ከመጻሕፍት ዓለም

መጻሕፍት የሁሉም የጥበብ ዓለም መነሾ እርሾ ናቸውና የነርሱ ውልደት ከምንም በላይ ደስ ያሰኛል:: “እንኳን ጥበብ ማረችህ! ማረችሽ!” እያሉ ለስሚያ ጥየቃ መሄዱም ከንቱ ድካም ሆኖ አያውቅም:: መጻሕፍቱ ሁሉ ከዓመት መባቻ፣ መስከረም ሲጠባ፣ ከወራት ሁሉ ወር መርጠው በህዳር መታጠን የፈለጉ ይመስል በተለይ ባሳለፍነው ሳምንት ለምርቃት የቆሙ በርካቶች ናቸው:: በወርሃ ህዳር ሁለተኛ ሳምንት የተመረቁ መጻሕፍት ብዛት ከቀናቱ ቁጥር ጋር የሚስተካከሉ ናቸው:: እንዲያ ቢሆንም ቅሉ ያዩት የሰሙትን ሁሉ ለመተንፈስ ሳንባም እየታከተ፣ ቦታና ሁኔታም አይፈቅዱምና ሁለቱን ብቻ መርጠን ብንሸራሸርባቸው ይበጃል::

አንደኛው መጽሐፍ የመመረቂያ ሪቫኑ ወደ ሀገር ፍቅር የቲያትር ቤት አዳራሽ ያደርሰናል:: መጽሐፉ ብቻም ሳይሆን ደራሲውም ጥበብ አፍቃሪውን የተዋወቀው ከዓመታት በፊት በዚያቹ አዳራሽ ላይ ነበር:: የቲያትር ባለሙያና መምህር፤ ዶክተር ተሻለ አሰፋ “የተውኔት ዝግጅት መሠረታዊያን” የሚል መጽሐፍ ጽፎ ለጥበብ እጅ መንሻ አቀረበ:: ቲያትርን ተምሮ ተመርቆ፣ ለዓመታት በሀገር ፍቅር ተውኔቶቹን ሲያቀርብ ከርሟል:: ለዓመታት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ቲያትርን ሲያስተምር ቆይቷል:: ከሁለቱም አቅጣጫዎች የሰበሰባቸውን ሙያዊ ክህሎቱን አሰባጥሮ ይህን መጽሐፍ ለመጻፍ አበቃው:: ሥራዎቹን ባቀረበበት አዳራሽ፣ ባስተማራቸው ተማሪዎች ፊትም አስመረቀው::

ታዲያ ምርቃቱም መጽሐፉ ለብቻው ሌጣውን ቆሞ አልነበረም:: የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የባሕልና ኪነ ጥበባት ቡድን በህብረ ዝማሬ ለማጀብ ከመድረኩ ላይ ተገኝተዋል:: የበዓሉ ግርማ የጥበብ አድባርም አልታደመም ለማለት አይቻልም:: በውድነህ ክፍሌ ተዘጋጅቶ የዛሬ አንድ ዓመት ገደማ ለመድረክ ከበቃው “ቤርሙዳ” ከተሰኘው ቲያትር ቀንጨብ ተደርጎ በዕለቱ ታይቷል:: ሙሉ ቲያትሩ ቀርቶ ተቀንጭቦ የቀረበው በራሱ ሙሉዕነት የነበረውና ምን ቀረው የማይባል ነበር:: ሳያጋንኑ ቢያወሩት ትወናው ላይ ራሱ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ከነሙሉ ግርማ ሞገሱ ነበረበት:: በዓሉ ግርማ ከተሰወረበት ቤርሙዳ አምልጦ መጣ ለማለት የሚቀረው ጥቂት ነገር ብቻ ነበር:: ጋዜጠኛው ጸጋዬና ነበልባሏ ፊያሜታም አካለ ሥጋ ለብሰው መድረኩ ላይ ታይተዋል:: ይህን ከመሰለው ቲያትር ጋር መጽሐፉን መመረቅ የተለየ ስሜትና ድባብ አለው::

የዶክተር ተሻለ የተውኔት መሠረታዊያን ውሎ አዳሩ በቲያትር ጽንሰ ሃሳብ ላይ ነውና ከስር ለመግባት ያህል የቀደመው ቲያትር መሠረት የነበረ አንድ ሰውንም ማንሳት ተገቢ ነው:: ስለ ሀገራችን ያለፈ የቲያትር ጥበብ ሲነሳ የማይረሳው ግርማቸው ተ/ሐዋርያት ነው:: የርሱ የተውኔት ጽሑፎች ዛሬም ስሙን ይዘው ከኩራዝ ውስጥ እንደተሰተሩ ክሮች ናቸው:: በጨለማ ውስጥ ሆነው እንኳን በእርሱ የጥበብ ብርሃን ቲያትርን መጻፍ የጀመሩ ቀጥሎም ሌላውን ማስከተል ጀመሩ:: አንዱ ከአንዱ ሲማር፣ እርስ በርስ ሲማማር፣ ከታች ፍሬን ሲያፈራ፣ ቀጥሎ ለመጣው በአደራ ሲያስረክብ፣ በቅብብሎሽ ሲወራረድ መጥቶ ዛሬ ካለንበት ደርሷል:: በዚህ ሁሉ መሃል ቲያትር ብዙ ቅርጽና ለውጥ አድርጓል:: የተሻለና ለኢትዮጵያ የኪነ ጥበብ እድገት ግብዓቶችን እንዳቀረበ ሁሉ ተበርዞ ደግሞ የነበረውንም ቀብሯል:: ሁላችንንም የሚያስማሙም የማያስማሙንም ነገሮችን አጭቆ ይዟል

በራሱ መሠረት አለቱን ያላጸና ማንኛውም ነገር ልክ እንደ ትቢያ ማለት ነው:: በክረምቱ ዝናብ ረስርሶ፣ በበጋው ፀሐይ ይደርቃል:: በመጣ አውሎ ንፋስ ሁሉ እየቦነነ፣ ከሚሄደው ጎርፍ ጋርም ጥርግርግ ብሎ ይሄዳል:: መንገድ ላይ እንደበቀለ ችግኝ በወጣ በወረደው ሁሉ መረጋገጡ አይቀርም:: ታዲያ የሀገራችን ቲያትር ራሱን ያጸናበት ጽኑ መሠረት አለው ወይ? ካልን የለውም ወደሚለው ማጋደሉ አይቀርም:: ገዘፍ ያለ የቲያትር ጥበብ ሳለን ጥበቡን የምንጠቀምበት መንገድ ግን የባዕድ ቅይጥ ነው:: ለዚህ እንደ ማሳያ የምንገለገልባቸውን ሙያዊ ቃላት መመልከቱ በቂ ነው::

በቲያትር ጥበባት ትምህርት ክፍሎች ውስጥ ለማስተማሪያነት የሚቀርቡትም ከውጭ የተተረጎሙ መጻሕፍትን ነው:: ተምሮ የወጣውም የሚሠራው በዚሁ ነው:: በሀገር በቀል ዕውቀት ላይ ተመሥርቶ የሚጻፉ የቲያትር መጻሕፍት የሉም ማለቱ ይቀላል:: አልፎ አልፎ ቢጻፉም ከውጭ ተጽዕኖ ነፃ ለመሆን ያልቻሉ ይሆናሉ:: በድምሩም የቲያትር መሠረታችን የጸናው ሥሩን ከማዶ፣ ቅርንጫፉን ከኛ ዘንድ፣ ግንዱን ደግሞ አግድም ከመሃል አድርጎ ነው:: ከኛው ሰማይ ስር የፀሐይ ብርሃኑን እያገኘና ፍሬውንም እየበላን ቢሆንም ሥሩን ወደራሳችን አፈር ካላመጣነው ግን መሠረት አልባ መሆኑ ነው:: በዩኒቨርሲቲዎችና በተለያዩ ተቋማት ውስጥ ከሚደረጉ የጥናትና ምርምር ሥራዎች በዘለለ እንደ አንድ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ መሠረት ተደርጎ የሚመራበት መጽሐፍ የለም:: ይህ ደግሞ በተለይ ለጀማሪ የቲያትር ባለሙያዎች ከየት ተነስተው ወዴት መሄድ እንዳለባቸው ባለማወቅ በመሰላቸው እንዲጓዙ ያደርጋል::

ቲያትራችን ከጀመረበት አንስቶ በወጥነት እንዳይጓዝ ራሱን ችሎ የሚመራበት ሥርዓት አለመኖሩ አንደኛው ምክንያት ነው:: ለዚህ እንደ መንስኤ ሊሆኑ ከሚችሉ ነገሮች ቀዳሚው ደግሞ በሀገርኛ የቲያትር ጥበብ መሠረት ላይ ቆመው የጻፉት መጽሐፍ በጉልህ አለመኖሩ ነው:: ሁሉም ፀሐፊ ተውኔት ይመጣል፤ በራሱ ዕውቀትና ክህሎትም በመሰለው ሠርቶ ይሄዳል:: አዘጋጁም ይመጣል፤ እርሱም እንደታየው ብቻ የወደደውን መልክ ይሰጠዋል:: ስክሪፕት አዘጋጁ እንዳሻውና እንደገባው ብቻ ቢያዘጋጀው ደራሲው እስካልተቃወመው ድረስ ሌላ ምንም የሚያግደው ገደብ የለውም:: የሚመጣው ሁሉም የሚሠራው ለርሱ በተመቸው ልክ ይሆናል::

ችግሩ ግን የቱንም ያህል ጥሩ ሥራ ቢሠሩ ያለምንም የጋራ መስመር በራሳቸው ሀዲድ ላይ ተጉዘው በመሆኑ ቀጣይ የሚመጣውም የራሱን አዲስ መንገድ ይፈልጋል እንጂ የቀደመውን መንገድ በመሠረታዊነት አይቀጥለውም:: ስለዚህ ታላላቅ ሥራዎች ብለን የምናነሳቸው ሁሉ በራሳቸው አጥር ታጥረው ብቻ ይቀራሉ:: በአንደኛው ዘመን የተወለደው ታላቅ ሥራ ግለቱ በዚያው ዘመን ላይ ብቻ ሆኖ ይቀራል:: ስሙ ዘመን ተሻግሮ ሥራው ግን ከዚያው ዘመን ላይ ተጣብቆ ይቀራል:: የቲያትር ጥበብ እንደ ግመል ሽንት መስሎ የሚታየን ለዚህም ነው:: እያንዳንዳቸው የየራሳቸውን የንግስና ዙፋን ይዘው በአንድ የቲያትር ግዛት ላይ ለብዙ ይነግሣሉ:: ሁሉንም በአንድ አስተሳስሮ ኃይላቸውን ከማጠናከር ይልቅ ሄዶ ከወደዱት ጎን በመለጠፍ አሊያም ልክ ካልሆነው በመፈልሰፍ ለአንዱ ቲያትር አንድ መሠረት እንዳይኖረው አድርጎት ቆይቷል::

አሁን በዶክተር ተሻለ አሰፋ የቀረበው “የተውኔት ዝግጅት መሠረታዊያን” ክፍተቶቹን ከመሸፈኑም ለወደፊቱ እንደ አንድ የተውኔት ሕገ ደንብ የምንከተለውና የምንመራበት ሊሆን ይችላል:: መጽሐፉ በውስጡ ከያዛቸው የተውኔት መሠረታዊያን መካከል በመጀመሪያው ምዕራፉ የተውኔት ዝግጅት ምንነትና ባህሪያት፣ መሠረታዊ የሆኑ የቃላት ትርጓሜዎቹና ዋና ዋና የክርክር ሃሳቦች ቀርበውበታል:: በሁለተኛው ምዕራፉ ደግሞ መድረክና ተዋንያንን የተመለከቱ የአዘጋጅ ማስተላለፊያዎች ናቸው:: በምዕራፍ ሦስት አብይ የዝግጅት አላባውያንን የሚመለከቱ ጉዳዮች ናቸው:: በአራተኛው ምዕራፍ አዘጋጁ ሊከተላቸው የሚገባው የተውኔት ቅደም ዝግጅቶችን ከተግባር ማሳያዎች ጋር ቀርበውለታል:: ምዕራፍ አምስት አጠቃላይ ስለ ልምምድ የሚናገርበት ነው:: ከቅስት መድረክ አንስቶ እስከ ሌሎቹም ዓይነቶች ተውኔቶች የሚቀርቡበትን፣ በሀገራችን ያለውንም የመድረክ ዓይነት በተመለከተ ደግሞ በስድስተኛው ምዕራፍ በዝርዝር ቀርቦበታል:: እኚህ ስድስት ምዕራፎች ለአንድ የቲያትር መንደር ወሳኝና መሠረታዊ የሆኑ ሀገር ተኮር ጥበባትን አጭቀው ይዘዋል::

ሙያዊ ዕውቀትና ጥበብ በአንድ አቆራኝተው የያዙ መጻሕፍት በተለየ መንገድ የራሳቸው የሆነ ተደራሲ ይኖራቸዋል:: የተውኔት መሠረታዊያንም ዋነኛ መዳረሻው በቲያትር ጥበብ ውስጥ ወዳሉት አንባቢያን ነው:: ሆኖም ግን ፀሐፊው ለመድረስ የፈለገው በዚያ ያሉትን ብቻ አይደለም:: እንደ አብዛኛዎቹ ሙያዊ መሠረት እንደያዙ መጻሕፍት ለአዋቂው ብቻ በሚገባው መልኩ አላጠጠረውም:: በሙያው እጅግ ከፍ ላሉም፣ እታች ላለው ተማሪውም፣ በጠቅላላው ለቲያትር ቤተሰቡ በሙሉ እንዲሆን ቀለል አድርጎ አዘጋጅቶታል:: ከሙያው ውጭ ሆኖ ለማወቅ ለሚፈልገውም የተቆለፈ ነገር የለውም:: ይህ ማለት ግን አንድ ሰው በቲያትር ጥበብ ልቡ ስለተነደፈ ብቻ ይህን መጽሐፍ አንብቦ ቲያትረኛ ሊሆን ይችላል ማለት አይደለም::

የፀሐፊው የተውኔት ምልከታ ያረፈው የቅስት መድረክን መሠረት አድርጎ ነው:: ምክንያቱም በሀገራችን የቲያትር አዳራሾች ውስጥ የሚገኙት አብዛኛዎቹ መድረኮች ቅስት በመሆናቸው ነው:: የአቀራረብ ስልቱም ‘እንትን ማለት እንዲህ፣ እንዲህ ማለት እንትን ማለት ነው’ ብሎ በደፈናው በቃላት መጋረጃ ብቻ አይዋዥቅም:: እያንዳንዱን ምዕራፍ ሥዕላዊ ይዘት ባለው የተግባር ምስል ቀረጾታል:: ሃሳቦቹን በፎቶግራፎች አስደግፏቸዋል:: “ነገር በምሳሌ ጠጅ በብርሌ” ሲሆኑ ደህና ይንቆረቆራሉና በምሳሌዎች ያወራርዳቸዋል:: ለመጻፍ ሲዘጋጅ እስከ ዛሬ ካካበታቸው ዕውቀትና ልምድ ባሻገርም የራሱ በሆነ ቤተ ሙከራ ሁሉን እየለካና እየወጠረ ቅስቶቹን መትሯቸዋል::

“የተውኔት ዝግጅት መሠረታዊያን” የተሰኘውን መጽሐፍ በማዘጋጀቱ ጥልቅ አሰሳና ዳሰሳ በማድረግ ፀሐፊው ቢያዘጋጀውም ከበስተጀርባ ግን የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ፕሬስ አለበት:: ፕሬሱ ሀገር በቀል የሆኑ ሳይንሳዊ የፈጠራ ሥራዎችን ማስፋፋት ከቆመለት ዓላማ አንደኛው ነው:: እንዲህ ለሀገራዊ ኪነ ጥበብ ወሳኝ ከሆኑ ሥራዎች ጋርም አብሮነቱን ያጸናልና የተውኔት መሠረታዊያን በማሳተም ከፀሐፊው ጎን መቆሙም ለዚሁ ነው::

ሌላኛውና ሁለተኛው መጽሐፍ መንገዱ ወደ ሰይጣን ቤት ነው:: ምስጋና ለአፄ ምኒልክ ይግባና “የሰይጣን ነው” ሲባሉም እምቢ ብለው ያስከፈቱት ቤተ ተውኔትና ፊልም ቤት ቢያረጅም ዛሬም አለ:: ቤቱንም እንድናስታውሰው ያደረገን ጋዜጠኛው መኮንን ወልደ አረጋይ የመጽሐፍት አበባዎቹን ይዞ መርቁልኝ ሲል ከዚሁ ቆሞ ነበር:: ስለዚህ ቤትም ገረፍ ባደረጋት መጽሐፉ ውስጥ “…አንድ ሙኩት ይገዛበት በነበረ መልቅ/አላፍ ሂሳብ ፊልም መታየት በመጀመሩ የሀገሬው ሰው “ወደ ሆድ አይገባ፣ አይበላ አይጠጣ፣ ለዓይን የሚያስከፍል ምኑ ዘመን መጣ” ብሎ ስንኝ መቋጠሩ በታሪክ ይነገራል…” ይለናል:: ታዲያ ፊልሞቹ ሲታዩ የነበሩት በዚሁ የሰይጣን ቤት ውስጥ ነበር::

የሰይጣን ቤት ዛሬ ላይ ልዩ ልዩ መሰናዶዎች የሚሰናዱበትም ሆኗል:: ባሳለፍነው ሳምንትም የጋዜጠኛ መኮንን ወልደ አረጋይ ሁለት ተከታታይ መጻሕፍትም ከዚሁ መርቁን ብለዋል:: ጋዜጠኛ መኮንን ወልደ አረጋይም “እነሆ ማሟሻ” ይላል:: ለ25 ዓመታት ያህል በጋዜጠኝነት ሙያ የሰነባበተው መኮንን ወልደ አረጋይ፤ በሀገራችን የመጀመሪያ የሆነውን ኪነ ጥበባዊ ጉዳዮች ብቻ የሚወጡበትን ጋዜጣ በማዘጋጀትም ፈር ቀዳጅ ነው:: በሙያው ሽቅብ ቁልቁል ሲል ቆይቶ ካከማቸው ዕውቀትና ልምድ በመነሳት “እነሆ ማሟሻ” በሚል ርዕስ ቅጽ 1 እና ቅጽ 2 መጻሕፍቱን አበርክቷል:: ቅሉ ለምርቃት የበቁት አሁን ቢሆንም የመጀመሪያው ከወራት በፊት፣ ሁለተኛውም ባሳለፍነው የጥቅምት ወር ላይ ኋላና ፊት ተከታትለው ለንባብ በቅተዋል:: አሁን ደግሞ በሰይጣን ቤት አብረው ተመርቀዋል::

እነዚህ ሁለት ወንድማማች መጻሕፍቶች በዓይነታቸው ለየት የሚሉ ይመስላሉ:: የውልደታቸው ሀሳባዊ ጽንስ የተቋጠረው ከጋዜጠኛው የቀድሞ የሬዲዮ ዝግጅቶች ውስጥ ነው:: በሸገር ኤፍ ኤም 100.2 ያቀርባቸው ከነበሩት በርካታ መሰናዶዎቹ መካከል “ስንክሳር” እና “እነሆ ማሟሻ” የተሰኙት ለመጻሕፍቱ የአንበሳው ጅራት ናቸው:: ስንክሳር በኢትዮጵያ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እውነታዎች ላይ የተጠመጠመ የጥናትና ምርምር ትሩፋት ነው:: በሬዲዮ ሲያጋራቸው ያደመጡት ብዙዎች መጽሐፍ ጻፍልን ሲሉ ሲወተውቱት ነበርና “እነሆ ቅምሻ” ሲል ቅጽ አንድን በመጽሐፍ አቀበላቸው:: በመቀጠልም ሁለተኛ ስጦታው የሆነለት ቅጽ ሁለት መጽሐፉም የስንክሳር ውላጅ ነው::

የመጻሕፍቱን ዘውግ ፍለጋ ከገባን ልቦለድ የምንላቸው አይደሉም:: በወግ አሊያም በግለ ታሪክ ዘርፍም አንጠቅሳቸውም:: በዘመናት ገመድ ላይ ከተንጠለጠሎ አስገራሚ የኢትዮጵያ ታሪኮች ላይ የተቆነጣጠሩ ጉርሻዎች ናቸው:: ፀሐፊውን ጨምሮ ብዙዎች “የታሪክ ፍንካቾች” ሲሉ ይገልጹታል:: ኢትዮጵያ የተገነባችባቸው የታሪክ አለቶች እንደሆኑም ጭምር ተናግረውታል:: በርግጥም ደግሞ ናቸው:: ከሁለቱም መጻሕፍት ላይ የተሰናሰኑት ይዘቶች በውስን ጉዳይ ላይ የአንድን ታሪክ ፍሰት ይዘው የሚቀጥሉ ሳይሆኑ፤ ውስን በሆኑ ቃላት የታሪክ አስኳሉን ቁጭ አድርገው ብቻ የሚያልቁ ናቸው:: ከግማሽ ገጽ እስከ ሁለት ገጾች፤ ከዚያ አያልፉም:: በዋናነትም ከመቶ ዓመታት ገደማና ወዲህ በሀገራችን ተክስተው ያለፉትን አስገራሚ ጉዳዮች ባጭር ባጭሩ፣ እጥር ምጥን ብለው ተቀምጠዋል::

ጋዜጠኛ መኮንን ወልደ አረጋይ እኚህን የታሪክ ሰበዞቹን ለመምዘዝ ከጥልቅ ማህደሮች ውስጥ ሰጥሞ ገብቷል:: ወርቆቹን ፍለጋ አድካሚ ቢመስልም ጥርሱን ነክሶ ገብቶበታል:: ትንንሽ ግን ደግሞ ትልቅ ዋጋና ሚዛን ያላቸው ናቸው:: አስቂኝ እየሆኑብን ፈገግ ያስብሉናል:: እያስደመሙን ከጭንቅላት ይወዘውዙናል:: እንዲህ ዓይነቱን መጽሐፍ ምናልባትም ከአንድ ታላቅ ሰው አንብበነው ይሆናል:: ከብዙ ዓመታት በፊት አፈ ሊቅ አክሊሉ “ኢትዮጵያ ታሪኳ ነው መልኳ” ሲሉ በጻፉት መጽሐፍ ውስጥ በቅንጭብጭብ ታሪኮች ኢትዮጵያን በዘመናት ቃኝተዋት ነበር:: “እነሆ ማሟሻ”ም የዚህኑ ዓይነት ወግ የያዙ መጻሕፍት ናቸው::

በሁለቱም መጻሕፍት፣ ከእያንዳንዱ ገጽ ላይ የተዳሰሱ ጉዳዮች እጅግ በርከት ያሉ ናቸው:: ከሁለቱም መካከል ጥቂቶቹን ለአብነት ለመጥቀስ ያህል ቀጣዮቹን እናገኛቸዋለን:: ከርቸሌና ዓለም በቃኝ፣ የጅብ መንጋ፣ ንጉሳዊ ቤተ መጻሕፍት፣ ገብረ ክርስቶስ ደስታ፣ የአለማየሁ ቴዎድሮስ ደብዳቤ፣ ወጣሪና ሰፊ፣ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤትን ለማቋቋም ርዳታ የሰጡ ሰዎች፣ የአፄ ምኒልክ የጉዞ ምኞት፣ ከደንዞ ደንዞ ወደ ጃንሆይ፣ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ዘመናዊ መርከብ፣ የጉንዳንና የጸጉር ግብር፣ የወፍጮ ታሪክ፣ጠጅ ማስጣል ያስከተለው መከራ፣ የቀፊራ እድሜ ጠገቡ ገበያ፣ በነጻ መጠጥ የተፈጠረ ሙግት፣ እኔም ብሆን እንዲህ ነበር የማደርገው፣ ተርቤያለሁ፣ የሐኪሞቹ ሰፈር ቀበና፣ ሴት አህዮች በአዲስ አበባ…የሚሉ ተካተውበታል::

ህዳር ሲታጠን ተጣጥነው ከወጡ ሰሞነኛ መጻሕፍት መካከል፤ በሁለት ፀሐፊያን ተከሽነው፣ በሦስት የባቡር ሀዲድ ላይ ሲከንፉ ከፌርማታው ቆመን እኚህን አግኝተናል:: ጥቂት መንገድም ቢሆን ተጉዘናል:: የበላነው ቁራሹን ሆኖ ባያጠግበንም በሽታው ይለፍ::

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ህዳር 19/2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You