የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩትም የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ሕዝቦች ሰፊው ታሪካቸው ከግጭት ትርክቶች ጋር የተያያዘ ነው። በዚህም የከፈሉት ሆነ እየከፈሉት ያለው ዋጋ በቀላሉ የሚሰላ አይደለም።አሁን ላሉበት ችግር እና ድህነት ዋነኛው ምክንያትም ይሄው እውነታ ነው።
ካለው ጂኦ – ፖለቲካል ስትራቴጂ አንጻር የብዙዎችን ትኩረት ከመሳቡ የተነሳ ፤አካባቢውን ለመቆጣጠር በግልጽም ይሁን በስውር የሚደረጉ ጥረቶች ለአካባቢው ሃገራት ሰላም እጦትና አለመረጋጋት እንደ አንድ ምክንያት የሚጠቀስ ነው።
በአብዛኛው በሀገራቱ የውስጥ ጉዳዮች የሚደረጉ ጣልቃ ገብነቶች፤ ግጭቶች ዘላቂ መፍትሄዎች እንዳያገኙ ከማድረግ ባለፈ፤ የሀገራቱ ሕዝቦች የተረጋጋና በሰላም የመኖር ህልማቸውን በማሳጣት በተደጋገሙ የግጭት አዙሪቶች ውስጥ እንዲጓዙ አስገድዷቸዋል።
የአካባቢው ሀገራት ሕዝቦች ከድንበር መስመሮች ባለፈ ቤተሰብ የሆኑ ፣ የትኞቹንም አለመግባባቶች በሰላም መፍታት የሚያስችሉ የዳበሩ ትውልድ ተሻጋሪ መንፈሳዊ ፣ ማኅበራዊና ባህላዊ እሴቶች ያሏቸው፤ በዚህም ዘመናትን ተሻግረው ዛሬ ላይ መድረስ የቻሉ ናቸው።
እነዚህ ሕዝቦች በተለያዩ ወቅቶች በተፈጠሩ የሰላም እጦቶች ብዙ ዋጋ ከፍለዋል፤ ከያንዳንዱ ግጭት ማግስት በብዙ የልብ ስብራትና አንገት መድፋት ተጋልጠዋል ። ከሁሉም በላይ እያንዳንዷ ግጭት በልማት ተመንድገው ትልቅ ሀገር የመሆን ራዕያቸውን ተናጥቋቸዋል።
ስለ ሰላም በየወቅቱ ብዙ ዋጋ ለመክፈል ቢገደዱም፤ በከፈሉት ዋጋ ልክ ሰላማቸውን አስጠብቀው፤ወደሚፈልጉት ልማት በመግባት ለራሳቸውም ሆነ ለመጪው ትውልድ የተመቸ አካባቢ ለመፍጠር የሚያደርጉት ጥረት ዛሬም በተግዳሮቶች የታጠረ ሆኗል።
የአካባቢው ሀገራት ሕዝቦች ትናንት ላይ ከቀደመው የግጭት ትርክት ወጥተው ፤ አዲስ የሰላም ፣ የትብብርና የልማት ትርክት ለመጀመር በሚያስችል አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ ገብተው እንደነበርና ይህም ለሃገራቱ ሕዝቦች ታላቅ የምስራች ሆኖ መበሰሩ የሚታወስ ነው።
በዚህ አዲስ ጅማሬ ውስጥ ሀገራቱ በርግጥም ለራሳቸው ሰላም እንደማያንሱ በተጨባጭ ታይቷል። በሃገራቱ ሕዝቦች የልብ ጽላት ላይ ወንድማማችነትና ከዚህ የሚመነጭ የጋራ ተጠቃሚነት በደማቅ ቀለም የተጻፈ መሆኑም ተመልክቷል።
ይህ እውነተኛ የሆነው የሃገራቱ ሕዝቦች የጋራ መሻት በብዙ ተግዳሮቶች ውስጥ እያለፈ ቢሆንም፤ ለሃገራቱ ሕዝቦች ብሩህ ነገዎች አልፋና ኦሜጋ የመሆኑ እውነታ ዛሬም ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም።ፈተናዎችን በጽናት ተሻግሮ የተስፋቸው ብስራት መሰረት መሆኑ የማይቀር ነው።
ዛሬ ላይ እነዚህ ሕዝቦች በብዙ ተግዳሮቶች እየተፈተኑ ናቸው፤ የጋራ ሰላማቸው ሊያጎናጽፋቸው ከሚችለው የጋራ ተጠቃሚነት አንጻር፤ ራሳቸውን በተሻለ መልኩ ማዘጋጀትና ለጋራ ሰላማቸው የሚሆን ሁለንተናዊ ዝግጁነት መፍጠር ይጠበቅባቸዋል።
ከሁሉም በላይ ትናንትም ሆነ ዛሬ የአካባቢያቸውን ሰላም በብርቱ እየተፈታተነ ያለው ችግር ከእነርሱ አቅም በላይ አለመሆኑን ተረድተው፤ ለችግሮቹ ዘላቂ መፍትሄ በማፈላለግ ለተስፋቸው ተጨባጭ አቅም መሆን ይኖርባቸዋል።
በተለይም አሁን ላይ በሱዳን ያለውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ በውይይትና በድርድር የሚቋጭበትን መንገድ በማፈላለግ ከሁሉም በላይ የአካባቢው ሃገራት ሕዝቦች በአስቸጋሪ ወቅት አንዳቸው ለአንዳቸው ተስፋ መሆናቸውን በተግባር ማሳየት ይጠበቅባቸዋል።
በግጭት ውስጥ ያሉ የሱዳን የፖለቲካ ኃይሎች ችግሮቻችውን፣ የሕዝቦቻቸውን የሰላም መሻት ታሳቢ ባደረገ መንገድ ፣ በሰከነ መንፈስ ተወያይተው ወደ ሰላም የሚመጡበትን አስቻይ ሁኔታ በማመቻቸት የመፍትሄው አካል መሆን ይገባቸዋል።
የሱዳን ሕዝብ በዘመናት ውስጥ ባካበታቸው መንፈሳዊ ፣ ማህበራዊና ባህላዊ እሴቶች ተደግፎ ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት የሰላሙ ባለቤት የመሆን አቅሙም ብቃቱም ፤ጥበቡም ማስተዋሉም ያለው ሕዝብ ነው። ለዚህ ደግሞ ነገዎች ሕያው ምስክር ይሆናሉ።
ኢትዮጵያና ሕዝቦቿም ለሱዳን ወንድምና እህቶቻቸው ያላቸው ክብርና ፍቅር ሁሌም የጸና እንደመሆኑ ሱዳናውያን በራሳቸው መንገድ የራሳቸውን መፍትሄ እንዲያመጡ ለሚያደርጉት ጥረት ከፍተኛ ቦታ ይሰጣሉ። ዘመናትን የተሻገረውን የኢትዮ ሱዳን ወዳጅነት በሀሰት ወሬ ለማበላሸት የሚፈልጉ አካላትም እኩይ ሃሳባቸው መቼም ቢሆን የሚሳካ አይሆንም!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 14/2015