
በኢትዮጵያ የሮቦቲክስ ሻምፒዮና ውድድር የተጀመረው በቅርቡ ቢሆንም፣ በውድድሩ ከሀገር ውስጥ አልፎ በአኅጉር አቀፍ ደረጃ በአጭር ጊዜ አበረታች ውጤቶች እየተመዘገቡ ይገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን ተወዳዳሪዎች በተወዳደሩበት ሜዳ በማሸነፍ የሀገራቸውን ስም ማስጠራትም ጀምረዋል፡፡ ባለፉት ዓመታት በተካሄዱ የአፍሪካ ሮቦቲክስ ሻምፒዮና ውድድሮችም ይሄው ታይቷል፡፡
የአፍሪካ የሮቦቲክስ ሻምፒዮና ውድድር በየዓመቱ የሚካሄድ ሲሆን፣ ሰሞኑን የተካሄደው ውድድርም ለሶሰተኛ ጊዜ የተዘጋጀ ነው፡፡ ኢትዮ ሮቦ ሮቦቲክስ የተሰኘው ድርጅት ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ይህ የአፍሪካ ሮቦቲክስ ሻምፒዮና የ2025 ውድድር ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በሳይንስ ሙዚየም ተካሂዷል።
በዚህ የአፍሪካ የሮቦቲክስ ሻምፒዮና ውድድር የመንግሥት፣ የግልና በኢትዮጵያ የሚገኙ የዓለም አቀፍ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ተሳትፈዋል፡፡ ውድድሩ የዲዛይን፣ የምህንድስና፣ የፕሮግራም አወጣጥ እና የቡድን ሥራ ችሎታን ለማስፋትና በዘርፉ ያለውን አቅም ለማጎልበት ያለመ መሆኑ በመድረኩ ተጠቁሟል፡፡
በሮቦቲክስ ውድድሩ ተሳታፊ ከሆኑት ተማሪዎች መካከል ተማሪ ሄራኒ አብነትና ጓደኞቿ ይገኙበታል፡፡ እነ ተማሪ ሄራኒ የብሪቲሽ ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት ተማሪዎች ናቸው፡፡ ተማሪ ሄራኒ የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ስትሆን፣ ጓደኞቿ ከዘጠነኛ እስከ አስራ አንደኛ ባሉት የክፍል ደረጃዎች የሚማሩ ናቸው፡፡ ተማሪዎቹ ሮቦት ሰርተው ለውድድሩ ቀርበዋል፡፡
ተማሪዎቹ በትምህርት ቤታቸው በኩል የመጣውን ይህን የውድድር እድል ለመጠቀም በቅድሚያ በኢትዮ ሮቦ ሮቦቲክስ የተዘጋጀ ስልጠና ተሳትፈዋል፡፡ ስልጠናው በትምህርት ቤት ከሚማሩት ትምህርት ባሻገር ስለሮቦቲክስ አዲስ እውቀት እንዲያገኙና ብዙ እውቀት እንዲጨብጡ እንዳስቻላቸው ተማሪ ሄራኒ ገልጻለች፡፡
ሮቦቲክስ በወደፊቱ ሕይወታችን ውስጥ ትልቅ ሚና አለው ስትል ተናግራ፣ ለዚህ ዝግጁ መሆን የሚያስችል ስልጠና ማግኘታቸውን ተናግራለች፡፡ ከዚህ ባሻገር ስለሮቦቲክስ በጥልቀት ለማወቅና ለመማር በእጅጉ እንደሚያስፈልግም አስታውቃለች፡፡
ስልጠናው በሮቦቲክስ ዘርፍ ፍላጎቱና ተሰጥኦ ላላቸው ተማሪዎች መሰጠቱን ጠቅሳ፤ ስልጠናውን ከወሰዱ በኋላም በትምህርት ቤቱ ከዘጠነኛ እስከ አስራ አንደኛ ክፍል ድረስ ያሉ 23 ተማሪዎች በበድን ሆነው ሮቦቱን መስራታቸውን ትገልጻለች፡፡ የጨዋታ ሮቦት በደንብ ሠርተው በውድድሩ አሸናፊ ለመሆን መጋጀታቸውን ጠቅሳ፣ ሀገራቸውን በሮቦቲክስ ዘርፍ ማስጠራት እንደሚፈልጉም ተናግራለች፡፡
በልጅነት እድሜ ውስጥ እንደመሆናችን መስራት የሚጠበቅብን የጨዋታ ሮቦት ነው ያለችው ተማሪዋ፣ ስለሮቦቲክስ እየተማርን የጨዋታ ሮቦት በመስራት ለማሸነፍ መፎካከር አንዱ ሥራ ነው ብላለች፡፡ ከዚያም ደረጃችንን እያሳደግን ሌሎች ለሀገር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ሮቦቶችን መስራት እንችላለን ›› ትላለች፡፡
ተማሪዎች በሮቦቲክስ ለመስልጠንም ሆነ ለመሳተፍ ሰዓት የለንም ብለው ሊያሰቡ ቢችሉም ውስጡ ገብተው ሲያወቁትና ሲማሩት በጣም የሚወዱት ብዙ ነገሮችን ሊሰሩበትና ሊፈጥሩበት የሚያስችላቸው ምቹ ሁኔታ የሚያመላክታቸው ነው ያለችው ተማሪዋ፤ ከብዙ ተማሪዎች ጋር እንዲቀራረቡ በቡድን መስራት እንዲለምዱ እንደሚያስችል ትገልጻለች፡፡
‹‹ሮቦቲክስ አስተሳሰባችንን ይቀይራል፤ በጥልቅ በማሰብና ማሰላሰል ምን አይነት ሮቦት መስራት እንደምንችል በደንብ እንድናውቅ ይረዳናል›› ስትል ገልጻ፣ ቴክኖሎጂ ይበልጥ እየዘመነ ከመሄዱ ጋር ተያይዞ የሮቦቲክስ ቴክኖሎጂ በእጅጉ አስፈላጊና አይቀሬ ነው፤ በዚህ ላይ ከአሁኑ መለማመድና በቂ እውቀት መያዝም ያስፈልጋል ›› ትላለች፡፡
ሌሎቹ የውድድሩ ተሳታፊዎች ተማሪ ኢንትሳር ኑርና ጓደኞቿ ደግሞ ከመካኒሳ አባድር ትምህርት ቤት ነው ለውድድሩ የቀረቡት፡፡ እነ ተማሪ ኢንትሳር የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ሲሆኑ፣ ለአንድ ዓመት ያህል በኢትዮ ሮቦ ሮቦቲክስ ስለሮቦቲክስ ስልጠና ወስደው ሮቦት ሰርተውም ነው ለውድድሩ የቀረቡት፡፡
ተማሪ ኢንትሳር፤ በሮቦቲክስ መሰልጠን የሚፈልጉና ተሰጥኦ ያላቸው ተማሪዎች ከትምህርት ቤቱ ተመርጠው ስልጠናውን እንዲወስዱ መደረጉን ትገልጻለች፡፡ እሷ እንዳለችው፤ ወደ ሮቦቲክስ ስልጠናው ከገቡ በኋላ ታዳጊዎች እንደመሆናቸው እድሜያቸውን የሚመጥን ስልጠና አግኝተዋል፡፡ በሮቦቲክስ ዙሪያ ሊኖራቸው የሚገባ መሰረታዊ እውቀት በስልጠናው አግኝተዋል፡፡ ስልጠናውን በሚገባ ከወሰዱም በኋላ በቡድን ሆነው፣ በእያንዳንዱ ቡድን አስር ተማሪዎች ተደልድለው፣ እየተረዳዱ ሮቦቶችን ሰርተው ለውድድር አቅርበዋል፡፡
ስልጠናውን የወሰዱ ሁሉም ተማሪዎች ችሎታቸው እና አቅማቸው እየታየ ሮቦቱን መስራት ላይ እንዲሳተፉ መደረጉን ጠቅሳ፤ የተወሰኑት ተማሪዎች በኮዲንጉ፣ የተወሰኑት ደግ በሮቦቲክሱ እውቀት፣ የተቀሩት ደግሞ ሮቦቱን በማንቀሳቀስ ሥራ ላይ እንዲሳተፉ በማድረግ ሁሉም ተማሪዎች የተሳተፉበት ሮቦት መስራቱን አስታውቃለች፡፡
ሮቦታቸው ‹‹ራፒድ ሪሌ›› የሚባል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን፣ ፈጥኖ ኳስ ሰብስቦ በበቂ ሁኔታ ኢላማ የተደረገበት ቦታ ላይ ማስገባት የሚያስችል የጨዋታ ሮቦት መሆኑን አብራርታለች፡፡ ይህንን ለመፈጸም በጣም ጥቂት ደቂቃዎች ብቻ እንደሚወስድበትና በጣም ፈጣን ሮቦት መሆኑን ትናገራለች፡፡ ሮቦቱን በደንብ እንደ ሰሩትና በውድድሩ አሸናፊ እንደሚያደርጋቸውም አመላክታለች፡፡
እነ ተማሪ ኢንትሳር፤ በዚህ በአፍሪካ ሮቦቲክስ ውድድሩ ካሸነፉ ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚካሄደው የሮቦቲክስ ውድድር የመሳተፍ እድሉ አላቸው፡፡ ‹‹ሮቦቲክስን የተማርነው የራሳችንን ክህሎት ለማሻሻል ብቻ ሳይሆን አገራችንን በሮቦቲክሱ ዓለም ላይ ለማስተዋወቅ ነው›› ስትል ተማሪ ኢንትሳር ጠቅሳ፣ ወደፊትም በዚህ ዘርፍ በደንብ ሰርተው ራሳቸውንና ሀገራቸውን ለማስተዋወቅ ዓላማ እንዳላቸው ጠቁማለች፡፡
የተሰጠን ስልጠና ሮቦቲክስን በደንብ እንድናውቅ ረድቶናል፡፡ ይህን እድል ላመቻቹልን አካላት ምስጋና ማቅረብ እፈልጋለሁ የምትለው ተማሪዋ፤ በተለይ በሰው ስራሽ አስተውሎት ላይ መስራት ለሚፈልጉ ታዳጊዎች ሮቦቲክስ መነሻ መሰረት እንደሚሆናቸውም ጠቁማለች፡፡ ይህን በደንብ እንዲያወቁትና እንዲሰሩበት ማድረግ ያስፈልጋል ብላለች። ይህ ስልጠና ከመሠረቱ ጀምሮ የሮቦቲክስ ግንዛቤያቸው በደንብ ማሳደግ የሚችለቡት መሆኑንም ጠቅሳ፣ ይበልጥ በትኩረት ሊሰራበት ይገባል ባይም ናት፡፡
በመድረኩ የተገኙት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ እንደተናገሩት፤ በአሁኑ ጊዜ ዓለም የሰው ልጅ ከደረሰበት የእድገት ደረጃ አኳያ ስትታይ የቴክኖሎጂ እድገት፣ የፈጠራ ፍጥነትና ጥራት የአገራት ተወዳዳሪነትና ተፎካካሪነት እንደመለኪያ መስፈርት በሚወሰዱበት ከፍተኛ ውድድር ውስጥ ትገኛለች ፡፡ በዚህ ዘመን የሰው ሠራሽ አስተውሎት፣ ሮቦቲክስና የመሳሳሉት አስፈላጊ ብቻ ሳይሆኑ የሕልውና ጉዳይ እየሆኑ መጥተዋል ብለዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ቀጣይነት ያለው ኢኮኖሚ ልማትን ለማረጋገጥ በከፍተኛ ትጋት እየሰራች ትገኛለች፡፡ ለቴክኖሎጂ ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ ተደራሽ፣ አካታች፣ ፍትሕታዊነቱና ደህንነቱ የተረገገጠ እንዲሆንና ቀጣይነት ያለው የዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባትም እየተሰራ ይገኛል፡፡
በተለይም ዘርፉን በፖሊሲ፣ በስትራቴጂ፣ በፕሮግራሞች በማገዝና በመደገፍ ለዘርፉ ምቹ የሆነ ምህዳር እንዲኖር ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ጠቅሰዋል። ከዚህ በፊት ተሰጥኦ፣ ፍላጎትና ክህሎት ያላቸው ወጣቶች ሥነ ምህዳሩ ምቹ ባለመሆኑ የተነሳ አመቺ ነባራዊ ሁኔታ ወደአለበት አካባቢ ይሰደዱ እንደነበርም አስታውሰዋል።
በሀገር ውስጥ የተፈጠረውን ምቹ ምህዳር በፖሊሲ በመደገፍ ተሰጥኦ፣ ፍላጎትና ክህሎት ያላቸው ዜጎች በዘርፉ እንዲሰሩ፣ በዘርፉ ልምድና ክህሎት ያላቸው በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም ወደ ሀገራቸው መጥተው እንዲሰሩ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር ለዘርፉ የሚያስፈልግ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ለመሳብ የሚያስችል የምህዳር ግንባታ ስራም እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው እንዳብራሩት፤ ኢትዮጵያ ከአፍሪካም ሆነ ከምስራቅ አፍሪካ በዘርፉ ምቹ ምህዳር ያላት እንድትሆን ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ባለፉት ዓመታት ለዚህ ዘርፍ የሚያስፈልጉ ፖሊሲዎችን፣ ስትራቴጂዎችንና ፕሮግራሞችን ከአስር ዓመቱ የልማት እቅድ ጋር በማጣጣም ከዓለም አቀፍ መስፈርቶች ጋር ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማድረግ የሚያስችሉ መሠረታዊ ሥራዎች ተሰርተዋል፡፡ ከዚህ ባሻገርም የግሉ ዘርፍ የራሱን ሚና መጫወት እንዲችል ለማድረግ ድጋፎች ተደርገዋል፡፡ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና ሌሎች የዘርፉ ተዋናዮች እያገዙና እየደገፉ ያለውን ሀብት፣ እውቀትና ተሰጥኦ በመጠቀም በዘርፉ መስራት የሚችሉ ዜጎችን ለማፍራት የሚያስችል ምህዳር እየተገነባ ነው፡፡
የኢትዮ ሮቦ ሮቦቲክስ ማናጀር ቤተልሔም ሃብታሙ በበኩላቸው እንዳሉት፤ ውድድሩ በኢትዮ ሮቦ-ሮቦቲክስ እና በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ትብብር ይዘጋጃል፤ በየዓመቱ የሚካሄድ ሲሆን፣ የሰሞኑ ውድድርም ለሦስተኛ ጊዜ የተዘጋጀ ነው፡፡ ውድድሩ የአፍሪካ ተማሪዎችን አንድ ላይ ያገናኛል፡፡ ለሳይንስ፣ ለቴክኖሎጂ፣ ለኢንጂነሪንግና ለሒሳብ ትምህርቶች ትኩረት እንዲሰጥ ማድረግን ያለመም ነው፡፡
በውድድሩ የመንግሥት፣ የግልና በኢትዮጵያ የሚገኙ ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ከ400 በላይ ተማሪዎች ተሳትፈውበታል። ተወዳዳሪዎቹም ከዩኒቨርሲቲ፣ ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ የተወጣጡ ናቸው፡፡
ውድድሩ ለሦስት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን፣ የውድድሩ አሸናፊ ተማሪዎች በአሜሪካ በሚዘጋጀው የሮቦቲክስ ውድድር ላይ ኢትዮጵያን ወክለው እንደሚወዳደሩ ማናጀሯ ጠቁመዋል። የሮቦቲክስ ውድድሩ ከተጀመረ አንስቶ በየዓመቱ አሜሪካ ሄደው መወዳደር የሚችሉ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎችን ማፍራት መቻሉን ያመላክታሉ፡፡ ውድድሩን የሚያሸነፉ ተማሪዎች ከዚህ በተጨማሪም በቻይና፣ ካናዳ እና የተለያዩ አገራት ላይ በሚደረጉ ተመሳሳይ ውድድሮች ኢትዮጵያን ወክለው እንደሚሳተፉ አመላክተዋል፡፡
ውድድሩ ትውልዱ በፈጠራ ስራው ጎልቶ እንዲወጣ ማድረግን ያለመ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ብዙ ተሰጥኦ ያላቸው ተማሪዎች እንዳሉም ተናግረው፣ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ኢንጀነሪንግና ሒሳብ ትምህርቶች ላይ ፍላጎትና ተሰጥኦ ያላቸው ተማሪዎች ተሳታፊ እንደሚሆኑ ያመላክታሉ።
ማናጀሯ እንዳሉት፤ ተማሪዎቹ ወደ ኢትዮ ሮቦ ሮቦቲክስ ሲመጡ ቅድሚያ የሚታየው ለሳይንስ ዘርፍ ትምህርቶች ያላቸው ፍላጎት ብቻ ነው፡፡ ወደ ስልጠና ማዕከሉ ሲመጡ ግን ስለሮቦቲክስ ወይም ስቴም (ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢንጀነሪንግና ሒሳብ) ትምህርቶች ብዙ የሚያውቁት ነገር የለም፡፡
በሚሰጣቸው ስልጠና ስለሮቦቲክስ እንዲያውቁና እንዲፈጠሩ የማበረታታት ሥራዎች ይሰራሉ፡፡ ከስልጠናው ያገኙትን እውቀት ወደተግባር ለውጠው የፈጠራ ሥራዎች እንዲሰሩ ይደረጋል፡፡ ይህም ነገ በተለያዩ ዘርፎች (በግብርና፣ በጤና፣ በሳይንሱ) ላይ ለሀገራቸው የተሻለ የሚሰሩና የሚፈጥሩ ኢኖቬተሮችን ማፍራት ያስችላል፡፡
ተማሪዎች ለአንድ ዓመት ያህል በሮቦቲክስና ስቴም ላይ አብረው እንዲማሩ ይደረጋል የሚሉት ማናጀሯ፤ የውድድር ጊዜው እስኪደርስ ሮቦቶታቸውን በመገንባት፣ በዲዛይኒንግ፣ ኢንጂነሪንግና ፕሮግራሚንግ ክፍሎች እየሰሩ እንዲቆዩ፣ ከዚያም በቡድን ተደራጅተው እንዲወዳደሩ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡
ማናጀሯ እንዳብራሩት፤ የአፍሪካ የሮቦቲክስ ትምህርት ቤት የመጀመሪያው ትምህርት ቤት በመሆኑ የሚያዘጋጀው ውድድር አህጉር አቀፍ ነው፡፡ በዚህ ውድድር ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ የወጡ ተማሪዎች በቀጥታ በአሜሪካ በሚካሄደው ዓለም አቀፍ ውድድር ላይ ይሳተፋሉ፡፡
ከተማሪዎቹ የሚጠበቀው ትምህርቱን መጨረስ ብቻ አይደለም፤ በሀገራቸው ፈጠራ ሥራ ላይ አሻራቸውን በማኖር አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱም ይጠበቅባቸዋል፡፡ በዓለም አቀፍ ውድድሩ የሚሳተፉ ተማሪዎች ወደሀገራቸው ሲመለሱ በመድረኩ ላይ ሲወዳደሩ ያገኙትን ልምድና ተሞክሮ ይዘው ወደ ተሻለ ፈጠራ ሥራ መግባትም ይኖርባቸዋል፡፡ በዓለም አቀፉ ውድድር አሸንፈው የሚመለሱትም ወደቀጣዩ ደረጃ እንዲሸጋገሩ እንደሚደረግ ጠቅሰው፣ ለእዚህ ደግሞ በሚቀጥለው ዓመት የተሻለ ትምህርት እንዲከታተሉ እንደሚደረግ ጠቁመዋል፡፡
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን መጋቢት 9 ቀን 2017 ዓ.ም