የዓለም አትሌቲክስ በቅርቡ የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮናን 40ኛ ዓመት እንደሚያከብር ይታወቃል። ይህንን ተከትሎም ካለፉት ቻምፒዮናዎች እጅግ አስደናቂ የነበሩ ክስተቶችን በመምረጥ አትሌቶችን አወዳድሮ የመሸለም መርሃ ግብር አዘጋጅቷል። በምርጫውም አምስት ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ተካተዋል፤ እነርሱም ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ፣ ምክትል ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ፣ ገዛኸኝ አበራ፣ ጥሩነሽ ዲባባ እና ሁለት ጊዜ የታጨው ቀነኒሳ በቀለ ናቸው።
የአትሌቶች ሀገር ለሆነችው ኢትዮጵያ በዚህ ምርጫ ውስጥ አትሌቶቿ መካተታቸው አግባብ ቢሆንም፤ ይህ ምርጫ ስፖርቱ እየተጓዘ ያለበትን መንገድ አንዳች ክፍተት መኖሩን የሚጠቁም ነው። እጅግ በርካታ አትሌቶች ያሏት ኢትዮጵያ በተለያዩ ውድድሮች ላይ አሁንም ባንዲራዋን በከፍታ ላይ የሚያውለበልቡላት ጀግኖች አላጣችም። ይሁንና ለምርጫው የቀረቡትን እጩዎች መነሻ በማድረግ በዚህ ወቅት በሀገሪቷ ምርጥ እንጂ እንደ ቀድሞዎቹ ዘመን ተሻጋሪ ተደጋጋሚ ድሎችን ለበርካታ ዓመታ
ወርቃማው የአትሌቲክስ ትውልድ አካል የሆኑት ብርቅዬ አትሌቶች በሚሳተፉባቸው የዓለም ቻምፒዮናዎች ተፎካካሪ እና አሸናፊ ከመሆን በዘለለ፤ የሚያሳዩት አስደናቂ ብቃት፣ ከሌሎች ተወዳዳሪዎች አንጻር ለውድድሩ ያላቸው የሞራል ከፍታና ጽናት፣ ት ማስመዝገብ የቻሉ አትሌቶች እንዳልተተኩ አመላካች ሁኔታዎች መኖራቸውን መገንዘብ ይቻላል።
ተፎካካሪዎቻቸውን ለማለፍ የሚጠቀሙት ብልሃት፣ የሚገጥሟቸውን ችግሮች ተቋቁመው በድጋሚ የሚቀርቡበት ሁኔታ፣… የስፖርት ቤተሰቡ የትዝታ ማህደር የማይደበዝዝ ነው። የዓለም ህዝብ በምርጫው የተካተቱን አትሌቶች ኢትዮጵያ ከሚለው ስም እኩል ሲያነሳቸው መኖሩም ለዚሁ ነው። አሁን ላይ በዚህ ብቃት የሚገኙ አትሌቶች መኖራቸውን ለማረጋገጥ ቁጥራዊ መረጃዎችን መመልከት ብቻውን በቂ ነው። በእርግጥ በሚካፈሉባቸው ውድድሮች ላይ የተመረጡ ወይም የተሻሉ ሆነው የሚገኙ በርካታ አትሌቶች አሉ። ነገር ግን በልዩነት በወጥ አቋማቸው ተለይተው የሚነሱና ድንቅ የሚለው ስያሜም የሚገባቸው አትሌቶች መኖራቸው አጠራጣሪ ይሆናል።
የዓለም አትሌቲክስ በሁለቱም ጾታ ባወጣቸው ዝርዝር መሰረት በምርጫው ውስጥ የገቡት ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች እአአ ከ1999 በስፔኗ ሴቪሌ አትሌቲክስ ቻምፒዮና እስከ በርሊን (2009) የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ድረስ የተካፈሉ ብቻ ናቸው። እነዚህ አትሌቶች በወርቃማው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ዘመን የተፈጠሩት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ፣ ምክትል ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ እና ገዛኸኝ አበራ ድረስ ያሉት ሲሆኑ፤ በእነርሱ እግር ከተተኩት አትሌቶች ደግሞ ቀነኒሳ በቀለ እና ጥሩነሽ ዲባባ ለምርጫ ቀርበዋል። እነርሱን የተኩት አትሌቶችስ ለእጩነት ብቁ ያልሆኑት በምን ምክንያት ሊሆን ይችላል? ከሴቪሌ እስከ በርሊን ስድስት ቻምፒዮናዎች ተካሂደዋል፤ ከዚያ በኋላም ከዴጉ እስከ ኦሪጎን በተመሳሳይ ስድስት ቻምፒዮናዎች ተደርገዋል ታዲያ እንዴት አንድም አትሌት አስደናቂ አቋም አልነበረውም?
ለዚህ ጥያቄ የእጩነት መስፈርትን ጨምሮ በብዙ መንገድ መልስ መስጠት ይቻል ይሆናል፤ ነገር ግን የተሻለ የሚሆነው ክፍተቱ ስለመኖሩ አምኖ ምክንያቱን መመርመር ነው። በእርግጥ በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ የስፖርት ባለሙያዎች ይህንን ጉዳይ አስቀድመው በማጤን ምክንያቱንና መፍትሄውን ለማመላከት ሞክረዋል። አሁንም ይኸው ሁኔታ እንዳለ በመሆኑ እንደቀድሞው ድንቅ አትሌቶች እየተመናመኑ ያሉት በአቋም መዋዠቅ ወይም ወጥ የሆነ ብቃት ስለሌላቸው እንደሆነ ማንሳት ይቻላል። በዚህ ወቅት በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ሊጠሩ የሚችሉና የተሻሉ ናቸው የሚባሉ አትሌቶች ተሳትፎና ውጤት በመገምገምም ይህንኑ ማረጋገጥ ይቻላል።
ለአብነት ያህል አንጋፋው አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ በ6 ዓለም ቻምፒዮናዎች ሲሳተፍ፤ አንድ ጊዜ ብቻ በተደራቢነት 5ሺ ሜትርን ከመሮጡ በቀር በ10ሺ ሜትር ነበር የሚካፈለው። በዚህም 4የወርቅ፣ 1የብር እና 1ነሃስ ሜዳሊያዎችን አስቆጥሯል። የዓለም አትሌቲክስም በዚህ ርቀት ተደጋጋሚ ቻምፒዮና በመሆን ኃይሌን የሚስተካከል አትሌት ባለማግኘቱ እአአ የ1990ዎቹ ድንቅ አትሌት ሲል ሊሰይመው ችሏል።
ድንቅ የተሰኙት እነዚህ አትሌቶች በሚሮጡበት ርቀት የራሳቸው መለያ እስኪመስል በርካታ ጀብዱዎችን ፈጽመው እና ሌሎች ሊያደርጉት ቀርቶ ሊያስቡት የማይቻላቸውን ክብረወሰኖች ሰባብረው ነው። በዚህ ወቅት ያሉ አትሌቶች በአንጻሩ በአንድ ርቀት ጥቂት ሮጠው ወደ ሌላ ስለሚያማትሩ በእነሱ ልክ ሊነሱ አልቻሉም። እንደ አትሌቶች ሀገር ደግሞ ይህ ሁኔታ ያስቆጫል፤ እናም ይህን ምርጫ ጨምሮ በየዓመቱ በሚካሄዱ ምርጥ የዓመቱ አትሌቶች ምርጫ ላይ በእጩነት የሚቀርቡ አትሌቶችን ማጣት በእርግጥም አካሄድን መፈተሽ ተገቢ ስለመሆኑ አመላካች ነው።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 16 ቀን 2015 ዓ.ም