እኛ ኢትዮጵያውያን እንደ ሕዝብ ለሰላም ትልቅ ትርጉም የምንሰጥ ሕዝቦች ነን። መንፈሳዊ፣ ባህላዊ እና ማህበራዊ እሴቶቻችን ለሰላም ቅድሚያ የሚሰጡና አብዝተው የሚሰብኩ ናቸው። የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችንም ለሰላም ትኩረት የሚሰጥ፣ የሚዘክርና አብዝቶ ለሰላም ጥበቃ የሚያደርግ ነው።
”አያ እከሌ ”በሰላም አደርክ፤ ቀዬው አገሩ ሰላም አድሯል ከሚለው የተለመደው የማለዳ ሰላምታ ጀምሮ፤ ቀኑን ሙሉ ባለው ማኅበራዊ መስተጋብራችን ጎልቶ የሚደመጠው ሰላም የሚለው ቃል፣ እንደ ሕዝብ ስለ ሰላም ያለንን ቀናኢነት አመላካች ነው።
ችግሮቻችንን በራሳችን ዘመናት በተሻገሩ የዳበሩ የሰላም እሴቶች በመፍታት፤ ሁሌም ለሰላም ያለንን ቁርጠኝነት በተጨባጭ የምናሳይና በዚህም ከፍያለ የስነ ልቦና ከፍታና መንፈሳዊ ልእልና ያለን ሕዝቦች ነን።
የህይወት መስዋእትነት በሚጠይቁ ዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ወስጥ በመሳተፍ፤ ለሰላም ያለንን ቁርጠኝነት በተግባር አስመስክረን ዓለም አቀፍ እውቅና አትርፈናል። በመሪም ደረጃ ዓለም አቀፉን የሰላም ኖቬል ተሸላሚ በመሆን ዓለም ስለ ሰላም ያለንን አቋምና ትክክለኛ መረዳት በተጨባጭ እንዲረዳ አድርገናል።
ይህም ሆኖ ግን በየወቅቱ በሚፈጠሩ አለመግባባቶች ሰላማችን እየተረበሸ ግጭት ውስጥ መግባታችን፤ እንደ አገር አላስፈላጊ ዋጋ መክፈላችን፤ በዚህም በብዙ የልብ ስብራት ውስጥ የማለፋችን እውነታ ዛሬ ድረስ ያልተሻገርነው ትልቁ ተግዳሮታችን ሆኗል።
በቅርቡ በሰሜኑ የአገሪቱ አካባቢዎች የተካሄደው ጦርነት የዚሁ እውነታ አንዱ መገለጫ ነው። በወቅቱ የተፈጠረውን ችግር በተረጋጋና በሰከነ መንፈስ በውይይት ልንፈታ የምንችልበት ሰፊ ዕድል የነበረን ቢሆንም፤ ይህንን ዕድል መጠቀም ባለመቻላችን አስከፊ ወደ ሆነ ጦርነት ለመግባት ተገደናል።
መላው ሕዝባችንም አልፈን ከመጣናቸውና የግጭትና የጦርነት ታሪኮቻችን ካስከፈሉን ከፍያለ ዋጋ አንጻር፤ ጦርነትን በየትኛውም መልኩ አምርሮ የሚቃወም፤ ጦርነት ትርፍ የሌለበት የጥፋት ድግስ መሆኑን በአግባቡ የሚረዳ ቢሆንም፤ ተፈጥሮ የነበረው ችግር የአገርን ህልውና ስጋት ውስጥ በመጨመሩ ተገድዶ በጦርነቱ ተሳታፊ ሆኗል።
በጦርነቱ ወቅትም በሕዝብ ይሁንታ በስልጣን ላይ ያለው መንግስት በአንድ እጁ ብረት በሌላ እጁ የሰላም ሰንደቅ በማውለብለብ፤ ሕዝባችን እንደ ሕዝብ ስለሰላም ያለውን ከበሬታ በተጨባጭ አሳይቷል። በዚህም የሚጨበጥ ፍሬ ማፍራት ችሏል።
በወቅቱም የሕዝባችን የሰላም መሻት ፍሬ እንዲያፈራ ሕወሓትን ጨምሮ በአፍሪካ ኅብረት እና በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በኩል የታየው ቀና ተሳትፎ፤ በብዙ መልኩ የሚበረታታ እና እውቅና ሊሰጠው የሚገባ እንደሆነ ይታመናል።
በተለይም የአፍሪካ ኅብረት ”ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ ”የሚለውን የአህጉሪቱ ሕዝቦች የራስን ችግር ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት የመፍታት መነቃቃት እውን በማድረግ ለችግሩ መፍትሄ ለማፈላለግ የሄደበት መንገድ በቀጣይ በአህጉሪቱ ተመሳሳይ ችግሮች ቢያጋጥሙ ለመፍታት የሚያስችል ስኬታማ ተሞክሮ ተደርጎ የሚወሰድ ነው።
ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብም፣ በአንድም ይሁን በሌላ ለችግሩ ትኩረት በመስጠት፤ በመንግስት በኩል ለተጀመረው የሰላም ጥረት ተጨማሪ አቅም በመሆን ችግሩ በሰላማዊ ድርድር በሰላም ስምምነት እንዲቋጭ ያደረገው ድጋፍ ምስጋና ሊቸረው የሚገባ ነው።
ምንም እንኳን የራሳቸው የቤታቸውና የአገራቸው ጉዳይ ቢሆንም በአገር ውስጥ ያሉ ታዋቂ ሰዎች ራሳቸውን የመፍትሄ አካል በማድረግ የሄዱበት ርቀት የሚበረታታ ነው። ይህ በአገራችን የቀደመ ታሪክ ብዙም ያልተለመደው አዲስ ተሞክሮ በቀጣይ አንድ የችግር መፍቻ አቅም ተደርጎ ሊወሰድ የሚገባውም ነው።
በአጠቃላይ የሕዝባችን የሁሌ መሻት የሆነውን አገራዊ ሰላም በማስፈን ሂደት ውስጥ በአንድም ይሁን በሌላ ተሳትፎ ያደረጋችሁ ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ ተቋማት፣ አገራት እና የአገራት መሪዎች እንዲሁም ታዋቂ ግለሰቦች ኢትዮጵያ ከፍ ያለ ምስጋናዋን ታቀርብላችኋለች። ይህ አስተዋጿችሁ በአገራችን ሰላም ግንባታም ሆነ በታሪካችን ውስጥ ትልቅ ስፍራ የሚይዝ ነው!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 15 ቀን 2015 ዓ.ም