ከአለማችን ትልልቅ የማራቶን ውድድሮች ዋነኛው የለንደን ማራቶን ነገ ይካሄዳል። ይህ ታላቅ የሩጫ ድግስ እንዳለፉት አመታት ሁሉ ዘንድሮም በርካታ የአለም ከዋክብት አትሌቶችን በአንድ ላይ የሚያፋልም ሲሆን በዚህ አመት ግን በአርባ ሁለት ኪሎ ሜትሩ ውድድር የሚፎካከሩ የርቀቱ ፈርጦች ቁጥር መበርከቱ የተለየ አድርጎታል።
በወንዶች መካከል የሚካሄደው ውድድር በበርካታ ከዋክብት አትሌቶች እንደሚደምቀው ሁሉ በሴቶች መካከል የሚደረገውም ፉክክር የበለጠ በኮከቦች የደመቀ ነው።በዚህም ርቀቱን ከ2:18 ሰአት በታች ማጠናቀቅ የቻሉ ስድስት ሴት አትሌቶችን ጨምሮ በርካታ የረጅም ርቀት ከዋክብቶች ለመጀመሪያ ጊዜ እርስበርስ ይፋለማሉ። ከእነዚህ መካከል ዋና ዋናዎቹን በጥቂቱ እንመልከት።
በነገው የለንደን ማራቶን ኬንያዊቷ አትሌት ብሪጊድ ኮስጌ ከሌሎች የበለጠ ትኩረት ያገኘች አትሌት ነች። በ2019 የቺካጎ ማራቶን 2:14:04 ሰአት በመሮጥ የርቀቱን የአለም ክብረወሰን በሰላሳ ሰከንድ ማሻሻል የቻለችው ይህች አትሌት የተለየ ትኩረት ቢሰጣት አይገርምም።
2019 እና 2020 ላይ የለንደን ማራቶንን በተከታታይ ያሸነፈችው ኮስጌ ዘንድሮ ሶስተኛ ድሏን አልማለች። ኮስጌ በአጠቃላይ ዘንድሮ በለንደን ማራቶን ስትፎካከር አራተኛዋ ሲሆን ከሁለቱ ተከታታይ ድሎቿ ባሻገር 2018ና 2021 ላይ ሁለተኛ ሆና ማጠናቀቋ ይታወሳል።
ያለፈው ውድድር አሸናፊዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ያለምዘርፍ የኋላው ዳግም ለቻምፒዮንነት የታጨች ሲሆን፤ የአለም አስራ ሁለተኛው ፈጣን ሰአት ባለቤት ናት። ይህም ሰአቷ(2:17:23) ከአመት በፊት በሃምቡርግ ማራቶን ያስመዘገበችው ነው። ይህም ማራቶንን ለመጀመሪያ ጊዜ በሮጠች አትሌት የተመዘገበ ፈጣኑ ሰአት እንደሆነ ይታወቃል። ያለምዘርፍ ለመጀመሪያ ጊዜ በለንደን ማራቶን ተሳትፋ ባለፈው አመት ስታሸንፍ መሃል ላይ ወድቃ እንደነበር ይታወሳል። ያምሆኖ ያስመዘገበችው 2:17:26 ሰአት በለንደን ማራቶን ታሪክ ሶስተኛው ፈጣን ሰአት ነው።
ባለፉት ቅርብ አመታት በመካከለኛና ረጅም ርቀት የመም ውድድሮች ከዋክብት የነበሩ በርካታ አትሌቶች ፊታቸውን ወደ ማራቶን እያዞሩ ይገኛሉ። በርካቶቹ በአትሌቶችም በነገው የለንደን ማራቶን በአንድ ላይ የ42 ኪሎ ሜትር ፉክክር ያደርጋሉ። ከነዚህ መካከል ኢትዮጵያውያኑ ከዋክብት አልማዝ አያናና ገንዘቤ ዲባባ ባለፈው አመት የመጀመሪያ የማራቶን ውድድራቸውን አምስተርዳም ላይ ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን በ2016 ሪዮ ኦሊምፒክ የ10ሺ ሜትር ክብረወሰንን መስበር
የቻለችው አልማዝ በ2:17:20 በሆነ ሰአት አሸናፊ ስትሆን ገንዘቤ ሁለተኛ ሆና ነበር ያጠናቀቀችው። ሁለቱ ኢትዮጵያውያን ከዋክብት ባለፉት ቅርብ አመታት በተለይም በ5ሺ ሜትር ያሳዩትን ድንቅ ፉክክር በታላቁ የማራቶን ውድድር ከሌሎች የርቀቱ ፈርጦች ጋር ይደግማሉ ተብሎ በጉጉት ይጠበቃል።
ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ የኔዘርላንድስ አትሌት ሲፈን ሃሰን ባለፈው ቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ በ5እና 10ሺ ሜትር የወርቅ በ1500 ሜትር ደግሞ የነሐስ ሜዳሊያ ካጠለቀች በኋላ የመም ውድድር ስኬታማ ዘመኗም ባለፈው አመት የአለም ቻምፒዮና ሲጠልቅ ታይቷል።
በዚህም ፊቷን ወደ ማራቶን አዙራ በነገው የለንደን ማራቶን የመጀመሪያ ፍልሚያዋን ታደርጋለች። ሲፈን በቶኪዮ ኦሊምፒክ ዋዜማ የአልማዝ አያናን የ10ሺ ሜትር የአለም ክብረወሰን መስበር ብትችልም 48 ሰአት ሳይሞላው በኢትዮጵያዊቷ ድንቅ አትሌት ለተሰንበት ግደይ መነጠቋ ይታወሳል።
ግዙፍ የአትሌቲክስ ስኬት ካላቸው ከነዚህ አትሌቶች በተጨማሪ በርካታ ጠንካራ ኢትዮጵያውያን አትሌቶችም በነገው ፉክክር ቀላል ተፎካካሪ እንደማይሆኑ ይጠበቃል። ከነዚህ መካከል 2022 ላይ በዚሁ ለንደን ማራቶን 2:18:32 በሆነ ሰአት ሶስተኛ ሆና ያጠናቀቀችው መገርቱ አለሙ ተጠቃሽ ነች። የነገው ውድድሯም ለንደን ላይ ሶስተኛዋ ሲሆን 2020 ላይ አምስተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ አይዘነጋም። 2017 ላይ በማራቶን መወዳደር የጀመረችው ይህች አትሌት የነገው ውድድሯ አስራ አራተኛ ይሆናል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 14 ቀን 2015 ዓ.ም