ብዙዎች በትወና ሥራዎቿ ያውቋታል። እሷ ግን ብዙዎች ከሚያውቋት ከትወና ሥራዎቿ በበለጠ ሰው ተኮር ለሆኑ ሥራዎቿ አብዝታ ታደላለች። የአርቲስትነት ሙያን በእጅጉ የምታከብር ብትሆንም ‹‹አርቲስት›› በሚለው የሙያ መጠሪያዋ ባትጠራ ትመርጣለች። ሕይወትን ቀለል አድርጋ መምራት ያስደስታታል። ውስጧ የሚያዝዛትን ለማድረግ ሁለት ጊዜ አታስብም። ፈጣን፣ ቀልጣፋና የውሳኔ ሰው ከመሆኗም በላይ ማንኛውንም ያመነችበትን ነገር ከውስጧ በመነጨ ዕምቅ ፍላጎት ትከውናለች። ለዚህ ባህሪዋም በነጻነት ግን ደግሞ ጥብቅ በሆነ ኢትዮጵያዊ ስነ ስርዓት ያሳደጓት ቤተሰቦቿ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳሉ።
በትወና ሥራ የተዋጣላቸው ናቸው ከሚባሉ አርቲስቶች ተርታ የምትሰለፈው የዕለቱ የስኬት እንግዳችን ከትወና ሥራዋ ባለፈ የህክምና ማእከል ባለቤት የሆነችው የስዊዝ ዲያግኖስቲክስ የህክምና ማዕከል መስራችና ባለቤት የትናየት ታምራት ወይም ሚሚ ናት። የትናየት፣ ‹‹ሚሚ›› በሚለው የቤት ስሟ በስፋት ትታወቃለች። ለህዝብ አይንና ጆሮ የደረሱ ጥቂት የማይባሉ የፊልም ሥራዎች ያሏት የትናየት፤ ከትወና ሥራዎቿ በላይ ጊዜዋን በበጎ ሥራ ማሳለፍ ያስደስታታል። ፈጣን፣ ቀልጣፋ፣ ተግባቢና ቅን አሳቢም ናት።
በልጇ ጤና ማጣት ብዙ ዋጋ ከፍላለች። ታድያ የከፈለችውን ዋጋ በማሰብ በአይነቱ ልዩ የሆነ የስዊዝ ዲያግኖስቲክስ የህክምና ማዕከልን በማቋቋም በወቅቱ ልጇ በአገር ውስጥ ማግኘት ያልቻለችውን አገልግሎት ዛሬ ለህዝቡ እንካችሁ ብላለች።
አዲስ አበባ ከተማ ልደታ አካባቢ ተወልዳ፣ አትላስ አካባቢ ያደገችው የትናየት መካከለኛ ገቢ ካላቸው ወላጆች ብትገኝም፣ አስተዳደጓ ከአብዛኛው ኢትዮጵያዊ የተለየ አይደለም። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን መጠነኛ ክፍያ በሚጠይቅ ትምህርት ቤት በክፍያ ብትማርም፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ደግሞ ከአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ጋር በመንግሥት ትምህርት ቤት ተምራለች። ይህም አብሮነትን መማር እንድትችል አግዟታል።
አንድ ቦታ ላይ ብዙ መቆየት የማትፈልገው የትናየት፤ ከትወና ሥራዎቿ አስቀድማ ገና በልጅነቷ የተለያዩ ሥራዎችን ሠርታለች። በሥራዎቿ ሁሉ ስኬትን መጎናጸፍ ለእርሷ አዲስ አይደለም። ቀልጣፋና ፈጣን በሆነ ተፈጥሮዋ ጎበዝ ተማሪነቷ ታክሎበት በሕይወት መንገድ ውስጥ የስኬት መሰላልን መውጣት ችላለች። የአካውንቲንግ ትምህርቷን በአድማስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ተከታትላ የመመረቂያ ጽሑፏን ባስገባች ማግስት ነው ሥራ መሥራት እንዳለባት የወሰነችው።
ያኔ የአባቷ ጓደኛ የሆኑ አንድ ሰው የቤትና የቢሮ ዕቃዎች ያስመጡ ነበርና እሳቸው ዘንድ ተቀጥራ መሥራት እንድትችል ወላጅ አቧቷ ሁኔታዎችን አመቻቹላት። ይህ አጋጣሚ ሌላ የሥራ ዕድል ፈጥሮላት ከተመረቀች በኋላ ዘመናዊ በሆነ የህጻናት መዝናኛ ማዕከል ውስጥ የመቀጠር ዕድል አግኝታለች። ይህም ትላልቅና ታዋቂ ሰዎችን የመተዋወቅ አጋጣሚን ፈጥሮላታል።
በዚሁ አጋጣሚ የተዋወቀችው ሌላ ሰው ደግሞ ሌላ ሥራ ይዞ ከቀልጣፋዋ የትናየት ጋር በጋራ ለመሥራት አጥብቆ በመሻቱ የማተሚያ ቤት ሥራን በጋራ ሠርታለች። አዲስ ነገር ለማወቅ ከፍተኛ ፍላጎት ያላት የትናየት፤ የግራፊክ ዲዛይን ሥራን ከሀ እስከ ፐ ከድርጅቱ ባለቤት ተምራለች። ስካን (scan) ከማድረግ ጀምራ የማተሚያ ቤት ሥራን በሙሉ ጥንቅቅ አድርጋ ማወቅ ቻለች።
አንድ ቦታ ላይ መቆየት ባህሪዋ ያልሆነው የትናየት፤ በፈጣን ውሳኔዋ ‹‹የራሴን ሥራ መሥራት አለብኝ›› በማለት ሥራውን ለቃ ወጣች። በአጭር ጊዜ ቆይታዋ በርካታ ሰዎችን መተዋወቅ የቻለችው ፈጣኗ የትናየት፤ ብዙም ሳትቆይ በቤተሰቦቿ ሳሎን ቤት የራሷን ማተሚያ ቤት ከፈተች። ያኔ ማተሚያ ማሽን ባይኖራትም የዲዛይን ሥራውን ጥንቅቅ አድርጋ በመሥራት የህትመት ሥራውን የማተሚያ ማሽን ያላቸው ድርጅቶች ጋ ወስዳ ታሳትም ነበር። በዚህ ሥራም በርካታ ደንበኞችን በማፍራት ከቢዝነስ ካርድ ጀምሮ ቢል ቦርድ፣ ኮፍያ፣ ቲሸርት፣ የመመረቂያ መጽሔትና ሌሎች በርካታ ሥራዎችን በጥራት መሥራት ጀመረች። ለዚህም አስቀድማ ትሠራበት ከነበረው ድርጅት ብዙ ዕውቀት መቅሰሟን አልሸሸገችም።
ሥራዋ እየሰፋ ሲመጣም የቤተሰቦቿ ሳሎን ቤት አልበቃትም። እናም የቤተሰቦቿን የሚከራይ ሶስት ክፍል ቤት ተከራይታ ከሳሎን ወጣች። ሥራው እየተሳለጠ ደንበኞቿም እየበረከቱ ሲመጡ ደግሞ ሌላ ፍላጎት መጣ። በቤተሰቦቿ ግቢ ውስጥ መሥራት ምቾት አልሰጥ አላት። ለዚህም መፍትሔ አላጣችም፤ ሁለት ጊዜ ሳታስብ በሰባት ሺ 500 ብር ግቢ ቤት ተከራይታ ከቤተሰቦቿ ግቢ ወጣች። ከቤተሰቦቿ ጉያ ተነጥላ ለመሥራት የወሰነችው የትናየት፤ በወቅቱ ከወላጅ እናቷ ተቃውሞ ቢገጥማትም አባቷ ግን ፈቃዳቸውን ሰጥተው በነጻነት ሥራዋን መሥራት እንድትችል አድርገዋታል።
በወጣትነት ትኩስ ኃይል የሥራ ዓለምን የተቀላቀለችው የትናየት፤ ገና ከልጅነቷ ጀምራ ሰዎችን ማቅረብ፣ መርዳትና ማገዝ ያስደስታታል። በምታገኘው ልክ ሰዎችን በመርዳት የምትታወቀው የትናየት ‹‹ያገኘሁትን በመስጠቴ ጎድሎብኝ አያውቅም›› ትላለች።
በወቅቱ በኤች አይ ቪ የተያዙና ሌሎች ተያያዥ ችግር ያለባቸውን የማህበረሰብ ክፍሎች ታግዝ እንደነበርም ታስታውሳለች። በአፍላ ዕድሜዋ በሥራ ዓለም ውስጥ ገብታ ከላይ ታች ያለችው የትናየት፤ ወደ አርት ሞያ ውስጥም ሆነ በአይነቱ ልዩ የሆነ ስዊዝ ዲያግኖስቲክስ ዘመናዊ የላቦራቶሪ ማዕከልን ለመገንባት ምክንያት የሆነቻት በልጅነቷ የወለደቻት የመጀመሪያ ልጇ እንደሆነች ትናገራለች።
በዘጠኙም ወራት የእርግዝና ጊዜዋ በጽኑ ስትታመም የነበረችው የትናየት፤ ልጇን በሰላም ወልዳ ማሳደግ ብትችልም፤ ህጻኗ ግን ልጆች በጊዜ ሂደት የሚያመጡትን የዕድገት ለውጥ ማምጣት አልቻለችምና የጤና ችግር የገጠማት መሆኑን በማረጋገጥ ወደ ህክምና ተቋም ወሰደቻት። ወደ ህክምና ተቋም በሄደች ጊዜ እርሷ ከገጠማት ችግር በበለጠ ብዙ ችግሮችን፣ ህመምና ስቃዮችን መመልከቷን ታስታውሳለች። በተለይም ለህክምና ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ባቀናችበት ወቅት የብዙ እናቶችን ስቃይ አይታ አብራ ተሰቃይታለች፤ ህመማቸውን ከህመሟ ጋር ደርባ በመታመም በብርቱ ተፈትናለች።
‹‹ጎሽ ለልጇ ስትል ተወጋች›› እንዲሉ ለወትሮ ተርብ የነበረችው የትናየት፣ በልጇ ጤና ማጣት ክንፏ እንደተመታች ወፍ ኩርምት ብላ ዓመታትን አሳለፈች፤ ዕምቅ ችሎታዋን አዳፍና በብርቱ የተፈተነችው የትናየት፤ ለሶስት ዓመታት ልጇን ከመንከባከብ ውጭ ሥራ አልነበራትም።
ይህን የተረዳውና ቅርቧ የሆነው ሰራዊት ፍቅሬ ከደረሰባት ከፍተኛ የስነ ልቦና ስብራት ወጥታ አቅሟን መጠቀም አንድትችል ምክንያት ሆኖ የትወናውን ዓለም እንድትቀላቀል እጇን ይዞ እንዳስገባት ታስታውሳለች። በነጻነት እምቅ ችሎታዋን አውጥታ መጠቀም በመቻሏም እንደ ቀልድ የጀመረችው የትወና ሥራ ዕውቅናን አተረፈላት። ከትወና ሥራዋ ጎን ለጎን ለአፍታም ቢሆን የማትዘነጋው የልጇን ጤና መከታተል ነውና ለፈውሷ ያልደረሰችበት አልነበረም።
በልጇ ህመም የደረሰባትን ጉዳትና የመንፈስ ስብራት ተቋቁማ ወደ አርት የገባቸው የትናየት፤ ከትወና በተጨማሪ የተለያዩ ፊልሞችንም ጽፋለች። ለአብነትም ሴት ልጅ ጠንካራ እንደሆነች ራሷን ምስክር በማድረግ ‹‹ያነገስከኝ›› በሚለው የፊልም ሥራዋ ሴቶች ከተደገፉ አገርን መለወጥ እንደሚችሉ አሳይታለች። ‹‹ሃምሳ ሎሚ›› በሚለው የፊልም ሥራዋ ደግሞ ህጻናት ላይ መሥራት ለለውጥ ትልቁ ምክንያት እንደሆነ መስክራለች። ከፊልም ሥራዋ በተጨማሪ የተለያዩ ሥራዎችን በመሥራት ከራሷ አልፋ ለብዙዎች ድካም ብርታትና መፍትሔ ለመሆን ከላይ ታች የምትለው የትናየት፣ ልጇ በገጠማት የጤና ችግር ምክንያት በቀላሉ መዳን የሚችለው ሕመሟ በህክምና ስህተት ይበልጡኑ መባባሱን አጫውታናለች።
ይሁንና አጋጣሚው ፈቅዶላት ልጇን ስዊዘርላንድ አገር ወስዳ ማሳከም የቻለችው የትናየት፤ ከአምስት ሰዓታት በላይ በወሰደ የቀዶ ህክምና የልጇ ጤና መሻሻል እንደታየበት ነው የገለጸችው። የትናየት ምንም እንኳን የህክምና ትምህርት ባይኖራትም በልጇ ህመም ምክንያት ለህክምናው ቅርብ ሆና ክፍተቶችን ታስተውል እንደነበር ታስታውሳለች። ይህን ክፍተት ለመሙላትም የህክምና ማዕከሉን በአገር ውስጥ አቋቁማ ዕድሉን ያላገኙ ሰዎች የህክምና አገልግሎቱን እንዲያገኙ ለማድረግ ስትወስን ሁለት ጊዜ አላሰበችም። ስዊዘርላንድ አገር ያየችውን ዘመናዊ ህክምና አገሯ ላይ ቢኖር ብላ ተመኘች። ህልሟን ዕውን ለማድረግም ያለ የሌለ ሃብትና ንብረቷን በመመደብ ስዊዝ ዲያግኖስቲክስ ዘመናዊ የላብራቶሪ ማዕከልን በመቶ ሚሊዮኖች ገንዘብ ማቋቋም ቻለች።
ኢትዮጵያ ውስጥ በህክምናው ዘርፍ ያለውን ክፍተት በሚገባ የተረዳችው የትናየት፤ እጅግ በጣም ጎበዝ የሆኑ ሀኪሞች ኢትዮጵያ ውስጥ ስለመኖራቸው ትናገራለች። ይሁንና እነዚህ ጎበዝ ሀኪሞች የተሳሳተ የላብራቶሪ ውጤት ሊደርሳቸው እንደሚችልና የህክምና ስህተት ሊፈጠር እንደሚችል ትገልጻለች። ይህ ዘመናዊ የላብራቶሪ ማዕከል ግን የህክምና ስህተት እንዳይፈጠር ከማድረግ ባለፈ ወደ ውጭ አገር ተልኮ ይመረመር የነበረውን ምርመራ በማስቀረት ፈጣንና ጥራት ያለው አገልግሎት የሚሰጥ፤ እጅግ ዘመናዊ የላብራቶሪ ማዕከል እንደሆነ ነው የተናገረችው።
ዘመናዊ ህክምና ለዜጎች የግድ እንደሆነ የምታምነው የትናየት፤ በልጇ ምክንያት ያስተዋለችውን የህክምና ክፍተት ለማሟላት በተነሳች ጊዜ ከመንግሥት አበረታች የሆኑ ድጋፎችን አለማግኘቷ ግን ቅር እንዳሰኛት ትናገራለች። እሷ ግን የሚፈለገውን መስዋዕትነት ከፍላ ዘመናዊ የላቦራቶሪ ህክምና ማዕከሉ አገልግሎት እንዲሰጥ አድርጋለች። በዚህ አጋጣሚ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ሆነው ሥራን የሚያደናቅፉ አካላት ስለመኖራቸው የታዘበችው የትናየት፣ ማገዝና መደገፍ ቢያቅታቸው ቢያንስ እንቅፋት እንዳይሆኑ ስትል መልዕክቷን አስተላልፋለች።
ወደ ሥራው ስትገባ ነገሮች አልጋ በአልጋ አልነበሩም፤ አስቸጋሪ የተባሉ ውጣ ውረዶችን አልፋ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ የሌሉ እጅግ ዘመናዊ የህክምና ማሽኖችን በአገር ውስጥ አስገብታ ህዝብ እንዲገለገልበት አድርጋለች። እነዚህ የህክምና መሳሪያዎች ለህብረተሰቡ በእጅጉ አስፈላጊ እንደሆኑ የምትጠቅሰው የትናየት፤ ስዊዝ ዲያግኖስቲክስ ከ40 በላይ የሆኑ ምርመራዎችን ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ ለማህበረሰቡ እየሰጠ መሆኑን በማስታወስ ማህበረሰቡ ይህን አጋጣሚ ተጠቅሞ የተለያዩ ምርመራዎችን በማድረግ ጤናውን እንዲጠብቅ ትመክራለች።
ከዚህ ቀደም ወደ ውጭ አገር ተልኮ ውጤቱ እስኪመጣ እስከ 45 ቀን ይፈጅ የነበረውን የላብራቶሪ ህክምና በአሁኑ ወቅት በባህሪው ሁለት ቀናት የሚፈልግ ውጤት ካልሆነ በስተቀር በአብዛኛው በሰዓታት ልዩነት ውስጥ የላብራቶሪ ውጤት ማግኘት ይቻላል። ‹‹ስዊዘርላንድና አሜሪካ እንዲሁም በሌሎች የዓለም አገራት አሁን ላይ ያለው የህክምና ቴክኖሎጂ በስዊዝ ዲያግኖስቲክስ ማዕከል ውስጥ ያለ የህክምና ቴክኖሎጂ ነው›› የምትለው የትናየት፤ አገልግሎቱ ለማህበረሰቡ እጅግ አስፈላጊ የሆነ የጤና መፍትሔ ነው ትላለች።
በኢትዮጵያ የላብራቶሪ ህክምና ማዕከል ልዩ የሆነው ስዊዝ ዲያግኖስቲክስ ከቢዝነስ በላይ እንደሆነ የምትናገረው የትናየት፤ የብዙዎችን ድካምና እንግልት ያስቀረና ሕይወት ማዳን የሚችል ነው። ከዚህም በላይ ማዕከሉ በአገልግሎት አሰጣጡ አገርን ከፍ ማድረግ የቻለና የዘመነ መሆኑን በኩራት ትገልጻለች።
በቀጣይም ስዊዝ ዲያግኖስቲክስ ኢትዮጵያን በላብራቶሪ ህክምና ዘርፍ ከፍ በማድረግ፤ ከምስራቅ አፍሪካ ምሳሌ የሆነች ቀዳሚ የጤና ማዕከል እንድትሆን ማድረግ ፍላጎቷ መሆኑን አጫውታናለች። እርግጥ ነው ለተግባራዊነቱ በርካታ መሰናክሎች ይኖራሉ የምትለው የትናየት፤ የትኛውም እንቅፋት ግን ፍጥነቷን ሊገታ ይችል ይሆናል እንጂ ከጉዞዋ ሊያስቀራት እንደማይችል ነው የተናገረችው።
በስዊዝ ዲያግኖስቲክስ የህክምና ማዕከል ውስጥ የሚገኙ ዘመናዊ የህክምና መሳሪያዎች በሙሉ ከስዊዘርላንድ፣ ጀርመንና ቻይና የመጡ መሆናቸውን ጠቅሳ፣ ለአገር ውስጥ ባለሙያዎች ስልጠና በመስጠት የቴክኖሎጂ ሽግግር ማድረግ እንደተቻለም ገልጻለች። በማዕከሉ ከ40 የሚበልጡ ባለሙያዎች የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው መሆኑን ገልጻለች።
ሰዎች የምርመራ ውጤታቸው ከእጅ ንክኪ ነጻ በሆነ መንገድ ተዘጋጅቶ ያለምንም እንግልት ባጠረ ጊዜ እንደሚያገኙት የገለጸችው የትናየት፤ ሰዎች ወደ ማዕከሉ መምጣት ሳይጠበቅባቸው ባለሙያዎች ካሉበት ቦታ ሄደው ናሙናዎችን እንደሚወስዱና ውጤቱም በተመሳሳይ የእጅ ስልክን በመጠቀም በተለያዩ አማራጮቾ ካሉበት ቦታ የሚደርሳቸው መሆኑን አስረድታለች። ለዚህም ማዕከሉ በቂ ባለሙያዎች፣ መሳሪያዎች፣ ሞተረኞችና መኪኖች አሉት። ይህም ሥራውን ቀልጣፋ አድርጎታል ስትል ታብራራለች።
ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ወጪ በማድረግ የብዙዎችን ችግር ለማቃለል የምትሰራው የትናየት፤ በግሏም ሆነ በድርጅቷ ስም የተለያዩ ድጋፎችን ታደርጋለች። መንግሥታዊ ለሆኑ ጥሪዎች ለአብነትም በኮሮና ወረርሽኝ ጊዜ ከአስር ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ብዙዎችን አግዛለች። ‹‹ገበታ ለአገር›› ለተሰኘው ፕሮጀክትም እንዲሁ አምስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ ያደረገች ሲሆን፤ በቀጣይም አገርና ህዝብን በሚጠቅም ማንኛውም የልማት ሥራ ተሳትፎዋን እንደምታጠናክር አረጋግጣለች።
የትናየት ‹‹እርስ በእርስ ከመወነጃጀል ወጥተን አገርን ከፍ በሚያደርግ ሥራ ላይ እንጠመድ፤ በሚከፋፍለን፣ በሚያራርቀንና የልጆቻችን ነገ የሆነችውን ኢትዮጵያን በሚያጠፋ ተግባር ውስጥ ገብተን ተባባሪ አንሁን›› የሚል መልዕክቷን በማስተላለፍ ሀሳቧን ቋጭታለች።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 14/2015