ቅንነት ቅንነትን ይፈጥራል!

ባለፈው ሳምንት የትዝብት ዓምዳችን፤ ‹‹ቅንነት ጤና ነው›› በሚል ርዕስ ስለቅንነት የአንዳንድ አስቸጋሪ ሰዎችን ገጠመኞች እና በፈጠሩት ግርግር አገልግሎት ማግኘት አለመቻላቸውንም ጨምረን ማስነበባችን ይታወሳል:: ዛሬ ደግሞ በትህትና የተገኙ ገጠመኞችን ላስታውስ::

በ2008 ዓ.ም ነው:: በያኔው ስያሜው የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን (አሁን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን) የሥራ ማስታወቂያ አውጥቶ፤ እኔና አንድ ጓደኛዬ የማመልከቻ ቀኑ የመጨረሻዋ ዕለት ልናመለክት ሄድን:: በወቅቱ ለብዙ የአዲስ አበባ አካባቢዎችና ተቋማት አዲስ ስለነበርን ፍላሚንጎን በቀላሉ ልናገኘው አልቻልንም:: ከብዙ ጥቆማ እና ፍለጋ በኋላ በተቋሙ ግቢ ተገኘን::

ስንደርስ ግን 6፡00 ሰአት አለፈ:: ከዚህ ሰዓት በኋላ ደግሞ የምሳ ሰዓት ነው:: ታዲያ ምን ይሻላል? ስንል መከርን:: በቃ እንግባና እንጠይቅ፤ ከተቀበሉን ተቀበሉን፣ ካልተቀበሉን እስከ 8፡00ሰአት አካባቢ መጠበቅ፤ አለበለዚያ ጥሎ መሄድ ነው::

ገባን:: በማስታወቂያው የተጠቀሰው ቢሮ ቁጥር ላይ ስንደርስ በሩ አልተዘጋም:: አንዲት ወጣት ሴት ኮምፒውተር ላይ የሆነ ሰንጠረዥ ነገር ታያለች፤ ምናልባት የተመዝጋቢዎችን ፋይል እያደራጀች ሊሆን ይችላል:: ቀና ብላ ስታናግረን፤ ፈራ ተባ እያልን ‹‹ለምዝገባ ነበር›› አልናት:: ‹‹ሰዓት እኮ አልፏል! አሁን የምሳ ሰዓት ነው›› አለችን:: አነጋገሯ ብዙ ቦታ የሰለቸን የቁጣ ድምጸት የለውም:: ሁለታችንም እየተቅለሰለስን፤ ቦታውን ስንፈልግ ሰዓት እንዳለፈብን ነገርናት:: ከምሳ ሰዓት በኋላ መምጣት እንዳለብን ነገረችን::

ምንም ተጨማሪ ልመና ሳናደርግ ሁለታችንም ምልስ አልን::

ተጨማሪ ልመና ያላደረግነው ‹‹አንለማመጥም››

በሚል ስሜት አልነበረም:: ጥፋቱ የራሳችን መሆኑን በማመን ነው:: እስከ ምሳ ሰዓት እንጠብቅ ወይስ ትተነው እንሂድ የሚለውን እየወጣን እንወስናለን በሚል ነው:: ሁለታችንም ተመሳሳይ ባህሪ ስለነበረን መብታችን ባልሆነ ነገር ላይ የመከራከር ፍላጎት የለንም:: እንኳን መከራከር መለመን ራሱ አልፈለግንም:: ምክንያቱም ያቺ ልጅ በቅንነት ካልሆነ በስተቀር በዚያ ሰዓት እኛን የማስተናገድ ግዴታ የለባትም::

ሁለታችንም የትምህርት ማስረጃችንን እንዳንጠለጠልን ለመመለስ ዞር ስንል ‹‹እሺ አምጡት!›› አለችን:: ተመዝግበን አመስግነን ወጣን::

ባለመከራከራችን (ለዚያውም መብታችን ባልሆነ ሁኔታ) እና አግባብ ያልሆነ ልመና ባለማድረጋችን ልጅቷ ይሉኝታ ያዛት ማለት ነው፤ ምናልባትም አሳዝነናታል ማለት ነው:: ብንጨቃጨቅ ኖሮ ግን አሳዛኝነታችን ወደ አናዳጅነት ይቀየራል:: ከመተባበር ይልቅ ወደ እልህ መጋባት ይሄዳል ማለት ነው::

ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በአንድ ወቅት ሲያወራ እንደሰማሁት፤ ርቱዕነት የሚባል ፅንሰ ሀሳብ አለ:: ርቱዕነት (ቅንነት ልንለው እንችላለን) ማለት ጥቅል ሀሳቡ፤ ህግና ደንብ ጥሶም ቢሆን በቅንነት ሰዎችን የሚጠቅም ነገር ማድረግ ማለት ነው:: እዚህ ላይ ታዲያ አንድ በትኩረት ልብ መባል ያለበት ነገር አለ:: ርቱዕነት የሚባለው የሚጣሰው ህግና ደንብ ጉዳት የማያመጣ ሲሆን ነው:: ምናልባት በሚገባ የሚገልጸው ‹‹ህግና ደንብ መጣስ›› ከሚለው ይልቅ ‹‹በህግና ደንብ ያልተፈቀደን ነገር ማድረግ›› የሚለው ሳይሆን አይቀርም:: ብቻ ግን ዋና ሀሳቡ የተጣሰው ህግ ምንም ጉዳት የማያመጣ ሆኖ፤ የሚደረገው በጎ ነገር ግን ባለጉዳዩን የሚጠቅም ማለት ነው:: ለምሳሌ፤ አንድ የፋይናንስ ክፍል ኃላፊ ለአንዲት የምትልሰው የምትቀምሰው ላጣች የኔ ቢጤ ገንዘብ አውጥቶ ቢሰጥ ርቱዕነት አይሆንም:: ምክንያቱም፤ ለሴትዮዋ ያደረገው ነገር በጎ ቢሆንም፤ ያወጣው የተቋም ገንዘብ ግን የሚያስከትለው ጉዳት አለው::

ለርቱዕነት ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው ከላይ የገለጽነው የሰው ሀብት ሰራተኛዋ የቅንነት ትብብር ነው:: በዚያ ሰዓት ‹‹አልመዘግብም!›› ማለት መብቷ ነው፤ ምክንያቱም በሥራ ህግና ደንብ መሰረት ያ ሰዓት የምሳ ሰዓት ነው:: እንኳን መክሰስ መውቀስ ራሱ አንችልም:: ምናልባት ‹‹ምናለ ብትመዘግቢን!›› ብለን ብንነጫነጭ ነው::

ያቺ ልጅ እኛን በመመዝገቧ የጣሰችው ህግና ደንብ ግን በተቋሙ ላይም ሆነ በእሷ ላይ የሚያመጣው ጉዳት የለውም:: ሲጀመርም ህግና ደንብ ጣሰች ለማለትም አያስችልም:: የራሷን የእረፍት ደቂቃዎች ለበጎ ነገር አደረገቻቸው ማለት ነው::

ሁለተኛው ገጠመኝ በ2005 ዓ.ም ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ እያለሁ እንደዚሁ ምዝገባ ላይ ያጋጠመኝ ነው:: ‹‹ሬጅስትራር›› የሚባለው ክፍል ሦስት አይነት ምዝገባ ነበር:: ለካ አንደኛውን አልተመዘገብኩም:: በወቅቱ ከትምህርት ክፍላችን ተማሪዎች ጋር ገና በደንብ ስላልተዋወቅን ማን እንዳልተመዘገበ ሁሉ አላውቅም:: ትምህርት ግን ተጀምሯል::

አንደኛው የዶርሜ ተማሪ እንደኔው ያልሰማ ነበርና አንድ ምዝገባ እንደሚቀረን ነገረኝ:: ሌሎችን ጓደኞቻችንን ስንጠይቅ ‹‹የት ከርማችሁ ነው?›› እያሉ ሳቁብን:: ‹‹ይህን ካልተመዘገባችሁ ዲፓርትመንቱ አያውቃችሁም›› እያሉ አስፈራሩን::

የሚያዘውን ሰነድ ይዘን የተባለው ቢሮ ሄድን:: የሆነ ጎልማሳ ሰውዬ አገኘን:: ልንመዘገብ መሆኑን ስንነግረው በስድብ አጥረገረገን:: ምንም የማናገለግል ከንቱ ሰዎች መሆናችንን እና ሻንጣችንን ሸክፈን ወደ ቤተሰባችን መሄድ እንዳለብን በቁጣ ነገረን:: በዚያ ቁጣው ውስጥ የልመናም ይሁን የክርክር ሀሳብ ሊመጣንል አልቻለም::

ተመልሰን ምን ልናደርግ እንደነበር አላውቅም! ብቻ ግን የያዝነውን ሰነድ ይዘን ለመመለስ ከበሩ ላይ ዘወር አልን:: ልክ ዘወር ከማለታችን እየተቆጣ ‹‹አምጡት!›› አለን:: እየተቅለሰለስን ገባን:: ለምን እስከዛሬ እንደዘገየን ሲጠይቀን ይሄኛውን ምዝገባ አለማወቃችንን እና አለመስማታችንን ነገርነው:: ‹‹ሥራችሁ ምን ሆኖ ነው ምዝገባ የሚያልፋችሁ?›› አለንና እየተረጋጋ መጣ::

ምንም እንኳን እንደዚያ መቆጣትና ማደነባበር ባይጠበቅበትም፤ በዚያ ሰውዬ ቅንነት ቀኑ ካለፈ በኋላ ተመዘገብን ማለት ነው:: እልህ ተጋብተን ተጣልተን ቢሆን ኖሮ የሕይወታችንን አደገኛውን ስህተት ሰርተን ነበር ማለት ነው:: በዚያች ትንሽዬ ስህተት የዩኒቨርሲቲ ትምህርታችን ላይቀጥልም ይችል ነበር ማለት ነው::

እነዚህን ገጠመኞች ያነሳኋቸው ያን ያህል ትልቅ ጉዳይ ሆነው አይደለም:: እንዲህ አይነት ገጠመኞች የሚሊዮኖች ሊሆኑ እንደሚችሉ ግልጽ ነው:: ብዙ የዚህ አይነት ቅን እና ተባባሪ የቢሮ ሠራተኞች መኖራቸውም ግልጽ ነው:: ዋናው ሃሳብ ግን በቅንነትና በታጋሽነት ሰዎችን ይሉኝታ ማስያዝ፣ ሰዎችን ቅን ማድረግ ይቻላል ለማለት ነው:: ይህ በብዙ አጋጣሚዎች የምናየው ነው::

ባለፈው ሳምንት እንዳልነው፤ ቅንነት የማይወድላቸው ክብረ ቢስ ሰዎች መኖራቸው እንዳለ ሆኖ፤ ዳሩ ግን ስለጥቂቶች ሳይሆን ስለብዙዎች ባህሪ ስናስብ ቅንነት የሰዎችን ቀልብ ይይዛል:: ተቆጥተው የነበሩ ሰዎችን ‹‹ምን ነክቶኝ ነው?›› ብለው ራሳቸውን እንዲታዘቡ ያደርጋል:: የባለጉዳዩን ቅንነት አይተው ይሉኝታ እንዲይዛቸው ያደርጋል::

እልህ መጋባት እና አንዳንድ ጊዜ ደግሞ እንዲሁ ደርሶ ‹‹መብቴ ነው!›› ማለት ቅን የነበሩ ሰዎችን ሳይቀር ወደ እልህ ሊያስገባ ይችላል:: አንዳንድ ጊዜ መብታችን የሆነውን ነገር ሁሉ ሊያሳጣን ይችላል:: ስለዚህ ሰው ነንና ሰዋዊ ነገሮችም ያስፈልጋሉ!

አስተናጋጅም ተስተናጋጅም፣ አለቃም ምንዝርም ቅን ሲሆኑ፤ እንደ ማህበረሰብ የሰለጠነ ሥርዓት እናዳብራለን!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ህዳር 7/2017 ዓ.ም

Recommended For You