ክበባትና ጥበባት በውበት

በክበባት ቤት ጥበባት እንዳሉ ሁሉ በጥበባት ቤትም ሌላ ትናንሽ ክበባት መኖራቸው እውነት ነው። ቅሉ ዛሬ ሳይሆን ያኔ…ክበባት ዋናዎቹን ጥበባት ለማዘጋጀት የሚጣለው ድፍድፍና ጥንስሱ እንደሚጠነሰስበት ማጀት ወይም መድኃኒት እንደሚቀመርባቸው ትንንሽ ቤተ ሙከራዎች ነበሩ ለማለት ይቻላል። መጋቢ ኪነ ጥበብ የነበሩትም ከጋዜጠኝነት እና ከስነ ጽሁፍ እንዲሁም ከራሱ ከኪነ ጥበብ መሠረት አድርገው የሚነሱ ክበባት ነበሩ።

እነዚህ ክበባትም ከዋናው የኪነትም ሆነ የስነ ጽሁፍ ቡድኖች ባልተናነሰ ሁኔታ ብዙ ሲያበረክቱ የነበሩ መሆናቸውም አይካድም። የእነዚህን ክበባት የአመሠራረት ሁኔታ ብንመለከት በሦስት ልንከፍላቸው እንችላለን። አንደኛውና የመጀመሪያው ትንሽ መስሎ የሚታየው በየትምህርት ቤት ውስጥ የሚገኙት እንደ “ሚኒ ሚዲያ” ያሉት ናቸው። ከፍ ብሎና አድጎ ደግሞ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ “ኪነ ጥበብና ባህል ማዕከል” በሚል ስያሜ እናገኘዋለን። ሁለተኛዎቹ ደግሞ በየከተማውና ቀበሌዎች ውስጥ የሚገኙት እንደ “ጸረ ኤድስ” ያሉትንም የሚያካትት ነው።

ሦስተኛው ሙሉ ጊዜያቸውን በኪነ ጥበብና በስነ ጽሁፍ የሚያሳልፉ አንጋፋዎቹ በጎን የሚመሠርቷቸውና እዚህ ውስጥ የሚሰባሰቡ አብዛኛዎቹ በሙያም ሆነ በፍላጎት በተመሳሳይ ሁኔታ የሚገኙ ናቸው። እጅግ በሳልና ረቀቅ ያሉ ጉዳዮች የሚንሸራሸሩበትም ጭምር ነው። “የአዛውንቶች ክበብ” ቲያትር ብቻ ሳይሆን ከጀርባ እውነተኛ አዛውንቶች ነበሩበት። እዚያ ቦታ ላይ ተወልደው ያደጉ መጽሐፍትና ቲያትሮችም ነበሩ። በአንድ ወቅት በአርቲስት ሰራዊት ፍቅሬ ተቋቁሞ የነበረውን “አፍለኛው የቲያትር ክበብ”ን ጨምሮ በአንድ አውራ ተነሳሽነትና አነሳሽነት ተመሥርተው፣ ከውስጣቸው ትልልቅ የጥበብ ሰዎችን ጭምር በማውጣት ኪነ ጥበቡን ሲመግቡ የነበሩ ክበባት እጅግ በርካታ ናቸው።

በጋዜጠኝነትና በስነ ጽሑፍ ጥላ ስር በቅለው ለኪነ ጥበቡ ዋርካ እስከመሆን የበቁም ነበሩ። በእነዚህ ዘርፎች ውስጥ ታዋቂ ከነበሩት መካከል ጳውሎስ ኞኞ፣ ፍካት፣ ትፍላሜ፣ ሐመረ-ኪን፣ ጮራ እና የመሳሰሉት ነበሩበት። እንግዲህ ነበሩ…ግን ታዲያ ዛሬስ ከነበሩት መካከል አለሁ ብሎ አቤት! የሚለን ማን ይኖር ይሆን?

በእርግጥ ከሰሞኑ አንድ ተገኝቷል። ከሰሞኑ የ30 ዓመት የልደት ሻማ አብርተው፣ ርችቱን ሲያፈነዱ ዛሬም ድረስ የመኖራቸውን ድምጽ አሰምተዋል። እንዳሰሙን እኛም ሰምተን ልናይ ልንመለከታቸው ከሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት ደርሰን፣ ካቋደሱን እኛም እንቋደስ።

ስለመጀመሪያው እናስቀድስ ካሉ የ1980ዎቹን የአዲስ ዘመን ጋዜጣን ከፍ አድርጎ፣ የዕለተ ሰንበት አንባቢያንን ገጽ በምናብ ለመደገም ያሻል። በዚሁ ዓመተ ምህረት አካባቢ አንድ ወጣት ከወደ ባሌ ሆኖ ልዩ ልዩ ጽሑፎችን እየጻፈ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ይልካል። ቀስ በቀስ ከአንባቢነት ወደ ጋዜጠኝነት መስመር መግባት ጀመረ። ጽሑፎቹን የሚቀበሉትና ወጣቱ ከውጭ ሆኖ የሚያገኛቸው ሰውም አቶ ሀዲስ እንግዳ ነበሩ። በጊዜው የሚያውቀው እሳቸውን ብቻ ነው። በዚህ መሀልም “የዕለት ሰንበት የአዲስ ዘመን ጋዜጣ አንባቢያን ማኅበር” ተመሠረተ። ይህ የአዲስ ዘመን ገጾች አንደኛው ክፍል የሆነው የዕለተ ሰንበት ዝግጅት ከአንባቢያኑ ወደ አንባቢያን የእርስ በርስ ቁርኝት የሚፈጥሩበትም ጭምር ነበር።

አንድ ለእናቱ በሆነው አዲስ ዘመን ዙሪያ የተሰለፉትን አንባቢያንን በአንድ መንደር አሰባስቦ፣ አንድ ወጥ ሰልፈኛ በመፍጠር ሂደት ውስጥ ፊታ ውራሪ የነበረውም ያ የባሌው ወጣት ነበር። እርሱም የዛሬው ጋዜጠኛ አስቻለው ጌታቸው ነው። በክብረ በዓሉ መድረክ ላይ ስለ አጀማመሩ ካወሳውም…“ውበትን ስንመሠርት በመጀመሪያ ላይ አውቶቡስ ተራ አካባቢ የነበርን ወጣቶች ነበርን። መነሻችንም የአዲስ ዘመን ጋዜጣ በልዩ እትምና ዲዛይን መጀመሩ ነበር። …ለአንባቢያን ተሳትፎ የዕለተ ሰንበት የአዲስ ዘመን ለአንባቢያን ክበብ መመስረት ዕድል ፈጠረ። ተወልጄ ያደግኩት ባሌ ቢሆንም ክረምት ወደ አዲስ አበባ ስመጣ ወደ አራት ኪሎ ጎራ እያልኩ የጋዜጣው አዘጋጆችን አገኛቸው ነበር። …ያኔ የቤት ስልክ ቁጥር እንደዛሬው 011 ምናምን አልነበረምና ቀጥታ ቁጥሩ ብቻ ነበር።

750048 የቤታችን ቁጥር ነበርና ይህን ቁጥር በጋዜጣው ላይ እንዲያወጡልኝ ለአዘጋጆቹ ሰጠሁኝ። ከወጣ በኋላ ፍላጎት የነበራቸው ወደ 26 ልጆች በዚህ ስልክ በመደወል ተመዘገቡ። ከእነዚህ መካከልም ወደ ስምንት የሚጠጉት አውቶቡስ ተራና መሳለሚያ አካቢቢ የሚገኙ ስለነበሩ እየተገናኘን በቅርበት ማውራት ጀመርን። …አዲስ ዘመን ጋዜጣ ዛሬ ላይ በየሚዲያው ላሉ በሙሉ ትልቅ ትምህርት ቤት ነበር። እኔ እጄን የፈታሁት አዲስ ዘመን ላይ ነው።

ትዝ ይለኛል በአንድ ወቅት ተጓዥ የሚል አምድ ነበር። እኔም የማያቸውን ነገሮች በሙሉ እጽፍ ነበር። ከአራቱ አምዶች መካከል ሦስቱን እኔ ነበርኩና የምልከው በአንድ ወቅት ጽሑፌን ስሰጣቸው የነበሩት ሀዲስ እንግዳም የጋዜጣው አዘጋጆች፤ ይሄ ልጅ ቱሪዝም ኮሚሽን ነው እንዴ የሚሠራው… ብለውሃል በማለት ሊያገኙህ ይፈልጋሉ አሉኝ” ሲል ነበር የተናገረው። በእርግጥም እንዲህ ማለታቸው ግምታቸው ልክ ባይሆንም ጥርጣሬያቸው ግን ቅርብ ነበር።

በወቅቱ የጉዞ ማስታወሻዎቹንና ሌሎችንም የሚጽፋቸው አስቻለው በአፍሪካ ሀገር አቋራጭ አውቶቡሶች ውስጥ ሠራተኛ ሆኖ በመሥራት ላይ ሳለ ነበር የአዲስ ዘመን ጋዜጣ የዕለተ ሰንበት አንባቢያን ማኅበር በተመሠረተ በስምንተኛው ወርም የማኅበሩ ስያሜ “ውበት አማተር የጋዜጠኞች ክበብ” በሚል ተለወጠ። ሰኔ 24 1986ዓ.ም ከኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ማኅበር ህጋዊ ሰውነት በማግኘት ሙሉእ ሆነ። ለምን በአዲስ አበባ ብቻ ሲልም ቀስ በቀስ ወደ ክልሎችም እየወረደ ዛሬ ላይ በ42 የኢትዮጵያ ከተሞች ውስጥ ይህ ክበብ ይገኛል።

በትንሹ የተጀመረው ክበብ እያደገና አድማሱን ከሥራ ጋር እያሰፋ ቀጠለ። “…ማኅበሩ ከተቋቋመ በኋላም ሦስት ሀገራዊ የስነ ጽሁፍ ውድድሮችን ያካሄድን ሲሆን፤ ማስታወቂያው በጋዜጣ የሚወጣልንም በነጻ ነበር። ሁለቱን ውድድሮች የጋዜጠኞች ማኅበር፣ አንዱን ደግሞ ደራሲያን ማኅበር ነበር ያወዳደረልን። ከአባላቶቻችንም ወደ 17 የምንሆነውን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አሰልጥኖ ብቁ እንድንሆን አድርጎናል” የሚሉ ጉዳዮችንም በማከል ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ አንስቶ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በክበቡ ውስጥ ስለነበረው ዐሻራ የክበቡ መስራች አስቻለው ጌታቸው አውስቶቷል። ዛሬ እንደቀደመው ባይሆንም ድርጅቱ ዛሬ በውበት አማተር ውስጥ ቢያንስ አንድ አባል አለው።

ውበት አማተር በዕለቱ…ቀደም ሲል እንዳነሳነው ዕለቱ ቅዳሜ፣ ቀኑም 25፣ ወሩም ነሐሴ ነበር። ዕለቱም ውበት አማተሮች ካሉበት የሀገሪቱ ክፍል ሁሉ ተጠራርተው፣ በ30ኛው የምሥረታ ልደታቸው በናፍቆት የተገናኙበት መድረክ ነበር። በጊዜው የዚህ ክበብ እናት የነበረው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በክብር እንግድነት ተጋብዟል። በተወካዩ በአቶ ጋሻው ታደሰም ምስጋና አዘል ንግግር ተደርጓል።

የውበትን ክብረ በዓል ለመታደም የሀገር ፍቅርን ደጅ የረገጡ ታላላቆችም ብዙ ነበሩ። “ኪነ ጥበብ ተዳክሟል፣ ስነ ጽሑፍ ወድቋል እንላለን እንጂ ዛሬም ብርቱ ብዕረኞች እንዳሉ በየሄድኩባቸው አጋጣሚዎች ውስጥ ሁሉ አይቻለሁ” በማለት የተናገረውን ደራሲ ኃይለ መለኮት መዋልን ጨምሮ ሌሎች አንጋፋ ጋዜጠኞችና የጥበብ ሰዎችም ታድመውበታል። “እኔ ሀገሬ ላይ ጀግና የምለው የስነ ጽሑፍ ሰው ነው።

ይሄን ያህል እስክሪብቶና ወረቀት ያልተወ የስነ ጽሑፍ ሰው ዛሬም ካለ…” ሲል አንድም መደሰቱን የተናገረው ጋዜጠኛ ትግስቱ በቀለ “…ነገር ግን ከዚህ ወጥተን እጃችን ላይ ባለው ስልክ ቅኝ የምንገዛ ከሆነ ሁሉንም ነገር እናላሽቀዋለን” የሚል ስጋቱንም አልደበቀም ነበር። በድምሩ ከአልባሳትና ዝግጅቶች አንስቶ ኢትዮጵያዊነት የሚነፍስበት ከባቤ አየር ነበር።

ታሪኩን ማንሳት ሌላ ራሱን የቻለ ታሪክ ነውና በደፈናው ግን፤ ከወደ ክፍለ ሀገር ድረስ የመጣ አንድ ቤተሰብ የሆነውን ታሪክ በመድረክ ሲናገሩትና ስሰማ ኃይለ መለኮት “የለም እንላለን እንጂ ስነ ጽሑፍ ዛሬም…” እንዳለ ሁሉ እኔም፤ ያ የምንናፍቀው ፍጹም ኢትዮጵያዊነት የለም እንላለን እንጂ የባላገሩ ልብማ ዛሬም ፍጹም ኢትዮጵያዊ ነው ብዬ እንድል አስገደደኝ።

በኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ እና ስነ ጽሑፍ ውስጥ ጋዜጠኝነት ያበረከተው ተቆጥሮ አያልቅም። ጋዜጠኝነትን ደግሞ እንዲህ ትንንሽ የመሰሉ የባህልና ኪነ ጥበብ ክበባትን ጨምሮ እንደ ውበት አማተር በሚል የተመሠረቱ ሁሉ ድምቀትና ፍካት ሆነው እንዲያብብ አድርገውታል። ነገሩ፤ በሦስት ማዕዘናት ውስጥ ሁሉም ለሁሉም ባለውለታና ተመጋጋቢ መሠረት ሆኗል። ዛሬ ላይ ደግሞ እነኚህን ሁሉ አጠቃሎ የሚይዝ ሚዲያ በሽ! በሽ! ነው። ይሁን እንጂ ለኢትዮጵያዊነት መሠረት ሊሆኑና መሆን የነበረባቸው ነገሮች የሚታዩት በግርድፉ ነው። ይህችን መቅረፍ ከሃሳቦቹ አንዱ እንደሆን ባለውቅም፤ ውበት አማተር ግን ከ30 ዓመታት ጉዞ በኋላ ወደ ሌላ አንድ ከፍታ ለመብረር ማቀዱን አሳውቋል።

ከአዲስ ዘመን የዕለተ ሰንበት አንባቢያን ተነስቶ፣ ውበት አማተር የጋዜጠኞች ክበብ ሆኖ፣ 30 ዓመታትን አስቆጥሯል። በጋዜጠኝነት፣ በስነ ጽሑፍና ኪነ ጥበብ ዘመን ተሻጋሪ፣ ታሪክ ሠሪ ለመሆን ራሱን ወደ መልቲ ሚዲያ ለውጦ የብዙኃን ሚዲያ አካል የመሆን የተስፋ መንገድ ጀምሯል። ብዙዎቹ ወድቀው በቀሩበት አውድማ ጋራ ሸንተረሩን እያቆራረጠ እዚህ ጋር ደርሷልና አሁን ካሰበበት የስኬት ማማው ላይ ለመታየት የሚቸግረው አይመስልም።

አባላቱ እንደሆን እንኳን አሁን አስቀድመውም ከትንሽ በመነሳት ራሳቸውን አብቅተዋል። ገሚሱን አፈርና ኑሮ ቢበላውም ጥቂት የማይባሉት ደግሞ በኪነ ጥበብ፣ በስነ ጽሑፍ እና በጋዜጠኝነት ከሀገር ውስጥ እስከ ባህር ማዶ ተንሰራፍተዋል። የዛሬ 30 ዓመታት ገደማ የተከሉት ዛፍ ዛሬ ፍሬ አፍርቷል።

ከእነዚህ ፍሬዎች መካከልም የዛሬው ደራሲ ጌቱ ሻንቆ አንደኛው ነው። የሠላሳ ዓመታት ፍሬውን በዚያው የ30ኛ ዓመት የልደት ዝግጅት ላይ ይዞ ቀርቧል። ከዚህ በፊት የትርጉም ሥራዎችን ጨምሮ የራሱን “የከዋክብት መንገድ” የሚል መጽሐፍ ለማስነበብ ችሎ ነበር። በዕለቱ ደግሞ ሁለተኛው የሆነውን “የሰው ዓመል 9” የተሰኘ በአዝናኝ ወጎች የተሰናሰነ መጽሐፉን አስመርቆ፣ ለንባብ እንካችሁ ብሏል። በመጽሐፍ ደረጃ ብቻ ካነሱ የሚጠራው የክበቡ አባላት ስም ዝርዝር ብዙ ነው። “መለየት አቃተን” በአልማዝ ምንዳዬ፣ “የማርገዝ ነጻነት” እና እንበለ ጥበብ(ግጥም) በሃይማኖት ታደሰ፣ “ሰብ ሰሉስ” ብሚች አልቦም፣ “ሀገሬን፣ መንገድ፣ ጎንደርን ፍለጋ፣ የመንገድ በረከት” እና ሌሎች መጽሐፍት ደግሞ በሄኖክ ስዩም(ተጓዥ ጋዜጠኛ) ተጽፈዋል። እኚህ ሁሉም እንደ አብነት እንጂ ነገሩን እንደመዘርዘር አይደሉም። በአንድ የውበት አማተር ይህ ሁሉ ፍሬ ከተገኘ፤ በዚያ ሁሉ ክበባት ደጅ ዞረን ዛሬን ስንመለከት ግን አንገት የሚያስደፋ ነው።

ክበባት ለጥበባት መድኃኒት ነበሩ። አሁን ግን ከክበባት ጥበባት ይልቅ የቴክኖሎጂው ጥፋት አንቆን ከሞት ሽረት ትግል ውስጥ ከቶናል። እንዲህ ዓይነት ክበባትን ለምንድነው ዛሬስ ልንመለከት ያልቻልነው? ብለን ከጠየቅን ለዚህ ምክንያት ቀንደኛው ጋሬጣ፤ ቴክኖሎጂው ያበዛው የማህበራዊ ሚዲያው ቀውስ መሆኑ አያጠራጥርም። ክበባት ከጥበባት ባሻገር ለወጣቱ መዝናኛና ከወዳጆቹ ጋር መገናኛ መድረክም ጭምር ነበር። እንደዛሬው ካለበት ሆኖ የፈለገውን ሁሉ ከእጅ ስልኩ ላይ አያገኝምና ተሰጥኦውን እያዳበረ ውስጣዊና ውጫዊ ህብረቱን ማጠናከሪያ ፍለጋ አማራጩ ክበባት ነበሩ።

ወትሮም ኢትዮጵያዊ ሆኖ እንኳንስ ወጣቱና አዛውንቱ እንኳን በሰፈር በአድባሩ ከአቻዎቹና ከመሰሎቹ ጋር ሰብሰብ እያለ ሳያወጋ የመኖር ደስታና ተስፋ የለውም። የክበባት መነሻም ሳይንሳዊ ባይሆንም እንዲህ ያለው ባህላችን ነው ለማለት ያስደፍራል። እንደዛሬው ቲክቶከር፣ ዩትዩበር …ወዘተ ወዘተ የሚባል ነገር አይታወቅምና ወጣቱ በተናጠል የቴክኖሎጂ ትግል ውስጥ ሳይሆን በአካልና በመንፈስ አንድነት በተገነባ ኢትዮጵያዊነትና የኢትዮጵያ ጥበብ ውስጥ ነበር።

ተገናኝቶ ይጨዋወታል። ተገናኝቶ ያነባል። ተገናኝቶ ይጽፋል። ይተርካል። ይወያያል። ስለ ሀገራዊም ሆነ አካባቢያዊ ችግሮች መፍትሄ ይፈልጋል። አንድነቱን እያጠነከረ ሀገርና ጥበብን ይገነባል። ከሆነ ጊዜ በኋላ ግን ብዙ ክበባትና ጥበባት ትግል ከመግጠም አልፈው እንደሚዋጋ በሬ ተያይዘው ወደገደሉ ገብተው ጠፍተዋል። ቀሪዎችም በትክክልም ስለመኖር መጥፋታቸው ውላ አልባና ግራ የገባ ነው።

አሁን በሀገራችን ውስጥ የሚገኙ የኪነ ጥበብ ማዕከላትን ብንመለከት ከላይ እስከ ታች አንድ ተኮር ዓይነት ናቸው። ኪነ ጥበቡን ተጠቅሞ እያንዳንዱ ብሔር ብሔረሰብ በግሉ መድመቁ የሚያስከፋ ባይሆንም ህብረ ብሔራዊ አድርጎ ሁሉን በአንድ ከማድረግ አንጻር ግን ወደፊት ሳይሆን ወደኋላ እየተጎተትን ነው። ለዚህ ትልቁ የመነሻ ችግር ደግሞ ልዩ ልዩ የኪነት ቡድኖች እየተመሠረቱ ያሉት ብሔር፣ አካባቢና መሰል ሁኔታን መሠረት እያደረጉ በመሆናቸው ነው።

የውበት አማተር ክበብ ውስጥ ያለውና የነበረውን መንፈስ ብንመለከት ብሔርን ይዞ ህብረ ብሔራዊነትን የሚያጎላ መሆኑን ነው። ከተመሠረተ በኋላ መሮጥ የነበረበትን ያህል ለመሮጥ ያልቻለ ቢሆንም እንደቀሪዎቹ በመሀል ቤት ከመጥፋት አደጋ ራሱን አስመልጧል። ከብዙ መቀዛቀዝ በኋላ ዛሬ በአዲስ ጉልበት ቆሞ ለመታየት በቅቷል። በ42 የኢትዮጵያ ከተሞች እንደዋርካ ወደ ላይም ወደጎንም ለመስፋት በማያዘው መንገድ ለመጽናት ከቻለ፤ ለማንሰራራት ያኮበኮበው እጅግ ወሳኙ ሰዓት ላይ ነው። ኢትዮጵያ ከኪነ ጥበቡ የምትፈልገውም ሆነ የሚያስፈልጋት ይህንን ዓይነቱን ነው።

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ነሐሴ 30/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You