የቃል ማዕድ!

በዚህ ምጥን ጽሑፍ ቃል፣ ቃላዊነት እና ቃላዊ ግጥም ምንነት፣ ተዛምዶና ክሰታ (ሃሳብ፣ ድረሳ፣ ድርሰት) አጠር ባለ አቀራረብ ከተለያዩ ብያኔዎች ጋር ለዛቸውን ጠብቀው ይቀርባሉ። ሦስቱ መሰረታዊ ነጥቦች ያላቸውን ትስስር፣ ገፅታ፣ ኪናዊነት እና ተፈጥሯዊ ክሰታ (በተለይም በቃላዊ-ግጥም) ላይ በማተኮር በዝርዝር እንመልከት።

ቃላዊ-ግጥም ላይ ይበልጥ የምናተኩረው፣ አንድም ቃላዊነቱ ከሌሎች ቃላዊ ሥነ ጽሑፎች ጋር ያለውን ዝምድና ስለሚገልጥ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ቃላዊነቱ ከቃልና ቃላዊነት ጋር የጠበቀ ትስስር ያለው በመሆኑ ነው። በገለጻ ሂደት አንዳንዴ አንዱን በአንዱ ላይ ለማሳየትና ለመግለጥ ሲሞከር ቢገኝ፣ ሆን ተብሎ የተደረገ መሆኑ ግምት ውስጥ ይግባ። ቃልን በማስቀደም፣ ቃላዊነትን በማስከተል በመጨረሻ ደግሞ ቃላዊ-ግጥምን ከእነ ምሳሌ መደምደሚያ በማድረግ ሃሳባችንን እንቋጫለን። መልካም ንባብ!

ቃል እና ቃላዊነት

ቃል ገዥ ነውና እንደ አምድ ሆኖ በህልውና ዋልታነቱ በሦስቱም ርዕሰ ጉዳዮች(ራሱን ቃልን ጨምሮ) ላይ ስናሰላስል በጉልህ በምናባችን ጓዳ ይመላለሳል። ቃላዊነት እና ቃላዊ-ግጥም ላይ ያሳደረው ጉልህ ገጽታዊ ተጽዕኖ በባህል መሰረት ላይ የቆመ ነው። ማኅበራዊ ዓውድ ውስጥ ባለ መስተጋብር ህልው ሆኖ ይከሰታል።

ቃል፣ አንደበታዊ እና ፅሁፋዊ ህልውና ያለው ነው። ስለሆነም አንደበታዊ ገፅታው ድምፅ ላይ ሲመሰረት፣ ፅሁፋዊ ቅርጹ ደግሞ ፊደላዊ፣ ምልክት ላይ ይገለፃል። ሁለቱ የመከሰቻ መንገዶች ናቸው። ረቂቅን (ሀሳብን ወይም ስሜትን) ወደተጨባጭ ይለውጣሉ። ራሱ ቃል ረቂቅም፣ ተጨባጭም የሚሆነው በዚሁ ባህሪው ነው፤ ፅንሰ ሀሳብ ይሸከማል። ይህም የውክልና ተግባሩ ነው። ምንጩም የፈለቀበት ባህል በመሆኑ ትዕምርታዊ2 (semiotics) ነው። ይህም ትዕምርታዊነት፣ ‹‹የቃላት ምንጭ ስምምነት ነው›› የሚለውን ያስታውሰናል። ስለሆነም ቃል ሰፊ እሳቤ ነው። ከነጠላ ድምፅ (ይህም ቢሆን አሻሚ ነው) እስከ ጥልቅ ፅንሰ ሃሳብ የሚገለጥበትና የተሸከመ ነው። ማለትም ‹‹መጀመሪያ ቃል ነበረ››፣ ‹‹ቃል ያባት እዳ ነው››፣ ‹‹ቃል ገባ›› እና ‹‹ቃለ ሕይወት ያሰማልን›› ወዘተ… አይነት አገላለፆች የኅብረተሰብ ስሪት ላይ የተመሰረቱ የኑሮ ማንፀሪያ ፅንሰ ሃሳቦች ናቸው። ይህ ባህሪው ውስብስብ የቋንቋ ስርኣት መፍለቂያ ነው።

የቃል ምንነትን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል፣ የአማርኛ መዝገበ ቃላት ላይ እንደሚከተለው ሰፍሮ እናገኛለን፣ ‹‹ቃል (ብ.ቁ.ቃላት) ስ 1.አንድን ፅንሰ ሃሳብ ለመወከል በድምፅ የተነገረ ወይም በፅሁፍ የሰፈረ የድምፅ ምልክቶች ቅንብር፣ አነስተኛው የአረፍተ ነገር ክፍልፋይ። 2. ስለ አንድ ነገር የተባለ፣ የተነገረ፣ የተፃፈ ሃሳብ፣ አስተያየት፣ መልእክት፣ … ። ቃሉ የእሱ ነው።›› ከላይ የገለፅነውን የቃልን ድርብ ተግባርና ባህሪ ገላጭ ነው። በሌላ አነጋገር የንቃተ ኅሊናን የቃል (የቋንቋ) እስረኝነትንና ከቋንቋ ውጭ ሊኖርና ሊዳብር እንደማይችል ጠቋሚ ነው።

ቃል ተግባቦት ነው። ተግባቦትን የሚገልፅበት መንገድ በራሱ እጅግ ጥንታዊነት ያለው ነው። የሰው ልጅ ድምፅን እና ቋንቋን መሰረት አድርጎ ስሜቱን፣ ሃሳቡን፣ ተሞክሮውን… የሚለዋወጥበት ቁልፍ ባህሪ ነው። ቃላዊ ከሆኑት መካከል ቃላዊ-ባህል፣ ቃላዊ ፎክሎር፣ ቃላዊ ስነጽሁፍ፣ ቃላዊ ልማድ፣ ቃላዊ ስልት፣ ቃላዊ መንገድ፣… ወዘተ. የሚሉ አገላለፆች ተዘውትረው ሲነገሩ የምንሰማቸው ናቸው። የሰውን ልጅ በቃል የመግባባት ልማድ በሦስት ዋና ዋና ደረጃዎች ተከፍሏል። እነሱም ቅቡል ስነፅሁፋዊ ቅርፆች፣ ገዢ ታሪካዊ እውቀቶች እና ግለሰባዊ ልማዶች ናቸው።

የቅቡል ስነፅሁፋዊ ቅርፆች ቃላዊነታቸው በተሳታፊው (audiences) ምክንያት ተጽኖ ይፈጠርበታል፤ ማንኛውም ክንውን ላይ ተግባራዊ ይደረጋል። ስለሆነም ቃላዊ ልማዶች ውጫዊ ግፊት እና የአተገባበር ለውጥ ይደረግባቸዋል። ከዚህ አንፃር ቃል፣ በቀጥታ የሚሰነዘር እና በቀላሉ መለየት የሚያስችል የስነጽሁፍ መገለጫ ነው።

ቃላዊነት ምንድን ነው? ቃላዊነት የስነፅሁፍ መገለጫ ነው። ተስተላልፎውም ሆነ መከሰቻው በቃል ነው። የፅሁፋችን ትኩረት ቃላዊ ግጥምን መሰረት ያደረገ በመሆኑ እንደ ሥነ ጽሑፍ ቃላዊ የሚያሰኙትን ነጥቦች እንጠቅሳለን። ቃላዊ በመሆኑ እንደየ ባህሉ እና እንደ ሚከወንበት ዐውድ የተለያየ ቢሆንም መሰረታዊ መገለጫዎቹ ለመድረስ የሚጋብዝ ተመስጦ፣ መተላለፊያ መንገዱ፣ የአከዋወን ትክክለኛነት እና እርግጥ የሆነ ምንጭ ናቸው።

በተጨማሪም ‹‹የማኅበረሰቡን የእለት ዕለት የሕይወት ገጠመኝን መሰረት በማድረግ የሚነገሩ ስነቃሎች የሚቀርቡበትና ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሸጋገሩበት መንገድ በዋናነት ቃላዊነት ነው።›› ቃላዊነት ለስነፅሁፍ መገለጫ መሆኑን ማጠናከሪያ ይሆናል።

ብዙ ጥቅም ላይ የዋለው ‘የቃል’ ቅጽል ብዙ ጊዜ እንደ ዋና መስፈርት ያገለግላል።

በልዩ ልዩ ሙያዎች የምርምር ፍላጎቶችን አጭሯል። አሳድሯል። በተለምዶ በአፍ ከሚተላለፉ ነገሮች አንፃር ይገለጻል፣ ቃሉ። ወቅታዊ ጉዳይም ነው።

ስለሆነም ቃላዊነት በንግግር የተነገረ፣ በአፍ የሚተላለፍ፣ የሚነገር። ቀዳሚ ትርጉሙ በብዙ ግልጽ በሆነ ቴክኒካዊ የቃላት አገባብ ‹የቃል ትውፊት›፣ ‘የቃል ሥነ ጽሑፍ’፣ ‘የቃል ትረካ’፣ ‘የቃል ምስክርነት’ ወዘተ…’ቃላዊ’ ብዙ ጊዜ ከ’ጽሑፍ’ ጋር ይቃረናል። እንደ ‘የቃል ሥነ ጽሑፍ’ በተቃራኒው ወይም ትይዩ ደግሞ ‹የተጻፈ ሥነ ጽሑፍ›፣ ወይም ‘የቃል ታሪክ’ ሰነድ የሌላቸውን ምንጮች አመላካች ነው። ‘ቃላዊ’ እንደ ‘ጽሁፍ’ ያሉ አጠቃላይ ቃላትንም ብቁ፣ ሙሉ ያደርጋል።

ቃላዊ ግጥም

ቃላዊ ግጥም ሕልውናውም ሆነ ተስተላልፎው ቃላዊ የሆነ በስነ ቃል ስር የሚመደብ ሥነ ጽሑፍ ነው። ስለሆነም በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚከሰቱ ገጠመኞችን ተንተርሰው ድረሳ የሚካሄድባቸውና ድረሳውንም በቃል ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚያስተላልፉ ናቸው። ገጣሚው ግጥምን ለማነብነብ የሚያስችለውን ገፊ ምክንያት የሚያገኘው ከማህበረሰቡ ውስጥ ባለ ማህበራዊ ክንዋኔ ነው። በዚህም ይነሸጣል። ያቅራራል፣ ያንጎራጉራል ወይም ይዘፍናል። ለዚህ ሳይሆን ይቀራል “ገጣሚ ውበትና ሀሳብ ሲያስስ የሚኖር ፍጡር ነው” -የሚባለው? በእርግጥ ቃላዊ ግጥሞችን ማን እንደገጠማቸው ማወቅ አዳጋች ነው። ለዚህም ነው ንብረትነታቸው የወል የሚሆነው።

ያም ሆኖ በግጥም የማይመተር፣ የማይዳሰስ ጉዳይ የለም። እስኪ ከቃላዊ ግጥሞች ውስጥ እግዜርን ጉዳይ አድርገው ከተደረደሩት ጥቂት ምሳሌዎች እናንሳ።

ሰው እጅግ በከፋው እና መውጫ መግቢያ ባጣ ጊዜ “ በቀረርቶ” እንደሚከተለው ምሬቱን ይገልፃል። ግጥሙን ያቅራራው እረኛ ነው ይባላል።

ሰው መግደል እንደግዜር ፣

ዱር መግባት እንዳውሬ መቼ ይቸግራል ?

ከጓደኛ ጋራ መጫወት ይቀራል።

ይህ የቀረርቶ ግጥም፤ በዋናነት የእግዚአብሔርን ተግባር ከአውሬነት ባህሪ ጋር በማነፃፀር ይኮንናል። “ስራው መግደል ብቻ “ የሆነ እስኪመስል፤ ኸረ እንዲያውም ከጓደኛ ጋር መጫወት የላቀ ተግባር ተደርጎ ለማሳያነት ቀርቧል። እግዜርን በመተቸት ሰውን (ተፈጥሮን) መተቸት ይሉሃል ይህ ነው። ምክንያቱም አብዛኛው ምድር ላይ የሚደርስ በደል በሰው ልጅ አማካኝነት የሚፈጠር በመሆኑ ሰውን የሚያማርረው ራሱ ሰው ነው። ይህም ማደሪያውን ጠርቶ መኖሪያውን፣ በተገላቢጦሽ መኖሪያውን ጠርቶ ማደሪያውን አገላለፅ ነው። ያማል።

እግዜር መሬት ወርዶ ፣

አምላክ መሬት ወርዶ፣ አንድቀን አግኝቸው፤

ቀጭን ዘንጌን ይዤ፣ ሞግቸው ሞግቸው፤

እሱም ዘዴኛ ነው አይወርድም እምድር

ሁሉም ሰው ደመኛው ማን ቤት ገብቶ ሊያድር።

(የእረኛ ግጥም)

በማህበረ-ባህላችን የግጥም ቦታ ከፍ ያለ ነው። የህልውና ቋጠሮ የሚፈታበት ብርቱ ጥበባዊ ግንዛቤ ነው። ይቀትራል። ማኅበረሰብ ሲታመም የሕመሙን ጠገግ ፅንፍ አፈፍ የሚያደርግበት መዳፋ ነው –ለከያኒ።

ግጥሙ በእግዜር እና በሰው መካከል ያለውን የሞራል ትስስር ያሳየ ነው። ሙግቱ የሕልውና ውል ነው። በእጃዙር ገላጩም ተገላጩም ሰው ነው። ሰው በራሱ ላይ የዘመተ ወይም ራሱን የከሰሰ ፍጡር መሆኑን ተጨባጭ ማሳያ ነው።

ቃላዊ ግጥሞች ለእንጉርጉሮ የቀረቡ ናቸው። በጥልቅ ቁዘማ ከምናብ የሚፈለቀቁ በመሆናቸው ነፍስን (ስሜትን) ይቀትራሉ። የቃላቱ ምትሀታዊ ኃይል ምንጩ ቅፅበት ነው። የማይኮረኮር ማዕዘን የለም–በቋንቋው። የሕልውናችን መስፈሪያ ነው- ዘዴው። ለዚህ ሳይሆን ይቀራል ዳንቴ፤ “ግጥምን የማያውቅ እግዜርን አያውቅም” የሚለን። የእግዜር (የፈጣሪ) መልክ ሕብር የሚገለጥበት ኪነ-ስፌት ነው–ያለ ይመስለኛል። እዚህ ላይ ገጣሚ በድሉ ዋቅጅራ፤ “ግጥም ተፈጥሮ እራሷን የቆለፈችበትን ቁልፍ ያስቀመጠችበት ሙዳይ ነው” ያለበትን ምክንያት እንደ ማለዘቢያ መጥቀስ አስፈላጊ ሆኖ አግኝቸዋለሁ። በፍጡር እና በፈጣሪ መካከል የሚምዘገዘግ የሀቅ በትር ነው -ግጥም።

በአንድ ወቅት ከስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ ወጥቼ ወደ አራት ኪሎ ስገሰግስ የካቲት 12 የሰማታት ሀውልት ዳርቻ አንድ እናት ተቀምጠው እንዲህ ሲያንጎራጉሩ ሰምቻለሁ፦

እስኪ ላነሳሳው የፈጠረኝን

ከጓደኛ በታች ያደረገኝን

እጃቸውን ደጋግመው ከወዘወዙ በኋላ ፊታቸውን ቅጭም አድርገው እንዲህ ቀጠሉበት፦

እናንተ ምታዩኝ እኔ ማላያችሁ

የብርሃን አበባ አይርገፍባችሁ።

አይናለም… አይናለም…

ላንድቀን ይከብዳል እንኳን ለዘላለም።

ጥልቅ ቁዘማ ነው፤ ሕልውና የተሰፈረበት። የሕመሙ ብርታት ይነዝራል። ይቀትራል። ስሜቱ እረፍት ስለሚነሳ ያቅበጠብጣል። በሕይወት መገፋት ከፈጣሪ ጋር ያላትማል። ለምን? የሚል ጥያቄ ወጥሮ ይፈታተናል። ከተፈጥሮ በደል የበለጠ በዙሪያችን ያሉ ሰዎች ችላ ሲሉን ሕመሙ ይበረታል። ለዚህ ይሆን

“እናንተ ምታዩኝ እኔ ማላያችሁ

የብርሀን አበባ አይርገፍባችሁ”

የሚሉት አላፊ አግዳሚውን። የማየትን ውብ ፀጋ በ “አበባ” በመመሰል። አጃኢብ ነው! ይቀትራል።

በአንድ ወቅት ጎዣም ውስጥ በሰሞነ ሕማማት ቁዘማ ስትብሰለሰል የሰነበተች ሴት የእየሱስን ከመቃብር መነሳት የሕመሟ መስፈሪያ በማድረግ እንዲህ ገልፃዋለች፦

“ስትታመም ታማ ስትሞት ተቀበረች

አንተ ስትነሳ የኔ እናት የታለች!?”

በንፅፅር የቀረበ ነው። ንፅፅሩ ደግሞ ሲቃይ፣ ሕመም ላይ የተመሰረተ ነው። የእናቴ እና ያንተ (እየሱስን መሆኑን ልብ ይሉዋል) ስቃይ ልዩነቱ አልታይሽ አለኝ! ያለች ይመስለኛል። ያው ሁለታችሁም በሕመም ስቃይ ውስጥ ነበራችሁ –እንደማለት ነው። ታዲያ በእኩል ሚዛን ያለፈ መጨረሻው ለምን ተለያየ ? መለኮታዊ ኃይል ለምን አድሎ አደረገ? የሚሉ ጥያቄዎች የሕመሟ መነሻ የሆኑ ይመስለኛል።

ሕይወት ያለ ሥነ ጽሑፍ ገሀነም ነው” ያለው ማን ነበር? የማይታየውን የማሳየት ብቃት አለው — እንደማለት ነው።

በአጠቃላይ ቃላዊ ግጥምን የወለደው ኅብረተሰብ በሁሉም የሕይወት ዘርፍ የሚገለገልባቸው ዓውዶች ያሉት ሲሆን ክልከላውን የሚሻገርባቸው የብሶቱ ማሳያም ጭምር ናቸው። በተቃራኒውም አይነኬ እሴቶቹን የሚጠበቅባቸው ሀብቶቹ ናቸው። የቃል ግጥም የሚያግባባና ልዩ የሆነ ጥበብ ነው። በታዳሚው ላይ የሚፈጥረው አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ጫና ከፍተኛ ነው። አመፅንና እንቢታና የማቀጣጠል ኃይሉም አቻ የለውም። የሰው ልጅ ለዘመናት ያዳበረው እሴቱ በመሆኑ የዳበረ ዘርፍ ነው።

አንለይ ጥላሁን ምትኩ

አዲስ ዘመን ሐሙስ መስከረም 2 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You