የኢትዮጵያ መንግስት ባለፉት ዓመታት በተለይ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ሲካሄድ የቆየው ጦርነት በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ያሳየው ጽኑ አቋም በጽኑ አቋሙ መሰረት ተፈጽሟል፡፡ ጦርነቱ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብና የተለያዩ ሀገሮች ጥያቄዎችን ሲያቀርቡም፣ ችግሩ አፍሪካዊ ነው፤ መፍትሄውም አፍሪካዊ መሆን አለበት የሚል ጽኑ አቋም አራምዷል፡፡ እንዳለውም መፍትሄው በአፍሪካ ልጆች እውን ሆኗል፡፡
በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶርያ መንግስትና ሕወሓት ባደረጉት ስምምነት ጦርነቱ ቆሟል፤ በአንዳንድ ሀገሮች እንደሚደረገው በስምምነቱ ጦርነቱ ብቻ አይደለም የቆመው፡፡ በስምምነቱ መሰረት የተቀመጡ ሌሎች አንኳር ጉዳዮችም እየተፈጸሙ ይገኛሉ፡፡
መንግስት ለሰላም ስምምነቱ ባለው ቁርጠኝነት ለሰብአዊ አገልግሎቶች የሚውሉ የምግብ፣ የመድኃኒትና የመሳሰሉት አቅርቦቶች በሁሉም አማራጮች ሳይውል ሳይድር ነው የተጀመሩት፡፡ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ብዙም ሳይቆይ ወዲያው ተጀምሯል፤ በጦርነቱ የተጎዱ መሰረተ ልማቶች እየተጠገኑ ወደ ስራ ተመልሰዋል፤ አገልግሎት አቁመው የነበሩ በርካታ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ስራቸውን ጀምረዋል። ሕወሓትም ከባድ መሳሪያዎቹን አስረክቧል፤ በትግራይ የሽግግር አስተዳደር ተመስርቷል፡፡ የትምህርትና የመሳሰሉት ተቋማት እንዲከፈቱ ዝግጅቶች እየተደረጉ ናቸው፡፡
የአውሮፕላን በረራ መጀመሩን ተከትሎ በጦርነቱ ሳቢያ ተለያይተው የነበሩ ቤተሰቦች መገናኘት ከጀመሩ ቆይተዋል፤ በቅርቡም የሀገር አቋራጭ አገልግሎት በአፋር በኩል ተጀምሯል። ተመሳሳይ አገልግሎት በአማራ ክልልም በኩል እንዲጀመር በጊዜያዊ አስተዳደሩ እየተጠየቀ ነው፡፡ በቅርቡም የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች በትግራይ ክልል ጉብኝት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፤ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርም እንዲሁ በሌሎች ክልሎች ጉብኝት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡
ከዚህ ሁሉ መረዳት እንደሚቻለው በሰሜን ኢትዮጵያ የሰላም አየር እንዲነፍስ የማድረጉ ስራ በተያዘለት አቅጣጫ መሰረት እየተፈጸመ መሆኑን ነው፡፡ ሁሉም ወገኖች ሰላሙን ለማጽናት ርብርብ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች ለሰላም ከዚህም በላይ ርብርብ ማድረግ እንዳለባቸው እየተገለጸ ነው፡፡ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ለሰላም ስምምነቱ ለሰሩ እውቅና በተሰጠበት ስነስርአት ለሰላም እንዲጀገን ባሳሰቡት መሰረት ሰላሙን ለማጽናት ርብርቡ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡
በሀገሪቱ ባለፉት አመታት የተፈጠረው የሰላም እጦት የስፋት፣ የጥበት፣ የጥልቀት ልዩነት ያለው ካልሆነ በቀር በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎችም ፀጥታ የደፈረሰበት ሁኔታ ታይቷል፡፡ በየትኛውም ስፍራ ለሚታየው የጸጥታ መደፍረስ ተጠያቂ የሆኑ አካላትን በህግ አግባብ መጠየቅ አንድ ነገር ሆኖ ለሰላም የሚጨምረው ነገር አለ ተብሎ እስከ ታመነበት ድረስ ከእነዚህ አካላት ጋር መነጋገርና ለሰላም ቅድሚያ መስጠት ብልህነት ስለመሆኑ ከሕወሓት የተደረሰው ስምምነትና በስምምነቱ መሰረት እየተከናወኑ ያሉ ተግባሮች ያመለክታሉ።
እንደሚታወቀው መንግስት በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ ዞኖች እየተንቀሳቀሰ ጥቃት የሚሰነዝረውን ሸኔ ለመቆጣጠር የሀገሪቱ የጸጥታ ኃይሎች ርምጃዎችን ሲወስዱ ቆይተዋል፤ አሁንም እየወሰዱ ነው፡ ይህ ከሸኔ ጋር ሲደረግ የነበረው ግጭት ኅብረተሰብን እየጎዳ ብዙ ጊዚያትን መውሰዱ ይታወቃል፡፡
ቡድኑ በንጹኃን፣ በመሰረተ ልማትና በተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ጥቃት አድርሷል። በሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች የሰዎች እንቅስቃሴና ሕይወት ስጋት ውስጥ ወድቆ ቆይቷል፡፡ በተለይ በወለጋ አካባቢ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች በአግባቡ እንዳይካሄዱ አድርጓል፡፡
መንግስት ከዚህ ቡድን ጋር ለመነጋገር ቀጠሮ መያዙን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ይፋ አድርገዋል። ይህ የመንግስት ውሳኔ አሁንም ለሰላም የተከፈለ ትልቅ ዋጋ ነው፡፡ መንግስት ከሕወሓት ጋር እንደተወያየና ለሰላም ስምምነት እንደደረሰ ሁሉ ከዚህ ቡድን ጋርም ተመሳሳይ እርምጃ በመውሰድ ለዘላቂ ሰላም ለምን አይሰራም ሲሉ ለቆዩ ወገኖችም ምላሽ ይሆናል፡፡
ቡድኑ በአሸባሪነት የተፈረጀ ፣ በዜጎች ህይወት፣ ሀብትና ንብረት፤ በመንግስት ሀብትና ንብረት፣ በሀገር ሰላምና ጸጥታ ላይ ብዙ ጉዳት ያስከተለ፣ አሁንም ስጋት ሆኖ የቀጠለ መሆኑ ይታወቃል፡፡ መንግስት ለእዚህ ውሳኔ የደረሰው አሁንም ለዘላቂ ሰላም ሲል መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ቡድኑ ያደረሰው ጥፋት በእጅጉ የሚያም ቢሆንም፣ ለዘላቂ ሰላም ከበጀ መወያየትም ትልቅ እርምጃ ተደርጎ ይታያል፡፡ ከዚህ አኳያ የመንግስት ውሳኔ ተገቢነት ያለውና በሀገሪቱ ሰላምን ለማጽናት የያዘው ቁርጠኛ አቋም የታየበት በድጋሚ ነው፡፡
ይህ የመንግስት ውሳኔ መንግስት ለዘላቂ ሰላም ሲል ከሕወሓት ጋር ለመወያየት ባሳየው ቁርጠኛ አቋምና እሱን ተከትሎ በተደረሰው የሰላም ስምምነት የመጡ ለውጦች የሰላም መደፍረስ ባለባቸው የሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች እውን እንዲሆኑ ትልቅ አቅም በመሆን ያገለግላል፡፡
የሰላም ጎዶሎ የለውም፤ ሙሉ ነው፡፡ በአንድ አካባቢ ሰላም ሰፍኖ በሌላ አካባቢ ሰላም የሚደፈርስ ከሆነ ሀገር ዥንጉርጉር ትሆናለች፤ ከችግርም አይወጣም፡፡ ሰላሙ አንጻራዊ ቢሆን እንኳ በአንዱ አካባቢ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ተሰርቶ ሌላው ዘንድ አለመስራቱ የሰላም ማስፈኑን ስራ ያዥጎረጉረዋል፡፡ በመሆኑም በሰሜን ኢትዮጵያ እየታየ ያለው ሰላም በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎችም እንዲደገም ለማድረግ መስራት በየትኛውም መመዘኛ ትክክለኛ ውሳኔ ነው፡፡
እንደሚታወቀው በሰላም ውይይት በኩል የኢትዮጵያ መንግስት የቅርብ ጊዜ ተሞክሮ አለው፡፡ ይህን ተሞክሮ ከሸኔ ጋር በሚደረገው ውይይትም በመተግበር በሀገሪቱ ዘላቂና ሙሉ ሰላም ለማምጣት የተጀመረው ጥረት ውጤታማ እንደሚያደርገው ይታመናል፡፡ በሸኔ በኩል የሚደራደሩ ወገኖችም እንዲሁ ሰላምን ለማጽናት ለሚያስችሉ ሀሳቦች ቅድሚያ በመስጠትና ከልብ በሆነ የሰላም ፍላጎት ለውይይቱ ራሳቸውን ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል!
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 18 ቀን 2015 ዓ.ም