ኢትዮጵያና ሱዳን ከጉርብትና ባሻገር በደም የተሳሰሩና የቆየ የጋራ ታሪክ ያላቸው ሕዝቦች ናቸው።ሁለቱ ሕዝቦች ከሚጋሩት ረጅም ድንበር ባሻገር ከጥንት ጀምሮ የባህልና የታሪክ መወራረስ የሚታይባቸውና ዕጣ ፈንታቸውም በአንድ ላይ የተጻፈ ነው።የአንዱ ቤት ሲንኳኳ በቀላሉ ሌላው ቤት የሚሰማውም ለዚህ ነው፡፡
ኢትዮጵያና ሱዳን ከጥንትም ጀምረው ነፃነታቸውን የሚወዱ እና ብሔራዊ ክብራቸውን አስጠብቀው የቆዩ ሕዝቦች ናቸው። ሁለቱ ኩሩ ሕዝቦች ነጻነታቸውን አሳልፈው ላለመስጠት በርካታ መስዋዕትነት የከፈሉና ከየትኛውም ወገን የሚቃጣን ጣልቃ ገብነት የማይቀበሉ ናቸው።የኢትዮጵያና የሱዳን ሕዝቦች በለጋስነት እና በእንግዳ ተቀባይነታቸው ስማቸው ጎልቶ የሚነሳ አገሮች ናቸው።
ሱዳን ከቅኝ ገዢዎቿ ነፃነቷን ከተጎናጸፈችበት እ.ኤ.አ ከ1956 ጀምሮ “በአንጻራዊ ሰላም” የኖረችው ለአስራ አንድ ዓመታት ብቻ ነው።በተረፈ ለ50 ዓመታት ያህል አንዳንዴ የባህል፣ አንዳንዴም የሃይማኖት፣ አልፎ አልፎም የብሔር ጉዳይ የጠብ መነሻ ሆኖ ስትታመስ ኖራለች።የመጀመሪያው የሱዳን የርስ በርስ ጦርነት ከ1955 እስከ 1972 እ.ኤ.አ. ከዚያም ሁለተኛው የሱዳን የርስ በርስ ጦርነት ከ1983 እስከ 2005 እ.ኤ.አ. ተከስቷል። በ1989 እ.ኤ.አ. በሰላማዊ መፈንቅለ መንግሥት ኦማር ሀሳን አህመድ አል-በሽር ሥልጣን ላይ የወጡ ሲሆን እርሳቸውም በሕዝባዊ አመጽ 2010 ዓ.ም ከስልጣን ወርደዋል።ሆኖም በእነዚህ የችግር ዓመታቶች ሁሉ ኢትዮጵያ ከሱዳን ሕዝብ ጎን በመቆም የምትታወቅ አገር ነች፡፡
የቅርብ ጊዜውን እንኳን ብንመለከተው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ስልጣን በያዙ ጥቂት ወራት 2010 ዓ.ም አካባቢ ለረጅም ዓመታት ስልጣን ላይ የቆዩት ፕሬዚደንት አልበሽርን ከስልጣን ለማውረድ የተቀሰቀሰው አመጽ የከፋ ጉዳት እንዳያስከትል መልክ በማስያዝና አገሪቱን የሚመሩ የሽግግር መንግስት አባላትን በጋራ ስምምነት እንዲዋቀር በማድረግ ሱዳንን ተጋርጦባት ከነበረው አደጋ መታደግ የቻለችው ኢትዮጵያ ናት፡፡
ሆኖም እአአ 2021 ላይ የሲቪል መንግሥቱ ከስልጣን መወገዱን ተከትሎ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ሱዳን በሉዓላዊ ምክር ቤት በሁለት የጦር ጄነራሎች ስትመራ ቆይታለች። ከዚህ ጊዜ ጀምሮም ወጣ ገባ የሚለው የሰላም ድባብ ብዙዎችን ሲያሰጋ ቆይቶ ሰሞኑን ዋና ከተማዋን ካርቱምን ጨምሮ ወደ ጦርነት ተገብቷል።ከሁከትና ብጥብጥ ማትረፍ የሚፈልጉ አካላትም ሱዳንን ወደ ማያባራ ጦርነት እንድትገባ በርካቶች እጃቸውን ለማስገባት ሲሞክሩ ታይተዋል።
አንዳንዶችም ወዳጅ መስለው በመጠጋት የበለጠ ሁከትና ብጥብጥ እንዲነግስ የራሳቸውን የቤት ስራ በመስራት ላይ መሆናቸውን የሱዳን ብሄራዊ ጣቢያ ጭምር አጋልጧል።ሆኖም የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ እንዳሉት የሱዳን ሕዝብ ካጋጠመው ሁኔታ ለመውጣት የሚያስችለው ጥበብና ችሎታ ያለው ሕዝብ በመሆኑ ያለማንም ጣልቃ ገብነት ችግሩን መፍታት ይችላል፡፡
ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ የምትታወቅበት የገለልተኝነት ፖሊሲ ዛሬም በሱዳን ላይ እንዲተገበር ትፈልጋለች።ኢትዮጵያ የጎረቤት አገራት ችግር ሲገጥማቸው ችግሮቻቸውን በራሳቸው እንዲፈቱ የምትመክርና ለዚህም በተግባር የምትንቀሰቀስ አገር ነቸ።የሱዳንም ጉዳይ ከዚህ አንጻር እንዲታይ ትፈልጋለች፡፡
ለዚህም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ሰሞኑን ‹‹የሱዳን ሕዝብ የራሱን ችግር በራሱ እንዲፈታ ለራሱ መተው ያለበት ሲሆን የማንኛውም የውጭጣልቃ ገብነት ዓላማም ሰላምን እና ድርድርን በተመለከተ ብቻ ሊሆን ይገባል። የኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕዝብ በበኩሉ የሱዳን ሕዝብ የውስጥ ችግሩን በለመደው ጥበባዊ አካሄድ በራሱ እንዲፈታ የሚመኝ እና የሱዳን ሕዝብ ጥቅም ተከብሮ ማየት ትልቁ ፍላጎቱ መሆኑን በድጋሚ እንገልጻለን ›› የሚል መልዕክትም ያስተላለፉት፡፡
ስለሆነም የሱዳን ሕዝብ ችግሮችን በራሱ መፍታት የሚችል ሕዝብ ነውና ለዘመናት ያካበተውን ጥበቡን ተጠቅሞ ችግሩን እንዲፈታ ዕድል ሊሰጠው ይገባል።ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የተፈጠረውን ችግር በራሷ መንገድና አቅም የፈታችበት መንገድም ጥሩ ትምህርት ሊሆን የሚችል ነው።የሱዳን ህዝብ በራሱ አቅምና መንገድ ወደ ቀደመ ሰላሙ እና መረጋጋቱ እንዲመለስ በሚያደርገው ጥረት የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት የበኩላቸውን አዎንታዊ ድርሻ ለመወጣት ምንግዜም ዝግጁ ናቸው!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 12/2015