በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ዋና ጊቢ ዙሪያ ያሉ መዝናኛ ቤት ተጠቃሚዎች ዘንድ ግራ አጋቢ ንግግሮችን የቃል ምልልሶችን ሲለዋወጡ መስማት የተለመደ ነው። አንድ ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ የዋናው ካምፓስ ተማሪ ቤቶቹ ሻይ ቡና፤ኬክ፤ ሳንቡሳ ቦንቦሊኖ፤ሳንዱችና ምግብ የሚሸጥባቸው እንደሆኑ በይፋ ባለቤቶቻቸው ቢያስታውቁም ሴት ፈላጊ ወንዶች ከደላሎች ጋር የሚቀጣጠሩባቸው እንደሆኑ ይናገራል።
ሱሱ በብርቱ የተፀናወተው አደንዛዥ እፅ ተጠቃሚ የዩኒቨርስቲ ተማሪ የገዛ ሴት ጓደኛውን ለነዚህ ደላሎች አሳልፎ እስከመስጠት የሚደርስ አሳፋሪ ተግባር እንደሚከውንም ይነገራል። አንዳንድ ወንዶች ልጃገረድ እንዲሁም ቆንጆና ላቅ ያለ ዕውቀት ያላት ሴት ተማሪ ለማጥመድ ወደዚሁ ስፍራ ጎራ ይላሉ። አደንዛዥ ዕጾችን የሚያዘዋውሩ ወንዶች በርካታ መሆናቸው ይነገራል።
የዩኒቨርስቲውን ዋና ጊቢ የውጭ አጥር ግራና ቀኝ ይዘው እስከ እቴጌ መነን የልጃገረዶች ትምህርት ቤት አጥር ሥር የተወጠሩት የላስቲክ ቤቶችና የቆሙት ኪዎስኮች በአብዛኛው ዋና ከሚሉት ተግባራቸው በስተጀርባ ሥራቸው እንደዚህ ዓይነት ዕፆችን ማቀባበል መሆኑም በስፋት ይነገራል። በነዚህ ቤቶች ቢራና ካቲካላ(የሀበሻ አረቄ) ይሸጣል። እስከ ሌሊቱ ስድስት ሰዓትና ከዚያ በላይም አገልግሎት ይሰጣሉ። አብዛኞቹ ተጠቃሚዎችም የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ናቸው።
ሰሞኑን ስካይ ላይት ሆቴል ከሚያዝያ 2015 እስከ ሚያዝያ 2016 በሚዘልቅ የአንድ ዓመት የፀረ አደንዛዥ እፅ ተጠቃሚነት መድረክ ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት ፕሮፌሰር ሰለሞን ተፈራ ሲናገሩ፣ አደንዛዥ እፅ ከደቡብ አሜሪካ ብራዚል በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል በሕገወጥ መንገድ ሲገባ በየጊዜው መያዙ በመገናኛ ብዙኃን ይሰማል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የአዕምሮ ትምህርት ክፍል ባልደረባና በግላቸውም የሪላሰን የአዕምሮ ሕክምና እና የሱስ ተሐድሶ ማዕከል መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ፕሮፌሰር ሰለሞን እንደሚናገሩት፣ ኮኬን የተባለው አደገኛ እፅና ቁጥጥር ሊደረግባቸው የሚገቡ መድኃኒቶች ያለማዘዣ ለወጣቶች ይሸጣሉ። በዩኒቨርስቲው ዙሪያ ባሉና በሌሎች መቃሚያ ቤቶች አማካኝነት አሁን የኮኬን ዕፅ ተጠቃሚነት ጨምሯል።
በእንዲህ ዓይነቶቹ ቤቶች አማካኝነት በሀገራችን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወጣቶች በሱስ ተገዢ ሆነዋል። ለዚህ ምክንያቶቹ ብዙ ናቸው። ኢትዮጵያ በዓለም ከፍተኛ የጫት አምራች አገር ናት፣ ከሚመረተው 85 በመቶ በላይ ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ይውላል። ባለፉት 20 ዓመታት የቢራ ምርት በከፍተኛ መጠን ጨምሯል። እንዲሁም ከጠላና የሀበሻ አረቄ ጀምሮ በጎጆ ኢንዱስትሪ በቤት ውስጥ የሚመረቱ ባሕላዊ መጠጦችም ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።
ከ21 ዓመት በታች ለሆኑ ታዳጊዎች እነዚህን የአልኮል ይዘት ያላቸውን መጠጦች መሸጥ ቢከለከልም እነዚህ በፋብሪካ የሚመረቱና በቤት ውስጥ የሚመረቱ ባሕላዊ መጠጦች በትምህርት በተለይም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዙሪያ ባሉ ቤቶች በስውርም ሆነ ሲሸጡ ይስተዋላል። በቤቶቹ በስውር ካናቢስ፤ኮኬንና ሄሮይን መሰሎቹን የተከለከሉ የአደገኛ እፅ ዝውውርም ይካሄዳል።
ጫት ይቃምባቸዋል ሲጋራም ይጨስባቸዋል። በነዚህ ቤቶች ምክንያት ተማሪዎች በተለይም የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች ለአልኮል መጠጦችና ለአደገኛ ዕጾች ሱሰኝነት የሚጋለጡበት ሁኔታ ቀላል አይደለም። ለሱሰኝነት ከመጋለጣቸውም በላይ የትምህርታቸውንና የጤንነታቸውም ጉዳይ አደጋ ላይ ይወድቃል።
እንደ ፕሮፌሰር ሰለሞን ገለፃ፣ አደገኛ እጾችና መድኃኒቶች በዋናነት ማዕከል የሚያደርጉና የሚጎዱት የሰውነት ክፍል አንጎልን ነው። አንጎል ደግሞ የአዕምሮ መነሻ ነው። አዕምሮ የማሰብ፤ የማገናዘብ፤ ትምህርት የመቀበል፤ሥራ የመሥራት ችሎታን የሚከውን ነው። በአጠቃላይ ሕይወትን በጤናማ መስመር የመምራት ችሎታን የሚወስን ነው። በመሆኑም በአዕምሯቸው ላይ የሚከሰት ጉዳት አጠቃላይ የሕይወት ቀውስ የሚያስከትልባቸው ነው።
ለአብነት ካናቢስን አዝወትረው የሚጠቀሙ ወጣቶች የአስተሳሰብ መጠን መለኪያ (የአይኪው) መጠናቸው በስምንት ከመቶ እንደሚቀንስ በጥናት ተረጋግጧል። ሀሺሽ የሚጠቀሙ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ውጤታቸው ከማይጠቀሙ ተማሪዎች በአንድ ከመቶ ያነሰ ነው። በአዕምሯቸው ላይ ተጽዕኖ እንደሚፈጥር ከዚህም በላይ በብዙ ጥናቶች ተረጋግጧል።
ዓለም አቀፍ ተሞክሮ እንደሚያሳየው ጥንቃቄ ካልተደረገና በጊዜ እርምጃ ካልተወሰደ የተጠቂዎች ቁጥር እየጨመረና እየተባባሰ ይሄዳል። የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካኝነት በስካይላይት በተካሄደው መድረክ ላይ የታደሙት አቶ ኤልያስ አካላይ፣ በትምህርት ተቋማት በተለይም በዩኒቨርሲቲዎች ዙሪያ ወጣቶችን ለእንዲህ ዓይነት ጉዳት የሚዳርጉ ቤቶች እንዳይኖሩ የሚደነግግ ሕግ እንዳለ ይናገራሉ። የመቋሚያ ማኅበረሰብ ድርጅት ኤክስኩቲቭ ዳይሬክተር አቶ ኤልያስ፣ የአደገኛ እፅ ተጠቃሚነት ቅድመ መከላከል ባለሙያ ሲሆኑ መቋሚያ ሱስ ሳይንስ መጽሐፍም ፀሐፊና ደራሲ በመሆናቸው ብዙ ተሞክሮ አላቸው።
ወጣቶች ወደ ሱስ እንዳይገቡ ለማድረግ ቀላል ቢሆንም ከገቡ በኋላ ለማስወጣት ረጅም ጊዜ እንደሚፈጅ ይናገራሉ። በፋብሪካና ከፋብሪካ ውጪ በቤት ውስጥ የሚመረቱ የአልኮል ይዘት ያላቸውን ምርቶች መቀነስ፤በተለይም በሀገር ውስጥ ከሚመረተው ጫት ከፍተኛ መጠን ያለውን ወደ ውጭ መላክ መፍትሔ መሆኑን ይጠቁማሉ። ከባሕል ጋር ተያይዞ የሚቃምባቸውን ሁኔታዎችም ቀስ በቀስ ከባሕል እየነጠሉ ሱሱን እርቃኑን በማስቀረት መከላከል እንደሚቻልም ይመክራሉ።
በትምህርት ተቋማት ዙሪያ ያሉ ለእጽና ለአልኮል መጠጥ መስፋፋት ምክንያት የሆኑ ቤቶችን ከአካባቢው ማስወገድ መፍትሔ እንደሚሆንም ይጠቁማሉ። እነዚህን ቤቶች በማፍረስ ለወጣቶቹ መፍትሔ የማምጣት እርምጃ በቅርቡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ዋናው ካምፓስ ተጀምሯል። አሁን ላይ በተለይ ለተማሪው ጠንቅ የነበሩትና በግራና ቀኝ አጥሩ ዙሪያ የተኮለኮሉት ቤቶች ፈርሰዋል። ይሄን ተከትሎም በየክልሉ ያሉ ዩኒቨርስቲዎችም ተሞክሮውን ያሰፉታል ተብሎ ይጠበቃል።
የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትርና የዕለቱ የክብር እንግዳ ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ለአንድ ዓመት የሚዘልቀውን ይሄንኑ የንቅናቄ መድረክ ሲከፍቱ፣ ‹‹ሀገር የሚገነባው በወጣቶች ነው። ተስፋ የሚጣለውም እንዲሁ በወጣቶች ነው። በመሆኑም ወጣቶች ከአደጋ መጠበቅ አለባቸው። ወጣቶች ለትምህርታቸው፤ለዕውቀት፤ለክህሎት ትኩረት እንዲሰጡ መታገዝ አለባቸው›› ሲሉ ተናግረዋል።
የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴታዋ ወይዘሮ ሙና አሕመድ በበኩላቸው፣ በመድረኩ ወጣቶችን እንደ ሀገር ችግር ውስጥ ከሚጥሉና ከአዘናጊ ችግሮች አንዱና ዋንኛው ወጣቶች በሱስ መጠመዳቸው መሆኑን አስታውሰዋል። ዓለም አቀፍ ችግርም እንደሆነም ጠቁመዋል። በመሆኑም ሚኒስቴሩ ለችግሮቹ ትኩረት ሰጥቶ የወጣቱ አዕምሮና አካል እንዲጠበቅ፤ እንዲሁም ውጤታማ በሆኑ ተግባራት ላይ እንዲሠማሩ እገዛ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 12/2015