አዲሱ ሥራ አስፈፃሚ የአትሌቶችን መብት ለማስከበር ቃል ገባ

ስመጥርና ውጤታማ የሆኑ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የዓለም አቀፍ ውድድሮችን መካሄድ ጨምሮ በተለያዩ ሁኔታዎች የአስቸጋሪ አሠራር ሰለባ በመሆን ቅሬታ ሲያቀርቡ ይስተዋላል። በቅርቡ የተካሄዱ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎችና ኦሊምፒክ መድረኮች የተፈጠሩ አነጋጋሪ ክስተቶችና ውዝግቦች ለዚህ ምስክር ናቸው፡፡ አትሌቶች ይህን መሰል ሁኔታዎች ሲገጥማቸው ችግሮች እንዲስተካከሉና መፍትሔ እንዲያገኙ የአትሌቶችን መብት ማስከበር እንዲችል የኢትዮጵያ አትሌቶች ማኅበር ቢኖርም ጥርስ የሌለው አንበሳ ሆኖ ይታያል፡፡

ማኅበሩ ለአትሌቶች ችግር መፍትሔ ማምጣት እንዳልቻለ የጠቆመ ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አሠራር እንዲሁም ለዓለም አቀፍ ውድድሮች በብሔራዊ ቡድን አባልነት የሚደረግ ምርጫ ተከትሎ በተደጋጋሚ የአትሌቶች የበደል ድምፅ ሲሰማ ቢቆይም መፍትሔ ማምጣት እንዳልተቻለው የማኅበሩ አባላት ገልፀዋል፡፡

ለአትሌቶች መብት የቆመው ማኅበር ባለፉት ዓመታት የመፍትሔ አካል እንዳልነበር ማኅበሩ 5ኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ባካሄደበት ወቅት ተገልጿል፡፡ የማኅበሩ አባላት በተለይም እአአ በ2023ቱ የቡዳፔስት ዓለም ሻምፒዮና እንዲሁም 2024ቱ የፓሪስ ኦሊምፒክ ላይ አትሌቶች ብሶትና በደላቸው እንዲማ ድምፃቸውን ቢያሰሙም በማኅበሩ በኩል የአትሌቶችን መብት ለማስከበር የተደረገ ጥረት እንዳልነበር ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም የብሔራዊ ቡድን አትሌቶች መምረጫ መስፈርት ቋሚ እንዲሆን አለመሠራቱ፣ አሠልጣኞች በአትሌቶች ላይ አድሏዊ ተግባራትን ሲፈጽሙ አለመጠየቅ እንዲሁም ከተበዳይ አትሌቶች ጎን በመሆን አቋሙን እንዳላሳየም በተደጋጋሚ ተነስቷል፡፡

በሌላ በኩል አትሌቶች ከፓስፖርት ጋር የተያያዙ እንግልቶችን ለመፍታት ጥረት አለመደረጉ፣ ማኅበሩ ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋር ተናቦ ከመሥራት አንጻር፣ ከዓለም አቀፍ አቻ ተቋማት ጋር ያለው ግንኙነት፣ የማዘውተሪያ ስፍራዎችና የስፖርት ቁሳቁስ እንዲሟሉ የሚደረገው ጥረት አናሳ መሆናቸውም በጉባኤው አባላት ተጠቁመዋል፡፡

የጉባኤተኞችን ጥያቄ ተከትሎ ባለፉት አራት ዓመታት ማኅበሩን በፕሬዚዳንትነት የመራው አትሌት ኮሚሽነር ማርቆስ ገነቴ ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ከዓለም አቀፍ ውድድሮች ጋር ተያይዞ አትሌቶች ያቀረቧቸውን ቅሬታዎች ማኅበሩ ለሚመለከታቸው አካላት በቃል፣ በጽሑፍ እንዲሁም በመገናኛ ብዙኃን በኩል ፍትሕ እንዲያገኙ ጥረት ሲያደርግ ነበር፡፡ በአንዳንድ አትሌቶች የቀረቡ ቅሬታዎች ደግሞ በሕግና ደንብ መሠረት አግባብነት የሌላቸው ነበሩ፡፡ ከዚህ ባለፈ የአትሌቶች የውጪ ጉዞን በሚመለከት በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን፣ ማኅበሩን ለማስተዋወቅ የ10 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር ማካሄድን ጨምሮ በርካታ ሥራ ሠርቷል፡፡ በማኅበሩ አባላት የተነሱ ሃሳቦች አብዛኛዎች ግብዓት ሲሆኑ ማኅበሩ ባለፉት ዓመታት በዕድሜ ተገቢነት፣ በስፖርት አበረታች ንጥረነገሮች ተጠቃሚነትን በመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ አለመሥራቱን አልሸሸገም፡፡

ጠቅላላ ጉባኤው ምርጫ ያካሄደ ሲሆን፤ የሥራ ዘመኑን ባጠናቀቀው የማኅበሩ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴን በአዲስ ተክቷል፡፡ በተካሄደው ምርጫ መሠረትም የትግራይ ክልልን በመወከል በፕሬዚዳንትነት የታጨው አትሌት የማነ ፀጋይ ሊመረጥ ችሏል፡፡ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በተደጋጋሚ ኢትዮጵያን የወከለውና በታላላቅ የማራቶን ውድድሮች ውጤታማ መሆን የቻለው አትሌት የማነ 9 ድምፅ በማግኘትም ነው በከፍተኛ ልዩነት ፕሬዚዳንትነቱን ያረጋገጠው፡፡ አትሌቱ በበርሊን፣ ሞስኮ እና ቤጂንግ ዓለም ሻምፒዮናዎች የብር ሜዳሊያ እንዲሁም ዲፕሎማ ማስገኘት ችሏል፡፡ ለረጅም ጊዜ ስኬታማነት ያሳለፈው በማራቶን ሲሆን፤ በኦቶዋ፣ ጉዋንዡ፣ ሮተርዳም፣ ዴጉ፣ ፎኮካ፣… ማራቶኖች አሸናፊ ነበር። የአትሌቶች ማኅበር ፕሬዚዳንት ሆኖ መመረጡን ተከትሎም የአትሌቶችን መብትና ግዴታ ለማስከበር ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እንዲሁም ከነባሩ ሥራ አስፈጻሚ ጋር በጋራ ለመሥራት መዘጋጀቱን ገልጿል፡፡

የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫን ተከትሎም አትሌት ተመስገን ወርቁ፣ አትሌት ባንቺአየሁ ተሰማ፣ አትሌት መርሲት ገብረእግዚአብሄር፣ አትሌት በላይነሽ ኦሊጂራ፣ አትሌት ግርማ ጥላሁን፣ አትሌት በሻንቄ እሙሼ እና ኮከብ ተስፋዬ ተመርጠዋል፡፡

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ኅዳር 22 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You