የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የ25 አፍሪካ ዋንጫ ሁለት ቀሪ የምድብ ጨዋታዎቹን ከታንዛኒያና ዲሞክራቲክ ኮንጎ ብሔራዊ ቡድኖች ጋር በቀናት ልዩነት ያካሂዳል፡፡ ዋልያዎቹ ባለፉት አራት የማጣሪያ ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ መሰብሰብ ቢችሉም ወደ 2025ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ለመመለስ ተስፋቸው ሙሉ በሙሉ አልተሟጠጠም፡፡ ከታንዛኒያና ከዲሞክራቲክ ኮንጎ ጋር የሚያደርጋቸው ሁለት ቀሪ የማጣሪያ ጨዋታዎች ውጤት የአፍሪካ ዋንጫ ተስፋቸውን የሚወስኑ ይሆናል፡፡ የዋልያዎቹ ወደ አፍሪካ ዋንጫ መመለስ ተስፋ በምድብ ማጣሪያው የሌሎች ሀገራት ውጤት ላይ የተንጠለጠለ ቢሆንም፤ ቀሪዎቹን ጨዋታዎች የግድ ማሸነፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከነዚህ ሁለት ጨዋታዎች ሙሉ ነጥብ ማግኘት ካልቻሉ የአፍሪካ ዋንጫ ተስፋቸው ያበቃል፡፡
ብሔራዊ ቡድኑ ለሚያደርጋቸው ሁለቱ የመጨረሻ ጨዋታዎች 10 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደሚደረግ ፌዴሬሽኑ ከትናንት በስቲያ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡ ብሔራዊ ቡድኑ የምድቡን አምስተኛ ጨዋታ ነገ ከታንዛኒያ እንዲሁም ስድስተኛና የመጨረሻ ጨዋታውን ከዲሞክራቲክ ኮንጎ ጋር ማክሰኞ ያከናውናል፡፡ ሁለቱም የምድቡ የመጨረሻ ጨዋታዎች በዲሞክራቲክ ኮንጎ ሜዳ የሚካሄዱ ሲሆን ወጪ ቆጣቢ በሆነ መልኩ ለማካሄድ እንደተወሰነ ተገልጿል፡፡
ከታንዛኒያ ጋር የሚደረገውን ጨዋታ ኢትዮጵያ በሜዳዋ የምታደርግ ቢሆንም፣ የካፍንና የፊፋን ደረጃ የሚያሟላ ሜዳ ስለሌላት እና የመጨረሻው የማጠሪያ ጨዋታ በኮንጎ ሜዳ በመሆኑ ሁለቱንም ጨዋታዎች እዛው ለማድረግ መወሰኑን ፌዴሬሽኑ አሳውቋል፡፡ ጨዋታዎቹን በአንድ ቦታ ለማካሄድም ከ9 እስከ 10 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደሚያደርግም ታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ባህሩ ጥላሁን፣ የብሔራዊ ቡድኑ ጊዜያዊ ዋና አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ቀሪ የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎችን እና የቻን ማጣሪያ ጨዋታዎችን እንደሚመሩ በፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውሳኔ መተላለፉን አስታውሰው፤ አምስተኛና ስድስተኛ የማጣርያ ጨዋታዎች በኮንጎ ኪንሻሳ እንደሚደረጉ ጠቁመዋል።
የካፍና የፊፋን ደረጃ ማሟላት የሚችል ስታድየም ባለመኖሩ ምክንያት፣ በሜዳ መካሄድ የሚኖርባቸው ጨዋታዎች ከሀገር ውጪ እየተካሄዱ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ይህም የሆነው በአንድ ጉዞ ሁለት ጨዋታዎችን ለማድረግና ወጪ ቆጣቢ የሆነ መንገድን ለመከተል ታስቦ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ በዚህም መሰረት ኢትዮጵያ ነገ ከታንዛኒያ ብሔራዊ ቡድን አስተናጋጅ ሆና አምስተኛና የሜዳዋን ጨዋታ ታከናውናለች፡፡
በአፍሪካ ዋንጫና ዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ብሔራዊ ቡድኑ በሜዳው ማድረግ የሚገባውን ጨዋታዎች ከሜዳው ውጪ እያደረገ በመሆኑ ፌዴሬሽኑ እንደ ተቋም ዋጋ እየከፈለ እንደሚገኝ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡ ቡድኑ የአንድ ጨዋታ ጉዞ ለማድረግ ከፍተኛ ገንዘብና ቁሳቁስን እንዲሁም ጨዋታን በሌላ ሀገር ከማስተናገድ ጋር ፈታኝ እንደሆነበት አቶ ባህሩ አስረድተዋል፡፡ በዚህም ለጨዋታና ጉዞዎች የሚወጡት ወጪዎችን ለመደጎም ታስቦ፣ የተለያዩ ማስታወቂያዎች ይሰራሉ፡፡ ከነዚህም መካከል የሜዳ ዳር ማስታወቂያዎች የሚጠቀሱ ሲሆን እነዚህም ማስታወቂያዎች ብዙ ከሆኑ ፌዴሬሽኑ የሚያገኘው ገቢ ከፍ ሊል እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ለዚህም ከእግር ኳስ ውርርድ ድርጅቶች ጋር አብረው እየሰሩ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ባህሩ፣ ባህልንና ማንነትን የሚፈታተኑ ነገሮችን እንደማይኖሩና ለፌዴሬሽኑ ገንዘቡ እጅጉን አስፈላጊ ስለሆነ አብሮ ለመስራት መወሰኑን አመላክተዋል፡፡
የታንዛኒያን ጨዋታ እዛው ጎረቤት ሀገራት ሜዳ ማድረግ ይቻል እንደነበር ጠቅሰው፤ ከኮንጎ ጋር መጨረሻ ጨዋታ በመኖሩ ሁለቱንም ጨዋታዎች በአንድ የአየር ትኬት ለመጠቀምና ወጪ ለመቀነስ ታስቦ እንደሆነም አስረድተዋል። በመሆኑም ሁለቱን ጨዋታዎች ለማድረግ ከ 9 እስከ 10 ሚሊዮን ብር ፌዴሬሽኑ እንደሚያወጣ ጠቁመዋል፡፡ በዚህም መሰረት ፌዴሬሽኑ ከፊፋ፣ ካፍና ከስፖንሰር በሚያገኛቸው ገቢዎች እየተንገዳገደ እስከ አሁን መጓዙን የሚጠቁሙት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ብሔራዊ ቡድኑ በገንዘብ የማይደገፍ ከሆነ በቀጣይ አዳጋች እንደሆነም አሳስበዋል፡፡ ከችግሩ መውጫ የሆነ እቅድ በፌዴሬሽኑ እየተዘጋጀ ሲሆን በቀጣይ የስፖርት ምሁራን፣ የቀድሞ ተጫዋቾች፣ አሰልጣኞችና መገናኛ ብዙኃን አካላት የሚሳተፉበት መድረክ እንደሚኖር ጠቁመዋል። በተጨማሪም የፌዴሬሽኑ ስትራቴጂክ እቅድ ክለሳ የ2029 የአፍሪካ ዋንጫን መሰረት ባደረገ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
ለብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኞች ረጃጅም ኮንትራትን ለመስጠትና ውጤታማ ብሔራዊ ቡድን ለመገንባት እቅድ መኖሩን እና የሚመለከታቸው አካላት እንዲደግፉ እቅድ ተነድፎ ጥያቄ መቅረቡን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል። ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር ይህንን በተመለከተ መድረኮች እንደሚኖሩም ገልጸዋል፡፡ ስለሆነም ብሔራዊ ቡድኑ ከመንግሥት የሚደገፍበት ሁኔታ ወደፊት ሊፈጠር እንደሚችል እምነታቸውን ተናግረዋል፡፡
ዋልያዎቹ ለጨዋታዎቹ ከጥቅምት 28 ጀምሮ ዝግጅታቸውን በአዲስ አበባ ስታድየም ሲያደርጉ የቆዩ ሲሆን፤ ትናንት ረፋድ 4፡00 ሰዓት ላይ 20 ተጫዋቾች የተካተቱበትን ልዑክ ይዘው ወደ ኮንጎ ኪንሻሳ አምርተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ካደረገቻቸው አራት ጨዋታዎች በሶስት ተሸንፋ በአንድ አቻ ስትለያይ በአንድ ነጥብ የምድቡን የመጨረሻ ደረጃ ይዛ ትገኛለች፡፡
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ህዳር 6/2017 ዓ.ም