
በትምህርት ሂደት ውስጥ የሚጠቀሱ ሦስት ደረጃዎች አሉ። ዕውቀት፣ ክህሎት እና አስተዋይነት(attitude)። ሦስተኛውን ደረጃ(attitude) በትክክል ሊገልጸው የሚችል የአማርኛ አቻ ቸገረኝ፤ ብዙም ሲባልበትም አንሰማም። ጥቅል ትርጉሙ ግን ከዕውቀት(knowledge) እና ክህሎት(Skill) በኋላ የሚገኝ አስተዋይነት፣ ሥልጡንነት፣ ብልህነት፣ አርቆ አሳቢነት፣ በአጠቃላይ የሰውን ልጅ የሥልጣኔ ደረጃ የሚመጥን አስተሳሰብ መገንባት ማለት ነው።
ዕውቀት ስለአንድ ነገር ማወቅ ነው፤ ክህሎት ደግሞ ባወቅነው መሰረት አንድን ነገር እንዴት እንደሚሰራ(ቴክኒካል ነገሩን) መተግበር መቻል ነው። አስተሳሰብ(attitude) ግን ከዚህ ሁሉ በላይ ነው። ሦስቱን ደረጃዎች ለመግለጽ፤ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያለሁ አንድ የስነ ዜጋና ስነ ምግባር መምህር የሰጠንን ምሳሌ ልጠቀም።
ደን ለሰው ልጅ የሚሰጠውን ጥቅም(አፈር እንዳይሸረሸር ማድረግ፣ ንፁህ አየር እንድንተነፍስ ማድረግ፣ ለዝናብ መፈጠር….) ማወቅ ዕውቀት ነው። ችግኝ ማፍላትና መትከል ደግሞ ክህሎት ነው። ደን እንዳይጨፈጨፍ ግንዛቤ መስጠት፣ ዛፎችን ልክ እንደ ሰው ሕይወት ማየት… የመሳሰሉት ደግሞ አስተሳሰብ(attitude) ናቸው።
በሦስቱ ደረጃዎች መሰረት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለብን ችግር የአስተሳሰብ ነው። በጭንቅላት የመሰልጠን ችግር አለብን። በተለምዶ ግን ‹‹አለማወቅ›› እየተባለ ይገለጻል። ያለማወቅ ችግር አይደለም ያለብን፤ የመሰልጠን ነው። በነገራችን ላይ ሥልጣኔ በቁስ አካል ብቻ አይደለም፤ በአስተሳሰብ መሰልጠን ነው።
ሥልጣኔ ሲባል ለብዙዎች ትዝ የሚለው ዘመናዊ ዕቃዎችን መጠቀም፣ የቴክኖሎጂ መተግበሪያዎችን መጠቀም እና እንደ አገር ደግሞ የፎቆችና አስፋልቶች መብዛት ነው። አዎ! እነዚህ የሥልጣኔ መለያዎች ናቸው፤ ዳሩ ግን በአስተሳሰብ ካልተሰለጠነ በአብረቅራቂው ሕንጻ ሥር ባለ ቆሻሻ ምክንያት አፍንጫ ተይዞ ነው የሚታለፍ። በረቀቀው ቴክኖሎጂ የብልፅግና ቃላት ነው ስንለዋወጥበት የምንውል።
ሥልጣኔን የገጠር ሰዎች የሚጠቀሙት አንድ ቃል የሚገልጸው ይመስለኛል። ‹‹እገሌ እኮ ሥልጡን ነው›› ይላሉ። ይህን የሚሉት በቁስ አካላዊ ሁኔታው አይደለም፤ በአስተሳሰቡና አመለካከቱ ነው። ለምሳሌ፤ ሰው የማይሳደብ፣ ትህትና ያለው፣ ረጋ ብሎ የሚያዳምጥ፣ ሰው የሚጎዱ ነገሮችን የማያደርግ ሰው ‹‹ሥልጡን›› ይሉታል። እንዲያውም ‹‹ሥልጣኔ›› የሚለውን ቃል በሕብረተሰብ ትምህርት ከማወቄ በፊት ‹‹ሥልጡን›› የሚለውን ቃል ነበር የማውቀው። ስለዚህ ሥልጣኔ ማለት ሥልጡን ዜጋ መፍጠር ነው።
አገራችን አሁን ያለችበት የጦርነትም ሆነ የድህነት ጣጣዎች የተፈጠሩት በአስተሳሰብ ባለመሰልጠናችን ነው። በ19ኛው ክፍለ ዘመን በተፈጠሩ ክስተቶች ዛሬ ላይ የምንጣላው በአስተሳሰብ መጥቆ መሄድ ስላልቻልን ነው። ከሠለጠኑ አገራት መማር ስላልቻልን ነው። የአውሮፓ አገራት የሥልጣኔ ምሳሌ የሚደረጉት በቁስ አካል ብቻ አይደለም፤ በአስተሳሰባቸው ነው። ከመቶ ምናምን ዘመናት በፊት በተፈጠሩ ነገሮች ስለማይጣሉ ነው። ዛሬ ላይ ሰላማዊ ኑሮ የሚኖሩ በአስተሳሰባቸው ሰልጥነው እንጂ የእርስበርስ ጦርነትን ለዓለም ያስተማሩት እኮ እነርሱ ነበሩ!
እውቀት ብቻውን ሥልጣኔ አያመጣም። ስለዓለም ጓዳና ጎድጓዳ ማወቅ ብቻውን አገር አያሳድግም። የነጭ ሳይንቲስቶችን ንድፈ ሀሳብ መሸምደድ ብቻውን ሥልጣኔ አይደለም። የግሪክ ፈላስፎችን ጥቅስ መደርደር የምሁርነት መገለጫ አይሆንም። ለሥልጡንነት ዋናው ነገር በአስተሳሰብ መሰልጠን ነው።
ከዚህ በፊት የገለጽኩት አንድ ትዝብት ነበር። በትልልቅ መስሪያ ቤቶች ውስጥ ያሉ ሠራተኞች የተማሩ የሚባሉ ናቸው። በዚህ ዘመን ዝቅተኛው የትምህርት ደረጃ ከ12ኛ ክፍል በታች አይሆንም፤ አብዛኛው የመጀመሪያ ዲግሪ እና ከዚያ በላይ ነው። ስለግል እና አካባቢ ንጽህና የምንማረው ከሙአለ ሕጻናት ጀምሮ ነው። አንዳንዶቹ ሠራተኞች ደግሞ መምህር ሆነው ያገለገሉ ናቸው።
ይህ ሁሉ ሆኖ ግን በመጸዳጃ ቤቶች ውስጥ የምናየው ነገር ‹‹አጃኢብ!›› የሚያሰኝ ነው። ማስተዋል የሚባል ነገር የለም። መቼም ምግብ የሚበላው በአንድ እጅ ነው አይደል? መጸዳጃ ቤት ውስጥ ያለውን መታጠቢያ ምግብ ባልበሉበት እጅ መክፈት ያን ያህል ውስብስብ ነገር ነው? ወጥ በነካ እጅ ሰዎች የሚገለገሉበትን ነገር መንካት አይከብድም? ተሳስተው ከነኩትስ በዚያ ልክ ወጥ በወጥ ሆኖ ሲያዩት ማጠብ እንዴት ትዝ አይልም?
ምግብ ቤት ውስጥ የተሰጣቸውን ብርጭቆ ወጥ በነካው እጃቸው የሚጨብጡ አሉ። የብርጭቆው ወገብ ወጥ በወጥ ይሆናል። ምናለ በዚያኛው(ወጥ ባልነካው) እጃቸው ቢይዙት? እነዚህን ጥቃቅን ነገሮች እንደ ማሳያ ያመጣሁት አገራዊ ችግር የሚያመጡ ሆኖ አይደለም፤ ግን ምን ያህል ከሥልጣኔ የተጣላን መሆናችንን ያሳያል። ሰዎች የሚገለገሉበትን ነገር ማበለሻሸት እንኳን የተማረ ከሚባል ከማንኛውም የሰው ልጅ ፍጡር አይጠበቅም።
እነዚህ ጥቃቅን ግዴለሽነቶቻችን እያደጉ ሄደው ነው በትልልቅ ጉዳዮችም ችግር የሚፈጠረው። ግዴለሽነት፣ የራስን ጥቅም ብቻ ማስቀደም፣ ነገ ምን ሊያስከትል እንደሚችል አለማስተዋል አገርን ወደኋላ ይጎትታሉ። ከላይ የጠቀስኳቸው ትዝብቶች ሁሉ በዕውቀት ችግር የሚከሰቱ አይደሉም። አሳቢ ባለመሆን የሚከሰቱ ናቸው። ቆሻሻ መንገድ ላይ የሚጥል ሰው ‹‹ጉንፋን ከምን ይመጣል?›› ቢባል ምናልባትም የሳይንስ ማጣቀሻዎችን እየዘረዘረ ሊተነትን ይችላል። የበሽታዎችን መንስኤና መከላከያ በንድፈ ሀሳብ ደረጃ ያውቃል፤ ዳሩ ግን ማሰብ የሚባል ነገር የለም።
የሰለጠኑት አገሮች አንዱ የሥልጣኔ መለያ ህግ አክባሪነት ነው። ሰዎችን የሚጎዳ ነገር አይደረግም። ሰዎች ያለመረበሽ መብት አላቸው። መቼ ነው ይህን ሥልጣኔ የምንገነባ? ሥልጣኔ አመለካከት ነው። ሥልጡን ዜጋ መፍጠር ነው። የምናየው ግን ተደራራቢ የትምህርት ማዕረግ ይዘው ምስኪን ለፍቶ አዳሪ አስተናጋጅ ሲሳደቡ ነው። ለምሳሌ ያዘዙት ምግብ ላይ ጨው ቢበዛ አስተናጋጇን ነው አበሻቅጠው የሚሳደቡ። እንዲያውም ባለቤቱ ሲመጣ ተቅለስልሰውና ተለሳልሰው ‹‹ትንሽ ጨው በዝቶበታል!›› ሊሉ ይችላሉ፤ ወይም ‹‹በጣም ጥሩ ነው!›› ሊሉ ይችላሉ። ምስኪኗ ሰራተኛ ላይ ግን ይደነፋሉ። ይሄ በአስተሳሰብ አለመሰልጠን ነው።
አገልግሎት ለማግኘት የሚደረግ ሰልፍ ልብ ብላችሁ ታውቃላችሁ? ሰልፍ ያስፈለገው በሰዎች አመጣጥ ቅደም ተከተል በሥነ ሥርዓት ለመገልገል ነው፤ ዳሩ ግን አገልግሎቱ ሲጀመር ለረጅም ሰዓት የቆየው ሰልፍ ድብልቅልቁ ይወጣል። በሥነ ሥርዓት መሆኑ ቆርቶ በጉልበት ይሆናል። የሥልጣኔ ዘመን መሆኑ ቀርቶ የጥንቱን የአደን ዘመን ይመስላል። የአስተሳሰብ ለውጥ ካልመጣ የቱንም ያህል የትምህርት ደረጃ ቢደራረብ ከኋላቀርነት አያድንም፤ የሰለጠነ ዜጋ አይፈጥርም። ስለዚህ ዕውቀታችን ለመሰልጠን ይሁን!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 16 ቀን 2015 ዓ.ም