ዘመን የመቀነስ ስሌት ነው፡፡ ከተሰጠን ላይ አንድ እያጎደለ ወደነገ የሚሰደን፡፡ በአዲስ ዘመን ስም የጣልነው ፍሪዳ፣ የጠመቅነው ጠላ ዋይ ዋያችን ነው፡፡ የጎዘጎዝነው ጉዝጓዝ፣ ያጨስነው ጠጅ ሳር መርዶ ነጋሪዎቻችን ናቸው።
ወደነገ ህይወት የለም..ካለም ከሞት የተረፈ ምናምንቴ ነው፡፡ ግን ከወደትናንት ይሻላል፡፡ የሚመጣው ለሁልጊዜ ካለፈው የተሻለ ነው፡፡ ልዩነቱ ከፊት ሞትና ተስፋ ያደፈጡ መሆናቸው ነው፡፡ ከኋላ እዬዬ ነው..ከጀርባ ባለቀለም ፈሮች ከውይብ ፈለግ ጋር፡፡
የአዲስ አመት ሰሞን ድባብ እንደላጪ ልጅ ቀልብ ነው፡፡ ምላጭ በማይፈሩ እና ብዕር በሚሰጉ ነፍሶች መሀል የሞከከ፡፡ የዘመን ጥባት እንደ እሰይና ዋይ ዋይ በሰርግና ሞት ያጌጠ የእልል እና የውይውይ ቀልብ ነው፡፡
እንኳን አደረሰን እፈራዋለው፡፡ ሞት የሚሉት እርኩስ በሰው ልሳን መልካም ምኞቱን የሚገልጽልኝ እንጂ ሌላም አይመስለኝ፡፡ ባለሁበት እንዳለሁ መቀጠል እንጂ ማንም የዘመን ጥባትን አስታክኮ ሞቴን እንዲነግረኝ አልፈቅድለትም፡፡ ወደነገ ጥጉ እስኪገኝ ሳቄን ካልሆነ እንባዬን ሊያረዳኝ ለሚንጦለጦል ርህራሄ የለኝም፡፡
አዲስ አመት ያለመኖር ጋሻ ጃግሬ ነው፡፡ በአዲስ ስም..በጥባት መልክ ከነገ የሚያኳርፍ፡፡ በእንኳን አደረሳችሁ ስም የመኖርን ጣዕም የሚያመር..የተስፋን አለላ የሚበርዝ፡፡ ባይመጣና ከነክንብንቡ አልፎኝ ቢሄድ ምን ገዶኝ?
በአዲስ አመት ስም ሁሉም ሞቱን እያከበረ ነው፡፡ ከእልል ወደ ስልል..ከአዬዬ ወደ እዬዬ፣ ከአሄሄ ወደ ወይኔ ወደ ወይኔ ወይኔም፡፡
ዝም ብሎ አይኬድም..ከጉም ባተቶ ስር ሰምብቶ እንደሚወጣ የብርሀን ወዝ ሞትም እሰይ እሰይን ተከትሎ የሚመጣ ነው፡፡እንደ ቀይና ጥቁር ሁሉም ማሳሳቻ አለው፡፡ አዋጅ አዋጅ ብሎ የምስራች እንደሚናገር አዋጅ አዋጅ ብሎ ሞታችንን ሊያረዳ በአንድ አፍ ሁለት ምላስ ዘመን አለ፡፡ እናም በዘመን ስም፣ በልደት ፈር በቶርታና በሻምፓኝ ያከበራችሁትና እያከበራችሁት ያለው ሞታችሁን ነው፡፡
‹እንኳን አደረሰህ? ሲሉኝ
‹እንኳን አብሮ አደረሰን› እላለሁ፡፡ ሞትን መጋራት ማለት ይሄ ነው፡፡ በሆነ ውብ ነገር ጀርባ ውበቱን የሚያስከነዳ ማስጠሎነት አለ፡፡ ያ ማስጠሎነት አልታየንም፡፡ ቃሎቻችን እየገደሉን እንደሆነ፣ ልማዶቻችን እያጠፉን እንደሆነ አልገባንም፡፡ ካልገባን ላልገባን ባሪያ ነን፡፡ ከገባን ደግሞ ለገባን አለቃ ነን፡፡ ከአንድ ውብ የሆነ ነገር ጀርባ ያለው ማስጠሎነት ይሄ ነው፡፡ ዘመን ጸጋ ነው፡፡ መኖር ዋጋ ነው፡፡ የዛሬን ጀምበር ለማየት ናፍቀው ሳያዩ ያለፉ አሉ፡፡ ለዛሬ ጠዋት እቅድ እያላቸው ማታ ከተኙበት ያልተነሱ እንዲሁ ብዙ ናቸው..እንዲህ ባለው ወግ ስር ከዘመን ዘመን መሸጋገር የጸጋ ጸጋ ነው፡፡ ግን በስተጀርባው የሸጎጠውንም ማስጠሎነቱንም ማወቅ ተገቢ ነው፡፡
ወድጄም ሆነ ፈቅጄ በአዲስ አመት ስም እንኳን ለሞትህ አደረሰህ ሲሉኝ እንኳን ለሞታችን አብሮ አደረሰን ስል እመልሳለሁ፡፡ አዲስ አመት ከዚህ የተለየ ምን ትርጉም አለው? ‹እንኳን አደረሰን እንኳን ለሞትህ አደረሰህ› ውጪ ለይቼ አላየውም፡፡ እንኳን አብሮ አደረሰንን እንኳን ለሞታችን በሰላም አደረሰን ውጪ ትርጉም አልሰጠውም።
ዘመን በጠባ ቁጥር ከእድሜአችን ላይ እየሸረፍን ነው፡፡ ከተሰጠን ላይ እያጎደልን ነው፡፡ ወደአለመኖር እየተጠጋን ነው፡፡ እኔ ዘመን ምኑም አይጥመኝ፡፡ ኪሴን አራቁቶ፣ ጓዳዬን ኦና አድርጎ ከማለፍ በቀር የጠቀመኝ የለም፡፡ ማድጋዬን፣ ገንቦዬን፣ ማሰሮዬን፣ ሌማቴን፣ ድብኝቴን፣ ጎተራዬን፣ ልቤን፣ ህልሜን፣ ተስፋዬን፣ ነገዬን አወይቦ ከማለፍ ሌላ ምን ፈየደልኝ? የተረሱ የባህል ዘፋኞችን ከተረሱ ሙዚቃቸው ጋር አስታውሶ ከማለፍ በስተቀር፣ በእዳና በብድር ነገን እንድሰጋው ከመሆን ባለፈ ምን ቸረኝ? በእከኩ እከካም አደረገኝ እንጂ፡፡ ምኑም አይጥመኝ..ሞትን ከመጥራት ሌላ የዘመን መጥቶ መሄድ ውበቱ አይታየኝም፡፡
ምንድነን? ምንም መሆን ማብቂያችን ከሆነ፣ ከነገ ወደነገ ዝማሜ ፊትለፊታችንን ካሰጋው ምንድነን? እንቁጣጣሽ እንኳን ደህና መጣሽ ባልንበት የሳቅ አፍ እንባ አርቧል፡፡ በጋ ሲሆን እንደተረኛ ክረምት ሳቅ ሲሆን እንባ አለ፡፡ ዘመን በጉያው ሞትን ሸጉጧል፡፡ ከህይወት ሊያጣላን እንቁጣጣሽ በብዙ አብሏል፡፡
ምንድነን? እንባና ሳቅ መላቸው የጠፋን..ፊት ኋላቸው የተሰወረን ሰጋሮች፡፡ ወደነገ ወደህይወት መስሎን..ወደፊት ወደመኖር መስሎን አለመርባትን ያነገስን..ምንድነን?
ዘመን አስልተን፣ እድሜ ቀምረን፣ እለት ቆርጠን በወዳጅ ዘመድ አጀብ በዘመን ስም ሞት ሆይ እንኳን ደህና መጣህ? ማለትን የመሰለ እብደት ታውቁ ይሆን? በሻማና ኬክ ከንቱነትን ማክበር፣ አለመኖርን መዘከር ምን የሚሉት አላዋቂነት ነው?
ትናንት ህይወት..
ዛሬ ህይወትና ሞት..
ነገ አለመኖር..
ከነገ በስቲያ ምንምነት..
ከዛም..
ከዛም..
ከዝም..
ሞትን ግደሉት እንጂ በዜማና ቅኝት፣ በአደይ አበባና በእሰይ እሰይ ቀይ ምንጣፍ አታንጥፉለት፡፡
የሚመጣው እንደሄደው ነው፡፡ የሄደውም እንደሚመጣው፡፡ ከንቱነታችንን ከማስታወስ ባለፈ እቅፍ አበባ ያስታቀፈን ዘመን የለንም፡፡ በመጠበቅ አበባዎቻችን ደርቀዋል፡፡ እንቡጦቻችን ጠውልገዋል፡፡ ተስፋ በማድረግ ሽንቁሮቻችን ሰፍተዋል፣ ጭላንጭሎቻችን ጸልምተዋል፡፡
ሁሉም ትናንት ላይ ነው፡፡ ሁሉም እንደዛሬና ነገ ነው።
ዘመን ማለት ሽርፈት፣ ክሽፈት ነው፡፡ አንድን ማለዳ ለሁልጊዜ መድገም፡፡ የትናንቱን ረፋድና ከሰአት አዲስ ነው ብሎ በአዲስ ስም መቀበል፡፡ ሰኞና ማክሰኞን በተሀድሶ መካደም፡፡ ከነበረ ወደነበረ መሸጋገር ምኑ ነው አዲስ ዘመን? ዛሬ ላይ ትናንትን መድገም፣ ነገ ላይ ዛሬና ከትናንት በስቲያን መቀበል ምኑ ላይ ነው ሽግግር? ከቁጥር ወደቁጥር መተላለፍ የቱ ጋር ነው አዲስነቱ?
የኔ አዲስ ዘመን ዛሬ ነው፡፡ ሞቴን ለሚያስታውስ የዘመን ቆሌ ሳቄን አልገብርም..ደስታዬን አልሸርፍም። ከህይወት ወደህይወት እንጂ ከህይወት ወደሞት አልራመድም፡፡ አሁን ሞት የሌለበት ነጻነቴ ነው፡፡ ከዛሬ ወደነገ እንጂ ከነገ ወደዛሬ ህይወት የለም፡፡ ከአሁን ወደበኋላ እንጂ ከበኋላ ወደአሁን ታሪክ የለም፡፡
ዘመን በአዲስ አመት አጊጦ፣ በአደይና ጸደይ ተሸልሞ በሆታ ሲመጣ ህይወት ያለው ይመስላል..ከኋላው ጉድፍ አለው፡፡ ዘመን ዘማዊ ነው፡፡ ጊዜ ትካዜ ነው፡፡ ባውካካንባቸው ዘመኖቻችን ላይ እንባዎቻችን ተረኞች ናቸው፡፡ በዘመን ስም ከጥቅል የህይወት ቱባ ላይ መመዘዝ..መተርተር..ምኑ ነው እልል?
በሱፍና ከረባት ሞትን ለህይወት መዳር አይነት ባህል..
ሞት በአካለ ስጋ የመገለጥ ብቃት ቢኖረው አዲስ አመቶቻችንን አብሮን ሲያከብር እናገኘው ነበር፡፡ በልደቶቻችን ቀን ላይ ጥቁር አበባ ሲሰጠን ታዩት ነበር፡፡
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ህዳር 6/2017 ዓ.ም