የኢትዮጵያ ታሪክና መንዙማ የሚጀምረው ቁርአን መቀራት ከያዘበት ዘመን አንስቶ መሆኑ ይነገራል። ነብዩ መሐመድና የኢትዮጵያውያን ታሪክ መሠረት በውል የተጋመደ ነው። ቢላልን ጨምሮ፣‹‹ሱሀባዎች›› የተሰኙ የነብዩ ረዳቶች፣ ሞግዚታቸው እሙ አይመንና የሌሎች በርካቶች ማንነት ከኢትዮጵያ የዘር ሐረግ ይመዘዛል።
አበሾቹ ነብዩ መሐመድን ከመውደዳቸው የተነሳ በዜማና ግጥም ያወድሷቸው፣ ያመሰግኗቸው ነበር። በወቅቱ ይህን ያወቁት ነብዩ መሐመድ በፈቃዳቸው ይሁንታ እንደሰጧቸውም ታሪክ ይነግረናል።
መንዙማ የዓረብኛ ቃል ነው። ትርጓሜውም ገጠመ፣ አደራጀ፣ ደረደረ የሚል ፍቺን ይሰጣል። ቃላትና ሐረጎችን፣ ስንኞችና ግጥሞችን በትክክለኛ አሰናነድ ማስቀመጥም መንዙማን ይገልጸዋል። መንዙማ የእስልምና ሃይማኖትን መሠረት በማድረግ የሚጻፍ በመሆኑ በባሕርይው ከሌሎች ግጥሞች ይለያል። መንዙማ ጥንታዊ የሚባል ታሪክ አለው። ለኢድ በዓልና ለታላቁ የረመዳን ወር ለምስጋናና ውዳሴ ይውላል።
መንዙማ በሀገራችን በተለይ በወሎና አሮሞ ሕዝቦች ዘንድ መለመድ የጀመረው ከአንድ መቶ ዓመታት በፊት ነበር። በሰሜንና ማዕከላዊ አቅጣጫም በወሎ ሙጃሂድ በስፋት ይዘወተር ነበር። የሶማሌና የሐረር መንዙማም በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ተጠቃሾች ናቸው።
የወቅቱ ዜማና ግጥሞችም ትክክለኛውን የኢትዮጵያዊነት ቀለም የተላበሱ ስለመሆናቸው ጥናት ያካሄዱ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። ብዙዎች እንደሚሉትም መንዙማ፣ እስልምናንና ነብዩ መሐመድን ነጣጥሎ ማየት አይቻልም። ሁሉም በአንድ ድር በተዋቀረ ጥብቅ ገመድ ይተሳሰራሉ።
የመንዙማ ግጥሞች ባብዛኛው ፈጣሪን የሚያመሰግኑ ፣የነብዩ መሐመድን ክብር የሚያወድሱ ናቸው። ይህ እውነታም ዜማው ለዓመታት ጆሮ ገብ ሆኖ ከልብ እንዲወደድ አስችሏል።
ሰዎች የፈጣሪን ጥበብ ማድነቅና ማወደስ ሲፈልጉ ፣ነብዩ መሐመድን ማክበር ማወደስ ሲሹ የእንጉርጉሮ ዜማን ይጠቀማሉ። የመንዙማ ግጥሞች በሚደመጡ ፣ ጊዜም ማንኛውም ፣ ሰው በዋዛ ፣የሚጽፋቸው፣ ስንኞች እንዳልሆኑ ማረጋገጥ ይቻላል። ይዘቶቹ ጥልቀት ያላቸውና በእጅጉ አመራማሪ የሚባሉ ናቸው።
ሼህ አሕመድ ሼህ ሲራጅ የተባሉ የወሎ ሰው የታወቁ ገጣሚ እንደሆኑ ይነገራል። እኚህ ሰው ግጥሞቻቸውን የሚያዘጋጁት በዓረብኛ ሲሆን በኦሮምኛ ቋንቋም ይገጥማሉ። ሼህ አሕመድ ፈጣሪን ለማወደስ የሚጠቀሙበት ቃል በእጅጉ የረቀቀና ለነብዩ መሐመድ የሚሰጡት ምሳሌም ከሌሎች የተለየ ነው ።
እንደ አጥኚዎች ግምት በመንዙማ ግጥሞች ውስጥ የሚስተዋሉትን ፍልስፍናዎች ባብዛኛው ትውልዱ የደረሰባቸው አይደለም። ብዙዎች እንደሚሉትም ግጥሞቹን መርምሮ በወጉ ለመረዳት ጥሩ አንባቢና ብቁ ተመራማሪ መሆን ያስፈልጋል ።
የመንዙማ ግጥሞች የተለየ ማራኪነት አላቸው። የፈጣሪን ኃያልነትና የነብዩ መሐመድን መወደድ ለማሳየት በተለየ ቃል ይገለጻሉ። ነብዩ በሚታወሱበት በዚህ የረመዳን ወር ታዲያ ቁርአን በማንበብና ታሪካቸውን በማንሳት ለፈጣሪ ያላቸውን ክብር በመንዙማ መግለጽ የተለመደ ነው። በታላቁ የረመዳን ወር በመንዙማ ፣ በእንጉርጉሮና ምክር፣እንዲሁም በነሺዳ ውስጠት ይገለጻል።
መንዙማ ከሁሉ አስቀድሞ እስልምና ሲታወጅ አንስቶ የተዋቀረ መሠረት አለው። በግብጽ፣ ፓኪስታንና፣ ቱርክም ይታወቃል። በነዚህ ሀገራት ትልቅ ዕውቅና የተቸራቸው ገጣሚያን ተሳትፎ አርፎበታል። ሁሉም በሚባል መልኩ ትኩረታቸው የሚገለጸው የነብዩ መሐመድን ታሪክና ማንንነት ዕውቅና በመስጠት ነው።
በሀገራችን የመንዙማ ጥበብ በተለየ መልኩ ይቀረጻል። መንዙማዎችን በማዘጋጀት፣ ግጥምና ዜማውን በመንደፍ፣ የነብዩን ማንነት ለዓለም በማስተዋወቅ ላይ ያተኩራል። የነብዩ መሐመድን የሕይወት ታሪክ መሠረት በማድረግም መልዕክታቸው ፣ ውጣወረድና ትግላቸው ሁሉ በመንዙማው ይንጸባረቃል።
ከገጠር እስከ ከተማ ያሉ የእስልምና ዕምነት ተከታዮች የነብዩ መሐመድን ገድል ለማውራት የሚያህላቸው የለም። ደግነታቸውን፣ ታላቅነታቸውን፣ የሚገልጹበት አንዱ መንገድ የመንዙማ ጥበብ ነው። መንዙማ የእስልምና ዕምነትን ዕውቀት ለማስጨበጥ ጭምር ያገለግላል።
ኢትዮጵያ የእስልምና ሀይማኖትን ተቀብላ ያስፋፋች ሀገር ነች። በሀበሻው ንጉስ ነጃሺ ዘመን ነብዩ መሐመድ ኢትዮጵያ ፍትሕና ሐቅ የማይጓደልባት፣ ምድር መሆኗን ለተከታዮቻቸው በገለጹት መሠረት መጀመሪያ አስራ ሁለት ወንዶችና አራት ሴቶች በእንግድነት ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን ታሪክ ይነግረናል።
በዚህች ምድር የነበረው ሰላምና መልካምነት እንደተባለው በመሆኑም ውሎ አድሮ ሌሎች አማኞች ወደ አገረ ኢትዮጵያ ተጓዙ። እስልምና ያለአንዳች ችግር ተስፋፍቶም የዕምነቱን ተከታዮች በብዙ ቁጥሮች ተበራከቱ።
ኢትዮጵያ ከሌሎች የእስልምና ተከታይ ሀገራት ዕምነቱን በመቀበል ቀዳሚውን ትይዛለች። ይህ ቀደምትነትም ከነብዩ መሐመድ ጋር የጠበቀ ቅርበት እንዲኖር አስችሏል። ይህ ጥብቅ ቁርኝት የፈጠረው ጽኑ ፍቅርም በመንዙማ ጥበብ የሚገለጽ ሆኗል።
በሀገራችን የእስልምና ዕምነት ተከታዮች መንዙማን በአማርኛና በዓረብኛ በማዜም ለምስጋና ይጠቀሙበታል። ከጥንት ጀምሮ አብዛኛው የእምነቱ ተከታይ ሕይወትና ኑሮ በገጠር ስለነበረም አማኙ ስለእምነቱ በቂ ዕውቀት እንዲኖረወና ፣ከሃይማኖት ሥርዓት ጋር እንዲገናኝ በመንዙማ መልዕክት ማስተላለፍ መቻሉ ይነገራል ።
ሰለእስልምና በቂ ዕውቀት ያላቸው ዑላማዎች ሙስሊሙን በዕውቀት ለመድረስ ሲሉ መንዙማን እንደቀኝ እጅ ሲጠቀሙበት ቆይተዋል። በዚህም ቁርዓንና ትርጉሙ፣ ሀዲስና የዓረብኛ ቋንቋ ጭምር ሲስፋፋ ኖሯል። ከሁሉም ደግሞ የነብዩ መሐመድ ታሪክና ማንነትን በማስተዋወቅ መንዙማ ያበረከተው አስተዋፅዖ ጎልቶ ይገለጻል።
መንዙማንና ስንኙን ለማዘጋጀት በጥበቡ የተካነ፣ በስጦታው የታደለ ሰው ያስፈልጋል። መንዙማ በማንኛውም ሰው አንደበት በግምት አይዘጋጅም። ቁርዓንን ማወቅ ሀዲስን መረዳት፣ ስለነብዩ ጥንተ ታሪክ በወጉ መመራመር ግድ ይላል። የዓረብኛ ቋንቋን መናገር፣ መስማትና መጻፍም ለጥበቡ እድገት በእጅጉ ያግዛል።
አማኞች እንደሚሉት ደግሞ በወሎ ምድር እስልምና በሰፋበት ማዕከል የምትገኘው ‹‹አዛሩል አበሻ›› የጠቢባኑ ዑላማዎች መገኛ ናት። በዚህች አካባቢ በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመን በሁለት አውራጃዎች ብቻ ከስድስት መቶ በላይ ሊቃውንት ተፈርተዋል።
ከነዚህ ሊቃውንት መካከል መንዙማን በመቅረጽ የሚታወቁ ከወረባቦ እነ ሼህ ጫሌ ፣ ሰይድ ኢብራሂም ፣ ዳንኤል አወል ፣ አንይና ሌሎችም ይጠቀሳሉ። ከነሱም ቀጥሎ እነሼሕ ሲራጅ፣ ሼሕ አሕመዲን፣ የመሳሰሉ በመንዙማ ጥበብ ከተካኑት መሐል ይነሳሉ። እነዚህ ሊቃውንት በነበሩበት ዘመን የመንዙማን ጥበብ ለትውልድ ለማስተላለፍ በዛፍ ጥላ ስር ሆነው ያስተምሩ ነበር።
በዘመኑ ከሊቃውንቱ አንደበት የፈለቁ ድንቅ የአማርኛና የዓረብኛ መንዙማዎች ለመታተምና ለመቀረጽ ዕድል አላገኙም። ያም ሆኖ በፍቅርና በክብር ከትውልድ ወደትውልድ እያለፉ ዓመታትን መዝለቅ ችለዋል ።
በገጠር የተዘጋጁት የዓረብኛ መንዙማዎች ጥበቡ ለተቀዛቀዘበት የዓረቡ ዓለም መነቃቃት ታላቅ አስተዋፅዖ አበርክተዋል። መረጃዎች እንደሚጠቁሙትም የሀገራችን የዓረብኛ መንዙማዎች ታሪክንና ሃይማኖትን በመደገፍ በኩል ለሀገራቱ የጀርባ አጥንት ናቸው።
ብዙዎች እንደሚስማሙት መንዙማን የእስልምና ዕምነት ተከታይ ያልሆነ ሰው ሊያዘጋጀው አይችልም ለምን ከተባለም ከዕምነቱ ጋር የተያያዙ እውነታዎችን ጨምሮ የቁርዓን ዕውቀት ሊኖር ስለሚገባ ነው። መንዙማ በአብዛኛው ግጥሞቹ ከዓረብኛ የተቀላቀሉ ናቸው። በውስጣቸውም ታሪክና ሃይማኖትን ሠንቀው በወጉ ይተርካሉ።
ሁሉም መንዙማ ግጥሙ ሲዘጋጅ ዜማው ጭምር አብሮ ይቀረጻል። በተለምዶ እንደሚለየውም ሁሉም መንዙማ ተመሳሳይ የሚባል ዜማ አይኖረውም። ይህን ስልትና ዘዴ አብሮ ለማራመድም የራስ ጥበብና ዕውቀት የሚጠይቅ ነው።
ነብዩ መሐመድ ይዘው በተነሱት የእስልምና ሃይማኖት ጠንካራ ዕምነት ለማቆም ችለዋል። በዚህ ብርቱ ማንነታቸው በርካቶች እንዲከተሏቸው ምክንያት ፈጥሮ የዓረብ አገራትን ለመመሥረት ችለዋል። ፋርስ፣ታናሽዋ እስያ፣ ሰሜን አፍሪካ፣ ስፔንና ከፊል የሕንድ ግዛት፣ ፓኪስታንና አፍጋኒስታንን በሃይማኖታዊ አስተምሕሮ በማዳረስ ዕምነቱን አስፋፍተዋል።
በነዚህ ሀገራት መካከል የተፈጠረው የባሕል፣ የሃይማኖትና የማኅበራዊ መስተጋብርም የዓረብኛ ስነጽሁፍና ቋንቋ ከሃይማኖትና ፍልስፍና ጋር ተቆራኝቶ በስፋት እንዲዳረስ ምክንያት ሆኗል። ይህ አይነቱ አጋጣሚ በፈጠረው ዕድልም በርካታ ታሪኮች ተጽፈዋል፣ግጥምና ዜማዎች ተዘጋጅተው ለጆሮ ደርሰዋል። ከነዚህ መገለጫዎች መካከልም አንደኛው መንዙማ መሆኑን ታሪክ ይነግረናል። ሁሌም ታዲያ የመንዙማ ግጥማ በዜማ ሲታጀብ ለነብዩ መሐመድ ክብር በመስጠት ፣ በማመስገን ፣ በማወደስ ይሆናል ።
እንዴት ነሁ፣
የኔ ጌታ፣
እነዴት ነሁ።
ጦይባ ላይ ቁጭ ብሎ፣
መዲና ቁጭ ብሎ፣
ከኋላ ከፊቱ ፋኖስ አስከትሎ።
ግመሉ መጣና አሕመድን ቢያየው ፣
ተንበረከከና ከጫማው ላይ ሳመው።
በመንዙማ የሰው ልጆችን ባሕርይ ፣ የኑሮ ውጣውረድና ዕለታዊ ፈተና ሁሉ ይዳሰሳል፣ የአንዳንዶች መከፋትና ብሶት ሳይቀር ይነሳል። የመንዙማ ሰንኝ ከጥንት እስከዛሬ ፈጣሪንና ነብዩ መሐመድን የሰው ልጆችን ሕይወትና ኑሮ ሲያነሳ ፣ሲያስታውስ ቆይቷል።
አዳኚቱን ውሻ ነከሰቻት በግ፣
በሰው እጅ ያለ ሰው የለውም ማዕረግ።
ባጥፈው ደነዘዘኝ፣ ምላሴን እንደቅል፣
ጤናና ገንዘብ ነው የልብ የሚያናግር ።
መንዙማ ብዙ ባይለመድም ሴቶች ጭምር ይሳተፉበታል። ለዚህ ደግሞ እማማ ዚነትንና ሌሎች ሴቶችን በምሳሌ መጥቀስ ይቻላል ። እማ ዚነት እንዲህ በማለት በመንዙማ የውስጣቸውን ተናግረዋል።
አቤት! አቤት !አቤት ! አቤት፣
የጨለማው ጌታ የብርሀኑ ባልተቤት፣
የዘለቁ ጊዜ ላይኛው መሥሪያ ቤት ።
አሜንን አለቅም የደም መሬቴ ነው፣
ሕመሜን የሻርኩት አሜን እያልኩ ነው።
መንዙማ መገለጫው ብዙ ነው። በደስታ ጊዜ ውስጣዊ ስሜት ይገለጽበታል። በሠርግ ወቅትም ሙሽሮች እንዲህ ይወደሱበታል።
ጀማሊል ዓለም፣
ጀማሊል ዓለም፣
ባየው ጊዜ አምሮ ፣
እንግዲህ ጀመርኩኝ ፣
የደስታ እንጉርጉሮ።
ያጣመረን አላህ- ከአንድ እናት ማህፀን፣
በአንድ ጎጆ አጥር- መለመለን አድገን፣
የልቤ ደስታ – እጅጉን አፈነው።
አሉሀም ዱህሊላሂ፣
አይኑን ባይኑ ላየው፣
ጀማሊል ዓለም፣
ጀማሊል ዓለም፣
እንግዲህ ተቀበል – የፍቅር አዝማሪ፣
ታጥቄያለሁ መውደድ- ታጥቄያለሁ ሱሪ።
በረካ እንዲንቧቧ- ሐሴት እንዲሞላ፣
እንበል ነብይ፣ ነብይ- እንበል ሰለላ ።
መንዙማ በተለየ ዜማ ታጅቦ በውብ ቅላጼ ተውቦ ለጆሮ ሲደርስ በእጅጉ ይማርካል። መንዙማን አስተውሎ ላደመጠው ከማራኪ ድምፀቱ ባለፈ ትርጉም ያለው መልዕክት ማስተላለፉ አይቀሬ ነው። አንዳንዴ ደግሞ መንዙማን የወደዱ፣ ምስጋና ማድረስን የለመዱ መልሰው ለመንዙማ ውዳሴን ያሰማሉ እንዲህ በማለት ።
በአሪፍ ሆጅ ሁሴን ላይ ተጠምጥማ
በእሷ እያዜሙ ስንቱ ሰው ደማ
ልቤን ወሰደች እቺ መንዙማ
መንዙማ ሙስሊሙ ማኅበረሰብ በጾም ጸሎት ፣ በስግደት በሚቆይበት በታላቁ የረመዳን ጾም ወቅቱን እየዘከረ ፤ ምስጋና የሚቀርብበት ጥበብ ነው።መንዙማና ረመዳን ተደጋግፈው፣ በአንድ ተጣምረው በሚደምቁበት በዚህ ጊዜ በግጥሞቹ የሚተላለፉ መልዕክቶች ትርጓሜቸው በተግባር ይገለጻል። መረዳዳት፣ መተዛዘን፣ እንዲሰፍን፣ መስጠት በረከት ሆኖ እንዲዘልቅ አስተዋፅዖው ይጎላል።
ለመላው የእስልምና ዕምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለአንድ ሺህ144 ኛው የዒድ አልፈጥር በአዓል በሰላም አደረሳችሁ እንላለን ። ‹‹ኢድ ሙባረክ››
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 12/2015