዊ እንዲያደርገው ስልጠና ተሰጥቷል። ቀደም ብሎ በአካባቢው የዓሣ ምርት አይታወቅም ነበር። በተሠሩ ሥራዎችም አርሶ አደሩ ዓሣን ከማርባት እስከ መመገገብ ደርሷል። ይህ ደግሞ ለምግብ ዋስትናቸው ጠቀሜታ አለው። ለዓሣው መራባት የዶሮ ተረፈ ምርት ጠቀሜታ ያለው ሲሆን ከዓሣው መራቢያ የሚወጣው ውሃ ደግሞ በውስጡ የሚይዘው ንጥረ ነገር ከፍተኛ በመሆኑ ለአፈር ለምነት እንዲውል ይደረጋል።አርሶ አደሩ ዓሣንና ዶሮን ማርባት በአንድ ላይ እንዲያከናውን እየተደረገ ነው።በዚህ 200 አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ሆነዋል።ሌላው አሳን፣ ዶሮንና አታክልትን በአንድ ላይ የያዘ ፕሮጀክት አለ።
እንደዚህ ዓይነት አሠራሮችን ወደ አርሶ አደሩ በፍጥነት ለማዳረስ እየተሠራ ይገኛል።በዚህ 15 አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ናቸው።በዶሮ እርባታ አርሶ አደሩ ተጠቃሚ እንዲሆን የአንድ ቀን ጫጩት እንደሚሰጣቸው በማድረግ እንዲያረቡና እንዲጠቀሙ ይደረጋል።በእንስሳት ህክምና እስከአሁን ለአባ ሰንጋ በሽታ አንድ ሚሊዮን ክትባት ተሰጥቷል። በኮሌጁ የዶሮ ዝርያዎችን የማዳቀል ሥራዎች የሚከናወኑ ሲሆን እስከአሁን አራት ዝርያዎች ተለይተው ወጥተዋል። በእንስሳት ማዳቀል ላይ ደጎሞ 500 ላሞች ከተለያዩ የላም ዝርያዎች ጋር እንዲዳቀሉ ተደርገዋል።ይህ ሲባል በደንብ ተሠርቷል ማለት አደለም። መንግሥት በሚመድበው በጀት ማህበረሰቡ ተጠቃሚ የሚሆንበትን ሁኔታ እየተሠራ ይገኛል። የዶሮ ጫጩቶችን ሁሉም አርሶ አደር ይወስዳቸዋል።
የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃን በተመለከተ በተፈጥሮ ሀብት አጠባበቅ ደግሞ የአፈር ለምነት ለመጠበቅ ባፉት ዓመታት የተበላሹ መሬቶች ላይ ዛፎችና ሳር በመትከል መልሶ እንዲያገግም እየተደረገ ይገኛል።ለአፈርና ውሃ ጥበቃ የሚሆን የሳር ዝርያ በማምጣት ጥቅም ላይ ውሏል።በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ላይም የሚሠሩ ሥራዎች አሉ።ዛፎችን በመትከል ጥበቃ ይደረጋል።ለምሳሌ መረዋ ገዳም ላይ ለሚሠሩ የደን ልማት ሥራዎች ላይ ኮሌጁ ተሳትፎ አለው።ኮሌጁ በየጊዜው ችግኞችን በመትከል የመንከባከብ ሥራ ያከናውናል።በመስኖ ልማት ደግሞ ሁለት ትላልቅ የውሃ መሳቢያ ማሽኖችን ለሁለት ወረዳዎች ተሰጥቷል።እያዳንዱ ማሽን 80 ሄክታር የማልማት አቅም አለው።በጅማ ዞን በቀርሳ ወረዳ 36 ሄክታር ላይ በመስኖ በቆሎ ተዘርቷል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 21/2011
መርድ ክፍሉ