ብሔራዊ ቴአትር በእድሳት ምክንያት ዝግ ሆኗል
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር በእድሳት ምክንያት እስከ ግንቦት 01 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ ዝግ ስለሚሆን ትርዒቶች እንደማይቀርቡ አስታውቋል። እድሳቱን የሚያደርገው የአውሮፓ ህብረት ነው።
የቴአትር ቤቱ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ በፍቃዱ ከፈለኝ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ እድሳቱ የአውሮፓ ህብረት ግንቦት 01 ቀን 2011 ዓ.ም ለሚያካሂደው አፍሮ-ኢሮፕያን የባህል ትውውቅ መድረክ የታሰበ ነው። ግንቦት 01 ቀን ከቀኑ 10፡00 ሰዓት ጀምሮ ሊካሄድ እቅድ በተያዘለት በዚህም ዝግጅት ላይ የሙዚቃ ድግስ የሚካሄድ ሲሆን፤ 12 ሙዚቀኞች ከአፍሪካና ከአውሮፓ ተጋብዘው ሥራዎቻቸውን ያቀርባሉ።
የክዋኔው አዘጋጅ የሆነው የአውሮፓ ህብረት ለዚሁ ክዋኔ ሲል በብሔራዊ ቴአትር አዳራሽ ላይ መጠነኛ እድሳቶችን የሚያደርግ ሲሆን፤ እድሳቱ አጠቃላይ ፅዳት፣ የብረታ ብረት ሥራዎችን እንዲሁም ከኤሌክትሪክና መብራት ጋር የተገናኙ ሥራዎችን የሚያጠቃልል ነው። ግንቦት 01 ቀን ከሚኖረው ክዋኔ ቀጥሎም ቴአትር ቤቱ ክፍት ሆኖ ወደ ቀደሞ ሥራው የሚመለስ ይሆናል ብለዋል።
ቴአትር ቤቱ ከሚያዝያ 16 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ዝግ እንደነበር ይታወሳል።
13ኛው አዲስ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል ማክሰኞ ይጀምራል
በኢኒሼዬቲቭ አፍሪካ የሚዘጋጀው አዲስ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል 13ኛው ዝግጅት ከነገ በስቲያ ማክሰኞ ሚያዝያ 22 ቀን 2011 ዓ.ም ይጀምራል።
እስከ ሚያዝያ 27 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ በሚቆየው በ13ኛው አዲስ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል፤ ሳምንቱ በሰብዓዊ መብት ሳምንትነት ይካሄዳል። በቆይታውም በማኅበራዊ ፍትሕ፣ ማንነትና የባህል ብዝሃነት ላይ ያተኮሩ 60 በላይ የተመረጡ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ፊልሞች ይቀርባሉ። ፊልሞቹ በአልያንስ ኢትዮ ፍራንሲስ፣ በቫምዳስ፣ በአገር ፍቅር ቴአትር እና በጣልያን የባህል ማዕከል እንዲሁም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት ኤጀንሲ /ወመዘክር/ ይታያሉ ተብሏል።
ፌስቲቫሉ ከፊልም እይታዎች በተጨማሪ ዓውደ ጥናቶች፣ የምክክርና የልምድ ልውውጥ መድረኮች እንዲሁም ወርክ ሾፖችን ያካተተ እንደሚሆንም ነው የፌስቲቫሉ ዋና ዳይሬክተር አቶ ክቡር ገና የተናገሩት። የመክፈቻ ሥነስርዓቱ ሚያዝያ 22 ቀን 2011 ዓ.ም የኪነጥበብ ባለሙያዎችና የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ማምሻውን ከ11፡30 ጀምሮ በጣልያን የባህል ማዕከል ይሆናል።
ኤጀንሲው 75ኛ ዓመቱን ያከብራል
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሐፍት ኤጀንሲ 75ኛ ዓመቱን ከረቡዕ ሚያዝያ 23 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ አምስት ቀናት በተለያዩ ክዋኔዎች ያከብራል።
በልደት በዓሉም በተለያዩ ዓውደ ጥናቶችና የውይይት መድረኮች፤ የጥንታዊ ቅርሶች ጉብኝቶች፣ የአንጋፋ ደራስያን ተሞክሮዎችንና የወመዘክር ትዝታዎችን በማውሳትና መሰል መርሐ ግብሮች ይከበራል ተብሏል። ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት ኤጀንሲ በ1936 ዓ.ም ነበር፤ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ «የሕዝብ ቤተመጻሕፍት ወመዘክር» በሚል ስያሜ የተቋቋመው።
ሰም እና ወርቅ 17ኛው ምሽት ሐሙስ ይካሄዳል
ሰም እና ወርቅ 17ኛው የኪነ ጥበብ ምሽት ሚያዝያ 24 ቀን 2011 ዓ.ም በቫምዳስ መዝናኛ ማዕከል ማምሻውን ከ11:00 ሰዓት ጀምሮ ይካሄዳል።
በዚህኛው ወር ልዩ የበዓል መዝናኛ ዝግጅት የሚኖር ሲሆን፤ ዶክተር ብርሃኑ ኃይለሚካኤል፣ መጋቢ ሀዲስ እሸቱ አለማየሁ፣ ጋዜጠኛ ንጉሴ አክሊሉ፣ ገጣሚ ወንድዬ አሊ፣ ጋዜጠኛ መሰለ መንግሥቱ (ኦያያ)፣ መምህርት እፀገነት ከበደ፣ ከገጣምያን ደግሞ ተሾመ ብርሃኑ፣ ዮፍታሔ ብርሃኔ፣ ቶማስ አድማሱ፣ ኤልሳ ሙሉጌታ እና አብስራ አሰፋ ይገኛሉ። ከመሶብ የባህል ቡድን ጋር በመሆንም ሥራዎቻቸውን እንደሚያቀርቡ አዘጋጆቹ ገልጸዋል።
የጎሳዬ ተስፋዬ «ሲያምሽ ያመኛል» የሙዚቃ ድግስ ሊካሄድ ነው
«ሲያምሽ ያመኛል» የድምፃዊ ጎሳዬ ተስፋዬ የሙዚቃ ድግስ ሚያዝያ 26 ቀን 2011 ዓ.ም በጊዮን ሆቴል ይካሄዳል።
የድግሱ አዘጋጅ ሀበሻ ዊክሊ ሰሞኑን በሰጠው መግለጫ፤ ድምፃዊው ሥራዎቹን ከቅላጼ ባንድ ጋር ያቀርባል። ማምሻውን ከ11፡ 30 የሚጀምረው ድግስ ላይ ከ11ሺ እስከ 20ሺ የድምፃዊው አድናቂዎች እንደሚገኙ ይጠበቃል። የመግቢያ ዋጋ መደበኛ 499 ብር፣ ቀድመው ለሚገዙ 399 ብር፣ ለተማሪዎች 299 ብር ሲሆን፤ የክብር መቀመጫ ሥፍራ (ቪ አይ ፒ) 899 ብር እንደሆነም ተገልጿል።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 20 ቀን 2011 ዓ.ም