የአፍሪካ ጦር ኃይሎች (ሚሊታሪ) ስፖርታዊ ፌስቲቫል ከኅዳር 11/2017 ዓ.ም ጀምሮ በናይጄሪያ አስተናጋጅነት ሲካሄድ ቆይቶ ከትናንት በስቲያ የተጠናቀቀ ሲሆን፤ በአትሌቲክስ ስፖርት ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፈው መቻል ስፖርት ክለብ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።
ሁለተኛው የአፍሪካ ጦር ኃይሎች ስፖርት ፌስቲቫል በናይጄሪያ ዋና ከተማ አቡጃ ከመላው አፍሪካ በተወጣጡ የሚሊታሪ ስፖርተኞች መካከል ለአስር ተከታታይ ቀናት ሲካሄድ ቆይቶ ከትናንት በስቲያ ሲጠናቀቅ መቻል ስፖርት ክለብ በአትሌቲክስ ተሳትፎ አመርቂ ውጤትን በማስመዝገብ ውድድሩን አጠናቋል። ውድድሩ አንድ ጊዜ ተካሂዶ ለረጅም ዓመታት መቋረጥ በኋላ ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ በተካሄደበት ወቅት መቻል በመጀመሪያው የውድድሩ ተሳትፎ ጥሩ ውጤትን በማስመዝገብ በአትሌቲክስ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቅ ችሏል። በዚህም በአትሌቲክስ ውድድር ተሳትፎን ማድረግ የቻለው መቻል ስፖርት ክለብ 17 ሜዳሊያዎችን ሰብስቦ በድል አጠናቋል።
ኢትዮጵያን በውድድር መድረኩ ወክሎ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካፈለው መቻል ጠንካራ አትሌቶችን አሰልፎ ደማቅ የሆነ ውጤትን በማስመዝገብ በአትሌቲክስ ከኬንያ ቀጥሎ በሁለተኝነት ሲያጠናቅቅ፤ በአጠቃላይ ደግሞ አምስተኛ ደረጃን ይዞ ውድድሩን ፈጽሟል። በተለያዩ የሩጫና ሜዳ ተግባራት ላይ የተሳተፉ የክለቡ አትሌቶች ከፍተኛ ትንቅንቅን በማድረግ በመጀመሪያው ተሳትፎ ተፎካካሪ እንዲሆንና ደረጃ ሰንጠረዥ ውስጥ ገብቶ እንዲያጠናቅቅም አድርገዋል። በዚህም በተለያዩ የአትሌቲክስ ውድድሮች 7 የወርቅ፣ 8 የብርና 2 የነሐስ ሜዳሊያን በመሰብሰብ በጥቅሉ 17 ሜዳሊያዎችን ይዞ በመጀመሪያው ተሳትፎው ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ ፈጽሟል።
በአምስት ሺ እና ሦስት ሺ ሜትር መሰናክል መቻልን ወክላ የተወዳደረችው ሃምሳ አለቃ ወርቅውሃ ጌታቸው ሁለት የወርቅ ሜዳሊያዎችን በማስመዝገብ ኢትዮጵያን ማስጠራት እንዲሁም ክለቧ በውጤት ታጅቦ እንዲያጠናቅቅ ትልቅ ተጋድሎን አድርጋለች። አትሌቷ ከፍተኛ ፉክክርን ባስተናገዱት እነዚህ ሁለት ውድድሮች ልምድና ችሎታዋን ተጠቅማ ክለቧ ሁለት ሜዳሊያዎች እንዲያገኝ ትልቅ የሆነ ሚናን ተጫውታለች። ሃምሳ አለቃ ትዕግስት ግርማ በ1500 ሜትር ሶስተኛውን የወርቅ ሜዳሊያ ለክለቧ ስታስመዘግብ፤በወንዶች አሎሎ ውርወራ ምክትል አስር አለቃ ነነዌ ጌንዳቦ አራተኛውን፣ በሴቶች ሱሉስ ዝላይ ምክትል አስር አለቃ በፀሎት አለማየሁ አምስተኛውን የወርቅ ሜዳሊያ አስመዝግባለች። ስድስተኛው የወርቅ ሜዳሊያ የተመዘገበበት ሌላው የሜዳ ተግባር ሲሆን፤ በሴቶች ጦር ውርወራ አስር አለቃ ብዙነሽ ታደሰ አሸናፊ ሆናለች። በተጨማሪም በውድድሩ መጠናቀቂያ ቀን 4 በ400 ሜትር ዱላ ቅብብል ውድድር ሰባተኛው የወርቅ ሜዳሊያ መመዝገብ ችሏል።
በወንዶች ጦር ውርወራ ምክትል አስር አለቃ ኡታጌ ኡጉላ ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያን አስገኝቷል። በሴቶች አሎሎ ውርወራ ምክትል አስር አለቃ ዙርጋ ኡስማን ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ለክለቧ የብር ሜዳሊያ ማስመዝገብ ችላለች። በወንዶች 1500 ሜትር ሃምሳ አለቃ ደጀኔ ተሾመ ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያ አስገኝቷል። አስር አለቃ በዓለም ላይ ሹመት እንዲሁ ሁለተኛ ወጥቶ የብር ሜዳሊያ ካስመዘገቡት አትሌቶች መካከል ነው።
በሴቶች 400 ሜትር ፍጻሜ ምክትል አስር አለቃ ራሔል ተስፋዬ ሶስተኛ ደረጃን ይዛ በማጠናቀቅ የነሐስ ሜዳሊያ አስመዝግባለች። በጉጉት በተጠበቀው የ500 ሜትር ወንዶች ውድድር ምክትል አስር አለቃ መሰረት ሙሉ ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ የነሐስ ሜዳሊያን ማስመዝገብ ችሏል።
በዘንድሮው የጦር ኃይሎች (ሚሊታሪ) ጨዋታዎች አልጄሪያ፣ ካሜሩን፣ ግብፅ፣ ኢትዮጵያ፣ ጋና፣ ኬንያ፣ ሞሮኮ፣ ደቡብ አፍሪካ እና አስተናጋጇ ናይጄሪያ ከተሳታፊ ሀገራት መካከል ይጠቀሳሉ።
የውድድሩ ዓላማ በአህጉሪቱ ለሚገኙ የሚሊታሪ ስፖርተኞች የውድድር ዕድል መፍጠር ሲሆን፤ አትሌቲክስን ጨምሮ በቅርጫት ኳስ፣ ቦክስ፣ እግር ኳስ፣ ጎልፍ፣ እጅ ኳስ፣ ጁዶ፣ ውሃ ዋና፣ ቴኳንዶ፣ መረብ ኳስና በሌሎችም ስፖርቶች መከናወን ችለዋል።
የአፍሪካ ጦር ኃይሎች (ሚሊታሪ) ስፖርታዊ ውድድር በርካታ ስፖርቶችን በማካተት ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት በተወጣጡ ሚሊታሪ አትሌቶች መካከል የሚካሄድ ውድድር ነው። የመጀመሪያው የአፍሪካ ሚሊታሪ ስፖርት ውድድር እአአ በ2002 ከዓለም አቀፉ ሚሊታሪ ካውንስልና ከአፍሪካ ሚሊታሪ ስፖርት ተቋም ጋር በትብብር በኬንያ ናይሮቢ አስተናጋጅነት ተካሂዶ ናይጄሪያ የውድድሩ አሸናፊ ነበረች።
በናይጄሪያ አስተናጋጅነት በተካሄደው ስፖርት ፌስቲቫል ኢትዮጵያን ጨምሮ በአጠቃላይ ከ25 የአፍሪካ ሀገራት የተወጣጡ 1 ሺ በላይ ስፖርተኞች በ19 የስፖርት ዓይነቶች ተሳታፊ ሆነዋል። የስፖርት ፌስቲቫሉ ሲጠናቀቅ አስተናጋጇ ናይጄሪያ የውድድሩ አጠቃላይ አሸናፊ ሆና አጠናቃለች። 3ኛው የመላው አፍሪካ የጦር ኃይሎች የስፖርት ፌስቲቫልና ውድድር በኢትዮጵያ ወይም ኢዃቶሪያል ጊኒ ይካሄዳል ተብሏል።
በውድድሩ የመከላከያ ሠራዊት የስነ ልቦና ግንባታ ዋና ዳይሬክተር ሜጄር ጀኔራል እንዳልካቸው ወልደኪዳንና የመቻል ስፖርት ክለብ ዳይሬክተር ብርጋዲየር ጀኔራል ኑሩ ሙዘይን የታደሙ ሲሆን፤ በናይጄሪያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለቡድኑ አባላት የእራት ግብዣ አድርገዋል።
አለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 23 ቀን 2017 ዓ.ም