እኛ ኢትዮጵያውያን በጀግንነት የምንታማ ሕዝቦች አይደለንም። እስከ ዛሬዋ ቀን ድረስ ነፃነታችንን አስጠብቀን የቆየነው በብዙ ተጋድሎ በታጀበ የጀግንነት ገድል ነው። ይህ ደግሞ ከእኛ ተርፎ ለጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ትግል መነቃቃት የፈጠረ ፤ ብዙዎች በነፃነት አንገታቸውን ቀና አድርገው ኮርተው እንዲኖሩ ያስቻለ የማንነታችን አንዱ ገጽታ ነው ።
የትኛውም ኢትዮጵያዊ ስለ ሃገር እና ስለ ነፃነት ጉዳይ ተነስ ፣ታጠቅ ከተባለ ጨርቄን ማቄን የሚል አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ስለሀገሩ እና ነጻነቱ መሞትን እንደ ክብር የሚቆጥር ነው። በትውልዶች መንሰላሰል ውስጥ የታየውና ትናንትም የተስተዋለው ይሄው ነው። አብዛኛው የታሪክ ትርክቶቻችንም ይህንን እውነታ በደማቅ ቀለሞች የሚያጎሉ ናቸው።
ይህ ታሪካችን ዓለም አቀፍ እውቅና ያተረፈልን የመሆኑን ያህል፣ ስለ ጀግንነታችን ለነፃነት ስላለን ቀናዒነት ብዙ ምስክሮችን የፈጠረልን ያህል፣ በየወቅቱ በሚፈጠሩ ግጭቶች የምንከፍለው ያልተገባ ዋጋ ሃገራዊ ገጽታችን ከጦርነትና ከዚህ ከሚመነጭ ድህነትና ጠባቂነት ጋር ተቆራኝቶ ብሔራዊ ክብራችንን ሲያጠለሽብን ቆይቷል።
ችግሮችን በሰከነ መንፈስ ቁጭ ብሎ በውይይት መፍታት ባለመቻሉ በሚከሰቱ ግጭቶች ማግስት በአሸናፊ ተሸናፊ ትርክት በመጓዝ፣ የቀደሙት ትውልዶች ብዙ ዋጋ ከፍለዋል፣ ይህ የተዛባ አስተሳሰብ አሁን ያለውንም ትውልድ ጠልፎት ምንያህል ዋጋ እንዳስከፈለው የትናንቱን ሃገራዊ እውነታ በሰከነ መንፈስ ተመልሶ ማየት ተገቢ ነው።
ችግሮችን ሁሉ በኃይልና በኃይል ብቻ በመፍታት ላይ የተመሠረተው የፖለቲካ ባሕላችን፤ ኃይል አምላኪ ግለሰቦችና ቡድኖችን በመፍጠር፤ ይህንን በአሸናፊ ተሸናፊ ትርክት ሥጋና ደም እንዲለብስ በማድረግ፣ ሃገር እንደሃገር ዘላቂ ሰላም እንዳይኖራት አድርጓል። ቂም በቀልና ሴራ የሃገራዊ ፖለቲካው የረጅም ዘመን መገለጫ እንዲሆን አስገድዷል።
ለዘመናት አሸናፊው የአሸናፊነት መሠረቱ የኃይል የበላይነት መሆኑ፤ የተሸናፊውም ሽንፈቱ የኃይል ሚዛኑ መሆኑ ለዘላቂ ሰላም መሠረት መሆን አልቻለም። ከዚህ ይልቅ አሸናፊው አሸናፊነቱን ለማጽናት፣ተሸናፊውን ከሽንፈቱ ወጥቶ በአሸናፊነት ሰገነት ላይ ለመውጣት በማያቋርጥ የደባ እና የሴራ ተግባራት ላይ እንዲቆሙ፤ ተስፋቸውም በዚሁ ላይ እንዲመሠረት አድርጓል ።
በዚህም ሕዝባችን እንዲከፍል የተገደደው ዋጋ ለመናገር የሚከብድና የፖለቲካ ትርክቱ ከፈጠረው የአሸናፊና ተሸናፊ ትርክት በላይ የሆነ ነው። የትውልዶችን የዘመናት የበለጸገች ሀገር ፈጥሮ እና አይቶ የማለፍ ከፍ ያለ ተስፋ እና ራዕይ ያኮላሸ ፤ ስለነገዎቹን ጽልመት አልብሶ በተሰበረ ልብና መንፈስ ወደ መቃብር እንዲወርድ ያደረገ ነው።
የአንድ ትውልድ ስኬታማነት ዋነኛ መለኪያዎች መካከል አንዱ የሚኖርበትን ዘመን ለመዋጀት ያለው አቅምና ዝግጁነት ነው፤ ከዚህ አኳያ ዛሬ ላይ ያለውን ትውልድ ከተሳሳተ ትርክት ከመነጨ የፖለቲካ ባሕላችን እስካሁን ከከፈለው ያልተገባ ዋጋ በላይ አይገባም። ካለበት ዘመን አንጻር ዘመኑን በሚዋጅ አስተሳሰብ ራሱን ማረቅ ይኖርበታል ።
ለዚህ ደግሞ ከሁሉም በላይ ራሳችንን ለሰላም ማጀገን፤ ለዚህ የሚሆን አዕምሯዊ እና መንፈሳዊ ዝግጁነት ማዳበር ይጠበቅብናል። ራስን ከግጭት ነጋዴዎች የጥፋት እና የግርግር ትርክት በመጠበቅ፤ ለራስ፣ ለምኖርበት ማኅበረሰብና ለሀገር ዘላቂ ሰላም በኃላፊነት መንቀሳቀስ ይኖርብናል። ይህንን ማድረግ ዘመኑን መዋጀት ነው ።
ይህንን ማድረግ የቀደሙት ትውልዶችንም ሆነ የራስን ሀገር ለምታና በልጽጋ የማየት ተስፋና ራዕይ እውን ማድረግ የሚያስችል ጠንካራ መሠረት መጣል፤ በግጭትና በጦርነት እንደሀገር የከፈልናቸውን ያልተገቡ ዋጋዎች በተሻለ መልኩ ለመካስ የሚያስችል አዲስ አስተሳሰብና የታሪክ ትርክት ማጽናት ነው!
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 19/2015