ውድድር ካቆመ እነሆ ስምንት ዓመታት ተቆጥረዋል፤ ዛሬም ድረስ ግን የትልልቅ መገናኛ ብዙሃን ርእስ ነው። ባለፈው ማክሰኞ የ50ኛ ዓመት ልደት ሻማውን መለኮሱን ተከትሎም መላው ዓለም የእንኳን አደረሰህ መልእክቱን አዥጎድጉዶለታል። ዓለም አቀፍ ጋዜጦችና መጽሄቶችም ኃይሌ ገብረስላሴን ‹‹የምንጊዜውም የዓለም ምርጡ አትሌት ነው›› በሚል ከአእምሮ በላይ የሆነ ድንቅ ብቃቱን የሚመሰክሩ ፅሁፎችን ለአንባቢ አድርሰዋል። በእርግጥም ታላቁ ኢትዮጵያዊ ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ በአትሌቲክስ ስፖርት ታሪክ የታየ የምንጊዜም ምርጡ አትሌት ነው። ይህም ዓለም በአንድ ድምፅ የሚስማማበት ሃቅ ነው።
አትሌቲክስ ዊክሊ የተሰኘው የአትሌቲክስ መጽሄት ኃይሌ ውድድር ማቆሙን ተከትሎ ለአንባቢዎቹ ባቀረበው የረጅም ርቀት ሯጭ ምርጫ፤ 45ነጥብ6 በመቶ ድምጽ በማግኘት የመጀመርያውን ስፈራ መያዝ ችሏል። ከዚያ ምርጫ በኋላ እንግሊዛዊው ሞ ፋራህ ብዙ የዓለም እና የኦሊምፒክ ስኬቶችን አሸንፏል። ኬንያዊው ኢሉድ ኪፕቾጌም በሁለት የኦሊምፒክ መድረኮች፣¸በትልልቅ የከተማ ማራቶኖች የዓለም ክብረወሰንን ከሁለት ሰዓት በታች በመግባት የማስመዝገብ የሙከራ በማድረግ ዓለምን ህዝብ በአግራሞት እጁን አፉ ላይ አስጭኗል። ነገር ግን አንዳቸውም ከኃይሌ የሚበልጥ ታሪክ መጻፍ አልቻሉም።
አገር ወዳዱ፣ ጨዋታ አዋቂው፣ የአገር ሽማግሌው፣ ስኬታማው የንግድ ሰው፣ ስራ ፈጣሪው፣ የጽናት ተምሳሌቱ፣ በጎ አድራጊው፣ … ቢሰነዝሩ የማይደርሱበት ከፍታ ላይ ይገኛል። የሰራቸው አስገራሚና ታላላቅ ገድሎች የክፍለ ዘመኑን ታላቅ አትሌትነት ስፍራን እንደተቆናጠጠ እንዲቆይ አስችሎታል። ኃይሌ የተወለደው በመጠናቀቅ ላይ በሚገኘው ሳምንት እአአ ሚያዝያ 18/1973 በአርሲ ዞን አሰላ ነበር። ከትምህርት ቤት የሚነሳው የሩጫ ህይወቱ እአአ በ1992 በሴኡል በተካሄደው የዓለም ታዳጊዎች ቻምፒዮና የ5 ሺ እና 10ሺ ሜትር ወርቅ በማሸነፍ ለመጀመርያ ጊዜ ስሙን በዓለም አቀፍ የውድድር መድረክ ማስመዝገብ አስችሎታል። በዚህ ወቅት በተለይ ትኩረትን ስቦ በነበረው የ10ሺ ሜትር ውድድር ሲሆን፤ በተቀናቃኙ ኬንያዊ አትሌት ጆሴፍ ማቹካ በቡጢ ተመትቶ የመጨረሻውን መስመር ማለፉ ነበር።
ይኸው ሁኔታ ኃይሌን ያስፈነጠረው ወደ መጨረሻው መስመር ብቻም ሳይሆን በአትሌቲክስ ስፖርት ታላቅ ወደሆነው ውድድር የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ይመስላል። ምክንያቱም በቀጣዩ ዓመት በጀርመን ስቱትጋርት በ10ሺ ሜትር የወርቅ በ5ሺ ሜትር ደግሞ የብር ሜዳሊያ ያገኘበት በመሆኑ ነው። ከዚያ በኋላ ከስኬት ጫፍ የወጣውን ኃይሌን የሚስተካከል አትሌት ማግኘት አልተቻለም። እአአ ከ1993 እስከ 2003 በተካሄዱ ቻምፒዮናዎችም 4 የወርቅ፣ 2 የብር እና 1 የነሃስ በጥቅሉ 7 ሜዳሊያዎችን በማጥለቅ የአትሌቲክስ ቤተሰቡን አጀብ አሰኝቷል።
የዓለም አትሌቲክስም በዚሁ ምክንያት በ1990ዎቹ የእሱን ያህል በተደራራቢ ክብር የተንቆጠቆጠ አትሌት የለም ሲል ስሙን በቀዳሚነት ያሰፍራል። ከወራት በኋላ በቡዳፔስት በሚካሄደው የዓለም ቻምፒዮና የሚከበረውን የውድድሩን 40ኛ ዓመት አስመልክቶም ምርጥ ክስተቶች በሚል ለዓለም የአትሌቲክስ ቤተሰብ ለምርጫ ከቀረቡ አትሌቶች መካከል አንዱ ሆኗል። ጀግናው አትሌት በኦሊምፒክ መድረክም አስደናቂ ገድል ያጻፈ ሲሆን፤ ለማሸነፍ በሚያደርገው ጥረት እና ብርታት የተመሰረተ (endurance) የሚል ፊልምም ተሰርቶለታል። የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮናን ጨምሮ በጎዳና ላይ ሩጫም የስፖርት ቤተሰቡን አጀብ ያሰኘ ተሳትፎና ስኬት ነበረው። በዚህም ለንደን፣ በርሊን፣ አምስተርዳም፣ ፎኮካ፣ ዱባይ፣ ኒውዮርክ እና ቶኪዮ ማራቶኖችን ለተከታታይ ዓመታት፣ በየዓመቱ ሁለትና ከዚያ በላይ ማራቶን በመሮጥ ለማመን የሚከብድ አስደማሚ ብቃቱን አስመስክሯል።
ሁሉም ድሎች ቀላል አልነበሩም። ኃይሌ ከኤሚል ዛቶፔክና ላሴ ቬሮን በመቀጠል በአስር ሺ ሜትር ውጤታማ መሆን የቻለ ሶስተኛ ሰው ያደርገዋል። እአአ በ2000 በሲድኒ ኦሊምፒክ ከፖል ቴርጋት ጋር ያደረጉት ትንቅንቅ በታሪክ ከምን ጊዜውም ምርጥ የ10ሺ ሜትር ውድድሮች አንዱ ተደርጎ ይጠቀሳል። በሩጫ ህይወቱም 27 የማይታመኑ የዓለም ክብረወሰኖችን አሰመዝግቧል። ታዲያ ይህ ድንቅ አትሌት በሩጫ ዘመኑ ከደርዘን ጊዜ በላይ ስሙ በአትሌቲክስ ዊክሊይ ገጽ መታተሙ፤ ውድድር በቃኝ ካለ በኋላም ርዕስ እንደሆነ መቆየቱ ሲያንስበት እንጂ አይበዛበትም የሚሉ ቁጥራቸው ቀላል አይደለምና እኛም ለ50ኛ ዓመት የልደት በአሉ እንኳን አደረሰህ ብለናል።
አለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 15/2015