ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ ከምታቀርበው ምርት ይልቅ ከውጭ ገበያ የምትሸምተው እንደሚልቅ ይታወቃል። ይህ በዋናነት የሆነው የሀገር ውስጥ ምርት አቅርቦት ከተጠቃሚው ፍላጎት ጋር ባለመጣጣሙ ይሁን እንጂ፣ ዜጎች የአገራቸውን ምርት የመጠቀም ዝቅተኛ ልምድ ያላቸው መሆኑም ተጨማሪ ምክንያት እንደሆነ ይታመናል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ማኅበረሰቡ ለአገሩ ምርት ያለው ዝቅተኛ ግምት አገሪቱን የውጭ ሸቀጥ ማራገፊያ ከማድረጉም በላይ፣ በኢኮኖሚ በኩልም በከፍተኛ ደረጃ የውጭ ጥገኛ እንዳደረጋት አይካድም። ይህም በውጪ ምንዛሪም ረገድ ከምታስገባው ይልቅ የምታወጣው እንዲበረክት በማድረግ ተደራራቢ ችግሮችን እንድትጋፈጥ አስገድዷታል።
በኢትዮጵያ ከሚመረቱ ምርቶች ውስጥ ጥራታቸው የዓለም ገበያ መስፈርትን ያሟላና ዋጋቸውም ተመጣጣኝ የሆኑ ቢኖሩም፣ ማኅበረሰቡ የአገሩን ምርት መጠቀም ላይ ያለው አመለካከት ዝቅ ያለ በመሆኑ፣ በብዛት ለምርቶቹ ቅድሚያ ሲሰጥ አይስተዋልም።
ከሀገር ቤት ምርቶች ይልቅ የውጪ ምርቶች በመጠቀም ረገድ እንደ ማኅበረሰብ ትልቅ ችግር መኖሩ አይካድም። ይህ ችግር ግን ማኅበረሰቡን በሚመሩ ፖለቲከኞች፣አርቲስቶችና ሌሎች ታዋቂ ሰዎችም በስፋት እንደሚስተዋል በየጊዜው መታዘብ ይቻላል። በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ መሪ የነበሩት(ካልተሳሳትኩ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ) ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎቻቸውን ሰብስበው ያነሱትን ጉዳይ ላስታውስ። የሀገር መሪው የሥራ ኃላፊዎቹን በተሰበሰቡበት “ሀገሬን እወዳለሁ ትላላችሁ፣ ሀገርን መውደድ የሚጀምረው የሀገር ውስጥ ምርቶችን በመጠቀም ነው፣ እስቲ ሁላችሁም ዝቅ ብላችሁ የተጫማችሁትን ጫማ ተመልከቱ?” ብለው ይጠይቃሉ። እውነትም ጎንበስ ብለው ጫማቸውን ሲመለከቱ አንዳቸውም የሀገር ውስጥ ምርት አልተጫሙም። ሁሉም ከጫማ እስከ ሱፍና ሸሚዝ የለበሱት የጣሊያን ምርቶችን ነበር።
በእርግጥ እንደ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም አይነት የኢትዮጵያ የቀድሞ መሪዎች ሀገር ውስጥ የተሠሩ የካኪ ልብሶችን በማዘውተር ለሕዝብ አርአያ ለመሆን ያደረጉትን ጥረትም እዚህ ጋር ማስታወስ ይቻላል። ይህ ጥረት ግን የአንድ ወቅት አጀንዳ ከመሆን አልፎ አያውቅም። ተፅዕኖ ፈጥሮም በሕዝብ አስተሳሰብ ላይ ለውጥ አላመጣም። በእርግጥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህም ቢሆን አንዳንድ የፖለቲካ ሰዎች፣አርቲስትና ታዋቂ ሰዎች ወደ ቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ሲሉ በሀገር ባሕል አልባሳት እያጌጡ ማየት ተለምዷል። ይህ ግን በብዛት የሚያደርጉት በሀገር ባሕል ከመኩራት አንፃር እንጂ በሀገር ምርት ከመኩራት ጋር የተያያዘ ነው ለማለት ከባድ ነው። ምክንያቱም ለሆነ ፕሮግራም የሀገር ባሕል ልብስ መልበስና በአዘቦት ቀናት የሀገር ውስጥ ዘመናዊ አልባሳት ሞልተው እያሉ በውጪ ሱፍና ከራቫት ማጌጥ ለየቅል ናቸውና። ይህ የሚያሳየው በሕዝብ ብቻ ሳይሆን ተፅዕኖ ፈጣሪ በሆኑ ሰዎች ዘንድም የአስተሳሰብ ችግሩ እንዳልተቀረፈ ነው።
የምሥራቅ እስያ አገራት የሆኑት እንደነ ቻይና፣ ጃፓን፣ ታይላንድ እና የመሳሰሉት ከምዕራባውያን ሀገራት የሚደርስባቸውን ጫና ለመመከትና ሉዓላዊነታቸውን ለማስጠበቅ ትልቁ መፍትሔ ኢኮኖሚያቸውን ማሳደግ መሆኑን በመረዳት፣ የሀገር ውስጥ ምርትን መጠቀም መጀመራቸው ዛሬ ለደረሱበት የተሻለ አቅም ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንዳበረከተላቸው ይነገራል።
‹‹Asian Tigers›› በመባል የሚታወቁትና በዚሁ በምሥራቅ እስያ ክፍለ ዓለም የሚገኙት ሲንጋፖር፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ታይዋን እና ሆንግ ኮንግም የፈጣን ዕድገታቸው ዋነኛ ምስጢር የሀገራቸውን ምርት፣ ቴክኖሎጂና ዕውቀት፣ እንዲሁም ሌሎች ከሀገራቸው ጋር ተያያዥ የሆኑ ውጤቶችን ለማሳደግና ለመጠቀም ያሳዩት ቁርጠኝነት ነው ተብሎ ይታመናል።
ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑት ሕንዶች ናቸው። ሕንዳውያን እንኳን ሀራቸው ውስጥ እየኖሩ በውጪ አገራትም ኑሯቸውን ቢያደርጉም ከሀገራቸውን ምርት ውጪ በተለይም በአልባሳት ረገድ አለመጠቀምን እንደ አንድ የሕይወታቸው መርሕ አድርገው እንደሚቆጥሩ ተመስክሮላቸዋል። በኢትዮጵያ በርካታ ሕንዳውያን በተለይም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ዩኒቨርስቲዎች ለማስተማር ኑሯቸውን እዚሁ ማድረጋቸው ይታወቃል። እነዚህ ሕንዳውያን እንኳን አልባሳትን ቀርቶ የሚያጨሱትን ሲጋራ ሳይቀር ከአገራቸው ምርት ውጪ “ወይ ፍንክች” እንደሚሉ በቅርብ የሚያውቋቸው ይመሰክራሉ።
ወደ እኛ አገር ስንመጣ በበርካቶች ዘንድ አንበሳ ጫማ ማድረግ እንኳን የኋላ ቀርነት ምሳሌና መበሻሸቂያ ሲሆን በብዙ አጋጣሚዎች መታዘብ ይቻላል። አስገራሚው ጉዳይ ግን ለውጪ ምርቶች ብቻ ተገዢ የሆኑ ሰዎች ተመልሰው ስለ ሀገር ወዳድነትና ስለ ሀገር ፍቅር ሕዝብን ሲመክሩና ሲያስተምሩ ማየት ነው። ሀገሬን እወዳለሁ የሚል አንድ ሰው ይህችን ትንሽ ነገር ለሀገሩ ማድረግ ካልቻለ እንዴት ለሌላው ነገር ይታመናል?።
ከሀገር ውስጥ ምርቶች ያነሰ ጥራትና የበለጠ ዋጋ ያላቸው ምርቶች ከውጭ አገር የተገኙ ስለሆኑ ብቻ እንደ ልብ ሲሸጡ ማየት ብርቅ አይደለም። ሌላው አስገራሚ እውነታ ከውጪዎቹ ይልቅ በተቃራኒው የኢትዮጵያ ምርቶች ሌላ አገር ገበያ ውስጥ አዲስ የገበያ ሥያሜ ተሰጥቷቸው በውድ ዋጋ መሸጣቸው ነው። ይህ አላዋቂነት እንጂ ሌላ ሊባል አይችልም።
ይህ ዜጎች የሀገርን ምርት ያለመጠቀም ልማዳቸው፣ የአገር ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪዎች እንዳያድጉ፣ የሠለጠነ የሰው ኃይል እንዳይኖር እና የሥራ ዕድል እንዳይስፋፋ በማድረግ በአጠቃላይ ሀገሪቱን በብዙ መልኩ የሚጎዳ አስተሳሰብ ነው። እኛ ግን አንድም ይህን ካለመገንዘብ ለሀገር ውስጥ ምርቶች ግድ የለንም። ግንዛቤው አላቸው የሚባሉ ሰዎችም አገራቸውን እንደሚወዱ የሀገር ምርት በመሸመት ለማሳየት ወይ ቸልተኛ ናቸው ወይ ደግሞ ፍላጎቱ የላቸውምና ሁላችንም እናስብበት።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 18 ቀን 2015 ዓ.ም