ሰላም ልጆች! በተለይም የእስልምና እምነት ተከታይ ልጆች እንኳን ለዒድ አል-ፈጥር በዓል በሰላምና በጤና አደረሳችሁ!!! ልጆች፣ በዓሉ ጥሩ ነበር አይደል? እንዲህ እንደ ዒድ አል-ፈጥር ባሉ በዓላት ወቅት ብቻ የሚዘጋጁ ጣፋጭ ምግቦችን ከቤተሰብ ጋር ሰብሰብ ብሎ መመገብ፤ አዲስ ልብስ መልበስ፤ ከእማማና አባባ ጋር በመሆን በዓሉን ምክንያት አድርጎ ሽርሽር መሄድ፣ ወይም ዘመድ መጠየቅ ደስ ስለሚል ጥሩ ነበር እንደምትሉ እርግጠኛ ነኝ።
ልጆች ስለ እስልምና በዓላት አመጣጥና ታሪክ ምን ያህል ታውቃላችሁ? ስታከብሩት ስለ ታሪኩም ሆነ ስለ አመጣጡ ጠንቅቃችሁ አውቃችሁ ቢሆን የበለጠ የተሻለና የሚመረጥ ነው አይደል? እናንተ ዛሬ በዚህ መልክ ግንዛቤ ኖሯችሁ በዓሉን ማክበራችሁ ነገ እናንተ ስታድጉና ትልቅ ሰው ስትሆኑ አሁን እናንተ ባላችሁበት እድሜ ደረጃ የሚተኩ ልጆች በዓሉን እያከበሩ እንዲያስቀጥሉ ያስችላል። በመሆኑም በጥሩ ሁኔታ ማክበራችሁ መልካም ነው። ስለዚህ፣ በዛሬው ጽሑፌ ስለ ዒድ ዓል-ፈጥር በዓል ትንሽ ግንዛቤ ላስጨብጣችሁ አስቤያለሁ።
ዒድ አል-ፈጥር በዓል በእስልምና እምነት ውስጥ በየዓመቱ ከሚከበሩ ሁለት ታላላቅ ክብረ በዓላት አንዱ ነው እሺ ልጆች። ልጆች እንዳልኳችሁ በእስልምና እምነት ውስጥ በየዓመቱ የሚከበሩ ሁለት ታላላቅ ክብረ በዓላት አሉ። አንደኛው ከትናንት በስቲያ ያከበራችሁት ኢድ ዓል- ፈጥር በዓል ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ኢድ አል አድሀ (አረፋ) በዓል ይሰኛል።
ልጆች ቢሆንም ዛሬ የምነግራችሁ ከትላንት በስቲያ ስላከበራችሁት የኢድ ዓል -ፈጥር በዓል ብቻ ነው። ሆኖም የዚህን በዓል ታሪክ ማወቅ ያለባችሁ የእስልምና ዕምነት ተከታይ ልጆች ብቻ ሳትሆኑ ክርስትናና ሌሎች ዕምነቶችን የምትከተሉ ልጆች በሙሉ ናችሁ። ምክንያቱም የአንዱን ዕምነት ታሪክ ሌሎቻችሁ ማወቃችሁ የዕውቀት አድማሳችሁን እንድታሰፉ ይረዳችኋል። ከዚህ በላይም ሰርክ አብራችሁ ትምህርት ቤት እንደምትሄዱት፤ አብራችሁ እንደምትጫወቱት ሁሉ በዓሉ ከሌሎች ሐይማኖት ዕምነት ተከታዮች ጋር ሥጋ ቢቀር ዳቦና ኬክ እየበላችሁና ለስላሳ እየጠጣችሁ፤ በአንድ ላይ የምታከብሩት በመሆኑ ስለበዓሉ ማወቅ ይገባችኋል።
ይሄን ከተገነዘባችሁ ስለ ኢድ አል ፈጥር በዓል ግንዛቤ እንዲኖራችሁ ትንሽ ልንገራችሁ። ልጆች የኢድ አልፈጥር በዓል ዘንድሮ ለ1ሺህ 444ኛ ጊዜ ነው የሚከበረው። በዓሉ እንደ ረመዳን ሁሉ ሕዝበ ሙስሊሙ፣ በመተዛዘን፣ በመደጋገፍና በመረዳዳት፤ በፆምና በሶላት የሚያሳልፍበት የተቀደሰ ልዩ ወር ነው። ሰባት ዓመት የሞላቸው የእስልምና ዕምነት ተከታይ ልጆች በሙሉም በጾምና በጸሎቱ ይሳተፉበታል።
ኢድ አል ፈጥር የጾም ወቅት ማጠናቀቂያና መሸኛ ነው ተብሎ ይወሰዳል። በዓሉ በረመዳን ወር መጨረሻና በሸዋል ወር የመጀመርያ ቀን ላይ ይውላል። በቅዱሱ የረመዳን ወር ከፀሐይ መውጫ እስከ ፀሐይ መግቢያ ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ሕዝበ ሙስሊሙ ራሱን ከምግብና መጠጥ በማቀብ በመልካምና በጎ ምግባር መትጋት ይጠበቅበታል።
ልጆች፣ ለምሳሌ አንድ ዳቦ ለእናንተ ቢሰጣችሁ ግማሹን ቤተሰቡ ዳቦ ኖሮት ሊሰጠው ወይም ሊሰጣት ላልቻለው ጓደኛችሁ ማካፈል ማለት ነው። ወሩ የጾምና የመታዘዝ፤ የድካምና የመፈተን ወቅት ነው። ሆኖም ከሚበላባቸውና ከሚጠጣባቸው ወራቶች ሁሉ ቅዱሱ ወር የኢድ አል ፈጥር በዓል ወር ነው።
ልጆች የዒድ በዓል ከመከበሩ በፊት ባሉት የመጨረሻ ቀናት የእስልምና ዕምነት ተከታይ በሙሉ ዘካት አልፈጥርን ማውጣት እንዳለባቸውም ይነገራል። ልጆች ዘካት ምን እንደሆነ ትርጉሙን ታውቃላችሁ? አዎ፣ ዘካት ማለት ትላልቅ የእምነቱ አባቶች እንዲሁም የዕምነቱ ተከታዮች በሙሉ እንደሚናገሩት ለድሆች የሚሰጥ እርዳታ ማለት ነው። ድሀ ምን ዓይነት ነው ብትሉ ሁሉም በአቅሙ፣ ለምሳሌ በልብሱ፤ በሚበላው ነገር፤ በሌሎች መሰረታዊ የምንላቸው ነገሮች እኛ ካለን የኑሮ ደረጃ በእጅጉ የሚያንስ ማለት ነው።
ልጆች ድሀ የሚባለው ማህበረሰብ የሚበላው የሌለው ብቻ ሳይሆን አካል ጉዳተኛና አቅመ ደካሞች፤ አረጋውያን፤ ህፃናት፤ እንዲሁም የተጎዱና የተገለሉ በተጨማሪም የእኛን ድጋፍ አጥብቀው የሚፈልጉ ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች ሊሆኑ ይችላሉ። በመሆኑም ዘካት ከራስ በፊት ለሌላው ማሰብን የምንማርበት ስርዓትም ነው እሽ ልጆች። ስለዚህም የፈጥር ዘካ ከኢድ በፊት የግድ መከናወን ይኖርበታል። ልጆች እንደ ዒድ ያለውን የደስታ በዓል በሚገባ ለማጣጣም በዕድሜ ትንሽ ነን ወይም ትልልቆች ነን ሳንል ባለን አቅማችንና ባገኘነው ነገር ሁሉ ከእኛ በፊት መቅደም ያለባቸውን የማህበረሰብ ክፍሎች ሁሉ ማየት፣ መጎብኘትና መደገፍ አለብን።
የዒድ በዓል ከአዲስ ጨረቃ መወለድ፤ ከአዲስ የንጋት ጀንበር መፈጠር፤ ከወርቃማ ጮራዎች መፈንጠቅ ጋርም የሚደመር ውብ በአል ነው። አዲስ ቀንና አዲስ ወር አድማሱ ላይ የበዓል ድባብ ይዘረጋል። ረመዳን ወር የፆም ፍቺና የኢድ አል-ፈጥር ሶላት በአብሮነትና በአንድነት በጀመአና አብሮነት ከምንም ጊዜ በላይ ይፈቅዳል፤ ይፈልጋል። በዓሉ ለብቻ አይከበርም። በየአካባቢው ያለውን ሁሉ ሕዝብ ሊሰበስብ በሚችልበት ቦታ ላይ በጀምዐ በመስገድና ተከቢራ በማሰማት ነው የሚከበረው። በመንደር፤ በሰፈርና በቤት ውስጥም ከቤተሰብ፣ ከጎረቤት፣ ከወዳጅ ዘመድ በተጨማሪ ከሌሎች ዕምነት ተከታዮች ጋር በመሆን በሀላል ምግብና መጠጥ በዓሉን በደስታ ይከበራል። መልካም በዓል!!
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 15/2015