በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ሦስት ብስክሌቶች የሠራው የፈጠራ ባለሙያ

የአርሶ አደር ልጅ ነው፤ ወላጆቹ የሚተዳደሩበትን የግብርና ሥራ እየሠራ አድጓል:: ወላጆቹ የእነርሱን ፈለግ እንዲከተል ቢገፋፉትም የሕይወት ጥሪው ግን ሌላ ነበር፤ አብዛኛውን ጊዜውን በቴክኒክ ሥራዎች ላይ በመሳተፍ የልጅነት ጊዜውን አሳልፏል::

ተሰጥኦውን ልብ ብለው ያስተዋሉና የተረዱ አንዳንድ የአካባቢው ሰዎች ወላጆቹን መክረው ወደ ትምህርት ቤት እንዲገባ አደረጉት:: እሱ ግን ከትምህርቱም ሆነ ከሥራው ዓለም ይልቅ ውስጡ የሚመላለሰው የፈጠራ ሥራ ጉዳይ ነው::

በውስጡ ተዳፍኖ የቆየው የፈጠራ ሃሳብ አጋጣሚ ፈልጎ ከውስጡ አፈትልኮ የሚመጣበትን ጊዜ ሲጠብቅ ነበርና ጊዜው ደርሶ ከውጭ የተገዙ የተደረጉ እንጂ በሀገር ውስጥ የተሠሩ የማይመስሉ የፈጠራ ሥራዎችን ለመሥራት በቃ:: ይህ የዛሬ የሳይንስና ቴክኖሎጂ አምዳችን ዛሬ ይዞት የመጣው የፈጠራ ባለሙያ አቶ ተሾመ ግርማ ይባላል::

አቶ ተሾመ፤ ገና ከልጅነቱ ጀምሮ የፈጠራ ክህሎት በውስጡ እንደነበር በሚሠራቸው የፈጠራ ሥራዎቹ ሲገልጻቸውና ለሚገጥሙት ችግሮች መፍትሔ ያላቸው ሃሳቦች እያመነጨ ወደ ፈጠራ እየቀየረ ሲሠራ ቆይቷል:: በዚህም ጊዜ በውስጡ የነበረውን ተሰጥኦ በተለያዩ መንገዶች ሲያወጣ የተመለከቱ የአካባቢው ሰዎች ይደነቁበት እንደነበርም ያስታውሳል:: በልጅነት እአምሮ ከማይረሳቸው መካከል የድንጋይ ወፍጮ ሠርቶ አፈር እና ጥራጥሬ በመጨመር እየፈጨ የአካባቢውን ሰዎች ሳይቀር ሲያስደንቅ የነበረበት ሁኔታ አንዱ ነው::

ወደ ትምህርት ቤት ገብቶ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቅቆ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ትምህርቱ ከገባ በኋላ ትምህርቱን አጠናቅቆ ወደ ሥራ ዓለም ቢሠማራም፣ የፈጠራ ሃሳቡን አውጥቶ ወደ ተግባር ለመቀየር እምብዛም ጥረት አላደረገም::

አሁን በንግድ ሥራ ተሠማርቶ እየሠራ ቢሆንም፣ በትርፍ ጊዜው በውስጡ ያለውን የፈጠራ ሃሳብ ወደ ተግባር ለመቀየር አቅዶ ተግባር ላይ ያውላል:: የፈጠራ ሃሳቡን ወደ ተግባር መቀየር ቢችል ሀገር እንደሚጠቅምም ስለተረዳ በፈጠራ ሥራ ትኩረቱን ማድረግ ጀመረ::

አቶ ተሾመ፤ አሁን ከንግድ ሥራው በተጨማሪ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ የትምህርት ዘርፍ የማታ መርሃ ግብር ትምህርቱን እየተከታተለ ነው:: በትርፍ ጊዜው የፈጠራ ሃሳቡን ወደ ተግባር በመቀየር በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ሦስት አይነት ብስክሌቶችን ሠርቷል::

ለብስክሌቶቹም የተለያየ ስያሜ አውጥቶላቸዋል:: የመጀመሪያ ኤዲ -36 ቮልት የኤሌክትሪክ ስኩተር (AD-36V electric scooter)፣ ሁለተኛው ኢቲ- 72 ቮልት የኤሌክትሪክ ሳይክል (ET-72V electric Bike) እና ሦስተኛው ኢቲ-48 ቮልት ኤሌክትሪክ ትራይ ሳይክል ለአካል ጉዳተኞች ( ET-48V electric Tricycle for Disablity) የሚል ስያሜ ተሠጥቷቸዋል::

አቶ ተሾመ እንዳብራራው፤ የመጀመሪያ የፈጠራ ሥራው የሆነው ኤዲ -36 ቮልት ኤሌክትሪክ ስኩተር የተሰኘው በኤሌክትሪክ የሚሠራ ብስክሌት ከተማው ውስጥ በደንብ ለመንቀሳቀስ እንዲችል ተደርጎ የተሠራ ነው:: ባትሪው በጣም ትልቅና ሁለት ክፍል ያለው ነው:: አንዴ ቻርጅ ተደርጎ በሰዓት ከ80 ኪሎሜትር በላይ መጓዝ ያስችላል:: አንድ ባይስክል መያዝ ያለበትን ሁሉንም ነገር ያሟላ ከመሆኑም በላይ ለአፍሪካ ሀገሮች መንገዶች እንደሚች ተደርጎ ተሠርቷል:: ባትሪው ቻርድ የሚደረግበት ፍጥነት እና ሳይክሉ ከመሬት በላይ ያለው ከፍታ እንዲጨምር ተደርጓል::

ሁለተኛው የፈጠራ ሥራው ኢቲ- 72 ቮልት ኤሌክትሪክ ሳይክል ደግሞ ከተማ ውስጥ ያሉ ሳይክሎችና ሞተር ሳይክሎችን ወደ ኤሌክትሪክ ሳይክልና ሞተር ሳይክል መቀየር እንደሚቻል ያመላከተ ነው:: በጣም አቅም ያለው 70 ቦልት 20 አምፒር እስከ 1000 ዋት ያለው ሲሆን፣ በአንድ ጊዜ ቻርጅ ከ120 ኪሎ ሜትር በላይ መሄድ ያስችላል:: ሦስት አይነት የፍጥነት ወሰኖች ያሉትም ነው፤ የመጀመሪያው የፍጥነት ወሰን በሰዓት እስከ 35 ኪሎ ሜትር ይነዳል:: ሁለተኛው በሰዓት 55 ኪሎ ሜትር የሚነዳ ሲሆን፣ ሦስተኛው በሰዓት 85 ኪሎ ሜትር መሄድ ይችላል:: ሁሉም አስፈላጊ ነገሮች የተሟሉለትና ተፈትሾ የተረጋገጠ ነው::

ሦስተኛው ኢቲ-48 ቮልት ኤሌክትሪክ ትራይ ሳይክል ባለሶስት እግር ተደርጎ ለአካል ጉዳተኞች እንዲሆን የተሠራ ነው:: በኤሌክትሪክ የሚሠራ ሲሆን፣ 48 ቦልት ይጠቀማል:: የሀገሪቷን ነባራዊ ሁኔታ ከግንዛቤ ውስጥ ያስገባ እንደ ልብ መውጣትና መግባት እንዲችል ታሳቢ ተደርጎ የተሠራ ሲሆን፣ ዲስክ ብሪክ የተሰኘ አዲስ ቴክኖሎጂም ተገጥሞለታል::

ይህን ትራይ ሳይክል ለመሥራት በብዛት የተጠቀምኩባቸው የሳይክል ቁሳቁስ ናቸው የሚለው ተሾመ፤ የሳይክል ቁሳቁስ በጣም ርካሽ ስለሆኑ በሀገራችን በቀላሉ የሚገኙ በመሆናቸው ምንም አይነት ችግር ቢያጋጥማቸው ከሳይክል ቤቶች ገዝቶ ለመቀየርና ለረጅም ጊዜ ለመጠቀም የሚያስችሉ ናቸው ሲል አብራርቷል::

ሌላው አዲስ የተጨመረው ደግሞ ከውጭ ከሚመጡ ሳይክሎች በተለየ መልኩ ሊትየም አየን የተሰኘ ባትሪ እየተገጠመ መሆኑ ነው:: የዚህን ባትሪ ፓኬጅ እዚሁ በሀገር ውስጥ በማምረት እንደሚጠቀም ይገልጻል:: ባትሪዎቹን ለመሥራት ከውጭ የሚመጣ ምንም አይነት ግብዓት እንደማያስፈልግ ተናግሮ፣ የላፕቶፕ ባትሪዎችን እንደገና ጥቅም ላይ በማዋል የባትሪዎቹን አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ እንደሚቻል አስታውቋል::

የፈጠራ ባለሙያው እንዳብራራው፤ ሊትየም አየንን መጠቀም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው:: የከተማ ባይስክሎች የሚጠቀሙት ሊድ አሲድ የተባለውን የቆየ ሞዴል ነው:: ይህንን መጠቀማቸው ደግሞ የቆይታ ጊዜያቸው በጣም አጭር እንዲሆንና ቻርጅ ለማድረግ ብዙ ሰዓታት እንዲፈጁ ያደርጋል:: ሙቀትን በራሳቸው መቆጣጠርም አይችሉም:: በዚህ የተነሳም ባትሪዎቹ ብዙ ጥቅም ሳይሰጡ ቶሎ ይሞታሉ::

ሊትየም አየን የተገጠመላቸው ብስክሌቶች ባትሪዎቹ ግን ብዙ ይቆያሉ:: እስከ ሦስት ዓመት የቆይታ ጊዜያቸው ይኖራቸዋል:: ሙቀት የመቆጣጠር አቅማቸው ከፍተኛ ነው:: ባትሪ የሚቆጣጠር ሲስተም የተገጠመላቸው ናቸው:: አገልግሎታቸው ካበቃ በኋላ በቀላሉ ሊወገዱም ሆነ ሊጠገኑም ይችላሉ::

‹‹ሊድ አሲድ ባትሪው ካቆመ ሙሉ ለሙሉ ማስወገድ እንጂ እንደገና መልሶ ጥቅም ላይ ማዋል አይቻልም፤ ያለው አማራጭ መጣል ብቻ ነው:: ሊትየም አየን ግን የተወሰኑ ሴሎቹ ከውስጡ ቢሞቱ እነዚያን በሌላ በመተካት አገልግሎቱ እንዲቀጥል ማድረግ ይቻላል›› የሚለው አቶ ተሾመ፤ ይህም ሳይክሎቹን ከሌሎች ከውጭ ከሚገቡ ሳይክሎች የተለየ እንዲሆን እንዳደረገው ያስረዳል::

የመጀመሪያ የፈጠራ ሥራው የሆነውን ኤዲ -36 ቮልቴጅ ኤሌክትሪክ ስኩተር ያለበትን ምክንያት ስያስረዳ ኤዲ/ AD/ በሚለው እናቱ ለማስታወስ፣ ከእናቱ ሙሉ ስም መጀመሪያ ፊደል ወስዶ መሰየሙንና 36V የሚለው ቮልቴጁን የሚገልጽ እንደሆነ ያብራራል::

ሁለተኛው ET-72V ኢቲ ኢትዮጵያ ፤ 72V ደግሞ ቮልቴጁን የሚገልጽ መሆኑን ጠቅሶ፤ ሦስተኛው ET-48V ኢቲ ኢትዮጵያ 48V የቮልቴጁን መጠን እንደሚገልጽ ያስረዳል::

የመጀመሪያ የፈጠራ ሥራ አይነት ኤሌክትሪክ ስኩተር ሳይክሎች ወደ ሀገሪቱ ብዙም አልገቡም፤ የሉም ማለት ይቻላል ሲል አቶ ተሾመ ተናግሯል:: የኮሪደር ልማቱ እነዚህን ነገሮች ያበረታታል በሚል ሃሳብ ሳይክሉን እንደሥራው ይገልጻል::

ስለሁለተኛው የፈጠራ ሥራው ሲያብራራም ሁለተኛው የፈጠራ ሥራው ከውጭ ከሚመጡት ባይስክሎች እንደሚለይ ተናግሮ፣ የዚህ አንዱ ምክንያት የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ከግንዛቤው ውስጥ በማስገባት የተሠራ በመሆኑ ነው ይላል:: እንደ ሀገር እነደዚህ አይነቶቹ ብስክሌቶች በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከምናስመጣ የተወሰኑ ነገሮች ብቻ በማስመጣት ለምን ሀገር ውስጥ መሥራትና ማምረት አንችልም በሚል ሃሳብ ለመሥራት እንደቻለ ይናገራል::

ሦስተኛውን የፈጠራ ሥራ ለመሥራት የተነሳሳው ካዛንቺስ አካባቢ አንድ አካል ጉዳተኛ የሚጠቀምበት ዊልቸር ተመልክቶ መሆኑን ያስታውሳል:: ከየት አመጣህ ? በስንት ብር ገዛኸው ? ብሎ ሲጠይቀው አካል ጉዳተኛው የሰጠው ምላሽ ልቡን እንደነካው አቶ ተሾመ ይናገራል:: አካል ጉዳተኛው በእኛ ሀገር አቅም መግዛት እንደማይቻል፣ በግብረ ሰናይ ድርጅት አማካኝነት ያገኘው መሆኑን ሲነግረው ለምን እኛ እንሠራውም በሚል ቁጭት ተነስቶ አካል ጉዳተኞች ለመርዳት እንደሠራው አስታውቋል::

አቶ ተሾመ እንደሚለው፤ እነዚህ የፈጠራ ውጤቶች በዋጋም ቢሆን ከውጭ ከሚገቡት ጋር የሚነጻጻሩ አይደሉም፤ ከውጭ የሚገቡት በጣም ውድ ናቸው:: በሀገር ውስጥ የሚመረቱት ግን ብዙ ቁሳቁሳቸው በቀላሉ ይገኛል፤ መልሶ ጥቅም ላይ የሚውሉ ቁሳቁስ በብዛት ይገኛሉ:: በዚህ የተነሳ ዋጋቸው ተመጣጣኝ ነው:: አሁን ባሉበት ያላቸው ዋጋና ወደ ማኑፋክቸሪንግ ተገብቶ በብዛት ሲመረቱ በራሱ ያላቸው ዋጋ ልዩነት ያመጣል:: የፈጠራ ሥራዎቹ ግሪን ቴክኖሎጂ የሚባሉም ናቸው፤ ይህን ያሰኛቸው ዋና ምክንያትም የአካባቢን ብክለት የሚቀንሱ መሆናቸው ነው::

አቶ ተሾመ በፈጠራ ሥራ በትኩረት መሥራት ከጀመረ ሁለት ዓመታት ያህል ያስቆጠረ ቢሆንም፣ ሥራዎቹን ለመጀመሪያ ጊዜ በሳይንስ ሙዚየም በተዘጋጀው ዓለም አቀፍና የሀገር በቀል ቴክኖሎጂ አውደ ርዕይ አቅርቧል:: በግሉ በንግድ ሥራ ላይ ተሰማርቶ እየሠራ ቢሆንም፣ በትርፍ ጊዜው ደግሞ የፈጠራ ሥራዎችን ይሠራል:: በተጨማሪ በማታው መርሃ ግብር እየተማረ ያለው ኤሌክትሪካል እና ኮምፒዩተር ኢንጂነሪንግ ትምህርት የፈጠራ ሥራዎች ለመሥራት ረድቶታል:: በኤሌክትሪካልና ኮምፒዩተር ኢንጂነሪንግ ያገኘውን እውቀትም ከመካኒካል ጋር አያይዞ ከመጀመሪያ አንስቶ እስከ መጨረሻ ያለውን ሥራውን ለመሥራት አስችሎታል::

‹‹የፈጠራ ሥራዎቹን ከሁለት ነገሮች በስተቀር ከዲዛይን ጀምሮ ኤሌክትሪኩን መገጣጠምና እስከ ቅብ ድረስ ያሉትን ሁሉም ሥራዎች በእኛ ነው የሚሠሩት:: እነዚህን የተወሰኑ የተባሉትን ነገሮች በሀገር ውስጥ ለመሥራት ከባድ ስለሆኑ ከውጭ እናስመጣለን:: ሀብ ሞተር እና ኮንትሮለር ብቻ ከውጭ እናስመጣለን›› ሲል አብራርቷል::

‹‹የፈጠራ ሥራዎች ለመሥራት ለረጅም ጊዜ ብዙ ማሰብ፣ ማሰላሰልና ማቀድን ይጠይቃሉ›› ሲል አቶ ተሾመ ይገልጻል፤ የፈጠራ ሥራዎቹን በትርፍ ጊዜው እንደሚሰራቸው ጠቅሶ፣ ጊዜውን ሁሉንም ሥራ በማይጎዳ መልኩ ከፋፍሎ እንደሚጠቀም ይገልጻል:: ‹‹ ሁሉንም ሰዓቴን በአግባቡ ከፋፍዬ እጠቀማለሁ:: ስፖርት ከመሥራት ጀምሮ ልጆቼን ትምህርት ቤት ማድረስ፣ የቢሮ ሥራዬን መሥራት እና የማታ ትምህርቴን መከታተሌ እንዳለ ሆኖ የሚተርፉኝ ሽርፍራፊ ሰዓቶች ደግሞ የፈጠራ ሃሳብ ማሰላሰልና ዲዛይን ማድረግ ላይ አውላለሁ›› ይላል:: እንደ ዩቲዩብ ያሉ ሶሻል ሚዲያዎችን ያሉትን መጠቀሙ የምፈልጋቸው ዲዛይኖች ለመሥራትና እውቀት ለማግኘት እንደረዱትም ይናገራል::

አቶ ተሾመ እነዚህን ሦስት የፈጠራ ሥራዎች ሲሠራ ቅድሚያ የሰጠው ለሥራው እንጂ የባለቤትነት መብትን ለማስጠበቅ እምብዛም እንዳልሄደበት አመልክቷል:: አሁን የባለቤትነት መብት ለማግኘት የፈጠራ ሥራዎቹን አእምሯዊ ንብረት ጽህፈት ለመውሰድ በሂደት ላይ መሆኑን አስታውቋል::

የባለቤትነት መብቱን ካገኘ በኋላ ወደ ኢንዱስትሪ ደረጃ ለመግባት ይፈልጋል:: ለዚህ ደግሞ እንደ መሥሪያ ቦታ እና ካፒታል የመሳሰሉት ነገሮች የግድ ናቸው:: ከውጭ ለምናስመጣቸው እቃዎች ከታክስ ጋር የተያያዙ ነገሮች ላይ በተወሰነ መልኩም ቢሆን አስተያየት ቢደረግ ወደ ሥራ ገብቶ ማምረት እንደሚችል ተናግሯል::

በሀገሪቱ በርካታ የፈጠራ ሃሳብ ያላቸው ሰዎች እውቀቱም እንዳላቸው ገልጾ፣ የፈጠራ ሃሳቡን ወደ ተግባር ለመለወጥ ብዙ እንደማይቸገሩ አስታውቋል:: አብዛኛውን ጊዜ ችግር የሚሆንባቸው የግብዓት አቅርቦት ነው ሲል ጠቁሞ፣ በሀገሩ ውስጥ የሌሉ ተራ የሚባሉ ቁሶችን ከውጭ ለማስመጣት ችግር ሊገጥም እንደሚችል ያስረዳል::

በተለይ ወደ ፈጠራ ሥራ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚገቡ ሁሉ ተስፋ መቆረጥ እንደሌለባቸው ገልጾ፣ በአእምሮአቸው የሚያሰላስሉትን ሃሳብ አውጥተው ወደ ተግባር መቀየር እንዳለባቸው አስገንዝቧል:: ‹‹እኔ ለረጅም ዓመታት ብዙ የፈጠራ ሥራዎችን በሃሳቤ አውጥቼ አውርጄለሁ:: ተግባር ላይ እንዳላውል የሚይዙኝ ነገሮች ነበሩ›› ሲል አብራርቶ፣ የፈጠራ ሥራ ጀማሪዎች ምንም ይሁን ምንም ያሰቡትን ነገር ከውስጣቸው አውጥተው በተግባር ሊያውሉ እንደሚገባ አስገንዝቧል:: ‹‹ፈጠራ በተግባር ካልተደገፈ በሃሳብ ብቻ ከንቱ ነው፤ አየር ላይ ነው የሚቀረው:: እኔ ካገኘሁት ተሞክሮ የተገነዘብኩት ሃሳብ ተግባር ላይ ሲውል ሁሉንም ሰው መሳብ እንደሚችል ነው›› ሲል አመላክቷል ::

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ታኅሣሥ 1 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You