ለሴት ልጅ የእጅ ጣት ውበት ነው፡፡ አለንጋ ጣት መሆንና አለ ለሴት ልጅ የእጅ ጣት ውበት ነው፡፡ አለንጋ ጣት መሆንና አለመሆን የተፈጥሮ ጉዳይ ነው፡፡ ጥፍሯን ማሳመር ግን ከተፈጥሮም ባሻገር እንክብካቤ ጊዜና ገንዘብ ይሻል፡፡ እናቶቻችን ሂና ተቀብተው እንሾሽላ ሞቀው ጣታቸው ላይ ቀለበት አድርገው ለራሳቸው ለተመልካችም ማራኪ ጣትና ጥፍር እንዲኖራቸው ያደርጉ ነበር፡፡ አሁን ግን ዘመን ተቀይሯል፡፡ ጥፍር ቀለም ተቀብቶ እፍ እያሉ መድረቅ ደረቀ አልደረቀ እያሉ መሳቀቅ እየቀረ መጥቷል፡፡ የአብዛኛው ምርጫ ሺላክ የተሰኘው የማይለቅና ለማድረቅ ማሽን የሚያስፈልገው የጥፍር ቀለም ዓይነት እየሆነ ሄዷል፡፡
አክለሪክ፣ ጄል፣ ኔል ሳሎን የሚባሉ ቃላት በዘመነኞቹ ሴቶች አፍ የሚሰሙ ቃላት ሆነዋል፡፡ አገልግሎቱ ቤት ለቤት፣ ለብቻ ጥፍር ብቻ የሚሰራባቸው ቤቶች እንዲሁም አጠቃላይ ሙሉ የውበት አገልግሎት የሚሰጥባቸው ቤቶች ተበራክተዋል። የመበርከታቸውን ያህልም የሚያስከፍሉት ገንዘብም የበረከተ ነው፡፡ ከእነዚህ የዘርፉ ባለሙያዎች አየር ጤና የሚገኘው ኤዳ የውበት ሳሎን ባለቤት ኤደን ታምራት አንዷ ነች፡፡ ተፈጥሮም የእሷ አያያዝም ታክሎበት ከልጅነቷ አንስቶ ከእኩዮቿ ጎልቶ የሚታይና “ጥፍርሽ ሲያምር” የምትባል ልጅ ነበረች፡፡ በዚህም የተነሳ ለጥፍር እንክብካቤ ለየት ያለ ፍቅር ነበራት፡፡ ያም ቢሆን የሕይወቷ ዘርፍ ሌላ ይመስል ነበር፡፡ በትምህርቷ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ በኮምፒዩተር ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪ አላት። ከግል ኮሌጅ በቢዝነስ አስተዳደር ሁለተኛ ዲግሪ ይዛለች፡፡ የተለያዩ ሥራዎችን ብትሰራም አብዛኛውን የቅጥር ሕይወቷ በግል ትምህርት ቤት በመምህርነት አሳልፋለች፡፡
የራስ ሥራ መሥራት የሚል ሃሳብ ነበራት፡፡ ለዚህም የመረጠችው በራሷ ጥፍር ውጤታማነት ያስመሰከረችው ጥፍርን መንከባከብን ነው፡፡ ለዚህም የጥፍርና የሜካፕ ሥራ አጭር ሥልጠና ወሰደች፡፡
‹‹የጥፍርና የሜካፕ ትምህርቱን በወሰድኩበትና ሥራውን በጀመርኩበት መሃል የዓመት ከስድስት ወር ልዩነት ነበር›› የምትለው ኤደን፤ ማህበራዊ ሚዲያዎችን በማየት ራሷን ከዘመኑ ሥራዎች ጋር ታስኬድ ነበር፡፡ ያም ቢሆን ወደሥራው እንደገባችም ደንበኞችን በክፍያ ከመሥራት ይልቅ በመንገድ የሚያልፉ ሰዎችን በነፃ በመሥራት እጅ መፍታቷን ታስታውሳለች፡፡ በነፃ ተሰርተው ሥራዋን የወደዱት ሰዎች በገንዘብ የሚሰሩ ሰዎችን እያመጡላት፤ እነሱም ቀጣይ ደንበኛ እየሆኑ ቀጥለዋል፡፡ በማህበራዊ ሚዲያዎች የሥራዋን ውጤት በተከታታይ መልቀቋን ተከትሎ አሁን እሷን ብለው ከሩቅ የሚመጡ ደንበኞች አፍርታለች፡፡
በጥፍርና በሜካፕ ሥራዋ እሷን መርጠው የሚሄዱት ደንበኞቿ ለጥፍርና ለሜካፕ ብቻ ከምንመጣ ለምን የውበት ሳሎን አትከፍቺም የሚል ጥያቄ በረከተ፡፡ አሁን አየር ጤና በሚገኘው ኤዳ የውበት ሳሎን እሷ ጥፍርና ሜካፕ ስትሰራ የጸጉር ሥራውን በባለሙያዎች ታሰራለች፡፡ ሰዎች ሥራው የሚያረካ ካገኙ አንድ ቦታ መሠራት ምርጫቸው ነው ትላለች፡፡ በአንድ ቦታ የልባቸው ካልደረሰ ድካም ቢሆንም የተለያየ ቦታ ሄደው እንደሚሰሩ ምስክር ነች፡፡
እሷ ጋር ጥፍር የሚሰሩት አብዛኞቹ ከተፈጥሮ ይልቅ በዘመኑ ቴክኖሎጂ ማጌጥ ምርጫቸው ነው፡፡ የተፈጥሮ ጥፍራቸውን እንክብካቤ ማግኘትና ጥፍር ቀለም የሚቀቡ ደንበኞቿ አነስተኛ ናቸው ትላለች፡፡ የሚለጠፉ፣ ጄል የሚሞሉና አክለሪክ የሚሰሩ ይበዛሉ፡፡ ልጥፍ በፋብሪካ የተዘጋጀ አርቴፊሻል ጥፍርን ለዛ በተዘጋጀ ማጣበቂያ ማጣበቅና የመረጡትን የጥፍር ቀለም መቀባት፣ ቁመቱን እንዲሁም ቅርጹን ማስተካከልን ያካትታል። ልጥፍ ጥፍር ቀለል ያለ ሲሆን እስከ አስራ አምስት ቀን ድረስ ይቆያል፡፡ በርካታ ሰዎች የእጃቸውን ጥፍር የሚለጠፉ ቢሆንም በርካቶች የእግር ጥፍራቸውን መለጠፍ ምርጫቸው ነው፡፡ የእግር ጥፍር ላይ ሲሆን ረዥም ጊዜ እንደሚቆይ ትናገራለች፡፡
እሷ ጋር የሚመጡት ደንበኞች በብዛት ምርጫቸው ጄል መሆኑን የምትናገረው ባለሙያዋ፤ ጄል ሲሆን አርቴፊሻል ጥፍር እንደሚጣበቅና ለዚህ ተብሎ የተዘጋጀ ኬሚካል አርቴፊሻል ጥፍሩ ላይ ይደረጋል፡፡ ኬሚካሉን ለማድረቅ የተሞላው ጥፍር ዩቪ ላይት የሚባል መሳሪያ ውስጥ ገብቶ ይደርቃል፡፡ እንደሰውየው ፍላጎትና ሁኔታ ቢለያይም በብዛት ከሁለት እስከ ሦስት ወር ይቆያል፡፡ ይህን ያህል እንዲቆይ በመሃል መሞላት (ሪፊል) መደረግ አለበት ትላለች፡፡ ለዚህም የተሠራው ሰው ውሃ ውስጥ በጣም የሚቆይ ከሆነ ጥፍሩ የማደግ እድል ስላለው ቶሎ ሪፊል ይፈልጋል፡፡ ቢፈጥን በ20 ቀን ቢዘገይ በአንድ ወር የድጋሚ ሙሌቱ ይደረጋል ትላለች፡፡
አክለሪክና ጄል ሁለቱም ተጨማሪ ጥፍር የሚያስፈልጋቸውና የሚሞሉ በመሆናቸው አንድ ይመሳሰላሉ ትላለች፡፡ ሆኖም አክለሪክ ዱቄት (ፓውደር) በመሆኑ ያለምንም መሳሪያ ይደርቃል፤ ጄል ግን ለመድረቅ ዩቪ ላይት የሚሰኝ ማሽን ያስፈልገዋል፡፡ የመቆየትና የውበት ሁኔታቸው ተመሳሳይ ቢሆንም አክለሪክ ሲሰራ ከባድ ሽታ ስላለው በአብዛኛው ደንበኞቿ ዘንድ ጄል ተመራጭ ነው፡፡ የሚሰሩት ጥፍር ቁመት ቅርጽ እንዲሁም የሚቀቡት የጥፍር ቀለም ከለርና ዲዛይን ከዚህ ቀደም ከሰራችው መሃል መርጠው ወይም ደንበኛው ይዞት የመጣውን ምርጫ ትሠራለች፡፡ በአንቺ ምርጫ ሥሪን የሚሉም ሆነ ከማህበራዊ ሚዲያ ያዩትን ሥራ እንደምርጫቸው እንደምትሠራ ትገልጻለች፡፡
የጾም ወቅት ላይ ሥራው የሚቀዘቅዝበት ሲሆን ሠርግ የሚበዛበት ጥር ደግሞ በርካታ ሰው ይሠራል ትላለች፡፡ ዓርብ፣ ቅዳሜና እሁድ ደንበኛ ጥፍር የሚሰራ ሰው ቁጥሩ ይጨምራል፡
ቤዛ እሸቱ
አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 23 ቀን 2017 ዓ.ም