ከአካል ጉዳተኞች መብት ጋር በተያያዘ በርካታ ጉዳዮች ይነሳሉ፡፡ ወደ ሁሉም አዕምሮ የሚመጡ ሃሳቦችም ቀላል አይደሉም፡፡ ከሁሉም ሃሳቦች ቀድሞ ወደአዕምሮ የሚመጣው ግን የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ምቹነት ነው፡፡ ከነዚሁ ተቋማት መካከል በዋናነት የሚጠቀሰው ደግሞ ትምህርት ቤት ነው፡፡
አካል ጉዳተኝነት በተፈጥሮ ብቻ ሳይሆን ድንገት በሚደርስ አደጋ በሁሉም ሰው ላይ ሊከሰት ይችላል፡፡ በተለያየ ምክንያት የአካል ጉዳት የሚደርስባቸው ሰዎች ምቹ አገልግሎት የማግኘት መብት ቢኖራቸውም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በማደግ ላይ የሚገኙ አገራት ብዙ መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተለይም የትምህርት ተቋማት ከመጸዳጃ ቤት እስከ መማሪያ ክፍል ድረስ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ሁኔታዎች በመፍጠር ረገድ ብዙ ርቀት አልተጓዙም፡፡
ትምህርት ቤቶች ለአካል ጉዳተኞች ከሌሎች ተማሪዎች እኩል መስተናገድ እንዲችሉ ተደርገው መገንባት ያለባቸው ቢሆንም በገሃድ የሚታየው ሁኔታ ተቃራኒ ነው፡፡ አካል ጉዳት የራሱ የሆነ ግልጋሎትን ይፈልጋል፡፡ መሰረታዊ የሚባሉ ፍላጎቶችም አሉት፡፡ እናም በትምህርት ተቋማትም እነዚህ ነገሮች ካልተሟሉ የችግሩ ተጋላጭ የሆኑ ዜጎች በቀላሉ መማር አይችሉም፡፡ በዚህም አካል ጉዳተኞች ዛሬም ድረስ እየተጎዱ ይገኛሉ፡፡
ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽና አመቺ ትምህርት ቤቶች ባለመገንባታቸው ብዙዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ ለመሆን ተገደዋል፤ ለተደራራቢ ችግርም ተዳርገዋል፡፡ በትምህርት ቤቶች የመጸዳጃ ቤት ጉዳይ እንኳን ለአብነት ቢነሳ እጅግ ውስብስብ ችግሮች አሉበት፡፡ በአብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች ውስጥ መጸዳጃ ቤቶች አይደለም ለአካል ጉዳተኞች ሙሉ አካል ላላቸውም ምቹ አይደሉም፡፡
መፀዳጃ ቤቶች ከጽዳት አንስቶ ለአካል ጉዳተኞች ምቹና ደህንነታቸው የተጠበቀ አይደሉም፡፡ አንዳንድ አካል ጉዳተኞች ችግሩን ተቋቁመው ወደ መፀዳጃ ክፍሎች ውስጥ ገብተው ለመጠቀም ሲጣጣሩ የመፀዳጃ ክፍሎቹ ብልሹና አመቺ ባለመሆናቸው ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› እንዲሉ ተንሸራተው ወድቀው ለተጨማሪ የአካል ጉዳት ሲዳረጉ ይስተዋላል፡፡ በተለይ ለአይነ ስውራንና በተሽከርካሪ ወንበር እንዲሁም ክራንች ለሚጠቀሙ አካል ጉዳተኞች ሁኔታው የከፋ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ይህንን ጉዳይ በተመለከተ የተለያዩ ሕጎችን በአዋጅ ደረጃ አውጥታለች፡፡ ከዚህ ውስጥ አንዱ የሕንፃ ግንባታ ህግ ሲሆን ህጉ አዋጅ 624/2001 ተብሎ ይጠራል፡፡ ይህ አዋጅ በአንቀጽ 36 መሰረት ማንኛውም የሕዝብ መገልገያ ሕንፃዎች ሲገነቡ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ መሆን እንዳለባቸው ይደነግጋል፡፡
ውስጣቸው በተሽከርካሪ ወንበር ለመንቀሳቀስ ወይም ለመራመድ የሚያስችሉ ሆነው መገንባት እንደሚኖርባቸውም ይጠቅሳል፡፡ በህንፃ ደረጃ መውጣት ለማይችሉ አካል ጉዳተኞችም ለመንቀሳቀስና ወደሚፈልጉበት ቦታ ለመድረስ የሚያስችላቸው መወጣጫ ማካተት እንዳለበትም አዋጁ ያስቀምጣል፡፡ የመጸዳጃ ቤቶችም ቢሆኑ ለአካል ጉዳተኞች አመቺ በሆነ መልኩ መሰራት እንዳለባቸው ይጠቁማል፡፡
ሆኖም የሕንፃ ግንባታውን ዲዛይን ከሚያደርጉ ሰዎች ጀምሮ እስከ ሕንፃ ባለቤቶች ድረስ ህጉን ተግባራዊ ሲያደርጉ አይታዩም። የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላትም የማስፈጸም አቅማቸው ዝቅተኛ ሆኖ ይታያል፡፡ ይህ ደግሞ አካል ጉዳተኞችን ትልቅ ዋጋ እያስከፈላቸው ይገኛል፡፡ ተማሪ አካል ጉዳተኞችም በዚሁ ችግር ምክንያት በቤታቸው እንዲቀመጡ አድርጓቸዋል፡፡
ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተገናኘ የተለያዩ ጥናቶች በአለማቀፍ ደረጃ ተሰርተዋል፡፡ ለምሳሌ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስነ-ህዝብ ፈንድ እና የስነ-ህዝብ ካውንስል የተሰራ የአንድ ጥናት ሪፖርት እንዳስቀመጠው፤ የአካል ጉድለት ካለባቸው ሶስት ልጃገረዶች አንዷ በቤትና በማህበረሰብ ውስጥ ስልታዊ እና የኃይል ጥቃት ይደርስባታል፤ እንግልት ይገጥማታል። በትምህርትና በስራ ቅጥርም እንዲሁ ተጨማሪ የከፉ ችግሮች ያጋጥሟታል፡፡ ለዚህ ደግሞ መንስኤው በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ትምህርት ቤት አለመሄዳቸውና አለመማራቸው እንደሆነ ጥናቱ ያስቀምጣል፡፡
እ.ኤ.አ በ2002/2003 በስነ-ህዝብ ካውንስል የወጣት አዋቂዎች የዳሰሳ ጥናት መሰረት ደግሞ፤ የአካል ጉድለት ከሌለባቸው 48 በመቶ ልጃገረዶችና 55 በመቶ ወንድ ልጆች ጋር ሲነፃፀሩ በትምህርት ቤት ውስጥ የነበሩት የአካል ጉዳተኛ ልጃገረዶች 23 በመቶ ናቸው። ለዚህ ሁኔታ መፈጠር መንስኤው ደግሞ አመቺ የመጸዳጃ ቤት ማግኘት አለመቻል ነው ይላል ጥናቱ፡፡
እንደጥናቱ ከሆነ አካል ጉዳተኞች በትምህርት ቤት ውስጥ በሚደርስባቸው መንገላታት የተነሳ ወላጆች ሳይቀሩ ከትምህርት ቤት እንዲቀሩ ያስገድዷቸዋል፡፡ ልጆቻቸው ከቤት ከወጡ የተለያዩ የመብት ጥሰቶች እና እንግልት ይደርስባቸዋል ብለው ይጨነቃሉ፡፡ በተለይ ኢትዮጵያን ጨምሮ በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ያሉ ልጃገረዶች የሚቸገሩት በትምህርት ቤቶች ውስጥ በቂ ውሃ እና መፀዳጃ ቤት ባለመሟላቱ ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ ደግሞ ችግሩ ለአቅመ-ሔዋን በደረሱ ልጃገረዶች ላይ እንደሚያይል ነው ጥናቱ የሚያሳየው፡፡ አካል ጉዳተኞች ከትምህርት የመቅረታቸው ምስጢርም በዋናነት ከዚሁ ጋር ይያያዛል፡፡
በየትምህርት ቤትም ይኸው ችግር ጎልቶ ይታያል፡፡ በችግሩ ደግሞ ሴቶቹ እጅጉን ይሰቃያሉ፡፡ የአካል ጉዳተኛ ሴቶች ባህሉም ይዟቸው ተፈጥሮም ሆኖባቸው እንደሌሎች ሴቶች እንደልባቸው አይጠቀሙም፡፡ ባህሉ ሸሸግ፤ ሸፈን ብለው እንዲጠቀሙ ያደርጋቸዋል፡፡ ተፈጥሮ ደግሞ ከወር አበባ ጀምሮ በተደጋጋሚ ንፅህናዋን እንድትጠብቅ ያስገድዳታል፡፡ በዚህ ምክንያት መጸዳጃ ቤት በተለይ ለአካል ጉዳተኛ ሴቶች መሰረታዊና አስፈላጊ ጉዳይ ነው፡፡ ይሁንና የአብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች ይህንን ሲያሟሉ አይታይም፡፡ ከትምህርት ቤት ጋር ባይገናኝም የአካል ጉዳተኞችን የመጸዳጃ ቤት ችግር በስፋት ያሳያልና በአንድ ወቅት የሆነውን ታሪክ እናንሳ፡፡
አይነ ስውር ናት፡፡ በሆዷ ፅንስ አለ፡፡ የመውለጃ ቀኗ እየደረሰ ነው፡፡ ምጧ ከመጣ ለመውለድ ያሰበችው በደቡብ ክልል ጌዲኦ ዞን ዲላ ዙሪያ ወረዳ በሚገኘው ጩጩ ጤና ጣቢያ ውስጥ ነው፡፡ የተፈጥሮ ህግ ነውና ምጧ መጥቶ ለመውለድ ወደዚሁ ጤና ጣቢያ አመራች፡፡ ጤና ጣቢያ ስትደርስ ግን ሀኪሞች ወደ ማዋለጃ ክፍል ሳይሆን መፀዳጃ ቤት አስገቧት፡፡ እርሷ አታይምና ይህን አላስተዋለችም፡፡
ነገር ግን ደግሞ የመፀዳጃ ቤቱ ጠረን በብርቱ ፈትኗታል፡፡ ከምጡ አይብስምና ችላው እዛው ቆየች፡፡ ቦታው እንኳን ለአይነስውር ነብሰ ጡር ይቅርና ሙሉ አካል ላለውም ሰው ምቹ አልነበረም፡፡ አይነ ስውሯ ሴት ማዋለጃ ክፍል ገብታ ልጇን እስክትገላገል ድረስ ሁሉን ችላ በስቃይ በመፀዳጃ ቤቱ ውስጥ ቆይታለች፡፡ ጉዳዩ መገናኛ ብዙሃን ጆሮ ደርሶ ድብልቅልቁ ወጣ እንጂ ልክ እንደርሷ ጥቂት የማይባሉ አይነስውራን ነብሰ ጡር ሴቶች ተፈትነው እንደነበር መገመቱ አያዳግትም፡፡
ለዚች አይነ ስውር ነብሰ ጡር ሴት የደረሰላትና ከችግሯ ያወጣት ማንም ሰው የለም፡፡ ሁሉም ነገር ከሰው ጆሮ የደረሰው በፈተና ውስጥ ካለፈች በኋላ ነው፡፡ ለዚህም ነው የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ መታሰብ ያለበት ሕጉን ከማክበር ጀምሮ ነው የሚባለው፡፡ ምክንያቱም ሕግ ሲከበር መሰረት ይጣላል፤ ተገልጋዩም ፍላጎቱን እያሟላ ይሄዳል፡፡
ታዲያ ይህ ጉዳይ እንዴት ትኩረት ያግኝ ፤ እንዴትስ ወደ ስራ ይገባበት ከተባለ መልሱ ቀላል ነው፡፡ አካል ጉዳተኝነት ሁሉም ሰው ሊገጥመው የሚችል ችግር ነው፡፡ ስለዚህ እያንዳንዱ ኃላፊነት እንዳለበት አምኖ መሥራት ይጠበቅበታል፡፡ ከዚያ ባሻገር ደግሞ ሕጉን የሚተገብሩና ለአካል ጉዳተኞች ትኩረት ሰጥተው የሚሰሩ ተቋማትን ማጉላት ያስፈልጋል፡፡ ለሌሎች ተሞክሯቸውን የሚያካፍሉበትን እድል መፍጠርም ይገባል፡፡
በዚህ ረገድ ለሌሎች ምሳሌ ከሚሆኑ ትምህርት ቤቶች አንዱ ደጅ አዝማች ወንድይራድ አፀደ ሕፃናትና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው፡፡ ይህ ትምህርት ቤት በከተማ ግብርና፣ አረንጓዴ ልማት፣ የተቀናጀ ፅዳትና ውበት እንዲሁም የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት ባለው የመጸዳጃ ቤት አገልግሎቱ ንጽህና ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለም አቀፍ ሽልማት አግኝቷል፡፡
የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር አቶ ሰለሞን ክቤ እንደሚናገሩት፤ የትምህርት ጥራትን ከሚያረጋግጡ መሰረታዊ ነገሮች አንዱ የትምህርትቤት ምቹነት ነው፡፡ በዚህም ሁሉም ተማሪዎች መሰረታዊ ፍላጎታቸውን እንዲያሟሉ ከማድረግ አኳያ በትምህርት ቤቱ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ አንዱ ደግሞ የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ነው፡፡
‹‹ፍትሀዊነትም አንዱ የትምህርት ጥራት ፓኬጅ በመሆኑ በትምህርት ቤት ማሻሻያ ሥራችን አማካይ በሆነ ቦታ ላይ አካል ጉዳተኞች የመጸዳጃ ቤት አገልግሎት እንዲያገኙ የማስቻል ሥራ ተከናውኗል›› ሲሉ ርዕሰ መምህሩ ይናገራሉ፡፡ የመጸዳጃ ቤት አገልግሎት ተደራሽነትን በፍትሀዊነት ከማረጋገጥ አኳያም የልዩ ፍላጎት አገልግሎት ተጠቃሚ ናቸው ተብለው የተለዩት 483 ተጠቃሚ የሚያደርግ 64 ዘመናዊ መጸዳጃ ቤቶችን ማዘጋጀት ችሏል፡፡ መጸዳጃ ቤቱ የተሰራውም እንደ አካል ጉዳታቸው ሁኔታ እንዲጠቀሙ ለማድረግ በሚያስችል መልኩ ነው፡፡
ከዚህ ባሻገር ትምህርት ቤቱ የልዩ ፍላጎት አገልግሎት ተጠቃሚዎች ፊዚዮ ቴራፒ ማዕከል አለው፡፡ በዚህ ማዕከል ተማሪዎች በልዩ ሁኔታ በአካቶ ትምህርት እንዲደገፉ ይሆናል፡፡ ማእከሉ ባለሶስት ወለል 36 የመማሪያ ክፍሎች ያሉት ሲሆን፤ ሦስቱም ወለል ላይ ዘመናዊ መጸዳጃ ቤቶች ተሟልተውለታል፡፡ በተጨማሪም ሕንጻው ላይ ሲወጡ ሙሉ ራንፕ ስላለው የአካል ጉዳተኞች አይቸገሩም፡፡ መለስተኛ የሕክምና መስጪያ ማዕከላት፣ ማረፊያ ክፍሎች፣ ማሰልጠኛ ክፍሎች፣ የመማክርት ክፍሎች፣ የክላስተር ሴንተሮችና ሪሶርስ ሴንተር አሉት፡፡
እንደ ርእሰ መምህሩ ገለፃ፣ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ የመጸዳጃ ቤት አገልግሎት አለመኖሩ የመማር ማስተማር ሥራውን በብዙ መልኩ ፈትኖት ነበር፡፡ ተማሪዎቹ በስነልቦናም ሆነ በትምህርታቸው ጫና እንዲያርፍባቸው አድርጓቸዋል፡፡ ለዚህም ማሳያው በ2009 ዓ.ም በተሰራው የዳሰሳ ጥናት መሰረት መጠነ ማቋረጡ መጨመሩ ነው፡፡ በዚህም ከትምህርት ቤት እስከመቅረት የደረሱበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡
የመጠነ ማቋጥ መጨመር ምክንያትም ይኸው በአካባቢው ላይ ያሉ አካልጉዳተኛ ተማሪዎች ቁጥር መጨመርና ለእነርሱ የሚመጥን የመፀዳጃ ቤት አለመኖር ነበር፡፡ ሆኖመም ችግራቸው ከተፈታ ተማሪዎችን በፍላጎትም በእውቀትም ማገዝ እንደሚቻል መተማመን ላይ በመደረሱ ወደ ሥራ ተገብቶ ውጤቱ እጅግ አስደሳች ሆኗል፡፡ ለአብነትም የ2015 ዓ.ም ውጤታቸውን ሲታይ ካሉት 483 ተማሪዎች ውስጥ በክፍል ፈተና 50 እና ከዚያ በላይ ያመጡት 87 ነጥብ 8 በመቶ ናቸው፡፡
አገልግሎቱ የጀመረው ከዛሬ ስድስት ዓመት በፊት ቢሆንም ንጽህናው አሁን ጭምር የሚጠቀሙበት አይመስልም፡፡ ልክ እንደሆቴሎች ሁሉ በአማካይ በአንድ ሰዓት ልዩነት ይጸዳል፡፡ አካል ጉዳተኞችን ለመደገፍ ከስልጠና ባሻገር እንደ ተሸከርካሪ ወንበር አይነት መሳሪያዎችን በመስጠት ትምህርት ቤቱ ያግዛቸዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ከከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ ጀምሮ የተለያዩ አካላት እገዛን አድርገዋል፡፡
ከሁሉ በላይ ግን የትምህርት ቤቱ አመራሮች ሥራ የላቀ ድርሻ አለው፡፡ ትምህርት ቤቱም ፕሮጀክት ቀርጾ ድጋፍ ሊያደርጉለት የሚችሉ አካላትን ከመጠየቅ ወደኋላ አይልም፡፡ ስለዚህም ሌሎች ትምህርት ቤቶችም ከእኛ ቢዎስዱ የሚሉት አጋዥ አካላትን ማፈላለግና በእገዛቸው ምን ምን ነገሮች እንደተሰሩ ማሳየት ነው፡፡ በተጨማሪም የራሳቸውን ክፍት ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ በተመሳሳይ እነርሱ የተሻሉ ከሆኑ ለሌሎች መድረስ መቻል አለባቸው ሲሉ ርእሰ መምህሩ መልዕክታቸውን ያስተላልፋሉ፡፡
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 16 ቀን 2015 ዓ.ም