የዛሬይቱ ኢትዮጵያ በሁሉም መስክ ተስፋ ሰጪ በሆነ ሁኔታ ላይ ያለች ሀገር ናት!

በዓለም አቀፍ ደረጃ የረጅም ዘመን የሀገረ መንግሥት ታሪክ ካላቸው ጥቂት ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ናት። ሀገሪቱ እስከዛሬ ለብዙዎች እንቆቅልሽ የሆኑ ሥልጣኔዎች ባለቤት ስለመሆኗም የታሪክ መዛግብት፤ የሚታዩ እና የሚጨበጡ ዘመናትን የተሻገሩ ቅርሶች በተጨባጭ የሚያመላክቱት ነው።

ኢትዮጵያውያን በነዚህ የረጅም ዘመናት የሀገረ መንግሥት ታሪክ ውስጥ ብዙ ክፉ እና በጎ የሚባሉ ጊዜያትን አሳልፈዋል። እንደሀገር ሊያጋጥሙ የሚችሉ ውጣ ውረዶችን አልፈዋል። በየዘመኑ መላው ዓለምን ብዙ ዋጋ ባስከፈሉ ተግዳሮቶች ውስጥ አልፈዋል፤ ይህ ያለ የነበረ እና የሚኖር ነው።

የሀገሪቱ ሕዝቦች በተለያዩ ዘመናት ባሳለፏቸው የከፍታ እና የዝቅታ ሕይወት ውስጥ ዛሬ ላይ በሥልጣኔ አንቱ የተባሉ ሀገራት ተቸግረው ረድተዋል፤ ራሳቸውም ከአቅማቸው በላይ በሆነ ችግር ውስጥ ገብተው ከሌሎች ተቀብለዋል። ይህ አዲስ ክስተት ሳይሆን የመጣንበት ዓለም አቀፍ ትርክት የተለያዩ ምዕራፎች መገለጫ ነው።

ኢትዮጵያውያን እንደ አክሱም፣ ላሊበላ፣ ጢያ ወዘተ የመሰሉ የቀደሙ ሥልጣኔዎቻችው በፈጠሩላቸው ሞገስ በዓለም አቀፍ ደረጃ የገነነ ታሪክ እና ስም ባለቤቶች ሆነዋል። በብዙ ተቸግረውም፤ የሌሎችን ርዳታ በመጠበቃቸው የችግርተኝነት ማሳያ ተደርገው ታይተዋል። በዚህም እንደሀገር ብሔራዊ ክብራቸውን በሚፈታተን አጋጣሚ ውስጥ ለማለፍ ተገድደዋል።

ከነዚህ ውስጥ በ1977 ዓ/ም በሀገሪቱ የተከሰተው የድርቅ አደጋ፤ በወቅቱ ከነበረው የርስ በርስ ጦርነት እና የተለያዩ ሴራዎች ጋር ተዳምሮ የፈጠረው የረሃብ አደጋ ተጠቃሽ ነው። በዚህም በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ የሀገሪቱ ዜጎች የሚላስ የሚቀመስ አጥተው ለተመፅዋችነት፤ ለሞት እና ለስደት ተዳርገው ነበር።

ይህ ሁኔታ አብዛኞቹ የዓለም ሀገራት እና ሕዝቦች ያለፈበት መንገድ ነው። ዛሬ ላይ አንቱታን ያተረፉ የአውሮፓ ሀገራት ሳይቀሩ አስጨናቂ እና ዘግናኝ የተባሉ የረሃብ ታሪኮችን እንዳሳለፉ የታሪክ ድርሳናት ይመሰክራሉ፡፡ ብዙ ዜጎቻቸውም ለእልቂት ተዳርገዋል፤ ክስተቶቹም የየሀገራቱ ታሪክ ጥቁር ነጥቦች ሆነው አልፈዋል።

የሀገራቱ ሕዝቦች ከነዚህ ዘግናኝ የትናንት ታሪካዊ ክስተቶች በመማር፤ ዛሬ ላይ የተሻለ ሕይወት የሚኖርበት ሌለ የታሪክ ምዕራፍ ላይ ይገኛሉ። ሀገራቱ በቀደሙት ዘመናት የዜጎቻችውን ሕይወት ለማትረፍ አቅመቢስ የሆኑትን ያህል፤ አሁን ለሌሎች የሚተርፉበት ተጨባጭ እውነታ ውስጥ ናቸው።

እኛ ኢትዮጵያውያንም ትናንት በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ሆነን ዜጎቻችን ለዓለም አቀፍ እርዳታ የተዳረጉበት ሁኔታ መኖሩ የአደባባይ ሚስጥር ነው። ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብም ሰብዓዊነትን መሠረት ባደረገ መንገድ ደግፎናል፤ ስለድጋፉም በወቅቱ ከፍያለ ምስጋና አቅርበናል። ዛሬም ቢሆን ላለማመስገን የሚያስገድደን ነገር የለም።

በወቅቱ ርዳታ ለማሰባሰብ ተብሎ ‘Do they know its Christmas?’ የሚል ሙዚቃ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስም እና ዝና ባላቸው ሙዚቀኞች ተቀንቅኗል። ሙዚቀኞቹ በሙያቸው ርዳታ ለሚሹ ወገኖቻችን የሠሩት ሥራ የሚመሰገን፤ በብዙ መልኩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ባለውለታ የሚያደርጋቸው ቢሆንም፤ በርዳታ ሰበብ የኢትዮጵያ ገጽታ በመጥፎ የተሳለበት መንገድ ግን የተሳሳተና ሊታረም የሚገባው ነው።

ይህን የአንድ ወቅት ክስተት የሀገሪቱ የሁሌ መገለጫ አይደለም፤ አድርጎ ለማየት መሞከርም ተገቢ አይደለም። በተለይም ለርዳታ ማሰባሰቢያ ተብሎ የተዘጋጀውን ይህን ሙዚቃ ቀን እየቆጠሩ ለአድማጭ ተመልካች ለማቅረብ የሚደረጉ ጥረቶች ፤ ኮንሰርቱ ቀደም ሲል የተዘጋጀበትን ዓላማ የሳተ፤ በኮንሰርቱ ላይ የተሳተፉ የጥበብ ሰዎችን ሰብዓዊነት የሚያሳንስ ነው።

የዛሬዋ ኢትዮጵያ ሚሊዮኖች በረሀብ አደጋ ውስጥ ያሉባት እና የሚላስ የሚቀመስ አጥታ እጆቿን ለምፅዋት ለዓለም የዘረጋች ሀገር አይደለችም። በረሃብ ጣር ውስጥ ያሉ ዜጎች ሲቃ የሚያሰሙበት፤ ሰቀቀን እና ተስፋ መቁረጥ የነገሠባትም አይደለችም ።

የዛሬይቱ ኢትዮጵያ በፈጣን ሁለንተናዊ ኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ የምትገኝ፤ ታላቁ የህዳሴ ግድብን ያለምንም የውጪ ርዳታ እና ድጋፍ በራሷና በሕዝቦቿ አቅም ያገባደደች፣ ከስንዴ ምርት ተዓምር የተባለ ውጤት ያስመዘገበች፣ በተከታታይ አስደማሚ ኢኮኖሚ ዕድገት ም ሕዋር የምትጓዝ ናት፡፡

ከዚህም ባለፈ እንደ ብዙዎቹ የበለፀጉ ሀገራት ድህነትን ታሪክ ለማድረግ ከፍ ባለ ሀገራዊ መነቃቃት ውስጥ ያለች፤ በዚህም ተስፋ ሰጭ ስኬቶችን እያስመዘገበች ያለች ሀገር ናት። የሕዝቦቿ ነገዎችም በስጋት ሳይሆን በብዙ ተስፋ የለመለሙም ናቸው ።

እንደ ሀገር በግብርናው ዘርፍ ሆነ በሌሎች መስኮች እያስመዘገበች ያለው የለውጥ ርምጃዎች፤ ከረሃብ አደጋ ስጋት እስከወዲያኛው የሚሻግሯት ናቸው፤ በጥቂት ዓመታት ውስጥ በስንዴ ምርት ከራሷ መትረፍ ችላለች። በአፍሪካ ሊጠቀስ የሚችል የግብርና አብዮት እያካሄደች ያለች ሀገር ናት!

አዲስ ዘመን ህዳር 19/2017 ዓ.ም

Recommended For You