ሙስሊሞች የርኅራሔ ፤የደግነት ፤የመረዳዳት እና የፍቅር ወር የሆነውን የሮመዳንን የጾም ጊዜ ሲጨርሱ የኢድ በዓል ቦታውን ይረከባል፡፡ ኢድ የሮመዳን ጾም የፍቺ በዓል ነው፡፡ ኢድ ማለት ደስታ ማለት ነው። ሙስሊሞች ለአንድ ወር ያህል በትጋት ሲያከናወኑት የነበረውን የጾም ጊዜ ጨርሰው በዓላቸውን የሚያከብሩበት የደስታ ወቅት ነው፡፡ በዚህ የደስታ በዓል ላይ ወዳጅ ከወዳጁ ይጠያየቃል፤ የተራቡና የታረዙ ወገኖች ይጎበኛሉ፤ ሁሉም ያለውን ያካፍላል፤ ደስታ በሁሉም ቤት ይገባል፡፡
ዛሬ የሚከበረውም 1444ኛውን የኢድ በዓል እነዚህን እሴቶች ተላብሶ የሚከበር ነው፡፡ ምክንያቱም ኢድ- የደስታ በዓል ነው፡፡ ኢድ አልፈጥር የቅዱሱ ረመዳን ወር ፆም መፍቻ በዓል በመሆኑ በጾም ውስጥ ከምግብና ከመጠጥ እንዲሁም ከአላስፈላጊ ተግባራት ተቆጥቦ የቆየ ሰውነት ወደ ተለመደው የአመጋገብ ሥርዓት የሚመለሰብት፤ እና ይህንኑም ከወዳጅ ዘመድ ጋር ማዕድ አብሮ በመቋደስ በደስታ የሚዋልበት ቀን ነው፡፡ በተለይም ልጆች እና ሴቶች ባማሩ ልብሶች አሸብርቀው የበዓሉ ድምቀት ሆነው ስለሚውሉ የበዓሉን ደስታ እጥፍ ድርብ ያደርገዋል፡፡
ኢድ፣ የአብሮነት በዓል ነው፡፡ ኢድ ወዳጅ ዘመድ ተሰባስቦ በዓሉን በጋራ የሚያሳልፍበት የፍቅር በዓል ነው፡፡ ከዚህ በሻገር ግን በኢትዮጵያ ያለው የኢድ አከባበር ለየት የሚልባቸው እሴቶች አሉት፡፡ ይሄም ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ የተለያዩ እምነቶችን በፀጋ የተቀበለች እና የተለያዩ እምነት ተከታዮችም ተከባብረው የሚኖሩባት የተለየች ሀገር ከመሆኗ ጋር የሚገናኝ ነው፡፡ ኢድን በመሳሰሉ የበዓል ወቅት ደግሞ በክርስትና በዓላት እንደሚደረገው ሁሉ የክርስትና እምነት ተከታዮች የሆኑ ጎረቤቶችን በመጥራት በዓሉን በጋራ ማሳለፍ የተለመደ ነው፡፡ ይህ አንዱ የኢትዮጵያውያን ዕሴት ሲሆን፤ ለዘመናትም ሲወርድ ሲዋረድ ዛሬ ላይ የደረሰ ድንቅ መገለጫችን ነው፡፡
ከበዓሉ አንድ ቀን አስቀድሞም ክርስቲያን ወንድሞችና እህቶች የኢድ ሶላት መስገጃ ቦታን ለሕዝበ ሙስሊሙ በማፅዳት በኢትዮጵያኖች መካከል ያለውን አንድነትና መከባበር በተግባር አሳይተዋል፡፡ በመሆኑም ይህ አኩሪ በዓላችን ከኢድም በኋላ ባሉት ቀናት ጭምር ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው ነው፡፡
ኢድ የስጦታ እና የመረዳዳት በዓል ነው፡፡ የኢድ በዓል ሲከበር ሰዎች ስጦታ በመለዋወጥ ፍቅርና አክብሮታቸውን ይገልጻሉ፡፡ እንኳን አደረሳችሁ ይባባላሉ፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎንም ያጡና የተቸገሩ ወገኖችን መርዳት አንዱ የበዓሉ ዕሴት ነው፡፡ የእስልምና እምነት በኢድ ወቅት ድሆችን ከሚያስብበትና በዓሉንም በደስታ እንዲያሳልፉ በአማኞች ላይ ግዴታ ከጣለባቸው ትዕዛዞች አንዱ ላጡና ለተቸገሩ ወገኖች የሚደረግ ድጋፍ ዘካተል ፊጥር ይባላል፡፡
የእምነቱ ተከታዮች በጋራ የሰላት ሥነሥርዓት ወደ ሚያካሂዱበት ቦታ ከመሄዳቸው በፊት ለተቸገሩ ወገኖች የዘካተል ፊጥር እርዳታ ማድረግ ግዴታቸው ነው፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ በችግር ላይ ያሉ ወገኖች የኢድን በዓል እንደሌሎች ወገኖቻቸው ሁሉ በደስታ እንዲያሳልፉ የሚያደርጋቸው ነው፡፡
በአጠቃላይ ኢድ የመረዳዳት በዓል በመሆኑ ከዚህ በሻገር እንደሀገር ትልቅ ፋይዳ ያለው በዓል ነው፡፡ በተለይም በአሁኑ ወቅት በፀጥታ ችግር ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉና የተሰደዱ በርካታ ወገኖች አሉ፡፡ በሌላ በኩል በድርቅ የተጎዱ ወገኖችም አሉ፡፡ በተለይ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ጦርነት ካሳደረባቸው ጠባሳ ያላገገሙ ወገኖች በችግር ውስጥ ስለሚገኙ እነዚህን ወገኖች መደገፍና ተባብሮ ወደ ቀድሞ ሕይወታቸው መመለስ አንዱ በኢድ ወቅት የሚከወን ተግባር ሊሆን ይገባል፡፡ የኢድ በዓል አንዱ መገለጫ ሃብት ካላቸው ሰዎች የሚሰበሰብ ዘካ(ምፅዋት) ለድሆች የሚከፋፈልበት ወቅት ስለሆነ ይህንን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም እንደ ሀገር በችግር ውስጥ ያሉ ወገኖችን ጫና ማቃለል ይገባል፡፡ ሙስሊሙ ማኅበረሰብ ኮቪድ 19 አስከትሎት የነበረው ቀውስ ከሌሎች ወገኖች ጋር በመተባባር ወረርሽኙ የከፋ ጉዳት ሳያስከትል ችግሩን ማለፍ እንደተቻለ ሁሉ፤ በዚህ ወቅትም በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል ቤት ንብረታቸውን ትተው የተሰደዱና የተፈናቀሉ ወገኖችን እንዲሁም በድርቅ የተጎዱ ወገኖቹን በማገዝ ሃይማኖታዊ ግዴታውን ሊወጣ ይገባል፡፡ የኢድ-የደስታ፣ የአብሮነት እና የመረዳዳት በዓል መገለጫውም ይሄው ነው፡፡
አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 13 ቀን 2015 ዓ.ም