ነገርን ከስሩ፣ ውሃን ከጥሩ፣ እንዲሉ አበው፤ መወደዳችን፣ ሰላምና ይቅርታችን፣ ትብብርና ኅብረታችን፣ ፍቅርና ወንድማማችነታችን ሁሌም ውድ የሆኑ ኢትዮጵያዊ እሴቶቻችን ናቸው። ከእውነት የሆነ እውነት ነውና አይሸረሸርም፤ ከልብ የሆነም ስር ሰዷል እና አይነቀልም። እኛ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ብዙ ነገሮቻችን ከልብ ጋር ቁርኝት እንዳላቸው በንግግሮቻችን ሳይቀር ስንገልጽ እንሰማለን። ሲናገሩ – ከልቤ ነው፤ ሲያዳምጡ – ከልብ አድምጡ፤ ሲወዱ – ከልቤ ገባ፤ ሲጠሉ – ከልቤ ወጣ፤ ሲያዝኑ – ልቤን ሰበረው፤… ማለታችን የተለመደ ነውና።
ኢትዮጵያውያን፣ አገራቸውን ከልብ ይወዳሉ፤ በሃገራቸው ክብርና ሉዓላዊነት የመጣባቸውን ከልብ ይዋጋሉ፤ ስለ ሕልውናቸው የተገዳደራቸውን ከልብ ያወግዛሉ፣ ታግለውም አደብ ያስይዛሉ። በአንጻሩ በፍቅር የቀረባቸውን በልባዊ ፍቅር ይቀበላሉ፤ በችግራቸው ጊዜ የደረሰላቸውን ከልብ ያከብራሉ፤ የደገፋቸውን ከልባቸው ይደግፋሉ፤ በድሎ ለይቅርታ እጁን የዘረጋም ሲኖር ከአንገት ሳይሆን ከልብ ይቅር ማለትን ያውቃሉ።
ይሄን ድንበር አቋርጦ አገር የደፈረን ወራሪ ጠላት ሳይቀር ድባቅ በመቱ ማግስት ስለ ጥፋቱ የበለጠ ከመቅጣት ይልቅ ይቅርታቸውን ከልብ ሰጥተው ወዳጅነትን መሥርተው ሲኖሩ መታየታቸውም ለዚህ ነው። ይሄ ደግሞ በወንድማማቾች መካከል ሲሆን ደግሞ ወንድም ወንድሙን ሲበድል ይቅር ማለትም ኢትዮጵያዊ እሴትም፣ ሃይማኖታዊ ትዕዛዝም ጭምር እንደመሆኑ ስሜቱ ከፍ ይላል።
በዚህ የወንድማማችነት ውስጥ በሚፈጠር ይቅርታ እና በፍቅር መልክ መገለጥ ምክንያትም በዘመናት መካከል የሚፈጠሩ መቃቃሮች በይቅርታ ታልፈው ኢትዮጵያውያን በአንድ ቆመው ጠላትን ሲመክቱ ታይተዋል። ቂምና ቁርሾን ሽረው ችግር በገጠማቸው ጊዜ አንዳቸው ለአንዳቸው አለኝታና መከታ መሆናቸውን አረጋግጠዋል። ስለ ሃገራቸው ሉዓላዊነት፣ ስለ ራሳቸው ክብርና ደህንነት ሲሉም ከውስጥም ከውጪም የሚነሱ የጥፋት ቡድኖችን አደብ ለማስያዝ በጋራ ተዋድቀው፤ በጋራ አገር አጽንተው በትውልድ ቅብብሎሽ ለዚህ በቅተዋል።
ዓለማችን የሁለት ተቃርኖዎች ስሪት እንደመሆኗ፤ በሰው ልጆች የኑሮ ሂደትም እነዚህ ሁለት ተቃርኖዎች መፈራረቃቸው አይቀሬ ነው። ይሁን እንጂ ጨለማ በብርሃን እንደሚሸነፍ ሁሉ፤ ጥላቻ በፍቅር፣ ፀብም በይቅርታ መሸነፋቸው አይቀሬ ነው። ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ላለፉት ሦስት ዓመታት የገጠማቸውም ይሄው ነው።
አለመግባባት ወደ ግጭት፣ ግጭት ወደ ጦርነት አድጎ አያሌ ዜጎች አካላቸውን፣ ሕይወታቸውን፣ ሃብት ንብረታቸውን አጥተዋል። ሃገርም በዚሁ ጦርነት አንድም ውድ የሆኑ ዜጎቿን፣ሁለተኛም ኢኮኖሚዋን ተነጥቃለች። በጥቅሉ በወንድማማቾች መካከል የተደረገው ጦርነት ከፍ ያለ ማኅበራዊ፣ ሥነልቦናዊ እና ኢኮኖሚያዊ ብሎም ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ ጠባሳዎችን አሳርፎ አልፏል።
ይሄ ክፉ ገጽ ታዲያ ጠይሞ አልቀረም፤ ኢትዮጵያውያን ለሃገራቸው ሉዓላዊነት እና ለራሳቸውም ደህንነት ሲሉ ከልባቸው ተዋግተው ሕልውናቸውን እንዳስቀጠሉ ሁሉ፤ አገር የሚጸናው፣ ደህንነትም በዘላቂነት የሚረጋገጠው በጦርነት ሳይሆን ፍቅር ውስጥ በሚገኝ ሰላም መሆኑን ያምናሉና፤ ስለ ሰላም ዘምረው ሰላማቸውን ለማጽናት ቁጭ ብለው መከሩ።
በምክራቸውም መሠረት የጦር ነፍጣቸውን ጥለው የሰላም ርግብን አነሱ። እናም ኢትዮጵያውያን ከግጭታቸው ማግስት በይቅርታ ልብ ተገናኝተው በፍቅር ተቃቀፉ። ይሄ ይቅርታና የሰላም መንገድ ጠላቶችን ቢያበሳጭም፤ ወዳጆችን አስፈንድቋል፤ ኢትዮጵያውያን ዳግም በኅብር ደምቀው እንዲገለጡ አድርጓል።
ኢትዮጵያም ስለ ሰላሟ የተጉላትን በአደባባይ አመሰገነች፤ ለሌሎች አርዓያነታቸውን ገለጠች። ከዚህም በላይ ልጆቿ ይሄን የሰላም ጅምር፣ የይቅርታ መንገድ፣ የፍቅር መድረክ ከፍ ወዳለ ምዕራፍ እንዲያሸጋግሩ የአደራ ቃሏን አስተላለፈች። በጠቅላይ ሚኒስትሯ አማካኝነትም፤ ለሕልውናዬ ስትሉ ከልባችሁ ተዋግታችሁ ከፍ እንዳደረጋችሁኝ ሁሉ፤ ቀጣይ የሚኖራችሁ አብሮነት ያማረና የሰመረ እንዲሆን ይቅርታችሁም ከልብ ይሁን አለች።
የይቅርታው መንገድ ሰምሮ በፍቅር ሊጸና፤ የሰላሙ ሰገነትም ጸንቶ ሊገለጥ ይገባዋልና የይቅርታችሁ ቦታ ከልባችሁ ይሁን፤ በሰላም ትግላችሁም ከፍ ያለው ጀንግነታችሁ ይገለጥበት፤ ወንድማማችነታችሁ እንደትናንቱ ደምቆ ይታይልኝ አለች። በመሆኑም የእናት ቃል ሊከበር፤ የወንድማማቾችም ይቅርታ ከልብ ሰርጾ የታለመውን ሰላም ያጸና ዘንድ የተገባ ነው። ስለሆነም ሁሉም ዜጋ ይቅርታውን ከልቡ፤ ሰላሙንም ከደጁ ሊያደርግ ያስፈልጋል!
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 17 ቀን 2015 ዓ.ም