
የምርምር ሥራዎች ችግር ፈቺ ከመሆናቸው ባሻገር በሀገር ኢኮኖሚ እድገት ላይ ከፍተኛ ሚና ያላቸው ስለመሆኑ በጽኑ ይታመናል። የሀገር ሀብት ጥቅም ላይ እንዲውል ምቹ ሁኔታ በመፍጠርና የኅብረተሰቡ ችግር እንዲፈታ እንዲሁም የኢኮኖሚ ምንጭ በመሆን ረገድም ጠቀሜታቸው የጎላ ነው። በተለይ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርቶች ለመተካት የሚሠሩ ምርምሮች ለኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግሥት ለምርምር ዘርፉ ምቹ ምህዳር በመፍጠር ትኩረት በመስጠቱ ብዙ የምርምር ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ። በተለይ ከዩኒቨርሲቲ፣ ኢንዱስትሪና ምርምር ተቋማት ጋር ትስስር በመፍጠር ተቋማቱ ምርምር ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሠሩ መድረጉ ለውጦች እንዲመጡ እያደረገ ይገኛል።
ከምርምር ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው የባዮና ኢመርጂንግ ኢንስቲትዮትም በምርምር ዘርፉ ላይ ትኩረት አድርጎ በርካታ የምርምር ሥራዎች ሠርቷል፤ በመሥራት ላይም ይገኛል። ኢንስቲትዩቱ እስካሁን ብዙ የምርምር ሥራዎችን ቢያወጣም፣ የአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ባለቤትነት ያገኙት ግን ጥቂት መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ። ባለፈው ሳምንት መጨረሻ አስራ አንድ ኢንስቲትዩቱ የምርምር ውጤቶች የአዕምሯዊ ንብረት የባለቤትነት መብትና የዩቲሊቲ ሞዴል የባለቤትነት ማረጋገጫ ከኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን አግኝተዋል።
ኢንስቲትዩቱ የአዕምሯዊ ባለቤትነት መብት ያገኘባቸው አስራ አንዱ የምርምር ውጤቶች በተለያዩ ዘርፎች ላይ የተሠሩ ናቸው። በምርምሩ ከተገኙ ምርምር ውጤቶች መካከል ከውጭ የሚገባውን ወረቀት የሚያስቀር ምርት ተጠቃሹ ነው።
መረጃዎች እንደሚያመላክቱት፤ ኢትዮጵያ የወረቀት ምርት ከውጭ ለማስገባት በዓመት 44 ቢሊዮን ብር ወጪ ታደርጋለች ተብሎ ይገመታል። ይህንን ምርት በሀገር ውስጥ ምርት መተካት የሚያስችል የምርምር ውጤት መገኘቱ ተመላክቷል። ሌሎችም በተለያዩ ዘርፎች ያሉ ችግሮችን የሚፈቱና ተኪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ማምረት የሚያስችሉ የምርምር ውጤቶች መገኘታቸው ይፋ ተደርጓል።
በመድረኩ የተገኙት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ(ዶ/ር) መንግሥት ትኩረት ከሰጣቸው ዘርፎች መካከል አንዱ ባዮና ኢመርጂንግ ነው ይላሉ። ኢንስትቲዩቱ ከምርምር አንጻር ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ሲሠራ መቆየቱን ይጠቅሳሉ። ኢንስቲትዩቱ የምርምር ውጤቶችን በማውጣት ተኪ ምርቶችን በማምረት ለሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እየሠራ መሆኑንም ይገልጻሉ። አሁን የአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ የሚደረግባቸው የምርምር ውጤቶች ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እንዳላቸው ተናግረዋል።
በእውቀት ላይ የተመሠረተ ኢኮኖሚ ለመገንባት የአዕምሯዊ ንብረት ሥራዎችን ማሳደግ ይገባል የሚሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በመንግሥት በኩል ለምርምር ልማት ምቹ ሥነ ምህዳር ለመፍጠር እየተሠራ መሆኑን ይጠቁማሉ። ለዚህ ሥራ የሚያስፈልጉ የፖሊሲና የሕግ ማሕቀፍ ዝግጅቶች እየተደረጉ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።
እሳቸው እንዳብራሩት፤ ዘርፉ እጅግ በጣም ወሳኝ ከመሆኑ ባሻገር፤ የድህነትን እድሜ የሚያሳጥር፣ ለእያንዳንዱ ችግር ምላሽ የሚሰጥ ፤ ዘለቄታ ያለው የረጅም ጊዜ እድገት እንዲኖር ማድረግ ያስችላል። ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ተቋማት ከኢንዱስትሪው ጋር ተቀናጅተው በመሥራት ውጤት እንዲያመጡ ማድረግ ተቀናጅቶ መሥራትን ይጠይቃል፤ በዘርፉ የተሠማሩ አካላት በቅንጅት መሥራትና የምርምር ሥራዎችንም እንዲያስተዋውቁም ይጠበቃል።
በፈጠራ የሚመራ ኢኮኖሚ በመገንባት የአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ የባለቤትነት መብት ሥራን ማሳደግ ይገባል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ መፍጠንና መፍጠርን ተግባራዊ በማድረግ ውጤታማ ሥራዎችን ለመሥራት በትብብር ይሠራል ብለዋል።
በምርምሮች የእውቀት ምንጭ መሆናችንና ኢትዮጵያን በዓለም ላይ መግለጽ መቻላችን ትልቅ ስኬት ነው ሲሉም ጠቅሰው፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከ435 በላይ የምርምር ሥራዎች በአንድ ተቋም ብቻ / በባዮ ኢመርጂንግ ኢንስቲትዩት/ መሥራታቸው ያለን እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ብዙ መሥራት እንደሚቻል ያመለክታሉ ብለዋል። የምርምር ውጤቶቹን ወደ ተግባር የመቀየር ሥራዎችም እንደሚቀጥሉ ጠቁመው፣ በዚህ ረገድ ሁላችንም ተረባርበን ከሠራን የተሻለ ውጤት ማምጣት እንችላለን ሲሉ ገልጸዋል፡፡
አሁን ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃም በምርምር ተወዳዳሪ ለማድረግ የሚያስችል ተግባር እያከናወነ መሆኑን ጠቁመው፤ ለምርምር ግብዓት የሚሆኑ ሀገር በቀል ሀብቶች በሌላ እንዳይወሰዱ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የምርምር ግብዓት የሚሆኑ ሀገር በቀል ሀብቶች እጅግ በጣም ብዙ መሆናቸውንና እነዚህ ሀብቶች በሌላ እንዳይዘረፉም ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ሚኒስትር ዴኤታው አመልክተዋል። ‹‹በዚህ ላይ እኛ ገና ብዙ አልሠራንም፤ ይህንን ያዩ አካላት እንዳይወስዱብን ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል። ገና ብዙ ሠርተን ውጤታማ የምርምር ውጤቶችን እናወጣለን፤ በእዚህም ለሀገር ብቻም ሳይሆን ለዓለምም መፍትሔ መሆን እንችላለን›› ብለዋል፡፡
የባዮና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ካሳሁን ተስፋዬ (ፕ/ር) በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ ባዮና ኢመርጂንግ ምርምር እንዲያከናወን በበላይነት እንዲመራና እንዲያስተባብር ታስቦ የተቋቋመ መሆኑን ይገልጻሉ። ከ2011 ጀምሮ በሙሉ መልኩ ወደ ምርምር ሥራ ገብቶ ብዙ ምርምሮችን ማከናወኑን ተናግረዋል።
እሳቸው እንዳብራሩት፤ ኢንስቲትዮቱ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ዘርፎች ያተኮሩ 109 በሂደት ላይ ያሉ ምርምሮች እየሠራ ሲሆን፤ የ43 አዳዲስ ምርምሮች የምርምር ተግባራትን እያከናወነ መሆኑንም ይገልጻሉ። ሀገሪቱ ያላትን ይህን እምቅ ሀብት ለሀገር ልማት ከማዋል አንጻር የባዮና ኢመርጂንግ ዘርፍ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለውም አመልክተዋል።
በተለይ ደግሞ የሀገሪቱ የባዮና ቴክኖሎጂ ምርምርና ልማት ሥራዎች በጅምር ላይ የሚገኙ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ የዘርፉ እድገት ከሰው ሀብት ልማትና ከመሠረተ ልማት እንዲሁም ምቹ ምህዳር ከመፍጠር አንጻር ብዙ እንደሚቀሩትም አስታውቀዋል። የተጀመሩ ሥራዎች ጥሩ ውጤት ማምጣታቸውንም ያመላክታሉ።
እሳቸው እንዳሉት፤ ኢንስቲትዮቱ ሀገሪቱ ያላትን እምቅ ሀብት የመጠቀምና ጠንካራ የባዮ ኢኮኖሚ መሠረት በሚጥሉ ችግር ፈቺ ምርምሮች ላይ አተኩሮ ይሠራል፤ ወደ ሀገሪቱ የሚገቡትን የኢንዱስትሪ ግብዓቶች ለመተካት እንዲሁም የዘርፉን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የሚያስችሉ ምርምሮች ላይም ይሠራል። ከእነዚህ መካከል የአዕምሯዊ ንብረት ባለቤትነት መብት ያገኙት 11 ምርቶችና የምርት ሂደቶች ይጠቀሳሉ።
ኢንስቲትዮቱ ቀደም ሲል የአእምሮ ባለቤትነት መብት ያገኘባቸው 12 ምርቶችና ቴክኖሎጂዎች እንዳሉትም ዋና ዳይሬክተሩ ይገልጻሉ። በአሁኑ ወቅት በአጠቃላይ የ23 የምርትና ምርት ሂደቶች የአእምሮ ንብረት ጥበቃ ባለቤትነትና ዩቲሊቲ ሞዴል ባለቤት እንዲኖረው አድርገውታል። ይህም አሀዝ ቀላል የማይባል በመሆኑ ከፍተኛ የአእምሮ ንብረት ባለቤነት መብት አስመዝጋቢ ያደርገዋል። ተቋሙ ለዚህ እንዲበቃ ያደረጉትን ተመራማሪዎች እና ሠራተኞችም አመስግነዋል።
ተቋሙ ባለፉት ሰባት የምርምር ዓመታት ከምርምር ውጤቶች ባሻገር 435 ምርምሮችን በዓለም አቀፍ ጆርናል መሳተም መቻሉንም አስታውቀዋል። ለሳይንስ ማኅበረሰቡ ጠቃሚ እውቀትና መረጃ በመስጠት ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተር ካሳሁን ተስፋዬ(ፕ/ር)፤ የምርምር ሥራዎች በእውቀት ላይ የተመሠረተ ኢኮኖሚ ለማምጣት ትልቅ ምዕራፍ እንደሚከፍቱ ይናገራሉ። ‹‹የአእምሮ ንብረት ባለቤትነት ሰርተፊኬት ማግኘቱ ለእእምሯችን ለአስተዋጽኦችንን ዋጋ ይሰጣል›› ሲሉ ጠቅሰው፣ በተለይ ደግሞ በቀጣይ በሀገር ኢኮኖሚ ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው የምርምር ሥራዎችና ከውጭ የሚመጡ ምርቶችን የሚተኩ ችግር ፈቺ ምርምሮች ላይ ትኩረት አድርገን እንሠራለን ሲሉም አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ወልዱ ይመስል እንደሚሉት፤ የአእምሮ ንብረት ጥበቃ የቴክኖሎጂ ሽግግርና ኢኖቬሽን ዋንኛ መሳሪያ ከሆነ ረዘም ያሉ ጊዜያትን አስቆጥሯል።
ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ጋር ተያይዞ የባለቤትነትና የአዕምሯዊ ንብረት ጉዳይ በግል ንግድ ሥራ የተሰማሩ ሀብት ለማካበት የሚያስቡ ግለሰቦችንና የቢዝነስ ተቋማት የሚሠሩበት ተደርጎ ይታይ እንደነበር አስታውሰው፤ በጊዜ ሂደት ዩኒቨርሲቲዎችና እንደ ባዮና ኢመርጂንግ ዓይነት የምርምር ተቋማት ቁልፍ ሚና የሚጫወቱበት ሁኔታ እየተፈጠረ መምጣቱን ይገልጻሉ።
እሳቸው እንደሚሉት፤ በዓለም ላይ እንደ 3ዲ፣ አርተፊሻል ኢንተለጀንስ ዓይነት ቴክኖሎጂዎች በዩኒቨርሲቲዎች ምርምር የተገኙ ናቸው። ይህም ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ተቋማት በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚጫወቱት ሚና እያደገ መምጣቱን ያሳያል፤ በቀጥታ ከፓተንት ጋር የሚይይዝ ነው። የአእምሮ ንብረት ጥበቃ ባለቤትነት መብት ከሌለ ሀብት መፍጠር አይቻልም፤ ምርምር ወደ ሀብት መቀየር አለበት፡፡
በዚህም ሂደት ዩኒቨርሲቲዎች ተጨባጭ ለውጥ ያመጡበትና የእውቀት ሽግግር ማዕከል እየሆኑ የመጡበት ሁኔታ መፈጠሩንም ይገልጻሉ። የምርምር ውጤቶች በአእምሯዊ ንብረት ባለቤትነት መመዝገብ ምርምሮቹ ለዲጂታል ኢኮኖሚው ከፍተኛ ሚና እንዲኖራቸው እንደሚያደርግ ያመላክታሉ።
ዋና ዳይሬክተሩ መረጃዎችን ዋቢ አድርገው እንዳብራሩትም፤ ከአውሮፓ አጠቃላይ የአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ 10 በመቶ ያህሉ ከዩኒቨርሲቲዎች የመጣ ነው። አንድ ሺ200 የሚሆኑ የአውሮፓ ዩኒቨርሲቲዎች በአእምሯዊ ንብረት ሥርዓት ውስጥ ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ናቸው። እንደባዩና ኢመርጂንግ ኢንስቲትዮት ያሉ የምርምር ተቋማትም እንዲሁ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
በዩኒቨርሲቲዎችና በምርምር ተቋማት የሚሠሩ ምርምሮች ለሌላ ቴክኖሎጂ ሽግግርና ምርምር ከፍተኛ እድል የሚሰጡ ከመሆናቸውም በላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ፈጣሪዎች ናቸው የሚሉት አቶ ወልዱ፤ ለሌላ ምርምር መሠረት እንደሚጥሉም ተናግረዋል። ምክንያቱም ደግሞ የምርምራቸውን ሙሉ መረጃ መስጠት የሚችሉ በመሆናቸው ነው ብለዋል። በግል የሚደረጉ ምርምሮች ከሆኑ ግን ሁሉንም መረጃ የማይሰጡበት ሁኔታ እንዳለ ይገልጻሉ፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ እንዳብራሩት፤ ከዓለም የአእምሮ ንብረት ጥበቃ አምስት በመቶ ያህሉ ድርሻ ያለው ባዮቴክ ዘርፍ የተሠራ ሲሆን፣ ይህም ዘርፉ በጣም በከፍተኛ ደረጃ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ያመለክታል። ኢትዮጵያ ያላት ሀብት ቀላል የማይባል በመሆኑ በባዮና ኢመርጂንግ ኢንስቲትዮት የተሠሩትና የአእምሮ ንብረት ጥበቃ መብት ያገኙት ምርቶች በሀገር ውስጥ ያለውን ሀብት ተጠቅመው የተሠሩ ናቸው። የባለቤትነት መብት ያገኙት አሁን በሀገሪቱ ካለው ነባራዊ ሁኔታዎች ጋር ተያይዞ ወደ ሀብትነት /ንግድ/ ሊሸጋገሩ የሚችሉ አቅሞችን እንደሚፈጥሩ ታይቷል፡፡
በተለይ የባዮና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ትልቅ አቅም እንዳለው ገልጸው፤ እነዚህን ወደ ተግባር ለማምጣት ብዙ ፈተናዎች ቢኖሩም ፈተናዎቹን ማለፍ የሚቻለው ሀብት በመፍጠር ነው ብለዋል።
የምርምር ተቋማት ምርምሮችን ወደ ተጨባጭ ሀብት ቀይረው ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ያሉት አቶ ወልዱ፤ የምርምር ሥራዎች የአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ማግኘት ተኪ ምርቶችን ለማስፋፋትና ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን ለማበራከት የሚያግዝ ነውም ብለዋል። በቀጣይም በዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን የአዕምሯዊ ንብረት መፍጠርና ማስመዝገብ ላይ በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
ሌሎች ሀገራት ስንመለከት በዓመት 1600 ያህል ምርምሮችን በአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ እንደሚያስመዘገቡ ጠቅሰው፤ በኢትዮጵያ ግን በ20 ዓመታት በምርምር ረገድ የተመዘገበው የአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ 800 ያህል መሆኑን ይገልጻሉ። ይህም ብዙ መሥራትን እንደሚጠይቅ አስታውቀዋል።
በዚህ ዓመት የባዮና ኢመርጂንግ ኢንስቲትዮቱ አርአያ እንደሆነ ሁሉ ሌሎችን ለማፍራትና ለውጥ ለማምጣት መሥራት አለብን ሲሉም ገልጸው፣ የአዕምሯዊ ንብረት እውቀቱን መመዝገብ ብቻ ሳይሆን እውቀቱ እንዲፈጠርም እንዲለማም በማበረታታት የተጀመሩ ሥራዎችን አጠናክሮ ያስቀጥላል ሲሉ አቶ ወልዱ ተናግረዋል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ማክሰኞ መጋቢት 30 ቀን 2017 ዓ.ም