በጉጉት ሲጠበቅ የቆየው የ2024 የዓለም ምርጥ አትሌቶች የሽልማት መርሃግብር ከትናንት በስቲያ ሲካሄድ ሁለት ኢትዮጵያውያን ኮከብ አትሌቶች በተለያዩ ዘርፎች አሸናፊ ሆነዋል። ሁለቱ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከስታዲየም ውጪ እንዲሁም በምርጥ ተስፈኛ አትሌቶች ዘርፍ አሸናፊ በመሆን ደምቀዋል። በአጠቃላይ በስድስት ዘርፎች በሚካሄደው ሽልማት ሶስቱ አሸናፊ አትሌቶች አፍሪካውያን መሆናቸውም የዘንድሮውን ሽልማት የተለየ አድርጎታል።
በአትሌቲክስ ስፖርት በተለይም በረጅም ርቀት ውድድሮች ውጤታማ የሆነችው ኢትዮጵያ በመድረኩ አትሌቶቿን ካስመረጠች ዓመታት የተቆጠሩ ቢሆንም በመጠናቀቅ ላይ በሚገኘው 2024 የውድድር ዓመት ግን ሁለት አትሌቶቿ አሸናፊዎች ሆነዋል።
የ3ሺ ሜትር መሰናክል ተወዳዳሪዋ ወጣት አትሌት ሲምቦ ዓለማየሁ በተስፈኛ አትሌቶች ዘርፍ አሸናፊ ስትሆን፣ በኦሊምፒክ ማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊው አትሌት ታምራት ቶላ ከስታዲየም ውጪ በሚደረጉ ውድድሮች የዓመቱ ምርጥ አትሌት ለመሆን በቅቷል።
ከወራት በፊት በፈረንሳይ አዘጋጅነት በተካሄደው የፓሪስ ኦሊምፒክ በ200 ሜትር የወርቅ እንዲሁም በ4በ400 ሜትር ደግሞ የብር ሜዳሊያዎችን በማጥለቅ የስፖርት ቤተሰቡን ያስደመመው ቦትሷዋናዊው አትሌት ሌትሲሌ ቲቦጎ በመም (ትራክ) ውድድሮች ዘርፍ የዓመቱ ምርጥ አትሌት ተሰኝቷል።
በፓሪስ ኦሊምፒክ የማራቶን ወርቅ እንዲሁም 5ሺ እና 10ሺ ሜትሮች የነሐስ ሜዳሊያዎችን ያስመዘገበችው ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ኔዘርላንዳዊት አትሌት ሲፋን ሃሰንም ከስታዲየም ውጪ በተካሄዱ ውድድሮች ምርጥ ሴት አትሌት በመሆን ተመርጣለች።
የዓለም አትሌቲክስ ቀደም ባሉት ዓመታት በሁሉም የውድድር አይነቶች አንድና ወጥ የሽልማት አይነት የነበረው ሲሆን፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የሽልማት ዘርፎቹን እንደየ ውድድሮቹ ባህሪ በማስፋት የዓመቱን ምርጥ አትሌቶች እየሸለመ ይገኛል።
ከእነዚህም መካከል አንዱ የሆነው የተስፈኛ አትሌቶች ምርጫ እአአ ከ2005 አንስቶ የሽልማት መርሃግብሩን ተቀላቅሏል። በዚህም እአአ በ2019 አትሌት ሰለሞን ባረጋ አሸናፊ በመሆን የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ አትሌት ነው። ከዓመታት በኋላም ከሰሞኑ በተካሄደው ሽልማት አትሌት ሲምቦ ዓለማየሁ ተስፈኛ አትሌት በመባል ተመሳሳይ ሽልማት ተረክባለች።
በውድድር ዓመቱ ከዕድሜያቸው ወጣትነት አንጻር ድንቅ ብቃት ያሳዩ አትሌቶች በሚመረጡበት በዚህ ዘርፍ፤ ሲምቦ አሸናፊ ልትሆን የቻለችው በተለይ በፓሪስ ኦሊምፒክ ባሳየችው ብቃት ነው። የ19 ዓመቷ የ3ሺ ሜትር መሰናክል አትሌት ፓሪስ ላይ 5ኛ ደረጃን በመያዝ ያጠናቀቀች ቢሆንም፤ ከቀናት በኋላ በዓለም ከ20 ዓመት በታች ቻምፒዮና ደግሞ የውድድሩን ክብረወሰን በማስመዝገብ የወርቅ ሜዳሊያ ማስመዝገቧ ይታወሳል።
በፓሪስ ኦሊምፒክ የኢትዮጵያ ማራቶን ቡድን በተጠባባቂነት ተቀላቅሎ የነበረው ታምራት ቶላ በመጨረሻ ሰዓት ባገኘው የመወዳደር እድል ተጠቅሞ ሳይታሰብ ባለድል መሆኑ አይዘነጋም። ጀግናው አትሌት በታምራት ቶላ የኦሊምፒክ ክብረወሰን በማሻሻል ጭምር የማራቶንን ድል ከ24 ዓመት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ የመለሰበት አስደናቂ ብቃት ከስታዲየም ውጪ በተደረጉ ውድድሮች የዓመቱ ምርጥ አትሌት እንዲሆን አድርጎታል።
የ2022ቱ የዩጂን ዓለም ቻምፒዮና የማራቶን አሸናፊው አትሌት ታምራት በቀጣዩ ዓመት የኒውዮርክ ማራቶንን በድል ማጠናቀቁ የሚታወስ ነው። በመጠናቀቅ ላይ ባለው የውድድር ዓመት የለንደን ማራቶንን ባያጠናቅቅም በኦሊምፒኩ ግን ድንቅ አቋሙን በማሳየት አሸናፊ መሆኑ የዓመቱ ምርጥ አትሌትነት ክብርን ሊያቀዳጀው ችሏል።
በሽልማት መድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የዓለም አትሌቲክስ ፕሬዚዳንት ሳባስቲያን ኮ፤ አሸናፊዎችን ጨምሮ በእጩነት ለቀረቡ አትሌቶች በዓመቱ ላሳዩት ምርጥ ብቃት የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል። በውድድር ዓመቱ የኦሊምፒክ መካሄድ እና 6 የዓለም ክብረወሰኖች መሰበርን ጨምሮ በርካታ ምርጥ ብቃቶች በየርቀቱና ውድድር አይነቱ መታየታቸውንም አስታውሰዋል።
እአአ ከ1988 አንስቶ መካሄድ የጀመረውን ይህን ሽልማት ለስድስት ጊዜያት በማሸነፍ ቀዳሚ የሆነው አትሌት ጃማይካዊው የአጭር ርቀት ሯጭ ዩሴን ቦልት ነው። ሞሮኳዊው የመካከለኛ ርቀት አትሌት ሂሻም ኤል ግሩዥ እና ሩሲያዊቷ ምርኩዝ ዘላይ ይሌና ኢሲንባዮቫ ደግሞ ሶስት ሶስት ጊዜ ሽልማቱን በመውሰድ ይከተላሉ። ጀግናው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በተከታታይ ለሁለት ጊዜያት (እአአ 2004 እና 2005) አሸናፊ በመሆን ብቸኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ሲሆን፤ ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ ደግሞ እአአ በ1998 የዚህ ክብር ባለቤት መሆን ችሏል። በሴቶች በኩልም አትሌት መሰረት ደፋር፣ ገንዘቤ ዲባባ እና አልማዝ አያና የዓመቱ ምርጥ አትሌት በመባል የተመረጡ ኢትዮጵያዊያን ናቸው።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ኅዳር 24 ቀን 2017 ዓ.ም