በሕገ መንግሥታችን አንቀጽ 52 ፣ ቁጥር 2 ( ሠ) ላይ የክልል ሥልጣንና ተግባር በሚለው ስር እንደተቀመጠው ክልሎች የየራሳቸውን የፖሊስ ኃይል በማደራጀት እና በመምራት ሰላምና ጸጥታቸውን የማስጠበቅ ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል። በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 55 ቁጥር 7 ላይ የሕዝብ ተወካዮች ስልጣን እና ተግባር በሚለው ሥር ደግሞ የፌደራል መንግሥት የሀገር እና የሕዝብ መከላከያ ፣ የደህንነትና የፖሊስ ኃይል አደረጃጀትን እንደሚወስን ተቀምጧል። በሕገ-መንግስቱ ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው ክልሎች ከፖሊስ ያለፈ ሌላ የጸጥታ ኃይል እንዲያደራጁ አልተፈቀደላቸውም።
ባለፉት የኢህአዴግ አገዛዝ ዘመን ምንም አይነት ሕገ-መንግስታዊ መሰረት ሳይኖራቸው ተፈጻሚ ከሆኑ አደረጃጀቶች መካከል አንዱ የልዩ ኃይል አደረጃጀት መሆኑ በበርካቶች ይተች ነበር። በተለይም በተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ያሉ ጉምቱ ፖለቲከኞችና አክቲቭስቶች የልዩ ኃይልን አደረጃጀት አጥብቀው ከሚተቹት መካከል ግንባር ቀደሞቹ ነበሩ።
ይህ አደረጃጀት ሕገ-መንግሥታዊ መሰረት የሌለውና በተጎራባች ክልሎች መካከል ያለውን ሰላማዊ መስተጋብር እያበላሸ ያለ በመሆኑ ልዩ ኃይል አስፈላጊ አይደለም በሚል ይሞግቱ ነበር። በእርግጥም ባለፉት ዓመታት ሙግታቸው ትክክል እንደነበር ያረጋገጥንባቸውን በርካታ ሁነቶች ተመልክተናል።
በክልሎች መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶችን በሕገ መንግሥታዊ አግባብ ከመፍታት ይልቅ በልዩ ኃይሎች ጡንቻ የመፍታት ሙከራዎች ይደረጉ እንደነበር የምናስታውሰው ነው። ለአብነትም በሶማሌና በኦሮሚያ ፣ በአማራና በቤንሻንጉል፣ በአፋርና በሶማሌ ክልል ወዘተ ልዩ ኃይሎች መካከል ለተደጋጋሚ ጊዜ ይደረጉ የነበሩ የተኩስ ልውውጦችን መከላከያ ሰራዊት ጣልቃ እየገባ ያረጋጋ እንደነበር የምንረሳው አይደለም።
በወሰን አካባቢ የሚኖሩ የሁለት ክልል ማህበረሰቦች በግጦሽ እና በውሃ ምክንያት በተጋጩ ቁጥር የክልል ልዩ ኃይሎች ችግሩን በየራሳቸው መንገድ ለመፍታት በሚወስዷቸው ርምጃዎች ግጭቶቹ እየተባባሱ በርካታ ዜጎች ዋስትና አጥተው ከአካባቢያቸው መፈናቀላቸውንም አንረሳውም።
በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅ የነበሩ የክልል አመራሮችን በመግደል ስልጣን የመቆጣጠር ሙከራ የተደረገውም በልዩ ኃይሎች ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ከአንድ ክልል ወደ ሌላው ክልል የሚደረጉ ማህበራዊ እንቅስቃሴዎችና የንግድ ትስስሮች ሳይቀሩ በልዩ ኃይሎች እቀባ ሲደረግባቸው ተመልክተናል።
የሕዝብ ልጅ የሆነው የሀገር መከላከያ ሰራዊት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ በሕገ-መንግሥቱ የተሰጠውን ስልጣን እና ኃላፊነት ለመወጣት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ልዩ ኃይሎች ሲያደነቃቅፉት እና አንዳንዴም ሲተኩሱበት ስናይ ደግሞ የዚህ ኃይል አደረጃጀት ትክክል አለመሆኑን የበለጠ እንረዳለን።
ዛሬ በመንግሥት እና በሕወሓት መካከል የተደረገው እርቅ እና አሁን ያለንበት የሰላም ድባብ በቅርብ ጊዜ ለተፈጠሩ አገራዊ ቀውሶች መንስኤ የሆኑ ጉዳዮችን እያነሳን እንድንማማርባቸው ላያደርገን ይችላል። ግን አንድ እውነታን ብናነሳ ክፋት ያለው አይመስለኝም።
በሰሜኑ የአገራችን ከፍል ለፈነዳው የእርስበእርስ ጦርነት እና ኢትዮጵያ ላለፉት ሁለት ዓመታት ላጋጠማት የሠላም ቀውስ እንዲሁም በጦርነቱ ቀጣና ያሉት ሕዝቦቿ ለከፈሉት ዋጋ ወይም ለወደመው ንብረት አንዱ ምክንያት ይሄው የልዩ ኃይል አደረጃጀት እንደነበር መርሳት የለብንም።
ይህን ስንል ግን በሶማሌ ክልል ድንበር ተሻግረው ጥቃት ለመፈፀም የሞከሩ የአልሻባብ ታጣቂዎችን በመደምሰስ እና ባለፉት ሁለት ዓመታት በሰሜኑ የአገራችን ክፍል የተከሰተውን ግጭት እንዲሁም በሸኔ ታጣቂዎች ላይ በሚወሰደው ርምጃ የሁሉም ክልል ልዩ ኃይሎች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ያደረጉት አስተዋጽኦ ዋጋ አልነበረውም ማለታችን አይደለም።
ይሁን እና የልዩ ኃይል አደረጃጀት ለኢትዮጵያና ለሕዝቦቿ ሕልውና ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ ይልቅ በሰላማችን ላይ እየፈጠረ ያለው ተጽዕኖ ሚዛን እየደፋ መምጣቱ ለሁላችንም ግልጽ ነው። ስለሆነም ይህ አደረጃጀት መስመር እንዲይዝ መድረጉ ሕዝብንም አገርንም ተጠቃሚ የሚያደርግ እንጂ የሚጎዳ አይደለም።
መከላከያ ሰራዊት በተሰጠው ስልጣን መሰረት የአገሪቱን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ በተንቀሳቀሰ ቁጥር የሚገዳደረው ሌላ ኃይል መፈጠሩ እንደ አገር አንድ ሆነን እንዳንቆም የሚያደርግ ብቻ ሳይሆን የሚበታትነንም ጭምር መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። ይህ ደግሞ በተግባር የታየ ጉዳይ ነው።
የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ከረዥም ጊዜ ልምድና ተሞክሮ ያገኘናቸውን መረጃዎች በመቀመር የአደረጃጀት ለውጥ እንደሚያደርግ ይፋ አድርጓል። በዚህም መሰረት የክልል ልዩ ኃይሎች በሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ በፌዴራል ፖሊስ እና በክልል ፖሊስ አደረጃጀት ውስጥ እንዲታቀፉ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታውቋል።
በዚህም ብዙኃኑ ሰላም ወዳድ ኢትዮጵያዊ ደስተኛ መሆኑን በማህበራዊ ሚዲያ ሲገልፅ ይታያል። አንዳንዶች እንደውም ውሳኔው በመዘግየቱ ብዙ ዋጋ እንዳስከፈን ጭምር በመጥቀስ በአፋጣኝ ወደ ተግባር እንዲገባ ሃሳብ ይሰጣሉ።
ከዚህ በተቃራኒ ግን ይህ በተፎካካሪ ፓርቲዎችና በአክቲቪስቶች ከበርካታ ዓመታት በፊት ሕገ-መንግሥታዊ መሰረት የለውም ተብሎ ሲተች የነበረው የልዩ ኃይሎች አደረጃጀት ዛሬ ደግሞ በሌላ አደረጃጀት እንዲዋቀር ሲደረግ እነዚሁ ፖለቲከኞች ለምን? ሲሉ እየሰማን ነው።
ፍላጎታቸው ምንድነው የሚለውን እንቆቅልሽ ለመፍታት ጊዜ አናጠፋም። እውነታው ግን ልዩ ኃይሎችን በአዲስ አደረጃጀት እንዲዋቀሩ ማድረግ የአገሪቱን ሰላም ከማስፈን ባሻገር ትልቁን የኢትዮጵያ ምስል የሚመለከት ጠንካራ የሀገር መከላካያ እና የፌዴራል ፖሊስ እንዲገነባ ያደርጋል። አንድ ወጥ የሆነ የጸጥታ ኃይል ሲገነባ ደግሞ ውጫዊም ውስጣዊም ስጋቶች እንዳይኖሩብን ያስችለናል።
እንደሀገር ካሉብን ስጋቶች አንጻር ጠንካራ እና ወጥ የሆነ ዘመናዊ የጦር ኃይል መገንባት ይጠበቅብናል። ይህንን እውን ለማድረግ ደግሞ የተበታተነውን ኃይላችንን ወደ አንድ በማሰባሰብ አስፈላጊውን ወታደራዊ ቁመና ተላብሰን በሁለንተናዊ ዝግጁነት በተጠንቀቅ መቆም ይጠበቅብናል፤ ለዚህ ደግሞ የልዩ ኃይሉን አደረጃጀት መቃኘት አስፈላጊና ወቅታዊ ነው።
ሜላት ኢያሱ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 14/2015