መስከረም የወራት አውራ

በኢትዮጵያውያን ዘንድ የመስከረም ወር የተለየ ስሜት ያለው በመሆኑ የወራት ጌታ ይባላል። አንዳንዶች የወራት እማወራ ሲሉት፤ ከፊሎች የወራት አባውራ ሌሎች ደግሞ የወራት አውራ በሚል ይገልፁታል። ይህ ስያሜው የሚያመላክተው ወሩ የዓመት መጀመሪያ በመሆኑ ክረምት አልፎ የመኸር ወቅት የሚመጣበት ስለሆነ ልዩ ፍቅር አላቸው። በዚህ ሳቢያም ከወራቶች ሁሉ ሰዎች ለመስከረም ያላቸውን ፍቅር ልዩ ያደርገዋል። መስከረም ወር ሊጠባ ሲል የልጃገረዶች፣ የልጆች፣ የኮረዶችና የኮበሌዎች ጨዋታ ይደራል። በንጉሡ ዘመን ተማሪዎች በመስከረም ወር

‹‹ መስከረም ለምለም

ከወራቱ ሁሉ እንዳንቺ የለም

መስከረም መስከረም የወራቱ ጌታ

አበቦች ጀመሩ ካንቺ ጋር ጨዋታ። ›› እያሉ ይዘፍኑ ነበር።

በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ቡሄ የሚባለው የወንዶች ጭፈራ እና ዝማሬ የሚደራው በነሐሴ አጋማሽ መሆኑ ይታወቃል።ያው ‹‹ቡሄ ከዋለ የለም ሌሊት ዶሮ ከጮኸ የለ ክረምት›› እንደሚባለው ጭፈራው ሁሉ አዲሱን ዘመን በማስታከክ የሚካሔድ ነው። የኮበሌዎቹ ጭፈራ ሲደራ ኮረዶች ደግሞ በተራቸው ለአሸንዳ/አሸንድዬ ሻደይ ዐይኒ ዋሪ ጭፈራ ይዘጋጃሉ። ባህላዊውን የፀጉር አሠራር ይሠራሉ ። በባህላዊ አልባሳት ይለብሳሉ በጆሮና አንገት ጌጦችም ያጊያጊጣሉ፤ ይደምቃሉ። ተኳኩለው፤ ተቀነዳድበው፤ አምረውና ተውበው የሚጠብቁት የሚናፍቁት ጊዜው ሲደርስ ከበሯቸውን እየመቱ ባህላዊ የጭፈራ ዘፈናቸውን እየዘፈኑና እየጨፈሩ በየቤቱ ይዞራሉ።

ደስታ ተክለወልድ ዐደይ የሚለውን ቃል ሲፈቱት፤ በቁሙ ዐደይ ጥለት ማለት ነው። ዐደይ አበባ በመስከረም የሚፈነዳ የምድር ጌጧ ሽልማቷ ሲሆን፤ ዐደይ ለአበባ ቅጽል ወይም ዘርፍ ሲሉ አስታውቀዋል። ዐደየ የበጨጨ ቢጫ መሰለ፤ ነጣ፣ ነጭ ሆነ ፣በአፋን ኦሮሞ ነጭ ዐዲ፣ ፀሀይ ዐዱ የሚባለው ከዚህ የወጣ ነው ሲሉ ይገልጻሉ። በተጨማሪም ዐደይ የበጨጨ ቢጫ የሆነ አበባ የመስቀል ዕለት ልጃገረዶች አክሊል (ዐደይ አበባ ጎንጉነው ግንባራቸው ላይ አድርገው በራሳቸው ላይ የሚያጌጡበት) ነው። ወቅቱ እንኳን ሰው ጋራው ሸንተረሩና ኮረብቶች ሁሉ በአደይ አበባ ስለሚያጌጥና በለምለም ሣር የሚዋቡበት መሆኑ ወሩን በሰዎች ዘንድ ተወዳጅ እንዲሆን አድርጎታል።

ዐደይ በተለያዩ ቋንቋዎች የራሱ የሆነ ብያኔ አለው። ለአብነት በትግርኛ እማዬ ፤ በጉራጌ ‹አዶ› እናት ማለት ነው። በአፋን ኦሮሞም አዴ ወይዘሮ ወይም እናት የሚል ትርጉም ይሰጠዋል። በሲዳምኛም አዴ እናት ማለት ነው። ስሙን ስታዩት መመሳሰሉ ምናልባት ከዐደይ አበባ ጋር የሚያመሳስለን የሚያስተሳስረን ነገር እንዳለ ሆኖ፤ ኢትዮጵያውያን በቋንቋ ብንለያይም መስተጋብር እንዳለን አንዱ አመላካች መሆኑን ያሳያል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ብዝሃ ሕይወት ትምህርት መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሰው ባንድ ወቅት በአሜሪካ ድምፅ ፤በአማርኛ አደይ አበባ ወይም የመስቀል አበባ፣ በኦሮምኛ ‘ኬሎ’፣ በትግርኛ ደግሞ ገልገለ መስቀል ተብለው የሚጠሩት ዕፅዋት በሳይንስ መጠሪያው ‘ባይደንስ’ እንደሚባል በኢትዮጵያ ብቻ የሚበቅል እንደሆነ ገልፀው ነበር።

መስከረም አእዋፋት እንስሳት እጽዋት፣ ነፍሳት (ንብና ቢራቢሮ) በምድር ልምላሜ ተደስተው የሚፈነጩበት ሣር እየነጩ ውሃ እየተጎነጩ የሚደሰቱበት ወራት ነው። መስከረም ባለ ብዙ ስም ነው። ዘመን መለወጫ፣ እንቁጣጣሽ፣ አዲስ ዘመን፣ አዲስ ዓመት፣ ዐውደ ዓመት የመሳሰሉት ስያሜዎቹ ናቸው። መስከረም በስያሜም የከበረ በልምላሜም ያመረ ወር ነው። የመስከረም ወይም የአዲስ ዓመት ‹ብራንዱ› ትዕምርቱ፣ (ምልክቱ) ደግሞ አደይ አበባ በየቦታው መብቀሉ ነው። በመስከረም የሚከበረው የመስቀል ደመራና የእሬቻ ጭፈራ አንዱ ድምቀት የአደይ አበባ ውበትና ለምለም ሣር ነው።

አደይ አበባ ዓመቱን ጠብቆ በአዲስ ዓመት መባቻ በኢትዮጵያ ብቻ የሚበቅል የኢትዮጵያውያን መለያ ነው። ትዕምርቱ ያልነውም ለዚሁ ነው። አደይ አበባን በመስክ ላይ መብቀሉን መፍካቱን አይተው ቀን መለየት የማይችሉ ሰዎች አዲስ ዓመት እንደባተ ያውቃሉ።

መስከረም አእዋፋት በክረምቱ ወራት ተዘርቶ የደረሰ አዝዕርት ላይ እያረፉ እንደልባቸው እየተመገቡ ልዩ ዝማሬ የሚያሰሙበት ከቦታ ቦታ እንደልብ የሚበሩበት የሚደሰቱበት ወር ነው። በክረምቱ ወራት ላሞችና ኮርማዎች በለመለመው መስክ የሚፈረጥጡበት ወቅት ነው። ይህን ጽንሰ ሀሳብ ሰዐሊና ገጣሚ ነፍስ ሔር ገብረክርስቶስ ደስታ አንተነህ መስከረም በሚለው ግጥሙ

‹‹… አንተነህ መስከረም

የሐምሌን ጨለማ

የነሐሴን ዝናም

የሻርከው አንተ ነህ

በብርሃን ውበትህ …

ዕንቁጣጣሽ አንተ ስጦታህ የበዛ

ለሰው መታሰቢያ ውበት የምትገዛ ።

በሽቱህ መዓዛህ ለውጠው ዓመቱን፣

ይታደስ ያረጀው ፍጥረት ሌላ ይሁን ።

ከምረው ዘመን ካው ባመት ባመት፣

በወሩ ደረጃ ፍጥረት ይጓዝበት።

ፍየሎች ይዝለሉ ቅጠል ይበጥሱ፣

ከተሰደዱበት ወፎች ይመለሱ።

ይልቀሙት እህሉን ይሥሩ ቤታቸውን

ይሥፈሩበት ዛፉን ።

የደስ ደስ ያሰሙ ንቦች ይራኮቱ፣

ይንጠራሩ አበቦች ይንቁ ይከፈቱ።

አንበሳና ግልገል በመስኩ ይፈንጩ፣

ከብቶች ሳሩን ይንጩ፣

ሕፃናት ይሳቁ ይሩጡ ይንጫጩ። …›› ሲል ገጥሞት ነበር።

ክረምት ለገበሬው የተስፋ ወራት ቢሆንም ለከተሜዎች የፈተና ወራት ነው። ገበሬው ክረምቱን ሳይሳቀቅ በረዶው ዶፉ እየወረደበት እርሻውን እያረሰ ዘሩን የሚዘራበትና የዘራውን የሚያርምበት ወቅት ነው። ዝናቡን በመሳቀቅ እርሻውን የማያርስ ከሆነ ለመጪው አዲስ ዓመት ለረሀብ ለስደት ይዳረጋል። ‹‹ መስከረም ሲጠባ እንኳን ሰው፤ ዘመዱን ይጠይቃል ባዳ ›› የተባለውም ዝናብ በማይዘንብበት ወንዝ ባልሞላበት ወቅት እንደልቡ መሄድ ዘመድ አዝማድ ወዳጅ ወላጅ መጠየቅ ስለሚቻል ነው።

መጽሐፉም “በለቅሶ የሚዘሩ በደስታ ያጭዳሉ“ ይላል። ስለዚህ የተሻለ ነገር ለማግኘት ፈተናን መጋፈጥ ግድ ይላል። መስከረም የሁለት ቃላት ጥምር ነው። መስ አለፈ ሲም ከረም ደግሞ ክረምት ማለት ነው። ፍቺው ክረምት አለፈ ማለት ነው። በያዝነው ክረምት እንደሀገር ብዙ መከራዎች አጋጥመውናል። ብዙ ዜጎች ህይወታቸው አጥተዋል።

በተለይ የመሬት መደርመስና መንሸራተት ጎፋን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ሰዎች ከመሞታቸውም በላይ ቤት ንብረታቸው የፈረሰባቸው ብዙ ዜጎች አይተናል። ህም ተልቅ የፈተና እና የመከራ ጊዜ ሆኖ አልፏል። በክረምት ሰዎች እርስ በርስ ለመጠያየቅ በተለይ በገጠር ዝናቡና የወንዝ ሙሌት ስለሚያስቸግር ከቦታ ቦታ እርስ በርስ እንደልብ ለመንቀሳቀስ ይቸገራሉ።

በመጽሐፍ ቅዱስ መዝሙረ ዳዊት 146፥8 ዘይገለብቦ ለሰማይ በደመና ወያስተዴሉ ክረምተ ለምድር ዘያበቊል ሣዕረ ውስተ አድባር ይላል።ትርጉሙ፡-ሰማዩን በደመና የሚሸፍን ለምድር ክረምትን የሚያዘጋጅ በተራሮች ላይ ሣርን የሚያበቅል ማለት ነው።

አንዳንድ ሰዎች ቀልደኛ ገበሬ በሰኔ ይሞታል እያሉ ሲናገሩ በተደጋጋሚ ሰምቻለሁ። መቼም ሞት ድንገተኛ ጥሪ ነው እንጂ ሰዎች ተዘጋጅተው የሚመጣባቸው እንዳልሆነ ይታወቃል። ለማለት የፈለጉት እርሻ በጣም በሚፈልጉት ወሳኝ ሰዓት ተሰወረ ለማለት ነው።

‹‹ ዕንቁጣጣሽ እንኳን መጣሽ፣

በአበቦች መሀል እንምነሽነሽ። ››

አበባ የሚለው ዘፈን በሬዲዮ ሲለቀቅ ትዝታ የሚጭር ሐሴት የሚፈጥር ነው። እንግጫ ነቀላና በኮረዶች መስከረም ሲደርስ የተለመደ ነው። በአፋን ኦሮሞ ቡቃሳ ይባላል። ለአዲሱ ዓመት እንግጫ ነቅለው ኮረዶች ቡቂሳ ቡቂፈና እያሉ ይዘፍናሉ። ይህም ዐደይ አበባን ዐይተን ባህላችን መስተጋብርና ትስስር እንዳለው መረዳት እንችላለን። አደይ አበባም በየቦታው መብቀሉ ኢትዮጵያውያን በባህል በእምነትና ቋንቋ ቢለያዩም አንድ መሆናቸውን ማሳያ ነው ማለት ይቻላል።

ሌላው መስከረም ሲደርስ ትዝ የሚለን የኮሮዶች አበባየውሽ ጨዋታ ነው። አዲስ ዓመት ሲብት አደይ አበባ ሲፈነዳ አበባዮሽ ጭፈራ በኮረዶች በየቤቱ እየዞሩ ይጨፍራሉ፤ ስጦታ ይቀበላሉ። ከአበየውሽ ዘፈኖቻቸው የተወሰኑት ብናነሳና መልካም አዲስ ዓመት ብለን መሰናበት ደስ ይለናል። አዲስ ዓመት የሰላምና የብልፅግና ይሁንልና።

‹‹ .. አበባዮሽ ለምለም አበባዮሽ ለምለም

ባልንጀሮቼ ግቡ በተራ

እንጨት ሰብሬ ቤት እስክሠራ

እንኳን ቤትና የለኝም አጥር

እደጅ አድራለሁ ኮከብ ስጥቆር

ኮከብ ቆጥሬ ስገባ ቤቴ

ትቆጣኛለች የእንጀራ እናቴ

አደይ የብር ሙዳይ

ኮለለ በይ። ››

ኃይለማርያም ወንድሙ

 

አዲስ ዘመን ረቡዕ መስከረም 1 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You