ከዚያም ይልና ታሪኩን በአለ ይጀምራል። አለ ስማቸው ነው። የሰዓሊ አለቃ ኅሩይ የልጅ ልጅ፤ አለ ፈለገሰላም፤ ስራዎቻቸው ደግሞ አለ ፈለገጥበብ ያስብላቸዋል ቢባል ማጋነን አይሆንም። በኢትዮጵያ የስዕል ታሪክ ውስጥ የእሳቸውን ያህል አሻራቸውን ማሳረፍ የቻሉ ምናልባትም አንድ ወይም ሁለት ሰዎች ይኖሩ ይሆናል። እንደሳቸው ግን ከአፍላ ወጣትነት እስከ እርጅናቸው ዘመን ድረስ ለስዕል ጥበብ እራሳቸውን የሰጡ ሰዎች ፈልጎ ማግኘት ከባድ ነው። ያምሆኖ የእኚህ ታላቅ የጥበብ ሰው ስራ በታሪካቸው ማህደር በአግባቡ ተሰድሮ ሳይቀመጥ ቀርቷል።
ሐምሌ 24 ቀን 1915 ዓ.ም በድሮዋ ሸዋ ጠቅላይ ግዛት በፍቼ ገነት ከተማ ውስጥ ነው የተወለዱት። አባታቸው ፈለገሰላም ኅሩይ በስዕል ጥበብ የተካኑ ሰው ነበሩ። አያቱን ሰዓሊ አለቃ ኅሩይን ጨምሮ በቤተሰቡ ውስጥ አራት ያህል ሰዓሊያን የነበሩ ሲሆን ይህቺ ታላቅ ጥበብ በልዩነት በአለ ፈለገሰላም ላይ ጎልታ ታይታለች። ከሰማይ ሁለቱንም ክንፏን ዘርግታ ያረፈችባቸውም ትመስላለች። ጥበቡ ውስጥ የተወለዱ ጥበብ ናቸው ማለት ይቀላል።
አሳዳጊያቸውና አያታቸው የሆኑት አለቃ ኅሩይ በልጅነታቸው ከሥዕል ይልቅ ወደ ቤተክህነት ትምህርት እንዲያተኩሩ ይገፋፏቸው እንደነበር ይናገራሉ። በዚህም በልጅነታቸው አለቃ ጥበቡ ከተባሉ መምህር ስር ቅኔ እየዘረፉ፣ ዜማ እየተቃኙ አድገዋል። በልጅነታቸውም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የድቁና ማዕረጋቸውን ተቀብለዋል።
ከፍቼ ከተማ አሀዱ ብሎ የሚጀምረው ደማቁ ታሪካቸውን ማየት ለቻለ በኢትዮጵያ የጥበብ ሰማየ ሰማያት ላይ ግሩም የቀለማት ህብርን ሰርቶ ቁጭ ብሏል። የፋሽስት ጣሊያን መንግስት ኢትዮጵያን ለቆ በወጣበት በ1934 ዓ.ም አለ ፈለገሰላም ከፊቼ ተነስተው የአጎታቸውን እጅ በመያዝ ተከትለው አዲስ አበባ ገቡ። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውንም 1940 ዓ.ም አጠናቀቁ። 1943 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ቴክኒክ ትምህርት ቤት ገብተው በጥሩ ውጤት ተመረቁ።
ከዚያ በኋላ ከአፄ ኃይለስላሴ በተቸራቸው ነጻ የትምህርት እድል ወደ አሜሪካ አቀኑ። በአሜሪካን ቺካጎ የስነጥበብ ተቋም ውስጥ በመግባት በ1946 ዓ.ም በፋይን አርትስ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ማግኘት ቻሉ። በኢትዮጵያ ውስጥ በዘመናዊ የስዕል ትምህርት የተመረቁ የመጀመሪያው ሰውም እሳቸው ነበሩ። በ1947 ዓ.ም ተመልሰው ወደአገራቸው በመምጣት በትምህርት ሚኒስቴር ውስጥ መስራት ጀመሩ። በዚያም የተለያዩ የህጻናት መማሪያ መጽሀፍትን እያዘጋጁ ቆዩ።
አለ ፈለገሰላም ህጻናትን እጅግ በጣም አብዝተው ይወዱ ስለነበር ከአሜሪካን አገር ቋጥረው ባመጧት ትንሽ ገንዘብ አዳራሽ ተከራይተው ህጻናቱን እየሰበሰቡ ስነ-ስዕልና ልዩ ልዩ የቀለም ትምህርቶችን ያስተምሩ ነበር። ጥሩ የእውቀት ገበሬ ናቸውና በህጻናቱ ለምለም አዕምሮ ላይ ጥበብን ዘሩበት። የዘሩትም በቀለ፤ በውብ ማሳ ላይ ውብ አዝመራ ታየ። በብዙ ጥረት፣ በብዙ ትጋት እየተንከባከቡና እየኮተኮቱ የዚያችን አዳራሽ አድማስ በማስፋት የስነ-ስዕል ትምህርት ቤት ለማድረግ በቁ። በአሁኑ ሰዓትም ትምህርት ቤቱ በስማቸው ተሰይሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስር ይገኛል። እንጦጦን የማልማት እንቅስቃሴ ውስጥ ዘመናዊ የአውደ-ርዕይ ማሳያ በትምህርት ቤቱ እስከመገንባት ደርሷል።
አለ ፈለገሰላም በሚሰሯቸው የስዕል ስራዎች ስማቸው እስከ ቤተመንግሥት ድረስ የናኘ ነበር። ከእሳቸው በፊትም ሆነ በጊዜው ሌሎቹ ሰዓሊያን የሚታወቁት በትውፊታዊ ስዕሎች ሲሆን አለ ፈለገ ሰላም ግን የዘመናዊ ስዕልን ዙፋን በብቸኝነት የተቆጣጠሩ ታላቅ የጥበብ ሰው ናቸው። የቀደምቶቻቸውን የስዕል ጥበብ ዱካ ተከትለው ቀለማትን ከጥበብ ጋር በማዋደድ ከሰሯቸው ድንቅ ስራዎች የመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል፣ የጎፋ ገብርኤልን ጨምሮ በመርካቶ የሚገኙትን የቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል እና የቅዱስ ራጉኤልን ቤተክርስቲያን መለኮታዊ ጥበብ ባረፈበት እጃቸው ቡሩሹን እያነሱ ዘመናት የማይሽሯቸውን ስራዎች ማስቀመጥ ችለዋል።
ሌላው በቤተክርስቲያን ውስጥ ከሰሯቸው ስራዎች ደግሞ የናዝሬት ደብረጸሐይ ቅድስት ማርያም ካቴድራል እንዲሁም በቁልቢ ገብርኤል ቤተክርስቲያን የጥበብ አሻራቸውን አኑረዋል። በዚህ ሳይገቱም ስራቸውን እስከ ባህር ማዶ በማስፋት በአሜሪካን አገር በዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘውን የመድኃኔዓለም ቤተክርስቲያንን የሥዕል ስራ ግሩም በሆነ መልኩ ሰርተውታል። የሚገርመው ነገር ደግሞ ሁሉንም በሚሰሩበት ወቅት ወጣ ባለመልኩ ሸራውን ግርግዳው ላይ ከለጠፉት በኋላ ነበር።
የዘውዳዊ ስርዓት አክትሞ የደርግ መንግስት ሲመጣ ከነበሩበት የስዕል ትምህርት ቤት 1967 ዓ.ም ከዳይሬክተርነት በፈቃዳቸው ተነሱ። ከዚህ በኋላ በመንግሥት ተሹመው በባህል ሚኒስትር ለአምስት ዓመታት የቅርስ ጥገና ክፍል ሲሰሩ ቆዩ። ነገር ግን ወደ መጨረሻ አካባቢ ከመንግስት ጋር ኮከባቸው አልገጥም አለና እሰጣገባ ውስጥ እየገቡ መቃቃር ጀመሩ። በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ እየሸፈጡ መንግስትን አስቸገሩት። እሳቸውም የመንግስት ነገረ ስራ ሁሉ አልጥም አላቸውና “እንካችሁ ወንበሩን” በማለት ጥለው ሄዱ።
ከዚህ ኋላ ግን ከሁሉም ቦታ ተገለው ቀሩ። የደርግ መንግስት አልፎ የኢህአዴግ መንግስት ዙፋኑን ሲረከብ እሳቸውም በ80ዎቹ ካሉበት በባትሪ ተፈልገው፣ ያቋቋሙትን የስዕል ትምህርት ቤት ዳግም እንዲይዙት ተደረገ። ከዚህ በኋላ ሰዓሊው አለ በጊዜው በግንባታ ላይ ከነበረው የናዝሬት ደብረሰላም ቅድስት ማርያም ካቴደራል አስተዳደር ጋር ስምምነት በማድረግ ወደ አዳማ አቀኑ። ከተማዋም የተለየ የፍቅር ስሜትን ስለዘራችባቸው ከዚያው ሳይወጡ ቤትና መሬት ገዝተው እስከ 2000 ዓ.ም ድረስ ከዚያው ከአዳማ ቆዩ። ወደ አዲስ አበባ ከተመለሱ ወዲያ ግን አቅማቸው ስለደከመ የሚሰሩባቸውን መሳሪያዎች ለተለያዩ ሰዎች በስጦታ መልክ ሰጡ። የሰጡት መሳሪያዎቹን ብቻ ሳይሆን ታላቅ የስዕል ጥበብን ከታላቅ አደራ ጋር ነበር።
አለ ፈለገሰላም ጥበብ በትውልድ መካከል እንዳትመክን ቤተሰቦቻቸው ያስተማሯቸውን ትውልድ አሻጋሪነት እሳቸውም በተለያዩ ጊዜያት የእሳቸው ለም መሬትና ተማሪዎቻቸው በነበሩት ላይ ዘርተውታል። እሳቸውም ያላገኟትን ሌላኛዋንም የጥበብ በር እንዲያገኙ ጭምር ይመክሯቸው ነበር። የነበሯቸውን የእነ ሚካኤል አንጄሎን፣ ሊዮናርዶ ዳቪንቺን እንዲሁም የሌሎችንም የቅርጻ ቅርጽ መጽሐፍቶቻቸውን እየገለጡ ያሳዩና ስራዎቹንም ለማሻሻል የሚረዱ ምክረ ሀሳቦችን ይሰጧቸው እንደነበረም ከጠቢቡ ሰዓሊ እግር ስር ቁጭ ብለው ጥበብን የተማሩት በአንደበታቸው ይመሰክራሉ። አለ ፈለገ ሰላም የሰሯቸውን ስራቸው ከአገር ውጭ በተለያዩ የአለማችን ክፍሎች እየዞሩ አሳይተዋል። በ1953 ዓ.ም የኢትዮጵያ ወቅታዊ ጥበብ በሚል በሩስያ ሞስኮ እንዲሁም በ1960 ዓ.ም በካናዳ ሞንቴሪያል የሥዕል ዐውደ-ርዕይ ማሳየት ችለዋል።
አለ የሞት ፍርድ ተበየነባቸው
ጊዜው ጣሊያን ኢትዮጵያን የወረረበት ወቅት ነበር። ታዳጊው አለና ጓደኛቸው ተያይዘው ከቤት ይወጣሉ። ከሰፈራቸው አቅራቢያ የሚጫወቱ ልጆችን አገኙና እነርሱም ተቀላቀሉ። አለ በእጃቸው አንድ ዱላ ይዘው ነበር። ይህንን የተመለከተ አንድ የጣሊያን አሽከር ቀልቡ ዱላዋ ላይ ያርፍና ‘ዱላውን አምጣው’ ሲል በትዕዛዝ ጠየቃቸው። በዚህ ጊዜ የአለ ጓደኛ ፈጠን ብሎ ‘ለምን ይሰጥሃል በራስህ ዱላ ተጫወት’ ይለዋል። አሽከሩ ይህን ሲሰማም ደፈርከኝ በሚል ንዴት በያዘው ዱላ ጭንቅላቱን መታው። አለም ከልጁ የባሰ ነደው፣ በዱላው የአሽከሩን አናት ብለው ይዘርሩትና በድንጋጤ ከጓደኛቸው ጋር ተያይዘው እልም ይላሉ።
በኋላ ነገሩን ሲሰሙም አሽከሩ ወዲያውኑ ጭጭ ብሏል። በማግስቱም ወታደሮች እቤት ድረስ መጥተው አንጠልጥለው ወሰዷቸው። አራት ቀንም ያለ እህልና ውሃ ከእስር ቤት ከቆዩ በኋላ የሞት ፍርድ ተፈርዶብሃል ተባሉ። ከሌሎች እስረኞችም ጋር ይዘዋቸው ወደ ገደል አፋፍ ከወሰዷቸው በኋላ የሚቀበሩበትን መቃብር እራሳቸው እንዲቆፍሩም ታዘዙ። አለ ፈለገሰላምም መሞቴ እንደሆን አይቀር ስለዚህ አሉና፤ ዙሪያ ገባቸውን ቃኘት ቃኘት ሲያደርጉ ከዙሪያው ገደል ተመለከቱ። እንደገና ዞር ቢሉ አንደኛው ፖሊስ ትንሽ እራቅ ብሎ ሲጋራውን ለኩሷል። አካፋውንም ጥለው እግሬ አውጪኝ ሲሉ፤ እግራቸው እንደመራቸው ቁልቁል ወደገደሉ ፈረጠጡ።
ወታደሮቹም ይተኩሳሉ፤ አለ ግን የባሩዱን ድምጽ እየሰሙም በድንጋጤ በየት ኩል አድርገው ወዴት እንደሄዱ አያውቁትም፣ ብቻ ሁሉም ነገር በደመነብስ ከሞት ሽሽት የሚደረግ ትግል ነበር። ከገደሉ ውስጥ ገቡና በቅጠል ተሸፋፍነው ድምጻቸውን አጠፋ። ወታደሮቹም ቢያዳምጡ ምንም ድምጽ የለም። በዚህ ጊዜ ከጥይቱ ቢያመልጥም እንኳን ከገደሉ ተርፎ ሊወጣ አይችልም በማለት ትተው ሄዱ። ቤተሰቦቻቸውም አለ ሞቷል ብለው ለቅሶ ተቀመጡ በመጨረሻ ግን አወቁ። ይህቺ አጋጣሚም እኚህ ትልቅ ሰው ዳግም የተወለዱባትና ለኢትዮጵያ የስዕል ጥበብ ወሳኟ ሰዓት ነበረች።
ታላቁ የጥበብ ሰው አለ ፈለገሰላም የሰሩት ብዙ ቢሆንም ምስጋናና ሽልማቱን ያገኙት ግን በጥቂቱ ነው ለማለት ያስደፍራል። ሆኖም ግን ካገኟቸው እውቅናና ሽልማቶች በአሜሪካ፣ በጀርመን፣ በህንድ፣ በሶቪየት ኅብረት፣ በቼኮዝላቫኪያ፣ በግሪክና በዩጎዝላቪያ የሥዕል ዐውደ-ርዕዮዎችን በማሳየት የተለያዩ ሽልማቶችም አግኝተዋል። የኢትዮጵያ ሚሊንየም በሚከበርበት ወቅትም ሲድ (SEED) በተባለ አሜሪካን አገር ያለ ተቋም የሥዕል ጥበብን ለማስተማር ላደረጉት ጉልህ አስተዋጽኦ ሽልማት አበርክቶላቸዋል።
በመጨረሻ አቅማቸው እየደከመ እርጅናቸውም እየበረታ መጣ። እስትንፋሳቸውም ከዳቸውና በወርሃ ሐምሌ 2008 ዓ.ም ነብሳቸው ከስጋቻው ተለየች። ሁሉም ከመቃብር ወዲያ ማዶ ሆኑ። ስማቸው ግን ለዘለዓለሙ ከመቃብር በላይ ናት። ይህቺ ባለሁለት ፊደላት ትንሿ ስም ‘አለ’ እኔም እላለሁ፤ እምቅ ቅኔ ሆና እኚህን ታላቅ ሰው ተሸክማ ኖረች። ከሞት በኋላም ታሪካቸውን ተሸክማ እነሆ ከመቃብር በላይ ገዝፋ በደማቁ እያበራች በትውልዱ ሁሉ ትኖራለች።
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 15/2015