የኮንትሮባንድ ንግድን ለመቆጣጠር የተለያዩ ስልቶች ተነድፈው እየተሰራ መሆኑን ተከትሎ ብዙ ቢሊዮን ብር የሚያወጡ የኮንትሮባንድ ምርቶችን መያዝ እየተቻለ ነው። የጉምሩክ ኮሚሽን በ2015 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ብቻ 52 ቢሊዮን ብር የሚያወጡ የኮንትሮባንድ ሸቀጦችን መያዝ የቻለበት ሁኔታም ይህንኑ ያመለክታል። ይህ የኮንትሮባንድ ሸቀጥ ወደ ሀገር ውስጥ ገብቶ እንዲሁም ከሀገር ወጥቶ ቢሆን ሀገርና ሕዝብ በእጅጉ ይጎዱ ነበር።
ኮሚሽኑ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴውን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ አሰራሮችን በመቀየስ ውጤታማ ተግባር እያከናወነ መሆኑን ይገልፃል፤ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴውም በዚያው ልክ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን እየጠቆመ ይገኛል። በስድስት ወሩ የታየውን የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴን አስደንጋጭ ብሎታል። 52 ቢሊዮን ብር የሚደርስ የኮንትሮባንድ ሸቀጥ መያዝ መቻሉ ትልቅ ነገር ሆኖ ፣ ይህን ያህል የኮንትሮባንድ ሸቀጥ በህገወጦች እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ሲታሰብ ችግሩ በራሱ ምን ያህል አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን በሚገባ ይጠቁማል።
የኮንትሮባንድ ንግድ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ስለመድረሱ የጉምሩክ ኮሚሽን የተለያዩ ቅርንጫፍ መስሪያ ቤቶችን ዋቢ ያደረጉ የመገናኛ ብዙሃን ዘገባዎችም ያመለክታሉ። በየጊዜው የሚወጡት እነዚህ ዘገባዎች በብዙ ሚሊዮን ብር የሚገመቱ የኮንትሮባንድ ሸቀጦች እየተያዙ ስለመሆናቸው ያሳያሉ። የጉምሩክ ኮሚሽን እንዲሁም የገቢዎች ሚኒስቴር በሚያካሂዷቸው መድረኮች ላይም የችግሩ አሳሳቢነት እየተጠቀሰ ይገኛል።
ጉዳዩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ተጠቁሟል። በቅርቡ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት እንደተናገሩት፤ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ በወጪ ንግዱ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያሳረፈ ይገኛል። የዘንድሮው የወጪ ንግድ አፈጻጸም ከአምናው ጋር ሲነጻጸር ትንሽ ዝቅ ብሏል። ዘንድሮ ለውጭ ገበያ ከቀረበው ወርቅና ጫት የተገኘው ገቢም ከአምናው ጋር ሲነጻጸር በጣም ዝቅ ብሏል።
አሶሳ ላይ ባለፈው ዓመት ወደ ማእከላዊ ገበያ 20 ኩንታል ወርቅ ቀርቦ የነበረ ሲሆን ዘንድሮ ግን ሶስት ኩንታል ነው የቀረበው። ይህ ማለት አብዛኛው በህገ ወጥ መንገድ ሄዷል ማለት ነው፤ ወርቅ እያመረትን ወደ ማዕከላዊ ገበያ ከማምጣት ይልቅ በአሻጥርና ኮንትሮባንድ ወደ ጎረቤት ሀገሮች በስፋት ይሄዳል። ታንታለም ጉጂ ይመረታል፤ ይሁንና ኢትዮጵያ ኤክስፖርት ከምታደርገው በላይ የማያመርቱት ጎረቤት ሀገሮች ኤክስፖርት ያደርጋሉ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለችግሩ አሳሳቢነት አስገንዝበዋል።
ይህንን በኮንትሮባንድ እንቅስቃሴው እያጋጠመ ያለውን ችግር ለመከላከል አብዛኛው ኃይላችን አሁን ሀብት ባለባቸውና ሽፍታ በበዛባቸው አካባቢዎች እንዲሰፍር ተደርጓል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር ፣ የፌዴራል ፖሊስ ቀዳሚ ተግባር ኮንትሮባንድን መዋጋት በኮንትሮባንድ የሚመዘበረውን የኢትዮጵያን ሀብት መከላከል ይሆናል ሲሉ ማስታወቃቸው ይታወሳል።
የጉምሩክ ኮሚሽን የኮንትሮባንድ ንግዱን ለመቆጣጠር የተለያዩ ስልቶችን ነድፎ እያከናወነ ያለው ተግባርና ይህን ተከትሎም እያስገኘ ያለው ለውጥ በአርአያነት የሚጠቀስ ነው። ይሁንና ተቋሙም እንዳለው የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴውም ፈታኝ እየሆነ መጥቷል። ይህን ፈተና ለማለፍ የመከላከል አቅምን አጎልብቶ ከመገኘት በተጨማሪ የኅብረተሰቡን፣ የክልል አስተዳደሮችንና የጸጥታ ኃይሎችን ርብርብ ማጠናከርም ይገባል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኮንትሮባንድን የመቆጣጠር ተግባር የመከላከያ እና የፌዴራል ፖሊስ ቀዳሚ ተግባር ይሆናል ባሉት መሰረት እነዚህ ኃይሎች የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴውን መቆጣጠር ውስጥ መግባታቸው ኢኮኖሚውን እየተስፋፋ ከመጣው የኮንትሮባንድ ንግድ ለመጠበቅ ፋይዳው የጎላ ይሆናል።
የኮንትሮባንድ ተግባሩ እየተስፋፋ ከመጣ ጤናማነቱ ሁሌም አጠያያቂ የሆነው የሀገሪቱ የንግድ እንቅስቃሴ ይበልጥ ታማሚ እንዲሆን ያደርጋል። ሀገርና ሕዝብም ለዋጋ ንረት፣ የምርት ጥራት ጉድለት እንዲስፋፋ፣ ህጋዊ ነጋዴዎች ቀስበቀስ ከገበያ እንዲወጡ በማድረግ በአጠቃላይ የንግድ ስራው ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳርፋል። ይህ ሁኔታ በንግዱ ማኅበረሰብ እና በአጠቃላይ በሸማቾች ላይ ከሚያሳርፈው ችግር በተጨማሪ የሀገር ኢኮኖሚም ችግር ውስጥ እንዲገባ ያደርጋል።
ይህም ችግሩን ለመቆጣጠር ርብርብ ማጠናከር ላይ ማተኮርን የግድ ይላል። ኅብረተሰቡ፣ የክልል መስተዳድሮች፣ ሌሎች የኮንትሮባንድ መከላከል አካላት ኮንትሮባንድን የመከላከልና መቆጣጠር ስራቸውን ይበልጥ ማጠናከር በሚኖርባቸው ወቅት ላይ መሆናቸውን በመገንዘብ መስራት ይኖርባቸዋል። እነዚህ አካላት ኮንትሮባንዲስቶች ሊያቀርቧቸው በሚችሉ መደለያዎች ሳይበለጡ እንዲሰሩ በሚያስችሏቸው የስነ ምግባር መርሆች ላይ አተኩሮ መስራት ያስፈልጋል።
ከመረጃዎች መረዳት እንደሚቻለው በኮንትሮባንድ ተግባሩ እየተንቀሳቀሰ ያለው ሀብት ከፍተኛ ነው። ይህ ሀብት በህገወጥ መንገድ የተገኘ ነው። ኮንትሮባንዲስቶች ይህን ሀብት ለመጠበቅ የማይከፍሉት ዋጋ እንደማይኖር በመገንዘብ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴውን ለመቆጣጠር የተቀናጀ ስራ መስራት ያስፈልጋል።
ለዚህም የሕዝቡን ፣ በየደረጃው ያለውን የመንግስት የአስተዳደር እርከን፣ የጸጥታና የደህንነት ኃይሎችን አቅም በአግባቡ መጠቀም ተገቢ ነው። መንግስት የሀገር መከላከያንና የፌዴራል ፖሊስን ለዚህ ተግባር ለማሰማራት የያዘው ቁርጠኛ አቋምም ተገቢም ወቅታዊም ነው። ይህ ኢኮኖሚውን ከኮንትሮባንዲስቶች ሊታደግ የሚችል ተግባር ውጤታማ እንዲሆንም የሕዝቡና የክልል አስተዳደሮች የቅርብ ድጋፍ ወሳኝ መሆኑም ሊታወቅ ይገባል!
አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 16 ቀን 2015 ዓ.ም