በሞተር ስፖርት በዓለም ላይ ከስድስት ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሚንቀሳቀስ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ባደጉት ሀገራት ይህ ስፖርት ተወዳጅና ከፍተኛ ሽልማትን ከሚያስገኙ የስፖርት ውድድሮች ጎራ ይሰለፋል። በአፍሪካም ሴኔጋልን በመሳሰሉ ሀገራት ሰፊ እንቅስቃሴ የሚደረግበት ሲሆን ቢያንስ በዓመት አንዴ የሚካሄደው ደማቅ ውድድር በፌስቲቫል ደረጃ የሚከናወንና እንደ አንድ የቱሪስት መስሕብ የሚያገለግልም ነው።
ያም ሆኖ የስፖርቱ ባሕሪ ከተሽከርካሪ ጋር የተገናኘ እንደመሆኑ እጅግ ከባድና አሰቃቂ ለሆነ አደጋ የመጋለጥ እድሉ ሰፊ በመሆኑ ጥንቃቄንም ይሻል። ስፖርቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰባቸው ሀገራት በሚደረጉ ውድድሮች እጅግ ዘመናዊ መኪኖችና ቴክኖሎጂዎች ጥቅም ላይ ይውላሉ። የስፖርቱ መወዳደሪያ ስፍራም ደረጃውን የጠበቀና ሰፊ ዝግጅት ተደርጎበት የሰለጠነ የሰው ኃይልና ቴክኖሎጂ ለውድድሮች ስኬት ትልቅ ድርሻ ይወጣሉ።
በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅና ዝነኛ ከሆኑት የዓለማችን የሞተርና የመኪና ውድድሮች መካከል ፎርሙላ ዋን (Formula one)፣ የሞናኮ ግራንድ ፕሪክስ፣ ዳካር ሪሌይንና ሪሌይ ፊንላንድ ይጠቀሳሉ። እነዚህን ውድድሮች ለማዘጋጀትም የሚጠይቀው በጀት እጅጉን ከፍተኛ ነው። በዚህ ደረጃ ተወዳጀና ከፍተና ወጪን የሚጠይቅ ድግስ ለማዘጋጀት የስፖርቱን ማደግ ብቻ ሳይሆን የሀገራትን ፈርጣማ የኢኮኖሚ ጡንቻን ይፈልጋል።
ኢትዮጵያ ቀደም ባሉት ዓመታት ከውጪ ሀገራት ጭምር በሚመጡ ተወዳዳሪዎች የሞተር ስፖርት ውድድሮች በየጊዜው ታስተናግድ ነበር። ስፖርቱ በኢትዮጵያ ተቀባይነትን ካገኘበት ጊዜ ጀምሮ በሕግና ሥርዓት በአሶሴሽን እየተመራ ይገኛል።
ስፖርቱ በኢትዮጵያ በርካታ ዓመታትን ቢያስቆጥርም የዕድሜውን ያክል ማደግ ግን አልቻለም። በኢትዮጵያ በሚዘጋጁ ውድድሮች ወጪዎችን የሚሸፍኑት እራሳቸው ተወዳዳሪዎች መሆናቸው ውድድሮችን በስፋት እንዳይካሄዱ እንቅፋት ከሚሆኑ ምክንያቶች አንዱ ነው። በተጨማሪም ስለስፖርቱ ያለው ግንዛቤ
አናሳ መሆን ለስፖርቱ አለማደግ የራሱ ድርሻ አለው። እነዚህንና መሰል ችግሮችን በመቅረፍ በቀጣይ በስፖርቱ የተሻለ ሁኔታን ለመፍጠርና አስፈላጊ የሆኑ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ሞተር ስፖርት አሶሴሽን አስታውቋል።
አሶሴሽኑ ብዙ ችግሮች ቢኖርበትም የሚያዘጋጃቸውን ውድድሮች በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ማገዝ እንደጀመረ ጠቁሟል። በተለይም ቴክኖሎጂዎቹ ተወዳዳሪዎች ውድድራቸውን በትክክል መጨረሳቸውን ለመከታተል እንደሚያግዙም ጠቅሷል። አሶሴሽኑ የሞተር ስፖርት ውድድሮች በሚካሄዱበት ወቅት አቅጣጫ ጠቋሚ (ጂፒ ኤስ) ቴክኖሎጂንና ሌሎች ዘመናዊ መሳሪያዎችን በመጠቀም ውድድሮችን መከታተል (ሞኒተር) ማድረግ መጀመሩን ገልጿል። ቴክኖሎጂዎቹን በቅርቡ በመጋቢት 17 በአዲስ አበባ ሞተር ስፖርት አዘጋጅነት በተካሄደው ወድድር ላይ መጠቀም የተቻለ ሲሆን፣ መሣሪያዎቹ በውድድሮች ማጭበርበርን በማስቀረት በዳኝነት ላይ የሚነሱ ቅሬታዎችን እንደሚቀርፉም ጠቁሟል።
የአሶሴሽኑ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ መዘምር ሰይፈ፣ ስፖርቱ ዘመናዊና ከሳይንስ፣ ምሕንድስና እንዲሁም ሒሳብ ጋር ልዩ ቁርኝት ስላለው ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ማስተዋወቁ አስፈላጊ መሆኑን ይናገራሉ። ስፖርቱን በማሳደግና ተሳትፎውን በመጨመር ለሀገር ገጽታ ግንባታም መጠቀም እንዲቻል ከዘመኑ ጋር አብሮ መራመድ የግድ መሆኑን ያስረዳሉ።
በሞተር ስፖርት ውድድሮች መንገድ ላይ የሚካሄዱ ፉክክሮችን ትክክለኛ መመዘኛ በመጠቀም ተሽከርካሪን በፍጥነት አሽከርክሮ እራስንና ሌሎችን ከጉዳት በመጠበቅ ማጠናቀቅ መቻል ትልቁ ጉዳይ ነው። ለዚህም ተሽከርካሪን በጥንቃቄ መያዝና ከጉዳት መጠበቅ ያስፈልጋል። ለዚህም አሶሴሽኑ ስፖርቱን የሚጠቅሙና የሚሳድጉ ዘመናዊ መሣሪያዎችን በሀገር ውስጥ ውድድሮች በስፋት ለመጠቀም ከዓለም አቀፉ የሞተር ስፖርት ፌዴሬሽን ጋር በትብብር እየሠራ ይገኛል።
በዚህ ዓመትም ከዓለም አቀፉ የሞተር ስፖርት ፌዴሬሽን ስምንት ጎ ካርት የተሰኙ ግምታዊ ዋጋቸው ከ1 ሚሊዮን 1መቶ ሺ በላይ የሆኑ የታዳጊዎች መወዳደሪያ በድጋፍ ማግኘቱን ጽሕፈት ቤት ኃላፊው ገልጸዋል። እነዚህ መወዳደሪያዎች እጅግ ዘመናዊና የአሶሴሽኑ ስምና ዓርማ የተደረገባቸው ሲሆኑ በስፖርቱ ለሚደረጉ ቀጣይ እንቅስቃሴዎች ጉልህ ሚናን እንደሚጫወቱም አስረድተዋል። ይህም የታዳጊዎች የጎ ካርት ሥልጠናዎችን ለመስጠት ይረዳል ተብሎ ይጠበቃል። በአሁኑ ወቅት ዕድሜያቸው ከ13- 17 የሆኑ 22 ታዳጊዎች ሥልጠናቸውን በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ በመከታተል ላይ እንደሚገኙም አስታውሰዋል።
አሶሴሽኑ በቀጣይ የተለያዩ ውድድሮችን ለማከናወን እቅዱን ለባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር ማቅረቡን የጠቆሙት አቶ መዘምር፣ አንደኛው የከተማ ውስጥ ውድድር ሲሆን በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች ውድድሮችን ለማድረግ አሶሴሽኑ እቅድ እንዳለው ተናግረዋል። ሁለተኛው ደግሞ ከከተማ ውጪ የሚደረግና የደጋ ራሊ የሚባለውን ውድድር ለማካሄድ ታቅዷል።
አሶሴሽኑ የዳኞችና የአሰልጣኞች ሥልጠና ለመስጠት ያቀደ ሲሆን፣ የመወዳደሪያና የማሰልጠኛ ማዕከል ችግር እንዳለበት ይታወቃል። ለጊዜው ግን ለሚያደርገው ሥልጠናና ልምምድ የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚን እንደሚጠቀም የተጠቆመ ሲሆን፤ በቀጣይ የራሱ የሥልጠናና መለማማጃ ማዕከል ለማግኘት ጥረት በማድረግ ላይም ይገኛል። አሶሴሽኑ ከዚህ በፊት ሳንሱሲ አካባቢ የውጪ ውድድሮች ጭምር የሚካሄዱበት ስፍራ ቢኖርም ለልማት በመፈለጉ ምትክ ቦታ ለማግኘት እየተጠባበቀ እንደሚገኝ አቶ መዘምር የገለፁ ሲሆን፣ በአጠቃላይ የሥልጠና፣ የመለማመጃንና የውድድር ቦታን ልዩ ባሕሪ መረዳት አለመቻል ብዙ ችግር እንደሆነም አክለዋል።
የተወሰኑ አመራሮች ለስፖርቱ የሚሰጡት ግምትና ጥሩ ያልሆነ ግንዛቤ ስፖርቱን እንዳያድግ እንቅፋት እንደፈጠረ የሚናገሩት አቶ መዘምር፣ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎችን በክልሎችም በማስፋት እንደሚሠራ አስታውቀዋል።
አሶሴሽኑ በቀጣይ እነዚህንና መሰል ችግሮችን በመቅረፍ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር በአሕጉራዊና ዓለም አቀፍ ውድድሮች የመሳተፍ ዓላማን ይዞ እየተንቀሳቀሰ ሲሆን፣ በቀጣይ ግንቦት ወር ለሚደረገው የከተማ ውስጥ የመኪና ውድድር ዝግጅት መጀመሩ ታውቋል።
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 12/2015