የመንገድ ትራፊክ አደጋ አሁንም ዋነኛ ዓለም አቀፍ የማኅበረሰብ ችግር ነው። አደጋው ለበርካታ ሰዎች ሕይወት መጥፋትና አካል መጉደል መንስኤ ሲሆን አሁንም የእለት ተእለት አሳዛኝ ክስተት እንደሆነ ቀጥሏል። በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ በአማካይ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሰዎች በትራፊክ አደጋ እንደሚሞቱ በቅርቡ የወጡ አኃዛዊ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ከ30 እስከ 50 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ ለአካል ጉዳት እንደሚዳረጉ፤ የትራፊክ አደጋ ከሀገራት አጠቃላይ ምርት በአማካይ ከሦስት አስከ አምስት በመቶ ያህሉን እንደሚሳጣም እነዚሁ መረጃዎች ያሳያሉ።
የትራፊክ አደጋ በኢትዮጵያም ዋነኛ የሞት መንስኤ ከሆነ ሰነባብቷል። በዚሁ አደጋ ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በትራፊክ አደጋ ምክንያት በየዓመቱ ሕይወታቸው ይቀጠፋል። ከአሽከርካሪ ሥነ-ምግባር ጋር የተያያዙና ሌሎችም ምክንያች እንዳሉ ሆነው ከፍጥነት ወሰን ገደብ በላይ ማሽከርከር ለአደጋው ዋነኛ መንስኤ እንደሆነ በተደጋጋሚ ተገልጿል።
የመንገድ ትራፊክ አደጋ ዋና ዋና መንስኤዎች ላይ ያተኮሩ፣ ውጤታማነታቸው በተረጋገጡና መረጃ ላይ መሠረት ያደረጉ የመንገድ ደህንነት የመፍትሔ ርምጃዎችን በመውሰድ አደጋውን መከላከል እንደሚቻል ብዙዎች ይስማማሉ። ጉዳዩ የተለያዩ ተቋማትን ያሳተፈ ፈርጀ ብዙ ሥራዎችን ተግባራዊ መደረግንም ይጠይቃል።
ለዚህ ደግሞ መረጃ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ከግምት ውስጥ በማስገባት የጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳት ምርምር ተቋም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኅብረተሰብ ጤና ትምህርት ቤት ጋር በመተባበር የአሽከርካሪዎችና የተሽከርካሪዎች ተጠቃሚዎችን የመንገድ አጠቃቀም የመንገድ ዳር ዳሰሳ ጥናት እ.ኤ.አ ከ2015 እስከ 2022 ለሰባት ዓመታት ሲያካሂድ ቆይቶ የጥናቱን ውጤት በቅርቡ ይፋ አድርጓል።
በትራፊክ ግጭት ዋና ዋና መንስኤዎች ላይ ማለትም በፍጥነት ማሽከርከር፣ የደህንነት ቀበቶና የልጆች የደህንነት መቀመጫ እና የጭንቅላት መከላከያ ቆብ አጠቃቀም ላይ የመንገድ ዳር ምልከታ ተደርጎ በተለይ በአዲስ አበባ ለሚከሰቱ የትራፊክ አደጋዎች ዋነኛ ምክንያት አሁንም ከፍጥነት ወሰን በላይ ማሽከርከር መሆኑና ችግሩ አሁንም መቀጠሉ ተጠቁሟል። ይኸው የዳሰሳ ጥናት 59 በመቶ የሚሆኑ ተሽከርካሪዎች ከፍጥነት ወሰን በላይ ሲያሽከረክሩ መስተዋላቸውንና ይህ አኃዝ በተከታታይ እየጨመረ ስለመምጣቱ አሳይቷል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኅብረተሰብ ጤና ትምህርት ቤት መምህርና ዋና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ዋቅጋሪ ደሬሳ ከፍጥነት ወሰን በላይ በማሽከርከር ለሚደርሰው አደጋ አሸከርካሪዎች ትልቁን ድርሻ ቢወስዱም ከመንገድ ሁኔታና ከትራፊክ መጨናነቅም ጋር ይያያዛል። የትራፊክ መጨናነቅ ሲባል አሽከርካሪዎች በፍጥነት ወደ ሥራ ቦታቸውና ወደተለያዩ ጉዳዮቻቸው ጋር ለመድረስ ከትራፊክ መጨናነቁ ለማምለጥ በፍጥነት ሲያሽከረክሩ አደጋ ሊደርሱ ይችላሉ።
ነገር ግን ይህ የአሽከርካሪዎቹ ሁኔታ በትክክል ከግንዛቤ ውስጥ ገብቶ አደጋው እንዳይከሰት የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ የሚገኙት። ለአብነትም በተለያዩ ቁልቁለታማ የከተማዋ መንገዶች ላይ ፍጥነት መቀነሻዎች ተሠርተዋል። እንደዛም ሆኖ ግን የአሽከርካሪዎች የፍጥነት መጠን በሚፈለገው ልክ ሊሆን አልቻለም። ስለዚህ በፍጥነት ማሽከርከር ምክንያት የሚደርሰው የትራፊክ አደጋ መንስኤ የተለያየ ሊሆን ይችላል። ይሄ ነው ብሎ አንድ መንስኤ ብቻ ማስቀመጥ አይቻልም። ከአሽከርካሪዎች ሥነ ልቦና፣ ባሕሪይ ሊሆንም ይችላል።
ጥናቱ ሲካሄድ የቆየው በመንገድ ዳር ምልከታ በመሆኑና በፍጥነት ሲያሽከረክሩ የነበሩ አሽከርካሪዎችን የማያካትት በመሆኑ ጥናቱ ጥልቅ የሆነ ከፍጥነት በላይ የማሽከርከርና አደጋ የማድረስ መንስኤው ምን እንደሆነ አይጠቁምም። በአሽከርካሪዎች ሥነ ባሕሪ ዙሪያም ጥልቅ ቃለ ምልልስ አልተደረገም። በመሆኑም በነዚህ የመንገድ ዳር ምልከታዎች ነው ፍጥነት አሁንም የትራፊክ አደጋ ዋነኛ መንስኤ መሆኑ የተለየው።
በአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ የመንገድ ትራፊክ ቁጥጥርና ሁነት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ቢኒያም ጌታቸው በበኩላቸው እንደሚገልፁት በአዲስ አበባ ከተማ ለትራፊክ አደጋ ትልቁ መንስኤ ፍጥነት መሆኑ በዳሰሳ ጥናቱ ተመላክቷል። የቀበቶ አጠቃቀምም ከሀምሳ በመቶ በታች ነው። የጭንቅላት መከላከያ ቆብም አጠቃቀም አነስተኛ መሆንም ለአደጋው መበራከት አስተዋፅዖ እያደረገ ይገኛል።
ነገር ግን 59 ከመቶ የሚሆኑት የከተማዋ አሽከርካሪዎች ከተቀመጠው የፍጥነት ወሰን ገደብ ላይ የሚያሽከረክሩ ናቸው። ለዚህም የፍጥነት ቁጥጥር ሥርዓቱ ክፍተት ያለበት መሆኑ፣ የንግድ ተሽከርካሪዎች ገቢያቸውን ለማሳደግ በፍጥነት ማሽከርከር እና አርፍዶ ወጥቶ ቶሎ ለመድረስ በፍጥነት ማሽከርከር እንደ ዋና ዋና መንስኤዎች ይጠቀሳሉ። ከዚህ አንፃር አደጋውን ለመከላከል በይበልጥ መሠራት ያለበት በዚሁ በፍጥነት ላይ ነው።
በፍጥነት ማሽከርከር ምክንያት የሚከሰተውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ በከተማዋ በርካታ ቦታዎች ላይ የፍጥነት ቁጥጥር በአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንትና በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ይካሄዳል። ይህንኑ የፍጥነት ቁጥጥር ሥርዓቱን ለማሳደግ ራዳሮች ቋሚ ሆነው የሚሰቀሉበትንና ከዛ መረጃ በመውሰድ ቅጣት የማበጀት ሥርዓት ለመዘርጋት እየተሠራ ይገኛል። በተለይ በአዲስ አበባ መገናኛ አካባቢ የትራፊክ ማኔጅመንት ማዕከል ከተቋቋመ ወዲህ እነዚህን ችግሮች እየቀነሳቸው መጥቷል።
ከዚህ በኋላም ቁጥጥሩ በካሜራ ስለሚሆን ወደ ዘመናዊነት ለመግባት ኤጀንሲው እየተንደረደረ ነው። በዚሁ መንገድ ችግሩ ይፈታል ብሎ ያስባል። በሌላ በኩል ደግሞ በመንገድ ላይ ያሉ የፍጥነት መቀነሻዎች በኮንክሪት ወይም በአስፓልት የተሠሩ ነበሩ። ይሁንና አሁን ከኮንክሪት ወደ ፕላስቲክ እንዲሸጋገሩ ተደርጓል። ይህም ከአንዱ ቦታ ወደሌላው ቦታ በቀላሉ ለማንቀሳቀስ ያስችላል ተብሎ ታምኖበታል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 19/2015