ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፣ “ጦርነት ይብቃ፤ ሰላምን እናጽና” በሚል መሪ ሀሳብ በተካሄደው ሰላም የማፅናት የዕውቅና መርሐ ግብር ላይ ያደረጉት ንግግር
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፣ “ጦርነት ይብቃ፤ ሰላምን እናጽና” በሚል መሪ ሀሳብ በተካሄደው ሰላም የማፅናት የዕውቅና መርሐ ግብር ላይ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል። መልዕክታቸውም “ሃገራችን ፋታ ትፈልጋለች፤ ሕዝባችንም ሰላም እና ደህንነቱ እንዲጠበቅ እና ሕይወቱ ወደተቃና አቅጣጫ እንዲመለስለት ይጠብቃል፤ ለዚህም ዓውዳችን ሰላም፣ ቋንቋችን ልማት እና አብሮነት መሆን ይኖርበታል፤” ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንንን ሙሉ ንግግር እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ክቡራን አፈጉባኤዎች፣ ክቡር ሙሳ ፋኪ ማሃማት የአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ኮሚሽን ሊቀመንበር፣ ክቡራን የቀድሞ ፕሬዚዳንቶች፣ ክቡራን የኅብረቱ የፓናል አባላት፣ ክቡራን የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች፣ ክቡራን ሚኒስትሮች፣ ክቡር የኢጋድ ዋና ፀሐፊ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ፣ ክቡራን የዕለቱ ጥሪ የተደረገላችሁ እንግዶች፣ ክቡራት እና ክቡራን፤
በቅድሚያ ሁሉን አውዳሚ የሆነው ጦርነት ቆሞ በተጀመረው ሰላም የማፅናት እና የዕውቅና ፕሮግራም ላይ ለመታደም ስለበቃን በሰላም ኮሚቴው እና በራሴ ስም እንኳን አደረሳችሁ! እንኳ አደረሰን ለማለት እወዳለሁ፡፡
ከአውዳሚው ጦርነት በመውጣት ወደ ሰላም ለመምጣት በኢትዮጵያ ባለቤትነት፣ በአፍሪካ ኅብረት መሪነት በተለይም “ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ” በሚለው መርሕ መሠረት የሠላም ስምምነት ተደርሷል። ሂደቱም በመልካም አፈፃፀም ላይ ይገኛል፡፡ ለእዚህ ስኬት የበኩላችሁን ወሳኝ አስተዋፅኦ ለተጫወታችሁ እና ድጋፍ ላደረጋችሁ ሁሉ ምስጋናችን የላቀ ነው፡፡
ባለፉት ዓመታት በነበረው የተሳሳተ ብሒል ማለትም እኔ ያልኩት ካልሆነ እልህና ራስን ብቻ የማዳመጥ የፖለቲካ ትርክት፤ ምን ያህል የከፋ ደረጃ ላይ አድርሶን እንደነበረ፤ አሁን የተፈጠረውን ሠላም ተጠቅመን በተረጋጋ መንፈስ ራሳችንን በመጠየቅ ሥልጡን ፖለቲካን ያልተከተለ እና ዘመኑን ያልዋጀ ጉዞ መዳረሻ ውጤቱ ከፍተኛ ውድመት እና አሳዛኝ ጥፋት መሆኑን ከታሪክ ሳይሆን ከተግባር ተምረናል የሚል እም ነት አለኝ፡፡
የዛሬው መርሐ ግብር ከመጣንበት ስሁት መንገድ በፍጥነት ወጥተን፤ አዲስ ሁሉን አካታች የመደጋገፍ የረጅም ጉዞ እርካብ ለመጨበጥ እንድንችል እና በመንገዳችን ላይ ለሚያጋጥሙን የፖለቲካ ስብራቶች ሀገራዊ መፍትሔ እየሰጠን የሰላም ሂደቱን ለማጽናት እንዲቻል በሂደቱ የተሳተፉትን ሁሉ ለማመስገን፤ አክብሮታችንን ለመግለጽ የተዘጋጀ የምስጋና ፕሮግራም ነው፡፡
እንደሚታወቀው ባለፉት ሁለት ዓመታት ያለፍንበት የጦርነት ወቅት በሃገራችን እና በሕዝባችን ላይ ዘርፈ ብዙ ጉዳት አስከትሏል፡፡ መተኪያ የሌለውን የባርካታ ዜጎቻችንን ሕይወት ቀጥፏል፡፡ ግጭቱ ከፍተኛ የሆነ የሥነ ልቦና ጉዳት አድርሷል፡፡ ሃገራችን በግጭቱ፤ በጦርነቱ ምክንያት በተሟላ ሁኔታ ለመገመት አዳጋች የሆነ ኢኮኖሚያዊ ፣ ማኅበራዊ የመሠረተ ልማት እና ሌሎች ከባድ ውድመት ደርሶባታል፡፡ ግጭቱ የብዙ ኢትዮጵያውያንን ተስፋ ነጥቋል፡፡ ወጣቶቻችን ነገን ለበጎ ሲያቅዱ እሩቅ አላሚ የቅርብ አዳሪ አድርጓቸዋል። ባጭሩ ላልተበደሩት እዳ ከፋይ ሆነዋል፡፡
በተስፋ የያዝነው ሰላም ሂደት ከግቡ እንዲደርስ ስምምነት የተደረሰባቸውን ነጥቦች ያላንዳች ማመንታት ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ ሃገራችን ፋታ ትፈልጋለች፡፡ ሕዝባችን ሰላም እና ደህንነቱ እንዲጠበቅ እና ሕይወቱ ወደተቃና አቅጣጫ እንዲመለስለት ይጠብቃል፡፡ ዓውዳችን ሰላም፤ ቋንቋችን ልማት እና አብሮነት መሆን ይኖርበታል፡፡ ይህ እውን እንዲሆን በሁሉም ረገድ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ያሻል፡፡ ሕዝብ የሚያነሳቸውን ጥቄዎች ሰላማዊ፣ ፍትሐዊ እና ዘላቂ መፍትሔ በሚያስገኝ አግባብ መፍታት ይኖርብናል። የግንኙነት አግባብነታችን እና የዕለት ግንኙነታችን ሕዝቡን የሚያቀራርብ እና ሰላምን የሚያጸና መሆን አለበት፡፡
ከአሉባልታ እና ስሜታዊነት በመራቅ ሁሉንም ወገን እና ባለድርሻ ያማከለ፤ ከሁሉም በላይ ሃገርን ማዕከል ያደረገ እና የሕዝብን ትክክለኛ ስሜት የተጋራ መሆን አለበት፡፡ የተወሰኑ ቡድኖችን እና የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለማስደሰት፤ ድጋፍ ለማድረግ የሚደረጉ ነጣይ እንቅስቃሴዎች ሁሉ ዘላቂነት አይኖራቸውም፡፡ የሁሉንም ድምጽ አዳምጠን፤ በየልኩ እውቅና ሰጥተን፤ የሚጎድለውን ሞልተን፤ የሕዝቦቻችንን ሃገር በቀል የመፍትሔ መንገዶችን በማጠናከር ሃገራዊ የምክክር ሥራችንን አጎልብተን፤ የሽግግር ፍትሕ እንቅስቃሴው መንገዶችን በማጠናከር ሃገራዊ የምክክር ሥራችንን አጎልብተን የሽግግር ፍትሕ እንቅስቃሴውን አጠናክረን የገጠመንን ታሪካዊ ችግር በታሪካዊ እሴት መወጣት ይገባናል፡፡ በግጭት የተነሳነው ስማችን አድሰን ከጎናችን ለቆሙት አፍሪካውያን እንዲሁም ለቀረው ዓለም አስተማሪ በሚሆን መንገድ የተስማማንበትን መፈጸም ይገባናል፡፡ ይህንን እንደምናሳካ ጥርጥር የለኝም፡፡ እንችላለንም! አመሰግናለሁ፡፡
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 18 ቀን 2015 ዓ.ም