ቴክኖሎጂ የሰው ልጅ ዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ አጋዥ በመሆን ጊዜን ፣ጉልበትንና ውጪን የሚጠይቁ ሂደቶችን ቀላል፣ፈጣንና ምቹ እያደረገ ይገኛል። ቴክኖሎጂ እያንዳንዱ የዓለም እንቅስቃሴ እየተቆጣጠረ ባለበት በዚህ ዘመን ከቴክኖሎጂ ውጭ መሆንም አይታሰብም።
በተለይ አሁን እየበለጸጉ የሚገኙት መተግበሪያዎች የቴክኖሎጂውን እድገት እያፋጠኑት እንደሆነ ይነገራል። በሀገራችንም በርካታ መተግበሪያዎች እየበለጸጉ አገልግሎት ላይ እየዋሉ ይገኛሉ። በዛሬው ሳይንስና ቴክኖሎጂ አምዳችንም “የእነዚህ መተግበሪያዎች መበራከት ፋይዳው ምንድነው?” ስንል የዘርፉን ባለሙያዎች አነጋግረን ያዘጋጀነውን ዳሰሳ ይዘንላችሁ ቀርበናል።
አቶ መርዕድ በቀለ የአይ ኢ ኔትወርክ ሶሉሽን መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጸሚ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ የሞባይል መተግበሪያዎች (አፕሊኬሽኖች) ሥራዎችን በኢንፎርሜሽን ኮሙኒዪኬሽን ቴክኖሎጂ (ICT) በሲስተም እንዲመሩ የሚያስችሉ አማራጮች የያዙ መሆናቸውን ያብራራሉ።
“የሞባይል መተግበሪያዎች የሚበለፅጉበት ዓላማ ውስን አገልግሎትን ለመስጠት ነው” በማለትም፤ ለምሳሌ ያህል የትራንስፖርት መተግበሪያ ከሆነ የትራንስፖርት አገልግሎትን ለማግኘት የምንጠቀምበት፤ የግብርና መተግበሪያ ከሆነ ደግሞ ግብርናን የተመለከቱ መረጃዎችን ለማግኘት፤ የሕክምናም መተግበሪያ ከሆነ ከሕክምና ጋር የተያያዙ ነገሮች ለማግኘት የሚውሉ እንደሆኑ ያብራራሉ።
መተግበሪያዎቹ እንደየዘርፉ አይነትና ባሕሪ የተወሰነ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ የሚጠቅሱት ሥራ አስፈፃሚው፤ ለእያንዳንዱ ዘርፍ የሚበልጸጉት መተግበሪያዎችን ሞባይል ስልክ ላይ ስለሚጫኑ ሰዎች ለሚፈልጉት አገልግሎት የሚጠቀሙበትን መተግበሪያ ብቻ በመጫን መጠቀም እንደሚችሉ ያስረዳሉ።
“ለእያንዳንዱ አገልግሎት የሚያስፈልገው የራሱ የሆነ መተግበሪያ አለ” የሚሉት አቶ መርዕድ፤ ለአብነት የቴሌ ብር መተግበሪያ ከክፍያ ጋር በተያያዘ አገልግሎት የሚሰጥ በመሆኑ የቴሌ ብር ደንበኞች የሚጠቀሙበት እንደሆነ ይጠቅሳሉ። ሁሉም ነገር ከወረቀት ሥራ እየወጣ በቴክኖሎጂ እየተደገፈ በመጣ ቁጥር አገልግሎቱን ሁሉም ሰው እንዲያገኝ ለማድረግ ሞባይል መተግበሪያዎች እየተፈጠሩ መምጣታቸውን ይጠቁማሉ።
አቶ መርዕድ እንደሚሉት ፤አሁን ላይ የመንግሥት አገልግሎቶችም ወደዚያ ሲስተም እየገቡ የሚሄዱባቸው ሁኔታዎች እየተፈጠሩ ነው። ሌላው ዓለም ላይ እንደሚታየው የመብራት፣ የስልክ፣ የውሃ እና የመሳሰሉት አገልግሎቶች ክፍያዎች በሞባይል መተግበሪያው አማካይነት ይከፈላሉ። የሞባይል መተግበሪያው የወር ሂሳብ ያሳውቃል፤ ከዚያ ሂሳቡን ባለበት ሆኖ የሚከፍልበት ሲስተም ተዘርግቶለታል። የኢሚግሬሽን ፓስፖርት የሚፈልግ ሰውም እንዲሁ በፓስፖርት መተግበሪያ ላይ በማመልከት አገልግሎቱ ሲጠናቀቅ በአድራሻው ይላክለታል።
‹‹የመተግበሪያዎች ዋንኛ ግብ ሥራን ማቀላጠፍና ጊዜን መቆጠብ ነው›› ያሉት አቶ መርዕድ ፤ረጅም ጊዜ የሚወስድባቸውን ቢሮክራሲ የሚበዛባቸውን ነገሮች በሙሉ ወደ ቴክኖሎጂ በማምጣት ሰዎች በቀላሉ ቤታቸው ቁጭ ብለው ብዙ አገልግሎቶች በፍጥነት፣በቅልጥፍና በጥራት እንዲያገኙ የሚያደርጉ አማራጮች እንደሆኑ ይናገራሉ ። ይህንን አገልግሎት በሞባይል ለመጠቀም ዋንኛ አስፈላጊ የሆነው ነገር ኢንተርኔት እንደሆነ የሚገልጹት አቶ መርዕድ፤ ‹‹እኛ ሀገር ያለው የኢንተርኔት አገልግሎት ገና በመሆኑ ሰዎች ዳታ ሲጠቀሙ ይቆጥርብኛል ብለው ስለሚፈሩ እያበሩና እያጠፉ የሚጠቀሙት ሁኔታ አለ።
መጀመሪያ ሰዎች ከዚህ መውጣት አለባቸው›› ይላሉ። ቀጥሎ ሁሉም የሞባይል ዳታዎች 4ጂና 5ጂ የሚባሉት ሁሉም ቦታ ተደራሽ ማድረግ እንደሚኖርባቸው ያመለክታሉ። በሌላው ዓለም ላይ ኢንተርኔት ተደራሽ ከመሆኑም ባሻገር የዳታ ዋጋም የሰዎችን አቅም ያገናዘበና ሁልጊዜም ክፍት ስለሚሆኑ ሰዎች የሚፈልጉትን መተግበሪያ በሞባይላቸው እንዲጭኑ ይረዳቸዋል፤ይሄም አገልግሎቶችን ሳይቆራረጡ እንዲያገኙ እንደሚያግዛቸው ያመለክታሉ።
አቶ መርዕድ እንደሚሉት፤ መተግበሪያዎች በስፋት በኢትዮጵያ አገልግሎት መስጫ አማራጭ ሆነው ከመስፋፋታቸው አስቀድሞ መጀመሪያ የቴሌኮም አገልግሎት አሰጣጥ በደንብ መስፋፋትና የኢንተርኔት ዋጋ ርካሽ ሆኖ ሰዎች በሚችሉት አቅም መጠን የሚያገኙት መሆን እንዳለበት ያነሳሉ። ይህ ሲሆን የሶፍትዌር ካምፓኒዎችና መተግበሪያዎችን በማበልፀግ የሚያስተዋውቁ አካላት እንደሚያበረታቱ ይጠቁማሉ።
የኢንተርኔት ዋጋ ውድ በመሆኑ መተግበሪያዎችም ቢበልጽጉ የሚጠቀምባቸው ሰው ከሌለ ያበለጸጉት ሰዎች ክፍያ አያገኙም በማለትም መተግበሪያ ማልማቱ ቀጣይነት እንዳይኖረው እክል እንደሚፈጥር አቶ መርዕድ ያስረዳሉ። ያበለጸጉት ሰዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ደግሞ ተጠቃሚው ብዙ መሆን እንዳለበት ይጠቁማሉ። ስለዚህ የኢንተርኔት ዋጋ መቀነስና ተደራሽነቱም መጨመር አለበት በማለት ምክረ ሃሳባቸውም ይሰጣሉ። ለዚህ ደግሞ ኢትዮ ቴሌኮም ሆነ ሳፋሪኮም ብዙ መሥራት ይጠበቅባቸዋል የሚል መልእክት ያስተላልፋሉ።
ቴክኖሎጂ ዓለም አቀፋዊ በመሆኑ ማንም ሰው ኢንተርኔት ላይ የሚያገኛቸውን ነገሮች መነሻ በማድረግ የተለየ ፈጠራ ሳያስፈልገው የሚሠራበት ሁኔታ መኖሩን የሚናገሩት አቶ መርዕድ፤ ሌላው ዓለም ላይ መነሻ የሆኑ ፕላትፎርሞች ስላሉ ችሎታ ያለው የሰው ኃይልና ሰፊ የገበያ ተደራሽነት ካለ ብዙ ችግሮች በቀላሉ መቅረፍ እንደሚችል ይገልፃሉ።
የተማረ ኃይል በበቂ ሁኔታ ገበያው ላይ እየቀረበ አለመሆኑን የሚገልፁት ዋና ሥራ አስፈፃሚው ‹‹እንደ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ኩባንያ የምናበለፅጋቸው ሶፍት ዌሮች ለቢዝነሶች የሚሆኑና ሥራ ሊያቀላጥፉ የሚያስችሉ ናቸው። ከኛ ልምድ ስንነሳ ትልቁ ችግር ችሎታ ያለው የሰለጠነ የሰው ኃይል ብዙ የለም›› በማለት በሰው ኃይል በኩል ያለውን ችግር ይጠቁማሉ።
ከዩኒቨርሲቲዎች በኮምፒዩተር ቴክኖሎጂ፣ በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ(Ict)፣ ከኤሌክትሪካልና ኮምፒዩተር ቴክኖሎጂ ተመርቀው የሚወጡ ተማሪዎች ያላቸው መነሻ ነገር መሆኑን ጠቅሰው፤ ተመርቀው የሚወጡ ተማሪዎችን እንደኛ ያሉ የግል ካምፓኒዎች እውቀታቸው የበለጠ እንዲያድግ መልሰው ማሰልጠን ይጠበቅባቸዋል። ከዩኒቨርሲቲ ብቻ የሚያገኙት እውቀት በፍጥነት ውጤት እንዲያመጡ አያደርጋቸውም ይላሉ።
እነዚህ መተግበሪያዎች እንዲስፋፉ መንግሥት በፖሊሲ ደረጃ ቁርጥ ያለ አቋም በመያዝ የመንግሥት አገልግሎቶችን በሙሉ በቴክኖሎጂ ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባውም ነው የሚጠቁሙት። ለአብነት የሌላውን ዓለም ተሞክሮ ብንመለከት ቤት መግዛት፣ መሸጥና የመሳሰሉትን ተግባራት ለማከናወን መንግሥት ቢሮ መሄድ ሳያስፈልግ እያንዳንዱ ነገር በመተግበሪያ የሚያልቅበት አሠራር ተዘርግቶ ፤ለመፈራረም እንኳን ውልና ማስረጃ መሄድ ሳያስፈልግ ሲስተም ላይ ኦንላይን መፈረም የሚችልበት አሠራር ተቀምጧል። በኛ ሀገር ብዙ ሰው እሮሮ ያለበት ፤ እንግልት የበዛበት አሠራር በቴክኖሎጂ በመተካት ብዙ የመንግሥት አገልግሎቶች መቀላጠፍ እንደሚችሉ አስታውቀዋል።
‹‹የግል ሴክተሩ አልታገዘም እንጂ አሁንም ጥረት እያደረገ ነው›› የሚሉት አቶ መርዕድ፤ የግሉ ሴክተር አጋጣሚውን በመጠቀም ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ ሥራዎችን ለማቀላጠፍ ሰፊ ርብርብ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ አንስተዋል። የፋይናንስ ዘርፉም ስታርትአፖችን፣ አነስተኛና መካከለኛ የሆኑ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ካምፓኒዎችን የማገዝ ባሕሉ መዳበር እንዳለበት ይጠቁማሉ። ‹‹የሞግዚት ዶት ኮም›› መተግበሪያ መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወጣት ሳምራዊት ታረቀኝ በበኩሏ የአቶ መርዕድን ሀሳብ በመጋራት ዝቅተኛ የኢንተርኔት ተደራሽነት፣ የኢንተርኔት ዳታ ውድነት፣ መተግበሪያዎች እንዳይስፋፉ የሚያደርጉ ተግዳሮቶች መሆናቸውን ታነሳለች።
ቴክኖሎጂን መጠቀም ቅንጦት አይደለም በማለትም፤ ቴክኖሎጂ በሁሉም የሀገሪቷ አካባቢዎች ተደራሽ መሆንን ይዞ የመጣ መልካም እድል መሆኑን ጠቅሳ፣ ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ትላለች። በተለይ በዚህ ዘርፍ በየዓመቱ ለሚመረቁ በርካታ ተማሪዎች የዲጂታል ዘርፍ ትልቅ ተስፋ መሆኑንም ትገልጻለች። ተመራቂዎች ቁጭ ብለው ሥራ ከመጠበቅ የራሳቸውን ቢዝነስ ፈጥረው መንቀሳቀስ እንደሚያስችላቸው ጠቅሳ፣ ለብዙዎች የሥራ እድል ለመፍጠር የሚያስችል እንደሆነ ትናገራለች።
ወጣት ሳምራዊት ታረቀኝ እንደምትለው፤ ዲጅታል ኢኮኖሚ ብዙ ዘርፎች አሉት። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ኢኮሜርስ ሲሆን፣ ይህም በበይነመረብ የሚፈልግን አንድ አገልግሎት ወይም ምርት ለማግኘት የሚጠቅም የመገበያያ መንገድ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ በጣም በአጭር ጊዜ ተቀባይነት ያገኛና እያደገ ያለ አንድ የመገበያያ ዘርፍ ነው። ብዙ ተግዳሮቶች ያለበት ይህ ዲጂታል ኢኮኖሚ፣ በኢትዮጵያ በየዓመቱ 18 በመቶ ያህል እድገት አሳይቷል ትላለች። ይህ ደግሞ ከመቼውም ጊዜ በላይ በዲጂታል ኢኮኖሚው ስለመሥራት እንድናስብ እንደሚያደርግ ትገልጻለች።
ከተግዳሮቶቹ በላይ ያሉ እድሎች አብረውት እየመጡ ነው የምትለው ሳምራዊት፤ እንደሳፋሪኮም ያሉ የቴሌኮም ካምፓኒዎች መግባታቸው ተፎካካሪነትን በመፍጠር የኢንተርኔት ተደራሽነትን እንዲሰፋ ያደርጋሉ ትላለች። አሁን ዲጂታል የክፍያ ሥርዓቶች ተፈጥረዋል፤ በኦንላይን /በቀጥታ/ መክፈል የሚቻልባቸው መንገዶች እየበዙ እና እየተለመዱ ነው ስትል ገልጻ፣ እንደ ቴሌብር አይነቶቹ የተለያዩ የመክፈያ ሥርዓቶች መፈጠራቸው ግብይቱን ቀልጣፋ እንደሚያደርጉ ትጠቅሳለች። ቀደም ሲል ቴክኖሎጂው ተደራሽ ቢደረግም የክፍያ ሥርዓቱ ግን እጅ በእጅ ይደረግ እንደነበር አስታውሳ፤ አሁን ግን የክፍያ ሥርዓቶች በዲጅታል መልኩ መፈጸማቸው የዘርፉን እድገት ያሳያል ትላለች።
አዲስ አበባ ውስጥ አገልግሎቶችን በኦንላይን ማዘዝና መቀበል እየተለመደና አንድ የሕይወታችን አካል እስከመሆን ደረጃ ደርሷል የምትለው ሳምራዊት፤ ኅብረተሰቡ ካለው የተጣበበ ጊዜ አንጻር ወደዚህ ሥርዓት በመግባት ተጠቃሚ እየሆነ ይገኛል ትላለች። ከአራት ዓመት በፊት የነበረው የአኗኗር ባሕል እየተቀየረ መምጣቱን ጠቁማ፣ ዲጂታል አገልግሎት ተጠቅሞ መገበያየት እየተለመደና ተመራጭ እየሆነ እንደሚገኝ አስታውቃለች። ሁኔታው ከዚህ በኋላ ለሚመጡም ሆነ እያደጉ ላሉ ኮምፓኒዎች ትልቅ የሆነ መነቃቃትን የሚፈጥር እንደሆነ ትገልጻለች።
በተለይ በአሁኑ ጊዜ የሥራ እድል ለመፍጠር እንደ አንድ እድል የሚቆጠር ነው የምትለው ሳምራዊት፤ ጎረቤት ሀገር ኬንያ ጋር በዚህ በኩል የማንወዳደርበት ደረጃ ላይ ነን ትላለች። እሷ እንደምትለው፤ ኬንያውያን በዘርፉ ዓመታዊ ገቢያቸው ከፍተኛ ነው። የሕዝቡ ዲጂታል ቴክኖሎጂ የመጠቀም ባሕል ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ ብዙ የውጭ ባለሀብቶች ወደ ኬንያ ይሄዳሉ። ይህ ደግሞ የውጭ ምንዛሪያቸው ከፍ እንዲል ያደርጋል።
በግብርና፣ በጤና፣ በቱሪዝም ሴክተሮችና በመሳሳሉት መድረስ የማንችልባቸው ቦታዎች ሁሉ ተደራሽ እንድንሆን ለማድረግ መሥራት ያስፈልጋል ስትል ታስገነዝባለች። የመንግሥት አገልግሎቶች በኦንላይን እየሆኑ፣ አገልግሎቶች እየተቀላጠፉ በቀላሉ ተደራሽ የሚደረጉበት ሁኔታ በደንብ ተጠናክሮ ሊሠራበት እንደሚገባም ትጠቁማለች።
እንደ ወጣት ሳምራዊት ገለጻ፤ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ ማኅበረሰቡ ያለው ችሎታ ገና የሚባል ነው፤ ይህን ችሎታ ለማሳደግ ግንዛቤ ማስጨበጫዎችንና ሥልጠናዎችን መስጠት ያስፈልጋል። የኢንተርኔት ተደራሽነት በሌለባቸው ቦታዎች ማኅበረሰቡ ኢንተርኔት መጠቀም የማይችል ከሆነ ጎን ለጎን የሚሄድ ሲስተም መፍጠር ይገባል።
መተግበሪያዎች በመጠቀም የዲጂታል አገልግሎት ማግኘት በእጅጉ እረፍት ይሰጣል የምትለው ሳምራዊት፣ ‹‹እኔ ቴክኖሎጂ መጠቀም መጀመሬ ሥራዬን በጣም አቅልሎልኛል ትላለች። በየወሩ የሚጠበቅብኝን ክፍያ በኦንላይን አሳውቃለሁ፤ የምከፍለውም በኦንላይን ሲሆን፣ ደረሰኙም በኦንላይን ይመጣልኛል›› ትላለች።
ሥራ እያቋረጡ ሄዶ ወረፋ ጠብቆ መክፈል የሚለው ነገር መቅረቱን ጠቅሳ፤ ቴክኖሎጂ በጣም በቀላሉ ሥራዎችን ማቀላጠፍ እንደሚያስችል ትናገራለች። በቴክኖሎጂ ከዚህ በበለጠ ሁኔታ ለመጠቀም ቴክኖሎጂውን አዳብሮ ሰዎች በቀላሉ ጥቅም ላይ እንዲያውሉት ለማድረግ ማስፋፋት ላይ መሥራት እንደሚገባም ጠቁማለች። መተግበሪዎች ሲሠሩ በቅድሚያ ተገልጋዩ መታወቅ አለበት ትላለች። ኅብረተሰቡ በቀላሉ ሊገለገልባቸው የሚችሉ፣ በዝቅተኛ የኢንተርኔት ዋጋ የሚሠሩ ቴክኖሎጂዎችን መፍጠር እንደሚገባ አስገንዝባለች።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 17 ቀን 2015 ዓ.ም