የለንደን ማራቶን ሁሌም የርቀቱን በርካታ ከዋክብት አትሌቶች በአንድ ላይ በማፋለም ይታወቃል። የዘንድሮው ግን ለየት ያለ ነው። በወንዶች በታሪክ በርቀቱ አምስት ፈጣን ሰዓት ካላቸው አትሌቶች ሶስቱን በአንድ ላይ አፋጧል። በዚህ ላይ ርቀቱን 2:04 ሰዓት ውስጥ ያጠናቀቁ ስድስት አትሌቶች የፊታችን እሁድ ሊያፋልም መዘጋጀቱ የዘንድሮውን ለንደን ማራቶን የተለየ አድርጎታል።
በዚህ ፍልሚያ የማይሳተፍ የርቀቱ ኮከብ ቢኖር ኬንያዊው ኢሉድ ኪፕቾጌ ብቻ ነው። እሱም ባለፈው ሳምንት በቦስተን ማራቶን ተሳታፊ በመሆኑ ነው የዘንድሮው ለንደን ማራቶን ያመለጠው። በተረፈ ግን ዓለም ላይ አሉ የተባሉ የማራቶን ከዋክብት፣ ከኦሊምፒክ እስከ ዓለም ቻምፒዮና፣ ከአገር አቋራጭ እስከ ቤት ውስጥ ውድድር ተደራራቢ የድል ካባ የደረቡ ዘመን አይሽሬ የአትሌቲክስ ፈርጦች የዚህ ታላቅ ድግስ ድምቀት ይሆናሉ። ከነዚህ መካከል ዋና ዋናዎቹን እንመልከት።
ጀግናው ኢትዮጵያዊ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ የዚህ ውድድር ድምቀት ሆኖ በቀዳሚነት የሚጠቀስ ኮከብ ነው። የረጅም ርቀት የምን ጊዜም ምርጡ አትሌት ቀነኒሳ በመም ውድድሮች ሁሌም ደማቅ የሆነ ታሪኩን በማራቶን ለመድገም ዛሬም እየተጋ ይገኛል። ሶስት የኦሎምፒክ ወርቆች፣ ስድስት የቤት ውስጥና ከቤት ውጪ የዓለም ቻምፒዮና ስኬቶች፣ አስራ አንድ የአገር አቋራጭ የቻምፒዮንነት ክብሮችን ማሳካት የቻለው አይበገሬው አትሌት ቀነኒሳ የ5ና10ሺ ሜትር የቀድሞ ክብረወሰኖቹ በዘንድሮው የለንደን ማራቶን ከተፎካካሪዎቹ የበለጠ እንዲደምቅ አድርጎታል።
በእርግጥ ቀነኒሳን ከሌሎች አትሌቶች የበለጠ ትኩረት እንዲሰጠው ያደረገው ምክንያት የቀድሞ ታሪኩ ብቻ አይደለም። ፊቱን ወደ ማራቶን ካዞረ ወዲህ ካደረጋቸው አስራ ሶስት ውድድሮች ሶስቱን አቋርጦ ቢወጣም በርቀቱ የአለማችን ሁለተኛው ፈጣን አትሌት ነው።
እኤአ 2014 ላይ የመጀመሪያውን የማራቶን ፍልሚያ ፓሪስ ላይ በማድረግ ማሸነፍ የቻለው አንበሳው አትሌት ቀነኒሳ 2016 እና 2019 ላይ ያሸነፋቸው የበርሊን ማራቶኖች በርቀቱ ትልቅ ስኬት ሆነው ይታወሳሉ። በተለይም 2019 ላይ ባሸነፈበት የበርሊን ማራቶን 2:01:41 በሆነ ሰዓት ሲያሸንፍ ሁለተኛው የርቀቱ ፈጣን አትሌት የሆነበት ታሪክ በሁለት ሰከንዶች ዘግይቶ የዓለም ክብረወሰን ከእጁ የወጣበት አጋጣሚ በርካቶች የተቆጩበት ነው።
ቀነኒሳ ዘንድሮ በለንደን ማራቶን ሲሳተፍ አምስተኛው ይሆናል። ከዚህ በፊት ባደረጋቸው አራት ፍልሚያዎች 2016 ሶስተኛ፣ 2017 ሁለተኛ፣ 2018 ስድስተኛና 2022 አምስተኛ ሆኖ ማጠናቀቁ አይዘነጋም። ዘንድሮ ግን ለንደን ላይ ከቀደሙት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ አስቧል።
ከቀነኒሳ በተጨማሪ የወቅቱ የርቀቱ የዓለም ቻምፒዮን ታምራት ቶላ ትኩረት የተሰጠው አትሌት ነው። 2019 እና 2020 ላይ በዚሁ የለንደን ማራቶን ስድስተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ታምራት ዘንድሮ በሶስተኛ ተሳትፎው ለቻምፒዮንነት ይፋለማል። ይህ ድንቅ ኢትዮጵያዊ አትሌት 2021 ላይ በአምስተርዳም ማራቶን ያስመዘገበው 2:03:39 ሰዓት በርቀቱ አስራ ሁለተኛው ፈጣን አትሌት ያደርገዋል። ባለፈው ዓመት በኦሪገን የዓለም ቻምፒዮን ከመሆኑ ባሻገር 2017 ላይ በለንደን የዓለም ቻምፒዮና የብር ሜዳሊያ ማጥለቁ ይታወሳል። 2019 በዱባይና 2022 በቶኪዮ ማራቶን ማሸነፉም ከብዙ በጥቂቱ የሚጠቀሱ ስኬቶቹ ናቸው።
ለሶስተኛ ጊዜ በለንደን የሚፎካከረው ልኡል ገብረስላሴ ባለፈው ዓመት በ2:05:12 ሰዓት ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀ ጠንካራ አትሌት ነው። 2018 ላይ በዱባይ ማራቶን ያስመዘገበው 2:04:02 ምርጡ ሰዓት ሲሆን በቫሌንሲያ ማራቶን ሶስት ጊዜ ተሳትፎ 2018 ላይ ድል ቀንቶታል። 2021 በአምስተርዳም ማራቶን ሶስተኛና 2022 በሮተርዳም ማራቶን ሁለተኛ ሆኖ ያጠናቀቀበት ውጤትም የአትሌቱን ጥንካሬ ያሳያል።
አራተኛው የማራቶን ፈጣን አትሌት ብርሃኑ ለገሰ ሌላኛው የለንደን ማራቶን ተፎካካሪ ኮከብ ነው። 2019 በርሊን ማራቶን ላይ ያስመዘገበው 2:02:48 ሰዓት የዓለም አራተኛው ፈጣን አትሌት ያሰኘው ነው። ይህ ጠንካራ ኢትዮጵያዊ አትሌት ባለፈው ለንደን ማራቶን ስድስተኛ ሆኖ ማጠናቀቁ የሚታወስ ሲሆን የዘንድሮው ተሳትፎ ለሶስተኛ ተከታታይ ጊዜ ነው። በ2019 እና 2020 ቶኪዮ ማራቶን ሁለት ተከታታይ ድሎችን አጣጥሟል። ቫሌንሺያ ላይ ደግሞ ኮከብነቱን ያስመሰከረበት 2:03:16 ሰዓት ሶስተኛ ሆኖ ባጠናቀቀበት 2020 ውድድር አስመዝግቧል።
ሌላኛው ኢትዮጵያዊ ክንዴ አጥናው ባለፈው የለንደን ማራቶን አራተኛ ሆኖ ያጠናቀቀ ሲሆን ዘንድሮ ከጠንካራ ተፎካካሪዎች አንዱ ነው። ይህ የሰላሳ ዓመት አትሌት በርቀቱ በርካታ ድንቅ ታሪኮች የሰራ ሲሆን በዘንድሮው የለንደን ማራቶን የኢትዮጵያውያንን ስብስብ አስፈሪ ከሚያደርጉት ምክንያቶች አንዱ ነው።
ሁሉም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ትልቅ ስም ያላቸው ቢሆንም የለንደን ማራቶንን አሸንፈው አያውቁም። በዘንድሮው ውድድር የለንደን ማራቶንን ከዚህ ቀደም አሸንፎ የሚሳተፈው ኬንያዊው አሞስ ኪፕሩቶ ብቻ ነው። ያለፈውን ዓመት ውድድር በድል የፈፀመው ይህ አትሌት በርቀቱ ምርጡን ሰዓት (2:03:13) ያስመዘገበው ከሁለት ዓመት በፊት ቶኪዮ ላይ ነው። ይህም በርቀቱ ታሪክ አስራ አንደኛው ፈጣን አትሌት የሚያደርገው ሲሆን ለኢትዮጵያውያኑም አትሌቶች ፈታኝ እንደሚሆን ይጠበቃል።
በ2019 የዶሃ የዓለም ቻምፒዮናም የነሐስ ሜዳሊያ አሸናፊ እንደነበር ይታወሳል። በዓለም ግማሽ ማራቶን ቻምፒዮና ተደጋጋሚ ድሎችን ያሳካው ሌላኛው ኬንያዊ አትሌት ጂኦፍሪ ኮምዎረር ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ለንደን ማራቶን ጎራ ብሎ ምን ሊፈጥር እንደሚችልም ለማየት በርካቶች ጓግተዋል። በተመሳሳይ ኢትዮጵያዊው አትሌት ሰይፉ ቱራ ለመጀመሪያ ጊዜ በለንደን ማራቶን ተፎካካሪ ነው።
ይህ አትሌት 2021 ላይ የቺካጎ ማራቶንን 2:04:29 ሰዓት ያሸነፈ ሲሆን በሚላንና ሻንጋይ ማራቶኖችም የድል ታሪክ አለው። በሁለት ኦሊምፒኮች አራት የወርቅና በሶስት የዓለም ቻምፒዮናዎች በርካታ ድሎችን በአምስትና አስር ሺ ሜትር የተጎናፀፈው እንግሊዛዊው ዝነኛ አትሌት ሞ ፋራህም የዚህ ታላቅ ፉክክር ድምቀት ይሆናሉ ተብለው ከሚጠበቁ ከዋክብት አትሌቶች አንዱ ነው።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 13 ቀን 2015 ዓ.ም