ትምህርት ቤቶች ለብዙ የፈጠራ ሀሳቦች መነሻዎች እንደሆኑት ሁሉ መምህራንም በብዙ መንገድ አርአያ ተደርገው ይወሰዳሉ። መምህሩ በንድፈ ሀሳብ ያስተማረውን ትምህርት ተማሪዎች ወደ ተግባር እንዲቀይሩት ከማገዝና ከማበረታታት ባሻገር ሰርቶ በማሳየት ምሳሌ መሆን ይጠበቅበታል። ይህንንም በተግባር ከመተርጎሙ መካከል መምህር ሮባ ሙክታር አንዱ ነው። መምህሩ ተማሪዎች በማስተማር የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎች እንዲሰሩ ከማበረታታትና ከማገዝ ባሻገር የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎች በመስራት ተምሳሌት ሆኗል።
መምህር ሮባ ስልጤ ወራቤ ዞን ሳንኩራ ወረዳ ገተም ጉርቤ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የፊዚክስ መምህር ነው። የተለያዩ ፈጠራ ሥራዎችን የሚሰራ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ደግሞ በኮንስትራክሽን ዘርፍ አገልግሎት ሊሰጥ የሚችል ‹‹ሚክሰር›› የተሰኘ ሲሚንቶ የሚያቦካ ማሽን ሰርቷል። ይህን የፈጠራ ሥራ ትምህርት ሚኒስቴር ከባለድርሻ አካላት ጋር ባዘጋጀው ዘጠነኛው ዙር ሀገር አቀፍ የሳይንስና ምህንድስና ቀን አውደርዕይ ላይ አቅርቧል።
መምህር ሮባ ቀደም ሲል ጀምሮ የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎች ሲሰራ ቢቆይም ከኛ ጋር ያገናኘው አዲስ ፈጠራ ሥራ ለመስራት መነሻ የሆነው ሀሳብ ያመነጨው ከመምህርነት ሙያ በተጨማሪ የምህንድስና ትምህርት ዘርፍ ለመቀላቀል ባሰበበት ወቅት ነበር። ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የምህንድስና ትምህርቱን እየተማረ ሳለ የተግባር ላይ ልምምድ ለማድረግ በወጣበት ወቅት ልምምድ የሚያደርግበት ኮንትራክተር የሲሚንቶ ማቡኪያ በሀገር ውስጥ መስራት ስለማይቻል በውድ ከውጭ ሃገር እያስመጣ እንደሚሰራ ሲናገር ያደምጣል። ይህም ከፍተኛ ውጪ የሚጠይቅ እንደሆነና አቅምን የሚፈትን መሆኑን በመረዳቱ ለምን ሀገር ውስጥ ማምረት አልተቻለም? የሚለው እንዲያስብና እንዲያሰላስል አድርጎታል።
በተለያዩ ጊዜያት የወሰዳቸው የምህንድስና የመካኒክ ትምህርቶች ቢኖሩም አስቦና አሰላስሎ ብቻ እንዲተው አላደረጉትም፤ ይልቁንም ይህ ማሽን በሀገር ውስጥ ማምረት የሚችልበት ዘዴ ተጨማሪ እውቀት እንዲያገኝ አስችለውታል። በመቀጠልም በሀገር ውስጥ እስካሁን ለምን ማሽኑን መስራት አልተቻለም፤ ተሞክሮስ ነበር የሚለው ለማወቅ የዳሰሳ ጥናት ካካሄደ በኋላ ሥራው ለመስራት አስቦና አቅዶ ማሽኑን ሰርቷል።
መምህሩ እንደሚለው፤ ይህ ሲሚንቶ የሚያቦካ ‹‹ሚክሰር›› ማሽን በኮንስትራክሽን ዘርፍ ዋነኛነት አስፈላጊ ሆኖ ያገለግላል። በተለይ በኮንስትራክሽን ዘርፍ መሠረት የሆነው የሲሚንቶን የሚያቦካ ማሽን አብዛኛው ጊዜ ከውጭ ሃገር በከፍተኛ ዶላር ነው የሚገባው። በተለይ በኢትዮጵያ ግንባታ በእጅጉ በተስፋፋበት በአሁኑ ወቅት ይህ የሲሚንቶ ማቡኪያ ከሁሉም በላይ በእጅግ አስፈላጊ ነው።
‹‹ሲሚንቶን በእጅ አቡክቶ ቤት ለመስራት ብዙ ጊዜ ይፈጃል›› የሚለው መምህሩ፤ ማሽኑን በአካባቢው ላይ የሚገኙ ብረታ ብረቶችን ተጠቅሞ እየሰራ መሆኑን ይገልጻል። ማሽኑ በሀገር ውስጥ በቀላሉ ከሚገኙ ቁሳቁሶች የተሰራ ሲሆን በርሜል፣ ኩሽኔታ፣ ዲናሞ እና መሰል ቁሳቁሶች እንደተጠቀመ ያስረዳል። እነዚህ ሁሉ ቁሳቁሶች በአካባቢው ላይ በቀላሉ ሊገኙ የሚችሉ መሆናቸውን ያመለክታል። ማሽኑ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰራ በጀኔሬተርና በማንዋል ወይም በእጅ በቀላሉ የሚሰራ ነው። በተለይ መብራት ሲጠፋም ሆነ በሌለባቸው ቦታዎች በማንዋል ወይም በእጅ በመጠቀም መስራት እንደሚችልም መምህሩ ያብራራል።
ማሽኑ ከውጭ በጣም በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከማስገባት ይልቅ በሀገር ውስጥ የተመረተ መጠቀም ቢቻል ያለው ጠቀሜታ ዘርፈ ብዙ ነው። ማሽኑ በሰዓት 20 ኪዩቢክ ሜትር ኮንክሪት ያመርታል። በማሽኑ ኮንክሪት ለማምረት መጀመሪያ ሲሚንቶ ከገባ በኋላ መሽከርከር ሲጀምር ውሃ እንዲገባ ይደረጋል። ቀድሞ ውሃ ከገባ ቀጥሎ ሲሚንቶ የምናስገባ ከሆነ ውሃውን በመያዝ ኮንክሪቱ እንዳይሰራ ያደርገዋል። በመሆኑም መግባት ያለበት ሲሚንቶ መሆኑን ያስረዳል።
‹‹ከውጭ የሚገባው ሚክስርም ቢሆን ውሃ ቅድሚያ አይገባበትም። ቅድሚያ ሲሚንቶ ገብቶ ሲሽከረከር ነው ውሃ መግባት የሚችለው። ማሽኑን ለመጠቀም ስኬቶቹን በመሰካት ጎማው እንዲያሽከረክረው በማድረግ ሲሚንቶና ውሃን ቀላቅሎ ኮንክሪት ማምረት ይቻላል›› ሲል ይገልጻል። ማሽኑ በሥራ ላይ ውሎ ተፈትሾ አገልግሎት እንደሚሰጥ የተረጋገጠ መሆኑን የሚያነሳው መምህር ሮባ፤ የመንገድ ሥራ ላይ የተሰማራ ኮንትራክተር ተጠቅሞበት እንደነበር ይናገራል። ይህ ኮንትራክተር ከዚህ ቀደም የሲሚንቶ ማቡኪያ ሚክሰር በቀን ከአምስት እስከ ስድስት ሺ ብር ይከራይ እንደነበር አስታውሶ፤ ይህ ማሽን ግን በነጻ እንደተገለገለበት ያስረዳል። ኮንትራክተሩ ከተጠቀመበት በኋላ ማሽኑ በደንብ የሚሰራ መሆኑንና በጣም ጥሩ እንደሆነ አስተያየት መስጠቱን ይናገራል።
በተጨማሪም ማሽኑ ከውጭ ከሚመጣው ማሽን ቢበልጥ እንጂ የሚተናናስ አለመሆኑን ኮንትራክተሩ ምስክር እንደሆነው ያመለክታል። እንዲሁም ማሽኑን እንደልብ ከቦታ ቦታ ለማንቀሳቀስ እንዲቻል ጎማ ቢኖረው የሚል አስተያየት እንደሰጠው ተናግሮ፤ እሱም በቀጣይ ማሽኑ የሚያስፈልገው አራት ጎማዎች በመግጠም በቀላሉ እንዲንቀሳቀስ ለማድረግ ማቀዱንም ነው የጠቆመው።
‹‹ከውጭ ሀገር የሚመጣው ማሽን በገበያ ላይ ከ500 ሺ ብር በላይ ይሸጣል። አንድ በኮንስትራክሽን ሥራ ላይ የተሰማራ ሰው ማሽኑን መግዛት ባይችል ተከራይቶ ለመስራት ቢፈልግ በቀን አምስት ሺ ብር እና ከዚያ በላይ ወጪ ማውጣት ይጠበቅበታል። ማሽኑ በሀገር ውስጥ ቢመረት ግን በተመጣጣኝ ዋጋ ገዝቶ መጠቀም ይችላል›› ይላል። አዲሱ ማሽን ሀገር ውስጥ የሚገኙ ብረታ ብረቶችን በመበየድ በቀላሉ የሚሰራ እንደመሆኑ ብዙ ውጪ የሚጠይቅ አለመሆኑን ጠቅሶ፤ ዲናሞ ለመግዛት ብቻ የተወሰነ ገንዘብ እንደሚያስፈልግ ይገልጻል።‹‹ አሁን እንኳን ማሽኑ ላይ የገጠምኩትን ዲናሞ ተከራይቼ ነው። ድጋፍ የሚያደርግልኝ አካል ቢኖር የዲናሞ ዋጋ ብዙ አይደለም፤ ዋጋ 30 ሺ ብር ያህል ብቻ ነው›› ይላል።
ይህ ቢሟላለት ማሽኑን በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ የሚያቀርብ የሚችል መሆኑን ጠቅሶ፤ አሁን ባለበት ደረጃ እንኳን ለገበያ ቢቀርብ ትልቁ ወጪው ዲናሞ ብቻ እንደሆነ ያስረዳል። በመሆኑም ኪስ በማይጎዳ ዋጋ በማቅረብ ከውጭ የሚመጣውን ማስቀረት የሚቻል መሆኑን ያመለክታል። ማሽኑ ከውጭ ከሚመጣ አኳያ ሲታይ ጥራቱን የጠበቀ በመሆኑ ከውጭ ከሚመጣ ቢበልጥ እንጂ አያንስም የሚለው መምህር ሮባ ይናገራል። ከውጭ ከሚመጣ ማሽን የሚለየው ጎማ ብቻ ስለሌለው እንደሆነ ጠቁሞ፤ ይህንን ማሽን ሀገር ውስጥ በቀላሉ መስራት ሲቻል እስካሁን ድረስ ሳይሰራ መቆየቱ በአቅራቢያ ያሉ ብዙ ያልታዩ ችግሮች መኖራቸውና ብዙ ሊሰራባቸው የሚገባ ጉዳዮች እንዳሉ ያስገነዝባል።
‹‹ማሽኑ ብዙ የሚበላሹ ቁሳቁሶች የሉትም፤ ቢበላሽ ደግሞ እንደገና መበየድ ይቻላል። ምናልባት ቢበላሽ ዲናሞ ብቻ እንጂ ሌሎች ብዙ ስጋት የሌላቸው ናቸው። እነዚህ ቢሆን በቀላሉ መጠገን የሚቻሉ ናቸው›› ይላል። ይህን ማሽን ለመስራት የአንድ ወር ጊዜ እንደፈጀበት የሚናገረው መምህሩ፤ ማሽኑን ከዚህ በላይ አሻሽሎ ለመስራት እያሰበ በበጀትና በጊዜ እጥረት የተነሳ ቀድሞ እንደሰራው በአውደርዕዩ ይዞ መቅረቡን ይገልጻል። አሁን ባለበት ከአንድ ቦታ ወደ አንድ ቦታ ለማንቀሳቀስ በሰው ጉልበት እንደሚንቀሳቀስ ጠቅሶ፤ ካሰባቸውና መሻሻል ካለባቸው ነገሮች መካካል ሚክሰሩን ከቦታ ወደ ቦታ በቀላሉ እንዲንቀሰቀስ ለማድረግ የሚያስችል ጎማ ለመግጠም አስቦ እንደነበር አንስቷል። ወደፊትም ማንኛውም ሰው እንደልብ ሊያንቀሳቀስ እንዲችል ጎማ የሚገጥመለት መሆኑን ያመለክታል፡
‹‹አንድ ፈጠራ ሲሰራ የአገር እና የዓለም ችግርን የሚፈታ መሆን አለበት እንጂ ሞዴል ብቻ ሆኖ መቅረት የለበትም። እንደሀገር በፈጠራ ሥራ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች አብዛኛውን ጊዜ የኅብረተሰቡን ችግር ሊፈቱ የሚችሉ በብዛት ያላቸው ፈጠራዎች እየተሰሩ ቢሆንም ከተሰሩ በኋላ ግን የተሰሩበት ዓላማ ከግብ አያደርሱም›› ይላል። የኅብረተሰቡንም ችግር ሳይፈቱ ሞዴል ሆነው ብቻ የሚቀርቡት ሁኔታ መኖሩን ጠቅሶ፤ እነዚህ ተግዳሮቶች አሁንም ድረስ ያሉና የቀጠሉ መሆናቸው ይጠቁማል። የተሰሩ የፈጠራ ሥራዎች በአግባብ ተግባር ላይ በማዋል ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ቢቻል የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ እንደሆነም ያስረዳል።
‹‹አሁን ላይ አንድ ማሽን ብቻ ነው የሰራሁት፤ ከዚህም ሌላ ብዙ ሥራዎች መስራት እፈልጋለሁ፤ ማሽኑን በብዛት በማምረት ተደራሽ ለማድረግ እቅዱ ስላለኝ በተለይ ድጋፍ የሚያደርግልኝ አካል ካገኘሁ በብዛት በማምረት ለገበያ ማቅረብ እችላለሁ። ማሽኑን በስፋት በሀገር ውስጥ በማምረት ከውጭ የሚገባውን በመተካት የውጭ ምንዛሪን ለማስቀረት እሰራለሁ››ይላል።
በመምህርነት ሙያው ለተማሪዎች አርአያ መሆን ስለሚያስፈልግ የፈጠራ ሥራዎችን በመስራት ለተማሪዎች እያበረታታ እንደሆነ የሚናገረው መምህሩ፤ በተለይ የፈጠራ ሥራዎች የሚሞክሩ ተማሪዎቹን በማበረታታት የፈጠራ ሥራዎች እንዲሰሩ እያደረገ መሆኑን ይገልጻል። ‹‹ያስተማርኳቸው ተማሪዎች የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎች እየሰሩ ነው። የመኖ ማቀናበሪያና ሌሎችን አይነት ማሽኖች መስራት ችለዋል። ትምህርቱን ሳስተምር በንድፈ ሀሳብ ይልቅ በተግባር በመደገፍ እንዲፈትሹ እያደረጉ ነው። ይህንን የፈጠራ ሥራ መስራቴ ደግሞ ተማሪዎች አይተው እንዲበረታቱ ለማድረግ ተነሳሽነትን ይፈጥራል›› ይላል።
ሌሎች መምህራን ተማሪዎቻቸውን ሲያስተምሩ በንድፈ ሀሳብ ላይ ከሚያተኩሩ ይልቅ በተግባር ላይ ትኩረት አድርገው ሊሰሩ ይገባል። ለዚህ ንድፈ ሀሳቡ ወደ ተግባር ሲቀየር የአካባቢ የኅብረተሰቡን ብሎም የሀገር ችግር ሊፈታ የሚችል ሥራዎች ላይ ትኩረት ሊያደርጉ ይገባል። ‹‹በተለይ እኛ መምህራን ተማሪዎቻችን በንድፈ ሀሳብ ያስተማርናቸው ትምህርት ወደ ተግባር እንዲቀየር በማበረታታት እና በመደገፍ ውጤታማ እንዲሆን መስራት አለብን። ለአብነት ለተማሪዎች ስለኢነርጂ ካስተማርናቸው ኢነርጂ በሕይወታቸው ምን ይጠቅማል እንዴትስ ከሕይወታቸው ጋር ይቆራኛል የሚለውን በትክክል ካስረዳናቸውና ካሳየናቸው ንቁና የፈጠራ ሀሳብ በፍጥነት እንዲያውቁና እንዲረዱ ማድረግን ይጠይቃል›› ሲል ይመክራል።
መምህር ሮባ እንደሚለው፤ ቀደም ባሉት ጊዜያት ሁለት አይነት የመኖ ማቀናባበሪያ ማሽን ሰርቷል። በአንደኛው ከተማሪዎቹ ጋር በመሆን በሙከራ ደረጃ የተሰራ በማኑዋል የሚሰራ ሲሆን በእጅ ሲሽከረከር የተዘጋጀው መኖን በመቆራረጥ የሚፈጭ ነው። ሁለተኛው ደግሞ በኤሌክትሪክ የሚሰራ የመኖ ማቀነባበሪያ ማሽን ሲሆን ይህ መኖ ማቀናባበሪያ ማሽን ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ሆኖ በአካባቢ ያሉ ሰዎች እየተጠቀሙበት ይገኛሉ። በቀጣይም ማሽኑ በብዛት አምርቶ ጥቅም ላይ በማዋል ኅብረተሰቡ እንዲጠቀምበት ለማድረግ እቅድ አለው።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ኅዳር 24 ቀን 2017 ዓ.ም